ክብራችን ሲገለብ!

Wednesday, 17 August 2016 12:33

                        ውሃ ክፍቱን አድሮ እንዳናጣ ጤና

ከዳድኜ እንደሆን ልየው እንደገና።

(እንዲል ባለቅኔ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?.... ሳምንቱ እንዴት አለፈሳ?... መቼም የ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ በአንድ ሳምንት ውስጥ መውረድና መወጣትን አሳይቶናል።… በዋና ውድድር ገንዳ ውስጥ ስንደፈቅ፤ በ10 ሺህ ሜትሩ የሴቶች ውድድር ደግሞ በአልማዝና በጥሩዬ እናሸበርቅ ዘንድ ተፈቅዶልናል።… እኔ የምለው ግን ዋናተኛችንን የአለምና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንዲያ ሲሳለቁበት ምን ተሰማችሁ?... የምሬን እኮ ነው፤ አሳነባሪው፣ ቦርጫሙ መባል ለኛስ ክብር ቢሆን አይደብርም? “ከዕዳ-ድኚ” እንደሆን ለየው እንደገና እንዳለው ባለቅኔ እስቲ እኛም በትዝብት መልክ ሰሞናችንን እንደገና እንመልከተው።

 

ከሁሉም ከሁሉም እኔን ያዝናኑኝ አባባሎች “ዋናተኛው ገንዳ ውስጥ አለመቅረቱ” የምትለዋ እና “ልጁ ከነቦርጩ በዓለም አደባባይ በድፍረት የቆመው የኢትዮጵያውያንን የርሃብ ዘመን ታሪክ መቀየሩን ለማሳየት ነው” የምትለዋ ነች። ለማንኛውም በዓለም አደባባይ ተወዳድሮ መሸነፍ ያለ ነው። ነገር ግን ከውርደት ጭምር መሸነፉ ትንሽ ደስ አይልም። እዚህች’ጋ በክብር መሸነፍ በራሱ እንደማሸነፍ ይቆጠራል ያለው ወዳጄ ትዝ አለኝ። ይኸውና በ3000 ሜትር ተወዳዳሪያችን እቴነሽ ዲሮ በአንድ እግር ጫማ በፅናት ሩጫዋን በማጠናቀቋ የነበራት ተጋድሎና ጥረት ታይቶ እንድታልፍ መደረጉን አይተን የለ? ይሄ ነው እንግዲ በክብር መሸነፍ ይሉት ነገር።

 

መቼም የዋና ፌዴሬሽኑ የሚወቀስበት ነገር ብዙ ነው። ያም ሆኖ ይህ ሳምንት ውርደቱንም አሸናፊነቱን እንዳናይ ሆኖ አልፏል። …. እዚህች’ጋ ከዋና ጋር በተያያዘ አንዲት የልጅነት ገጠመኝ ትዝ አለችኝ። ልጅ ሆነን የማያምረን የጨዋታ አይነት አልነበረም። የዛሬን አያድርገውና ከሰፈራችን ራቅ ብሎ የሚገኝ አንድ ወንዝ አለ። (የዛሬን አያድርገውና ያልኩት ዘንድሮ ወንዞቻችን የአተት መተላለፊያዎች እንጂ የዋናተኛ መፈልፈያዎች አይደሉምና ነው። ቂ…ቂ…ቂ!) ይህ ወንዝ ወዛችንን አጥፍቶ ነጫጭባ የሚያስመስለን ቢሆንም እንኳን በልጅነት የመጫወቻ ምርጫችን ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ ያለው ነው። ታዲያ አንድ የተረገመ ቀን የሰፈር ልጆች ተጠራርተን ከሰፈራችን ርቆ ወደሚገኘው ወንዝ ለመዋኘት ሄድን። በግምት አምስት፣ ስድስት ቢበዛ ሰባት እንሆናለን። ታዲያ ወንዙ አጠገብ እንደደረስን ሁላችንም ልብሳችንን እያወለቅን ወደወንዙ በዝላይ ጠለቅን።

 

ዳሩ ምን ያደርጋል፤ የወንዙ አካባቢ ልጆች የሆኑና በወቅቱ “ጉልቤ” የምንላቸው ጐረምሶች ድንገት ደርሰው እየተሳለቁብንና እየተሳሳቁብን አውልቀን የከመርናቸውን ልብሶች አንድም ሳያስቀሩ ይዘውት ከዓይናችን ተሰወሩ።…. ነገሩ እንግዳ ሆነብን። እርቃናችንን አፈር መስለን ወደሰፈር መመለስ የማይታሰብ ሆነ። ምን እንደምናደርግ ግራ እንደገባን ከመካከላችን አንደኛው “ለምን አንድ ሰው መስዋትነት ከፍሎ ወደቤት በመሄድ ከእያንዳንዳችን ቤት ልብስ ይዞልን አይመጣም?” የሚል ሃሳብ አቀረበ። ሃሳቡ ግን የሚሆን አልነበረም። (ልክ በአይጦች ጉባኤ በድመት አንገት ቃጭል እንደማጥለቅ አይነት ሃሳብ ነበር።) ሁላችንም ከቤተሰብ ተደብቀን የመጣን ነን። በዚያ ላይ ወንዝ ለመዋኘት ገብተው ተገኙ ቢባል ወላጆቻችን ለነገ አያስተርፉንም የሚል ስጋት ነበረን።

