አንድም ሰው ብዙ ነው!

Wednesday, 24 August 2016 14:07

 

ጎበዝ እንደምን ሰነበታችሁ?!. . .

የወንበሩ ምቾት ሁሉን ካስረሳሽ

እኔ ነኝ ሌላዋን የምተካብሽ።

           (ያለው አዝማሪ ማን ነበር?)

 

እኔ የምለው የመተካካቱ ውጤት እምን ላይ ደረሰ?. . . ልክ ነዋ የስልጣን ሸግሽጉ ተገምግሞ ውጤቱ ይፋ ቢደረግ ምን ይለናል?. . . የስልጣን ነገር ከተነሳ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ጉዳይ በፍፁም እንዳንረሳ። ሶስት ኦሎምፒኮችን ሳይለውጥ ከቀጠለው እቅዳቸው ጋር ወይ ይቀጡ አልያም ይለወጡ።

መቼም ሰሞኑን በምንሰማውና በምናየው ዜና ውስጥ ሁሉ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች” አይጠፉም። እኔ የምለው እነዚህ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” እንዲህ በዝተውና ድምፅ አግኝተው ስንሰማቸው፤ አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎንስ ምነው ልካቸውን ብናውቅ። የምር ግን ይህቺ “አንዳንድ” የሚሏት አገላለፅ አትመቻችሁም?. . . በተለይ በተለይ የመንግስታችን ወንበር የሚነቀንቁና፤ አደባባዮችን በአቤቱታ የሚያደምቁ ሲሆን “አንዳንድ ፀረ- ሰላም ኃይሎች” የምትለዋ አገላለፅ ትመቸኛለች።

ጎበዝ እስቲ ልጠይቃችሁ “አንዳንድ” ማለት ስንት ነው?. . . ፊልሙ ላይ አይታችኋል አይደል? ሰውዬው ስድስት ቁጥር ፃፍኩ ብሎ ወረቀቱን ለአንደኛው ሰውዬ ሰጠው። ወረቀቱን ገልብጦ ያነበበው አንደኛው ሰው “ዘጠኝ ነው!” ሲል ሌላኛው “ስድስት ነው!” እየተባባሉ ይከራከራሉ። . . . እናም የኛም “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” እና “አንዳንድ ፀረ - ሰላም ኃይሎች” ቁጥራቸው እንደስድስት እና እንደዘጠኝ ግራ የሚያጋባ ሆኖብኛል።

 

የሰሞኑን “የአንዳንዶች” ጉዳይ የታዘበ አንድ ወዳጄ ግን ምን ሲል ሰማሁት መሰላችሁ?. . . “አንድም ሰው ብዙ ነው!” ጎሽ አትሉልኝም። እውነቱን እኮ ነው። ዋጋ ከሰጠነው አንድም ሰው ቢሆን ብዙ ነው። (እዚህች ጋ ድምጹን ዝቅ አድርጎ ማንን ቢያስታውሰኝ ጥሩ ነው? የዘንድሮ የሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ጀግናችንን ፈይሳ ሌሊሳ! . . . በነገራችን ላይ “ከነገሩ አነጋገሩ” የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ካስገኘው ብር ይልቅ የፈፀመው ወርቅ አስገኝቶለታል ማለታቸውን ሰምቼ አሁንም ድረስ ድንቅ ብሎኝ አለሁ።)

እናላችሁ ዘንድሮ የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር እና የአንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ቁጥር ለየቅል ሆኖ ለመረዳት ቸግሮናል። የቁጥርና የአቆጣጠርን ነገር ካነሳን አይቀር ከዚህ ቀደም ሰምታችኋትም ቢሆን እንኳን የዛሬ ትዝብታችንን ታደምቅልናለችና ተከታይዋን ወግ እንካችሁ፡-

 

