የምላስ ቁልቁለት. . . የተግባር አቀበት

Wednesday, 10 August 2016 13:51

 

አጀብ!

ባዳራሹ ሙሉ

ሰው በሰው ሲጠበብ፣

ተግባር መሬት ወርዶ

ላፍ እንዴት ይጨብጨብ!

      (ገጣሚ ገዛኸኝ ታደሰ - በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር “የዘመን ቀለማት”

የግጥም መድብል ላይ እንዳሰፈረው)

እንደምን ሰበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . መቼም ዘንድሮ “አጀብ!” የሚያሰኘን ነገር ያለቅጥ በዝቷል። እናም ልብ የሌለው ሁሉ በከንቱ ፅድቅን ይመኛል። አበው ደግሞ እንዲህ ይላሉ፣ “ልብ የሌላት ውሻ ፅድቅን ትመኛለች”. . . ከላያችን ያሉት ጌቶቻችን በምላስ ቁልቁለት ሲወርዱ እኛ እዚህ ስንትና ስንት አሪፍ ነገር እንጠብቃለን። ዳሩ ግን ዘንድሮ ነገራችን ሁሉ የምላስ ቁልቁለት የተግባር አቀበት ሆኖ ችግራችን በዝቷል።

በየቦታው፣ በየቢሮው፣ በየተቋሙ፣ በየመንግስት መስሪያ ቤቱ ስትሄዱ የአመት ዕቅድና አፈፃፀሙ ሁሉ “አራምባና ቆቦ” ሆኖ ታገኙታላችሁ። እንዲህም እናደርጋለን፤ እንዲያም እንፈፅማለን ሲሉ ቃላቸውን ተቀብለንና አምነን ለስንቱ አጨብጭበን ጉድ እንደሆንን ቤቱ ይቁጠረው። ይኸውና በ1997 ዓ.ም ለቤት ፈላጊዎች ተብሎ የመጣው የኮንዶሚኒየም ቤቶች የዕጣ ድልድል ከአስራአንድ ዓመታት በላይ ተጉዞ አሁንም ወገቡን ይዞ ለአስራ አንደኛ ዙር ዕጣ መጣሁ ሲለን ታዝበናል። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የኮንዶሚኒየም ነገር ከተገባው ቃል ጋር ሲነፃፀር እኛን አጨብጫቢ አድርጎ የሚያስቀር ይመስለኛል። ለምን አትሉም? የተመዘገበው ቤት ፈላጊ ኮንዶሚኒየሙን ከመረከቡ በፊት የምፅአት ቀን የሚመጣ ይመስለኛል።

እኔ የምለው የተስፋን ቃል በየአዳራሹ የሚያዘንቡት ወንበሮተኞቻችን ትንሽ እንኳን “ሼም” የሚባል ነገር አያውቁም እንዴ ጎበዝ!?. . . የምሬን እኮ ነው ድሮ -ድሮ በጨዋው ዘመን ተዘወትራ የምትነገር አንዲት አባባል ነበረች። “ቃል አትግባ፤ ቃል ከገባህ ግን ቃልህን አክብር፤ ምክንያቱም ቃል የእምነት ዕዳ ነውና” ትላለች።

ህዝብ አዳራሽ ሞልቶ የሚሉትን ሁሉ ሰምቶ፤ እልልል ብሎና አጨብጭቦ ሲያበቃ የተናገሩትን በተግባር እንደሚጠብቅ የሚዘነጉ አስተዳዳሪዎች ልባቸው ይገርመኛል። ይህን መሰል ትዝብት ያነገበው ወዳጄም “አጀብ!” የተሰኘውን ግጥም ካነበበ በኋላ የሚከተለውን ይቀጥላል፡-

አጨብጫቢው በዝቶ ላፍ ብቻ ሟቹ፤

ለሰረቀው መንገድ ፈጠረለት ምቹ።

እንዲህ አደርጋለሁ

እንዲህም እፈጥራለሁ፤

ይላል እንጂ መሪው

ነገር አሳማሪው

የተናገረውን በተግባር ማሳየት

መቼም አልተማረው።

አጨብጫቢው በዝቶ. . .

