ከምንተማማ እስቲ እንሰማማ

Wednesday, 07 December 2016 14:09

 

“የቱ ነው እውነቱ?” ማለት የሚፈራ

ሀሞተ-ቢስ ትውልድ አንዳ'ገር ካፈራ. . .

እያደር -እያደር

አፈር ያላብሳል -እውነት ስትቀበር

ቤቱን ይገነባል- በዋዘኞቹ በር

     (ብዬ አልነገርኩህም?)

እያደር -እያደር

እውነት በቀበረች -በዚች የጉድ ሀገር

“እምነትና እውነት፤ ቅን አሳቢና ገር. . .”

     (እንኳን ሊገኙበት)

ተረት ነው “ሚሆነው -ያ'ገር ታሪክ ነገር!

(“ፍርድ እና እርድ” ከተሰኘው የአበረ አያሌው

የግጥም መድብል “ተረትና ታሪክ” በሚል ርዕስ ሰፍሮ የተገኘ)

እንደምን ሰነበታችሁ ጎበዝ!? . . . እኔ የምለው ያለምንም መደባደብና ያለምንም መሰዳደብ ስልጣንን መልቀቅ በአፍሪካችንም በገቢር ይታይ ጀመር አይደል? ይኸውና ለዘመናት ጋምቢያን ሲመሩ የነበሩት ያህያ- ጃህሜ ለተቃዋሚ ፓርቲ  መሪው በህዝቡ ድምፅ በተገኘው የምርጫ ውጤት መሠረት ስልጣናቸውን ለማስረከብ መሰናዳታቸውን ሰምተናል። (እልልል!). . . ታዲያ አፍሪካ በክፉ ብቻ ስሟ እየተነሳ እስከመቼ?! አንዳንዴም እንኳን እንዲህ “ሰበር ዜና” አይነት የምርጫ ውጤትና ይሁንታን እንስማ እንጂ ጎበዝ!. . . አፍሪካን ማማት ለማን ጠቀመ? ሁልጊዜ አፍሪካውያን እኮ እንዲህ ናቸው፤ እንዲያም ናቸው እየተባባልን መጥፎ ስም ከመለጣጠፍ፤ አንዳንዴም በጎ-በጎውን ብናነሳ ጥሩ አይመስላችሁም?. . . ከአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ዘፈኖች መካከል የምትከተለዋን ስንኝ እዚህ'ጋ ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።

ያም ሲያማ -ያም ሲያማ

ወገኔ ለኔ ብለህ ስማ።

አፍሪካ ውስጥ በስልጣን የባለጉ ባለስልጣናት እንዳሉ እንሰማለን፤ እናያለን። አፍሪካ ውስጥ በሙስና የተጨማለቁ ባለስልጣናት እንዳሉ እናያለን እንሰማለን፤ አፍሪካ ውስጥ በጀት የሚዘርፍ የስራ ኃላፊዎች እንዳሉ እንሰማለን፤ እናያለን። አፍሪካ ውስጥ ዘረኝነትና ጎሰኝነት ጥግ መድረሱን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በተለይ ከመሪዎች እናያለን፤ እንሰማለን። . . . የሚገርመው ግን ስልጣናቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ባለስልጣናት፣ ሙስና የሚፈፅሙ ባለጊዜዎች፣ ዘረኝነትና ጎሰኝነት የሚያጠቃቸው መሪ የሚያስፈልጋቸው መሪዎች ቢኖሩም “ቄሱም ዝም መፅሐፉም ዝም” ነውና እየመሩ ይቀጥላሉ። (ይህ ትልቁ የአፍሪካ ስላቅ ወይም ስታየር ኮሜዲ የምንለው ነገር ነው)

እስቲ አስቡት ራሱን እየሰደበ ሀገር የሚመራ መሪ፤ ራሱን እየሰደበ ሀገር የሚመራ ፓርቲ፤ ራሱን እየሰደበ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም፤ ራሱን እያፈረሰ ግንባታ የሚያበዛ ድርጅት ምን የሚሉት ነው። እዚህች'ጋ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን ለማሳመር ያህል “የአባቶች ጨዋታ” ከተሰኘው የመጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናው መፅሐፍ ያገኘናትን ወግ እንካችሁ።