 

ያም ሆኖ ከሰባታችን መካከል ሁለት ጓደኞቻችን መስዋዕት ለመሆንና እርቃናቸውን ወደሰፈር ሄደው ልብስ ሊያመጡልን ተስማሙና አበረታተን ሸኘናቸው። ቂ…ቂ…ቂ… አቤት የዛኔ ከድንጋጤያችን በኋላ የሳቅነው ሳቅ አሁንም ድረስ አይረሳኝም። መስዋትነት ለመክፈል ቆርጠው ወደሰፈራችን እርቃናቸውን የሄዱት ሁለቱ ጓደኞቻችን በመንገድ ያያቸው ሰው ሁሉ ያዘነላቸው። እያማተበባቸው፤ የተገረመባቸው እየሳቀባቸው ሰፈር ደርሰው ልብስ ይዘውልን መጡ። (የኛን እርቃንነት በጀግንነት ጋረዱልን ማለትም አይደል?)

 

ከዚያን ጊዜ በኋላ የወንዝ ዋና ነገር እርም አልን። ይኸውና አሁን ከአመታት በኋላ አገራችን ኢትዮጵያ በዋና ስፖርት እንዲህ የውርደት መዓት ስትከናነብ “ወይኔ ያኔ ዋናችንን ጠንክረን በሰራን ኖሮ” ሳልል አልቀረሁም።…. መቼም ሰሞኑን ከሚሰሙት ትዝብት አዘል ማጉረምረሞች መካከል “ዕድሉን አጥተን እንጂ እኛ እንሻል ነበር” የሚለው ይበረክታል። ለማንኛውም ፍትሐዊ ምርጫ አልተካሄደ እንደሆን የውሃ ዋና ስፖርት ፌዴሬሽን አሰራር በብዙ ተቋማቶቻችን ውስጥ የሚመነዘርን ችግር ያሳየ ነው ብለን በትዝብት አንሳለቅበት ዘንድ ግድ ነው።

 

ለማንኛውም በዚህ የሪዮ-ኦሉምፒክ እንደ ሀገር ከዋና ገንዳ ውስጥ እርቅናችንን በሃፍረት ስንወጣ፤ አልሚና ጥሩዬ ደግሞ በወርቅና በነሃስ በዓለም አደባባይ የተገለበ ክብራችንን በጀግንነት ጋርደውታል። ከልብ እናመሰግናቸዋለን።…. ከተወዳዳሪዎቹ በላይ ኮሚቴዎቹ፣ ከህዝቡ በላይ መሪዎቹ፣ ከቀበሌ ነዋሪው በላይ ሊቀመንበሮቹ፣ ከተቋሞቹ በላይ አለቆቹ የሚመቻቸውን ብቻ የሚያደርጉና ሁሉንም ነገር እኛ እንዳልነው ወይም እኛ አንደመረጥነው የሚሉ ከሆነ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሀገርም እንዲህ እንደሰሞኑ እርቃኗን ልትቀር ትችላለች ልብ ያለው ልብ ይበል።

 

እዚህች’ጋ ከመሰነባበታችን በፊት ከድምፃዊና ኮሜዲያን ይርዳው ጤናው ዘፈን ውስጥ የሚከተሉትን ወሳኝ ስንኞች እነሆ፤

አይደለም ከሀገሩ ወይም ከፈረሱ፣

እንደጋላቢው ነው እንዳደራረሱ።

እውነት ነው እንደጋላቢያችን ነው። አገር የሚያልቡ፣ ህዝብን የሚጋልቡ፣ ተቋማትን የሚጋልቡ፣ ፓርቲዎችን የሚጋልቡ፣ የሃይማኖት ተቋማትን የሚጋልቡ፣ የኦሎምፒክ ቡድናችንን የሚጋልቡ ፍትህ ተቋማቱን የሚጋልቡ፣ ቤተሰብንም ቢሆን በአባወራነት የሚጋልቡ ሁሉ የአገላለባቸውን ትክክለኛነት እና ሚዛናዊነት ልብ ሊሉት ይገባል። ግጥሙን እንደግመዋለን፡-

 

አይደለም ከሀገሩ ወይም ከፈረሱ

እንደጋላቢው ነው እንዳደራረሱ።

ወደ ሰላምና አንድነት፤ ወደመተሳሰብና ፍቅር፣ ወደፍትህ፣ ወደሞራልና ሰብዓዊነት የሚጋልቡ ጋላቢዎችን አንድዬ አያሳጣን አቦ! ቸር እንሰንብት።¾   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
523 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 926 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us