“አልሸሹም ዞር አሉ”

Wednesday, 31 August 2016 12:22

 

እንደምን ሰነበታችሁ ጎበዝ!? . . . ሰውዬው በጣም ስካር ያጠቃዋል። ባለቤቱ ከትዳር አማካሪዋ ጋር ተነጋግራ ሰውዬው መጠጡን እንዲቀንስ ለማድረግ እየጣረች ነው። እናም ከቀናት በኋላ የሰጣትን ምክር ውጤት በተመለከተ ሊነጋገሩ የትዳር አማካሪው ቢሮ ተገኘች። “ባለፈው ጊዜ እንደነገርኩሽ ባለቤትሽ አዘውትሮ የሚጠጣባቸውን ብርጭቆዎች ሰወርሽበት አይደል?” ጠየቃት አማካሪው፣ “አዎ አንድም የብርጭቆ ዘር በቤቴ ውስጥ የለም” ሚስትየው መለሰች። አማካሪው ቀጠለና “ታዲያ ባለቤትሽ ብርጭቆ በማይጨብጥበት ወቅት ምን ያደርጋል?” ለውጡን ለመስማት እንደጓጓ ጥያቄውን ሰነዘረ፣ “ብርጭቆ በማይጨብጥበት ጊዜ ሁሉ ጠርሙሱን መታቀፍ ጀምሮልሃል” ብላላችሁ እርፍ። ቂ-ቂ-ቂ-! “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም” የሚሉት አበው ይሄን ጊዜ ሳይሆን ይቀራል።  ዘንድሮ በነገራችን ሁሉ አልሸሹም ዞር አሉ ነገር አልበዛበትም ብላችሁ ነው?

 

የምሬን እኮ ነው፤ “አንድን የማይረባ አሰራር ለማስቀረት ሌላ የሚረባ አሰራር ማምጣት፤ አንዱን መጥፎ ነው ለማለት ሌላ መጥፎ ነገር መፍጠር፤ አንዱን ክፉ ለማስባል ስንጥር ራሳችን ክፉ ሆነን መገኘት፤ አንዱን ለስራው ብቁ አይደለም ልቀቁ ስንል ሌላው ብቁ ያልሆነ ባለሙያ/ ባለወንበር በቦታው የመተካካታችን ነገር ሁሉ “አልሸሹም ዞር አሉ” አይነት ከሆነ ከራርሟል።

 

በተለይ ደግሞ የመንግስታዊ ተቋሞቻችን የክብ ሩጫ በኛ ለነዋሪው አዙሪት እንደሆነብን ሳትታዘቡት የቀራችሁ አልመሰለኝም” . . . መብራት ኃይል መንገዳችንን ይቆፍራል። ምነው፤ ስንለው መብራት ልዘረጋላችሁ ነው ይለናል። ይሁን ብለን ዝም እንላለን። ለመብራት ዝርጋታ የተቆፈረው መንገድ ግን ለኛ ለነዋሪዎቹ መሰናክልም መሰባበርንም ያሳየናል። ይቀጥላል ደግሞ ውሃ ልማት። አንዲት ጠብታ ብርቃችን ለሆነብን ለኛ ሲል ሰፈር ይቆፍራሉ። አንዳንዴ ሳስበው ሰዎቹ የውሃ መስመር ለመዘርጋት ይሁን የባቡር ሃዲድ አይገባኝም። . . . ይቀጥልና መንገዶች ባለስልጣን ይመጣል። መንገዳችንን ቆፍሮ ቀናትን ያስቆጥረናል። ምነው ስንለው “ቱቦ ልዘረጋላችሁ ነው” ይለናል። እኛም ይሁን ብለን ዝም እንላለን። ይዘረጋል የተባለው ቱቦ ቀርቶ ስንቱ የኔ ብጤ በጉድጓድ ተደፍቶ እንዳይሆን ይሆናል። መብራት የለ፤ ውሃ የለ፤ መንገድ የለ።. . .  ይለጥቅና ደግሞ ቴሌ ይመጣል። በስንት ጥበቃ ያለቀውን መንገድ መቆፈር ይጀመራል። ምነው? ስንለው ኔትዎርክ ዝርጋታ ነው ይለናል፤ ይሁና ብለን ዝም እናላለን። ዳሩ ግን መንገዱን ቆፍሮ ዘረጋው ያለውን ኔትዎርክ አስቀብሮ ሲያበቃ ድንገት ጥሎን ይሄዳል። ከቀናት በኋላ ሰው ይጎዳል። ለአምቡላንስ ድረሱልን ለማለት ስልክ ስንደውል ኔትወርክ የለም።

 

እናላችሁ መንገዱም በአግባቡ አልተሰራ፤ መብራቱም በጊዜው አልበራ፣ ስልኩም ማዶ ለማዶ አላዋራ፣  ውሃውም አንድ ብርጭቆ አልሞላ ካለን ምን ዋጋ አለን ጎበዝ!?. . . ነገራችን “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዲሉ ከሆነ በስራችን ሁሉ ኃላፊነት ከመቀበል ይልቅ የእምዬን ወደአብዬ እያዟዟርን “አልሸሹም ዞር አሉን” ዓይነት ተረቶች የምናስተርት በየመልኩ በዝተናል።  