አንድ የኔቢጤ ምስኪን ዕድል ቀንቶት አንድዬን ፊት ለፊት ያገኘዋል። “እኔ የምልህ አንድዬ አንተ ዘንድ የጊዜ አቆጣጠር እንዴት ነው? ለምሳሌ አንድ ደቂቃ በአንተ ዘንድ ስንት ነው?” ሲል ይጠይቀዋል። አንድዬም በሰውዬው አጠያየቅ ፈገግ እንደማለት እየቃጣው፣ “በኔ ዘንድ አንድ ደቂቃ ማለት አንድ መቶ አመት ማለትነው” ሲል መለሰለት። በአንድዬ ምላሽ በእጅጉ የተደነቀው ምስኪን ሰውም ለጥቆ፣ “ለመሆኑስ የአንድ ብር ዋጋው በአንተ ዘንድ ስንት ነው ጌታዬ?” ሲል ጠየቀ። አንድዬም “በኔ ዘንድ አንድ ብር ማለት አንድ ሚሊዮን ብር ማለት ነው” ሲል ለጥያቄው መልስ ሰጠው በዚህ ጊዜ የኔ ቢጤው ምስኪን ሰው የአንድዬን በረከት ለማግኘት እየቋመጠ “እንግዲያውስ አንድዬ እስቲ ለኔ ለምስኪኑ አንድ ብር ስጠኝ” ሲል ለጠየቀው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ፣ “መልካም አንተ ሰው ሳትለፋ ሳትደክም ከኔ አንድ ብር የምትፈልግ ከሆነ አንድ ደቂቃ ብቻ ታገሰኝ እሰጥሃለሁ” ብሎት ሄደ ይባላል።

 

የአንድዬን አንድ ደቂቃ ስሌትና የምስኪኑን ሰውዬ የአንድ ብር (የአንድ ሚሊዮን ብር) የማግኘት ጉጉት ሳስበው፤ ድቅን የሚልብኝ በቲቪ የሚታዩት “አንዳንድ” የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና “አንዳንድ” ፀረ-ሰላም ኃይሎች ቁጥር ነገር ነው።

 

ለማንኛውም ወዳጄ እንዳለው፤ “አንድም ሰው ብዙ ነው!”. . . በምድር ላይ አንድ ብቻቸውን ሆነው መዓት ለውት (ነውጥ አላልኩም) ያመጡ ሰዎችን መጥቀስ ይችላል።. . . በክፉም ይሁን በደጉ፤ በፀቡም ይሁን በፍቅር፣ በመንጠቁም ይሁን በመስጠቱ፤ በመምራቱም ይሁን በመመራቱ፤ በፅናቱም ይሁን በእብለቱ በርካታ ሰዎች አለማችን አስተናግዳለች።

 

“አንድም ሰው ብዙ ነው!”. . . የሚያስብሉ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል እንደፍጡር ኢየሱስ፤ ማንዴላ፣ ማህተመ ጋንዲ፣ አልበርት አነስታይን፤ ሶቅራጦስ፤ ማርክ ዙከንበርግ እና ሞዛርትን በገደምዳሜ መጥራት እንችላለን።. . . እነዚህ “ሰዎች” አንድ ይመስላሉ እንጂ ብዙ ናቸው። . . . ጠላቶታቸው ቢያሳንሷቸውም ቢያንኳስሷቸውም፤ ቢያስሯቸውም ሆነ ቢገድሏቸው አንዳንድ ሰዎች ማለት ብዙዎች መሆናቸውን በህያው በታሪካቸው ማሳየት የቻሉ ናቸው።

በስተመጨረሻም በዚህ ሳምንት በድጋሚ ለህትመት ከበቃው የደበበ ሰይፉ የግጥም መድብል ውስጥ “በደል” የተሰኘውን ተገባብዘን ብንሰነባበት ምን ይለናል?ምንም።

 

በደል

ዝናብ ቢኖር በጃችሁ

      ምን ያደርጋል፤

አንዲት ጠብታ ሞታችሁ!

አዝመራችሁን ወፍ አይቀምሰው

የለማኝ አቆፋዳ አያውቀው።

እንደሌላው አንድ አፍ ሲፈጥርላችሁ

      አይደል የበደላችሁ?

ያዘመራችሁትን እንዳትበሉ

የጎሮሮአችሁ ጥበቱ።

ያላችሁን እንዳታድሉ

የእጃችሁ እጥረቱ።

      (ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ፤ የብርሃን ፍቅር ቅፅ -2)

      ቸር እንሰንብት! !!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
536 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 994 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us