የመተንፈሻም፤ የማስተንፈሻም ያለህ!

Wednesday, 07 September 2016 14:03

 

መጪውን አዲስ ዓመት ሳናየው እንዳያልፍ ስጋት አለን ጎበዝ . . . ነገራችን ሁሉ ድፍንፍን - ጭልምልም እየሆነ በአያሌው ተቸግረናል። . . . እናም ያላየነው አዲስ ዓመት መዓት ይዞብን እንዳይመጣ በፀሎት እንተጋለን። ወይ ደግሞ በምትሃትም ቢሆን ነገሮች ተስተካክለው በአዲስ ዓመት፤ በአዲስ መንፈስ እንገናኝ ዘንድ ምኞታችን ነው።. . . ኧረ ጎበዝ ጊዜው እኮ መተንፈሻም፣ ማስተንፈሻም የሚያስፈልገው ነው።

እኔ የምለው ህዝቤ መተንፈሻም ማስተንፈሻም ጠፍቶት ሲቸገር ጠቅላያችን ድንገት ከች ብለው ኢህአዴግ አሁንም ተማሪ መሆኑን ግልጽ አደረጉልንም አይደል? ጎሽ ጎበዝ እንዲህ ግልጽ ግልጹን መነጋገር ሳይሻለን አይቀርም። ዳሩግን ምን ያደርጋል ምን አይነት ተማሪ እንደሆነ ጠቅላያችን አልነገሩንም።

 

አውራው ፓርቲ በ25 ዓመት አፍላ ዕድሜው ገና ተማሪ መሆኑን ስሰማ፤ “ለትምህርት መቼም ቢሆን ዕድሜ አይገድበውም” ከምትለዋ መፈክር ቀጥሎ ትዝ ያለችኝ የአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ዘፈን፡-

 

ተማሪ ነኝ አልገባኝ

የምታውቁ አስረዱኝ. . . የምትለው ናት!

 

ይልቅዬ የተማሪ ነገር ከተነሳ ይህቺን ጨዋታ እንካችሁ፤. . . መምህሩ በመቅረትና በማርፈድ የተማረሩበትን ተማሪ ፊት ለፊት ያገኙትና፣ “ለመሆኑ ትላንትና ስለመቅረትህ መፃፍ የነበረበት የወላጆችህ ማስታወሻ የታል?” ሲሉ ይጠይቁታል። ተማሪውም ኮስተር ብሎ፣ “እማዬ ዛሬ ጠዋት ስራ ሲለበዛባት ልትፅፍልኝ አልቻለችም” ሲል መለሰ። በዚህ ጊዜ መምህሩ እንደመቆጣት ብለው፣ “ታዲያ አባትህ አይጽፍልህም እንዴ? ከማለታቸው ተማሪው ፍጥጥ ብሎ ምን ቢመልስላቸው ጥሩ ነው? “ቲቸርዬ እሱማ ምክንያት መፍጠር አይችልበትም። ሰበብ በፈጠረ ቁጥር ሁሌም ቢሆን እማዬ እንደነቃችበት ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ለማንኛውም አዲሱን ዓመት የመነቃቃት ያደርግልን አቦ!

 

እግረመንገዳችንን የመተንፈሻና የማስተንፈሻ ነገራችን ቢታሰብበት ጥሩ ነው። የምሬን እኮ ነው፤ ይህው በክረምት አዲስ አበባ ውስጥ ዝናብ በዘነበ ቁጥር መኪኖችን ሁሉ እንደታንኳ እንድንቆጥር ተገደድን እኮ ጎበዝ!. . . የዚህ ሁሉ ችግር የመንገዳችን አሰራር እና የማስተንፈሻ ቱቦ አለመኖር ወይም በአግባቡ አለመሰራት ነው። መተንፈሻም ሆነ ማስተንፈሻ አይደለም ለሰው ለመንገድም ቢሆን ያስፈልጋል። አንድ ወዳጄ ሰሞኑን ከዝናብ በኋላ ቀጠሮ ነበረንና ደወልኩለት። የት ነህ ስለው “ብሔራዊ አካባቢ ነኝ” አለኝ። ምን እየሰራህ ስለው “እንደልጅነቴ ታዝዬልሃለው” ብሎ አሳቀኝ። ለካንስ በከተማይቱ እንብርት ላይ ጎርፍ አስፓልቱን ሞልቶት ሰው ሁሉ በአዛይ ሞግዚቶች ነበር የሚንቀሳቀሰው። ቂ-ቂ-ቂ

 

ለማንኛውም መተንፈሻውም ሆነ ማስተንፈሻው የሚያስፈልገን ለጎርፍ ብቻ እንዳልሆነ “አለቆቻችን” ልብ ሊሉት ይገባል። እንደውም እንደዘንድሮ ማስተንፈሻ የሚያስፈልግበት ጊዜ የለም። (አንድዬ እድሜውን በዕጥፍ ድርብ ይጨምርለትና የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ባይኖር ኖሮ ስንት ነገራችንን አፍነነው በፈነዳን ነበር)

