ግብር እስከመቃብር

Thursday, 01 December 2016 15:21

 

የወደደ

ዓለምን የወደደ፣

እንደዴማስ ሄደ።

አምላኩን የወደደ፣

እንደጴጥሮስ ካደ።

(አርነት የወጡ ሃሳቦች፤ ከተሰኘው የዳዊት ፀጋዬ የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ጎበዝ!? . . . አንዳንድ ጊዜ ነገራችንን ለማሳመር ሀበሻ ለወደደው ሟች ነው” ሲባል እንሰማለን። እውነት ይሆናል፤ ግን አንድ ነገር አለ፤ ማንም ሰው ቢሆን አንድን ነገር ከልቡ ከወደደ የምር ለወደደው ነገር  ሟች ነው ማለት ይቻላል። . . . መውደድ ወይም ፍቅር ደግሞ ከነገር ይልቅ በተግባር ሲገለፅ ነው የሚያምረው። እናም ሀበሻ አንድ ሰው ለሚወደው ነገር ሲል (በክፉም ይሁን በደግ) ምግባሩ መቃብሩ ድረስ ሲከተለው፤ ሁኔታውን ታዝቦ፣ “ግብር እስከመቃብር” ይለዋል። አመል ያወጣል ከመሀል ብቻ ሳይሆን አመላችን መለመላችንን እስክንቀብርም ድረስ አብሮን ይዘልቃል እንደማለት መሆኑ ነው።

እስቲ ደግሞ ለዛሬ “ግብር እስከመቃብር” የሚለውን ርዕስ ስታነቡ ትዝ ካላችሁ መፅሐፍ አንድን አንቀፅ በመውሰድ ልጀምር። እርግጠኛ ነኝ፤ “ግብር እስከመቃብር” የምትለዋን ሀረግ ስታነቡ “ፍቅር እስከመቃብር” የተሰኘው የደራሲ ሃዲስ አለማየሁ ጎምቱ ረጅም ልቦለድ መፅሐፍ ድንገት ብቅ ብሎላችሁ እንደነበር ይሰማኛል። እናም ዝም ብለን ወጋችንን ከመለጠቅ ከመፅሐፉ “ሰላሳ አራተኛ” ምዕራፍ ላይ የሚገኘውን “ፍቅር እስከመቃብር” የተሰኘውን ንዑስ ትረካ የመጀመሪያ አንቀፅ እንካችሁ ብዬ ልለፍ። . . . “አባይ ለቆላው የመኪና መንገድ ለወንዙ ድልድይ ሳይሰራለት ከጎጃም ወዳዲስ አበባ፤ ካዲስ አበባ ወደጎጃም የሚሄድ መንገደኛ ሁሉ ጎሀ ፅዮን ወይም ደጀን እስኪደርስ ድረስ ልኮ የመከራ ትንቢት እንደተነገረበት ሰው ካሁን አሁን መከራ ደረሰብኝ ብሎ ልቡ እየፈራና እየራደ የሚያልፍበት ቦታ ነበር።” ሲል የመጨረሻውን ምዕራፍ የመጀመሪያ አንቀፅ ይተርካል።  