በኢትዮጵያ የነበሩ አንድ ግብፃዊ ሊቀጳጳስ በየቀኑ ሲገቡና ሲወጡ አገልጋያቸውን “አንተ ወደል አህያ፤ ጠብደል ባሪያ” እያሉ ይሰድቡት  ነበር። አገልጋያቸው ግን ምንም የከፋው ሳይመስል በረጋ መንፈስ በፍፁም ትዕግስት ኖረ። ከዕለታት አንድ ቀን ሊቀ-ጳጳሱ ወደ አእምሯቸው ተመልሰው፣ “ምናልባት ይህ አገልጋዬ አዝኖብኝ ይሆናል” ብለው አሰቡ። ወዲያውም ጠሩትና “አንተ ልጄ! በየቀኑ ወደል አህያ ጠብደል ባሪያ” እያልኩ በቀልድ መልክ ስናገርህ ከፍቶህ ይሆን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም በአክብሮት ሲመልስላቸው፣ “አባታችን ወደል አህያም ሆነ ጠብደል ባሪያ ቢሉኝ ያው የእርሶ ልጅ ስለሆንኩ ምንም አይከፋኝም” አላቸው። ሊቀ-ጳጳሱም፣ “ለካስ ራሴን በራሴ ኖርዋል የምሰድበው” ብለው አፋቸውን ይዘው ዝም አሉ ይባላል።

እናላችሁ አንዳንዴ ስለሌላው ስንናገር ራሳችንንም እየተናገርን እንደሆነ መረዳት ያሻል። በውስጣችን ሙሰኞች አሉ፤ በውስጣችን ስልጣናቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙ አሉ፤ በውስጣችን የአመለካከት ችግር ያለባቸው አሉ እያሉ መናገር በራሱ እራስንም ይመለከታልና “ጌቶቻችን” ቢያስተውሉት ምን ይላቸዋል። (አዎና ሂስ እና ሻወር ከራስ ሲጀምሩት አሪፍ ነው ሲባል ሰምተን የለ?)

እናላችሁ ጎበዝ!.. .  ገጣሚው እንዳለው “የቱ ነው እውነቱ?” ብሎ መጠየቅ የሚፈራ ትውልድ ከመሆን ይሰውረን። አለበለዛ ግን እነርሱ የሚናገሩትን ብቻ እየሰማንና እየተቀበልን ስንኖር፤ እውነት ስትቀበር እያየን እኛ አፈር እየከመርን ከቀጠልን ታሪካችን ሁሉ ተረት ሆኖ መቅረቱ አይቀሬ ነው።

የምር-የምር ቅን አሳቢዎች ካልበረከቱልን በስተቀር የምንናገረው ሁሉ በኋላ ለራሳችንም ይተርፋልና ትዝብት ላይ ከሚጥል የአደባባይ ዲስኩር አንድዬ ይሰውረን። የምሬን እኮ ነው፤ አንዳንድ ተናጋሪዎችና አድማጮች ይግባቡ ዘንድ አስተርጓሚና ተንታኝ (ምሁራን) በመሀከላቸው ሳያስፈልጉ እንደማይቀር የምታሳይ የአለቃ ገብረሃናን ጨዋታ አስታውሼ የዛሬ ትዝብቴን ላብቃ።

አለቃ ሰውን ሁሉ በነገር ወጋ፤ በነገር ተንኮስ ሲያደርጉት ኖረው በመንደሩ አላዋቂ የነበረ አንድ ሰው ግን “አለቃ እኮ እኔን አንድም ቀን ሰድበውኝ አያውቁም” እያለ ይፎክር ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ይህ ሰው አህያውን እየነዳ ወደገበያ ሲሄድ አለቃ ገብረሃና በመንገድ ያገኙትና “እንደምን ዋላችሁ!” ብለውት ሰላምታ ተለዋውጠው አለፉ። ይህንን ነገር ተደብቆ የሰማ አንድ ሰውዬ “አንተ አለቃ አንድም ቀን ሰድበውኝ አያውቁም ብለህ የለ? ይኽው ዛሬ በስድብ አጥረገረጉህ!” አለው። ተሰዳቢውም ሰው ነገሩ አልገባው ኖሮ፣ “መቼ ሰደቡኝ ያውም እኮ ሰላምታ ሰጥተውኝ ነው ያለፉት አንተ መቼ አየሃቸውና ነው የምታወራው?” ከማለቱ የአለቃ ቅኔ የገባው ሰው፣ “አንተና አህያህ፤ ብቻችሁን እየሄዳችሁ አለቃ፣ ደህና ዋላችሁ? ማለታቸው እኮ ሊገባህ ይገባል፤ አንተንም ከአህያህ እኩል ቆጥረውሃል” አለው ይባላል።

ለማንኛውም ጓደኛህ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ ማለት ጥሩ ነው። አንዳንዴም ቢሆን፤ በሽተኛው ላለመዳኑ የዶክተሩ አቅም፤ የአንድ ቡድን መሸነፍ የአሰልጣኙ አቅም፤ የአንድ ተቋም ፓርቲም ሆነ መውደቅ የአመራሩ አቅም የሚለካበት ነውና. . . ሌሎችን ከማማትና ሰበብ ከማብዛት ይሰውረን፤ ከምንተማማ እስቲ እንስማማ ጎበዝ!. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
540 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 972 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us