 

እናላችሁ መተንፈሻም ማስተንፈሻም የሚሆን ነገር በእጅጉ የሚያስፈልገን ጊዜው አሁን ነው። . . . ግልጽና ክፍት ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የምንተነፍስበት አደባባይ (ሚዲያ) ያስፈልገናል። ከዘረኝነትና ከመፈራረጅ ወጥተን ጉዳዮቻችንን በቀናነት የምንተነፍስበት መድረክ ያስፈልገናል። ካልሆነ ግን ዘረኝነትና መፈራረጅ ጎርፍ ሆነው ያጥለቀልቁናል።

 

ልዩነታችንን በአንድነታችን በኩል ማስተንፈስ ካልቻልን፤ ጥርጣሬያችንን በመተማመን ማስተንፈስ ካልቻልን፤ ጥላቻችንን በፍቅርና በይቅር ባይነት ማስተንፈስ ካልቻልን፤ ቂማችንን በካሳ ማስተንፈስ ካልቻልን፤ መካረራችንን በመነጋገር ማርገብ ካልቻልን በስተመጨረሻ ሰዓት ነገራችን ማስተንፈሻና መተንፈሻ ሲያጣ እኛኑ እንደሚያጥለቀልቀን የክረምቱ ጎርፍ እንደሚሆን፤ “ስልጡን ነው” ያልነው የአዲስ አበባ መንገድ በገሃድ ማሳያችን ይመስለኛል።

 

በስተመጨረሻም የምንናገረውን የሚሰማ ህዝብና የምንሰብከውን የሚያስታውሰን ምዕመን ማግኘት ሸጋ መሆኑም የምትጠቁም አንዲት ጨዋታ እነሆ፤ ከአንድ ገዳም ፊት ለፊት ባለሜዳ ላይ ልጆች ኳስ ይጫወታሉ። በየጊዜው ኳስ ወደገዳሙ በተጠለዘ ቁጥር መነኩሴዎቹ እየተረበሹ ተቸገሩና ማንም ሰው ወደገዳሙ ዘልቆ እንዳይገባ በማሰብ፤ “ማለፍ ሃጢያት ነው” የሚል ማሳሰቢያ በሩ ላይ ለጠፉ። ሆኖም ከአፍታ በኋላ ከማሳሰቢያው ስር የሚከተለው ፅሁፍ ተጽፎ ተገኘ፣ “እባካችሁ ሃጢያታችንን ይቅር በሉን!” ገበዝ በርን ጥርቅም አድርጎ ከመዘጋጋት ይልቅ ሃጢያትን ይቅር እንደመባባል ምን መልካም ነገር አለ? ምንም።

 

ይህን “አሮጌ ዘመን” ከመሰነባበታችን በፊት ግን 2008ን ባሰብኩ ቁጥር ድቅን የሚልብኝ “የማታ እንጀራ” ከተሰኘው የዓለምጸሐይ ወዳጆ የግጥም መድብል ውስጥ “ስንት ቀን ይፈጃል?” ስትል የጠየቀችበትን ግጥም “ሼር” ላድርጋችሁ።

 

ስንት ቀን ይፈጃል?

ስንቱ በበሽታ ስንቱ በጦር ሜዳ

ስንቱ ሰው በጥይት ስንቱ በረሃብ ፍዳ

በሞት እያለቀ እየተቀጠፈ

እውነት እየሸሸ ጊዜው እያለፈ

እግዚኦ! አቤት! እንቢ! የማንለው ምነው?

እንዳላየን አይተን ሰምተን እያወቅነው።

ስንት ሰው ይታሰር? ስንት ሰው ይበደል?

ምን ያህል ሰው ይለቅ? ስንት ሰው ይገደል?

እንዲያንገሸግሸን እንዲበቃን በደል።

ስንት ቀን ይምሽልን? የስንት ለሌት ይንጋ?

ገብቶን እንድንጠይቅ የነፃነት ዋጋ

አምባገነንነት ጉልበት ሳይበግረው

መብት እንዲረጋገጥ ህግ ሃይል እንዲኖረው

ስንት ቀን ይቀራል? ስንት ሰው ዕድሜ?

ገደብ ለማበጀት ለበደል ፍጻሜ

 

“ለመኖር ብቸኛው አማራጭ ሌላው እንዲኖር መፍቀድ ነው” እንዲል መሐተመ ጋንዲ፤ እኛ መተንፈሻም ሆነ ማስተንፈሻ እናገኝ ዘንድ ሌላው እንዲተነፍስ መፍቀድ ግድ ነው። እናላችሁ ዘመን ከሚያስቆጥር የፍትህ መጓደል አንድዬ ይጠብቀን፤ እናም መተንፈሻም ማስተንፈሻም አያሳጣን። መልካም አዲስ ዓመት። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
501 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 967 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us