እስቲ ደግሞ ወጋችንን ከፍቅር እስከመቃብር ጣፋጭ አንቀፅ ወደ “ግብር እስከመቃብር” መሳጭና ሰቅጣጭ ትርከት እናዙር። የምር ግን የአንዳንድ ሰው ተግባር እስከመቃብር የሚደርስ አይመስላችሁም?. . . ስራቸው እስከመቃብራቸው ከተከተላቸው ጨዋታ አዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከል በቀዳሚነት አለቃ ገብረሃና ይጠቀሳሉ። አለቃ በርካታ ጨዋታና ሽሙጦችን ታሪክ አድርገዋል። እርሳቸው በሞት ተለይተውን እንኳን አሁን ድረስ ቀልዶች በስማቸው እየተፈበረኩና እየተነገሩን ይገኛሉ። ይህን ካነሳን ዘንዳ የአለቃ ነገር እስከመቃብር ለማሳየት ያክል በአረፋይኔ ሐጎስ “አለቃ ገብረሃና እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው” ከተሰኘው  መጽሐፍ የሚከተለውን ቁንጽል ታሪክ እንወስዳለን። ታሪኩ በአለቃ ዕድሜ በስተመጨረሻ ዘመን የሆነ ነው፤. . . “ጥቂት እንደቆ በጨዋታ የተነሳ አንዱን ካህን ተርበው ቢያስቁባቸው ካህኑ፣ “በሰማይ ቤት እንዳይኮነኑ እንዲህ አይነቱን ነገር ቢተው ይሻላል” አሏቸው። አለቃ ግን እየሳቁ፣ “እስካሁን የሞተው ሰው ሁሉ ስፍራውን ሞልቶታልና ለኔ ስፍራ ስለማይኖር አያስቡ” ሲሉ መለሱላቸው። ቢሆንም እርጅና ጓዙን ከቶ መጣ። አለቃ በጠና ታመው ሲፈራገጡ ጎረቤታቸው የሆነ አንድ ቆዳ አልፊ ሊጠይቃቸው መጥቶ “ዛሬስ ደከሙ መሰለኝ?” ቢላቸው፣ “እንግዳውማ ቆዳ ሳለፋልህ ልኑር?” በማለት ሰደቡት። ጎረቤታቸው ተቆጥቶ እንደወጣም በርከት ያሉ ካህናት ሊጠይቋቸው መጡና ሲጨዋወቱ ከጠያቂዎቹ አንዱ፣ “አለቃ እንዲያው ሁልጊዜ እንደቀለዱ ለነፍስዎ ስንቅ ሳይዙላት ሊቀሩ ነው?” ቢሏቸው፣ “ንሳ፣ አንተ ማነህ! አንድ ማድጋ በሶ በስልቻ አድርግና ክንዴ ላይ እሰርልኝ” አሉ ይባላል።

በመፅሐፉ አለቃ ገብረሃና በሰማኒያ አራት ዓመታቸው በሞት ከመለየታቸው በፊት ብቸኝነትን አብዝተው በሰሩትም ስራ ተፀፅተው እንደነበር ተጠቅሷል። አሁንም ድረስ በአለቃ ስም የሚቀልዱና የሚያሽሟጥጡ ሰዎች ሲገጥሙኝ ታዲያ የአለቃ ነገር፣ “ግብር እስከመቃብር” እንደተከታተላቸው አስባለው።

አንዳንድ ሰው የጫቱ፣ የመጠጡ፣ የጭሱና የቀሚስ ግልቢያ ሱሱ እስከመቃብር ድረስ ይከታተሉታል። እናም የምንወደውን ነገር መምረጥና መጠንቀቅ ብንችል ምንኛ መልካም ነበር ያሰኛል። ምነው ቢሉ ለወደዱት መሞት ያለና የነበረ ነውና።

ኢትዮጵያን ከዘመነ-መሳፍንት ከፋፍለህ ግዛ አውጥተውና አንድነቷን አጠናክረው በመንገስ የሚታወቁት አጤ ቴዎድሮስም እንዲሁ ግብራቸው እስከቀብራቸው የተከተላቸው ሰው ናቸው ማለት ይቻላል። ከጀግንነት ውስጥ ኖረው፤ ጀግኖችን ፈጥረው፤ እጅ አልሰጥም ባይነትን ሲሰብኩ የኖሩት አጤው፤ በስተመጨረሻ እርሳቸውም ለእንግሊዞች እጄን አልሰጥም ብለው መቅደላ ላይ ራሳቸውን በጥይት ሰውተዋል። “በሰዎች እጅ ከመውደቅ በእግዜር እጅ መውደቅ ይሻላል” ያሉት ንጉሱ፤ ጋዜጠኛና ደራሲው ጳውሎስ ኞኞ ስለመጨረሻ ሰዓታቸው “አጤ ቴዎድሮስ” በተሰኘ መፅሐፉ ሲናገር የሚከተለውን ታሪክ ይተርካል። “አጤ ቴዎድሮስ ወደ መቅደላ ተራራ የሚያስገባውን የቋቲት በር ለመጠበቅ የመሸጉትን ወታደሮቻቸውን ለማበረታታት ሄዱ። እዚያ ሲደርሱም አንድ እንኳ ወታደር ሳያገኙ ቀሩ። ወደ መቅደላ የሚያስገባውን በር ለመከላከል የቀሩት ወታደሮች አስር ብቻ መሆናቸውን አዩ። ወዲያውኑም ራስ እንግዳና ጠባቂያቸው አማኒ ከእንግሊዝ ጦር በተተኮሰ ጥይት ተገደሉ። የአጤ ቴዎድሮስ ጠመንጃ ያዥ ወልደጋብር ጠመንጃቸውን አቀባብሎ ለንጉሱ ሰጣቸው። አጤ ቴዎድሮስም አብረዋቸው ከቀሩት ጥቂት ታማኞቻቸው ጋር ሆነው በቋጢት በር ቀዳዳ እያሾለኩ ወደ እንግሊዞች መተኮስ ጀመሩ። ተስፋ የሌለው አተኳኮስ ስለነበር ያንን ቦታ ትተው ወደ መቅደላ ሜዳ ወጡ።