ተመቸው እልልታ፣ ተመቸው ጭብጨባ

በምላሱ ልሶ እሱ ብቻ ሰባ።

እናላችሁ ብዙ ቦታ ላይ “እቅድ ወዲህ ተግባር ወዲያ አይነት የአራምባና ቆቦ ተምሳሌት የበዛበት ጊዜ ሆኗል። ዕቅድ ሁሉ እንደቀልድ ለአዳራሽ ጭብጨባ ብቻ የሚታወጅበት ከተግባር የራቀ ከሆነ እኛስ ምን ተረፈን?. . . የመንገድ ሽፋን፣ የውሃ ሽፋን፣ የቴሌኮም ሽፋን፣ የመኖሪያቤት ሽፋን፣ የመብራት ኃይል ሽፋን የመልካም አስተዳደር ችግርን የመቅረፍ ሽፋን፣ የመንግሥት ሌቦችን ሰዶ የማሳደድ ሽፋን. . . ከዓመት አመት እቅዱና ተግባሩ በምላስ ቁልቁለት፤ በተግባር አቀበት እየሆነ ውጤቱ አስተዛዛቢ ሆኗል። ኧረ ጎበዝ ተቋማቱ ምን እየሰሩ ነው?

ለማንኛውም ለዛሬ ትዝብት አዘል ጭውውታችን ማሳረጊያ ይሆን ዘንድ ከጲላጦስ “ጥበብ - አንድ” መፅሐፍ ውስጥ ያነበብኳትን ወግ እንካችሁ። ወጓ የፍቅር ትምሰል እንጂ ለተናገሩት ነገርን፤ ለገቡት ቃል ዋጋ የሌላቸውን ሰዎች መጨረሻ የምታሳይ ናትና እነሆ፡-

አንድ ሰው ከአንዲት ወጣት በፍቅር ይወድቅና ቀንና ሌሊት አእምሮው በእሷ ሃሳብ ይያዛል። ጭንቀቱም ያይልና ዕለት - ተዕለት ሲከታተላት ሰንብቶ አንድ ቀን ተሳክቶለት በመንገድ ላይ ለብቻዋ ያገኛታል። በመንገድ ላይም አስቁሞ ከምንምና ከማንም በላይ እንደሚወዳት፤ ለሷ ያለው ፍቅርም የማይሞትና የማይጠፋ መሆኑን  መናገር ይጀምራል።

ወጣቷ የሰውዬውን የፍቅር ልመና ለጥቂት ጊዜ በትዕግስት ሰምታ አቋረጠችውና ጥያቄ ወረወረችለትት፣ “ቃላትህ ይጥማሉ፤ ነገር ግን እነዚህን የፍቅር ቃላት ለእህቴ ወርውረሃቸው ቢሆን ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር። እህቴን ብታያት ከእኔ በላይ እጅግ የተዋበች ቆንጆ ናት። ከእኔም በላይ እንደምታፈቅራት አልጠራጠርም. . .” አለችው።

አፍቃሪው ሰውዬ ይህን ሲሰማ እህቷን ለማየት ፊቱን ወደኋላ አዞረ። ይኸን ጊዜ ወጣቷ በእጇ ጀርባውን መታ መታ አደረገችው፤ “ለእኔ ያለህ ፍቅር የማይጠፋና የማይሞት ነው ስትለኝ አልነበረም? ነገር ግን አሁን በነገርኩህ እንኳን ፊትህን አዞርክብኝ። የምትናገረውን ፍቅር ትርጉሙን አታውቀውም።” ወጣቷ መንገዷን ቀጠለች።

ስለሚናገሩት ፍቅር፣ ስለሚደሰኩሩት ነገር፣ ስለሚገቡት ቃል እና ስለሚያፀድቁት ዕቅድ ተፈፃሚነት የማይታትሩና ቁርጠኝነት ከሌላቸው ሰዎች አንድዬ ይጠብቀን ።. . . ነገሩን ሁሉ ቀለል አድርገው በምላስ ቁልቁለት የሚወርዱ ሰዎች ለጊዜው ጭብጨባና ፉጨት ያገኙ ይሆናል። ዳሩ ግን በተግባር ላይ አቀበት ካደረጉት ልክ እንደቅዱስ መጽሐፉ ናቡከደነፆር እንዲህ እንላቸዋለን፤ “እነሆ ተመዘንክ ቀለህም ተገኘህ”. . . እናም ጎበዝ በመግቢያችን ያሰፈርነውን ግጥም በመውጫችን እንደግመዋለን፡-

“አጀብ”

ባዳራሹ ሙሉ

ሰው በሰው ሲጠበበብ፤

ተግባር መሬት ወድቆ

ላፍ እንዴት ይጨብጨብ!

                  ቸር እንሰንብት።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
742 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1081 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us