 

እናላችሁ ለጠየቅነው ጥያቄ ሁሉ መልሱን ወደገደለው እንዲሉ መስጠት ሲቻል እንዳምና ካቻምናው አይነት መልስ መስጠት በራሱ “አልሸሹም ዞር አሉ” ያስብለናል። . . . ከሁሉም - ከሁሉም ምን ይገርምሃል አትሉኝም። አለቃን የፈራ ምንዝር ዘንድ አንድ ጉዳይ ወደቢሮው ይዛችሁ ስትሄዱ በቀጥታ ወደ አለቃው ይመራችኋል። አለቅዬውም በስልጣኑ ልክ የሆነውን ስራ/ፊርማ እንደመፈፀም መልሶ ወደምንዝሩ ይልካችኋል።. . . ከአለቃ ወደምንዝር ከምንዝር ወደ አለቃ ስንወዛወዝ ትዝ የሚለን ዘፈን የድምፃዊ ጌትሽ ማሞ ስራ ነው።

 

አንቺም አባወራ፣ እኔም አባወራ

ግራ ገባው ቤቱ በማ እንደሚመራ።

 

አንድዬ ብቻ ግራ ከመጋባት አውጥቶ፤ ከአልሸሹም ዞር አሉ የፀዳ መፍትሄን አያሳጣን አቦ! እናላችሁ ላይሸሹ ዞር ከማለት ምን ይሻላል መሰላችሁ?. . . “ከማይረባ ጉልበት ልብ አርጉልኝ ማለት” ማንን ገደለ ጎበዝ!?. . . እዚህች ጋ እስቲ ከመሰነባበታችን በፊት ጳውሎስ ኞኞ ከፃፈው የአፄ ቴዎድሮስ የታሪክ መፅሐፍ ውስጥ የተቀነጨበች ወግ እንካችሁ።

 

ታሪኩ ደጃዝማች ካሳ ከእቴጌ መነን መማረክ በኋላ የተከሰተ ነው። ከእቴጌ መማረክ በኋላ ልጃቸው ራስ አሉላ ከጎጃሙ ገዢ ከደጃዝማች ጎሹ ጋር በአንድነት ሆነው ካሳን ለመውጋት ወደ ደንቢያ ዘመቱ። ካሳም ከአንድ ላይ ተሳፍሮ የመጣባቸውን ከፍተኛ ሰራዊት ነጣጥሎ ካልሆነ አንድ ላይ መውጋቱ አደጋ እንዳለው አመዛዘኑና ደንቢያን ለቀው ወደትውልድ ቦታቸው ቋራ ሸሹ። ራስ አለም የካሳን መሸሽ እንዳዩ ደጃዝማች ጎሹን የደንቢያ ገዢ አድርገው ሾሟቸውና ወደጎንደር ተመለሱ።

 

ደጃዝማች ጎሹ ከነበራቸው የጎጃም ግዛት ላይ ደንበያ በመጨመሩ በጣም ተደሰቱ። ደንቢያ ሆነውም ጦራቸውን በየአካባቢው አሰማሩ። የራስ አሊን ርቀው መሄድ ያወቁት ካሳ ደጃዝማች ጎሹን ለመውጋት ጉርአምባ ወደተባለ ቦታ ጉዞ ጀመሩ። ይህንን የካሳን ጦር መንቀሳቀስ የሰሙት ደጃዝማች ጎሹም ጦራቸውን ከያለበት አሰባሰቡና ጣፋጭ የሚባል የደጃዝማች ጎሹ አዝማሪም በተሰበሰበው ሰራዊት መሀል ገብቶ፤

 

አያችሁት የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ሆኖ ጉርአምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሳ፣

ወርደህ ጥመድበት በሸንብራው ማሳ።

 

 በማለት በካሳ ላይ በግጥም ተሳለቁ። የካሳና የደጃዝማች ጎሹ ሰራዊቶችም ውጊያ ጀመሩ። ደጃዝማች ጎሹ በፈረስ ላይ ሆነው እያዋጉ ሳለ በጥይት ተመቱና ወደቁ። ድሉም የካሳ ሆነ። በዚህ ጦርነት ካሳ ብዙ ሃብትና ምርኮ አገኙ። ጣፋጭ የሚባለው አዝማሪም ተማርኮ ነበርና ካሳ  ፊት ቀረበ። ካሳም፣ “ምን ብለህ  ነው የሰደብከኝ?” ብለው ጠየቁት። አዝማሪውም አሳስቋቸው እንዲምሩት በመፈለግ፡-

 

አወይ የግዜር ቁጣ

አወይ የአምላክ ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ስራ ሲያጣ

ብትር ይገባዋል የአዝማሪ ቀልባጣ።

 

በማለት ገጠመ። ካሳም ቂም ይዘውበት ስለነበር አዝማሪው በራሱ ላይ የሰጠውን ፍርድ መሠረት አድርገው በዱላ ተደብድቦ እንዲገደል ፈረዱበት ይለናል።

“ከማይረባ ጉልበት ልብ አርጉልኝ ማለት” አስፈላጊ እንደሆነ ተረዳችሁኝ አይደል?. . . ቸር እንሰንብት።    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
626 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1054 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us