አጤ ቴዎድሮስ በሜዳው ላይ እየተራመዱ ሳሉ ቆም አሉና ከታማኛቸው ከወልደጋብር በስተቀር ሌሎቹን፤ “. . ሽሹ። ቃል ከገባችሁልኝ መሃላም ፈትቻችኋለሁ። እኔ ግን በጠላቴ እጅ ፈፅሞ አልወድቅም” አሏቸው። እነኝያም ታማኞቻቸው እያለቀሱና እያዘኑ ተለይተዋቸው ሄዱ። እነሱ እንደሔዱላቸውም ወደ ወልደጋብር ዞር ብለው “አለቀ፤ በእነዚህ ፈረንጆች እጅ ከመውደቅ ራሴን እገድላለሁ” አሉትና ሽጉጣቸውን አፋቸው ውስጥ ከተቱ። ተኮሱ። ወደቁ። ይህ የሆነውም ከቀኑ 10 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ ነበር።

አሁን ላይ በጣም የሚገርመው ግን አንዳንድ ነገሮች ለምዕራባውያንና ለአፍሪካውያን የተለያዩ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ምዕራባውያን ዘንድ ስልጣን (ወንበር) እስከ ምርጫ ሲሆን፤ በርካታ አፍሪካውያን ዘንድ ግን ስልጣን ህዝብ እስኪንጫጫ ብቻ ሳይሆን፤ ወንበር እስከመቃብር ይሆናል። ሌላ ምሳሌ ጥቀስ ካላችሁኝም እጠቅሳው ምዕራባውያን ዘንድ ምግብን እስክንጠግብ ሲሉ፤ እዚህ እኛ ዘንድ ደግሞ ምግብ እስካልተራብን ድረስ የማናገኘው ነገር የሆነ ይመስላል።

የዛሬዋን ትዝብት አዘል ጨዋታ ከመቋጨታችን በፊት ቀደም ብዬ ከሀገራችን ጨዋታ አዋቂዎች አለቃ ገብረሃናን እንደጠቀስኩ ሁሉ፣ በአረቡ ዓለም በእጅጉ የሚታወቀውን ቀልድ አዋቂ ሙላህ ነስረዲንን የመጨረሻ ቀናት ጨዋታዎች እንካችሁ. . . ነስረዲን በመጨረሻዎቹ ቀናት በጠና ታሞ ከአልጋው ውሎ ነበር። እናም በሀዘን ተቆራምዳ ፊቱ የቆመችውን ሚስቱን እየተመለከተ፣ “ለምንድነው እንደዚህ በሀዘን ተጎድተሸና ጥቁር በጥቁር ለብሰሽ እዚህ የምትቆሚው፤ ይልቅስ ምርጥ -ምርጡን ለብሰሽ ፣ ፀጉርሽንም አሰማምረሽ በፈገግታ እንድትመለከቺኝ ነው የምፈልገው” ሲል ተናገረ። ሚስቱም እርሱ እንዲያ በጠና ታሞ እያጣጣረ እያየች የእርሷ መልበስና ማማር እንዴት ሊታሰብ ይችላል በሚል፤ የማይሆን ተግባር ነው የጠየከኝ ስትል ተናገረች። “ይህን የምጠይቅሽ እኮ ምናልባት የሞት መልአክ ወደኔ ሲመጣ አምሮብሽ ሲያገኝሽ ድንገት ሀሳቡን ቀይሮ አንቺን ቢወስድሽ ብዬ እኮ ነው” ብሎ እንደመሳቅ እየቃጣው በዛው መሞቱን የቀልዱ መዛግብት ይናገራሉ። እናም ቀልዱ እስከመቃብር የዘለቀለት ሰው ሆኗል። በተረፈ ግን ጎበዝ!. . . አንድዬ ለምንወደው ነገር ብቻ ሳይሆን ለሚወደድም (ለመልካም ተግባርም) ሟች ያድርገን አቦ! ፍቅራችን ብቻ ሳይሆን መልካም ምግባራችንም እስከመቃብር ይሁን!. . . ቸር እንሰንብት።   

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
1335 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 959 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us