እንዲህ ነው የኛ “ስታይል”

Wednesday, 14 December 2016 13:53

 

ሕዝብ፣ እግዜር፣ መንግስት!

እግዚአብሔር፣

      ምን ብሎ ይመልስ የህዝብን እሮሮ

መንግስት፣

      እንዲናገር እንጂ እንዳይሰማ ፈጥሮ!

(ከገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ “አርነት የወጡ ሐሳቦች” የግጥም መድብል የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . እኔ የምለው አንድዬ ምነውሳ አሳይቶ የሚነሳንን ነገር አበዛው? የምሬን እኮ ነው . . . ምነው አሁን ይሄን ሰሞን አፍሪካዊ በተለይ ደግሞ ጋምቢያዊ መሆንን ከምርጫው ውጤት ጋር ተያይዞ የሚያቃጥል አይደል?. . .” ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል” ማለት ዘንድሮ ነው። በተለይ ጋምቢያውያን ልፉ ሲላቸው አንድዬ እያላመጡትና እያጣጣሙት ያሉትን የምርጫ ውጤት ከአፋቸው ነጥቆ፤ ኩም አሰኝቶ የአለም መሳቂያና መሳለቂያ አድርጓቸዋል። ያህያ ጃሜ ግን ምን ነክቷቸው፤ ምን ክፉ መካሪ አጋጥሟቸው ነው እንዲህ በሳምንት ውስጥ ከሙገሳ ወደወቀሳ ቁልቁል የወረዱት? (ለነገሩ የሰውዬው ስም ለሀገር መሪነት ሳይሆን ለቤት እንስሳነት የቀረበ ነውና እንዲህ ነው የኛ “ስታይል” ብለን እንለፋቸው መሰለኝ።)

የምር ግን ምርጫን ማጭበርበር፣ ስልጣንን እስከመቃብር መያዝ፣ ሙስናና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት ሁሉ የአፍሪካውያን መለያ ሆኖ መሪዎቹ ሁሉ በአንድ ድምፅ “እንዲህ ነው የኛ ስታይል” እያሉ በየቤተመንግስቱ “ሙድ” የሚይዙብን አልመሰላችሁም?. . . ድንቄም ዴሞክራሲያዊና ግልጽ ምርጫ! . . . የምር ግን አፍሪካውያን መሪዎች ቤተመንግስቱን እና መኖሪያ ቤታቸውን የሚያለያዩት መቼ ይሆን? ኧረ ግድ የላችሁም መሪ ለመሆን አፍ ብቻ ሳይሆን ጆሮም ይሰጣችሁ ዘንድ ትጉና ፀልዩ!

መቼም ለኛ ለአፍሪካውያን እንደባለስልጣንና እንደሰይጣን ምድራዊ ፈተናችንን የሚያበዛው ያለም አይመስለኝም። እንደውም አንዳንዴ ነገሩን ከስሩ ስመረምረው አፍሪካውያን መሪዎች የስልጣን ጥማትን ከሰይጣን የተማሩ ይመስለኛል። ለነገሩማ የስልጣንና የምርጫ ነገር ከተነሳ ከሰሞኑ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ የለመደባት አፍሪካዊቷ ጋናም የምስራች አሰምታናለች። (ነገሩ የሳምንት ጉዳይ ብቻ ሆኖ ድንገት ሀሳባቸውን ቀይረው፤ “እንዲህ ነው የኛ ስታይል” እንዳይሉን እንጂ)

ምስኪን አፍሪካዊ (ጋምቢያዊ) ስልጣን በሰለጠነ መንገድ ተለወጠ ብሎ፤ ፈንጠዝያውን ሳይጨርስ (መሪዎቹ ሁሉ ከአህያ (ከያህያ አላልኩም) የዋለች ጊደር “ምን” ተምራ ትመጣለች” የተማረች ጊደር.. . እንዲሉ ምርጫው ተጭበርብሯል፤ ይደገም ብለውት አረፉ. . . በተለይ የጋምቢያውያን ደስታ በአጭሩ ተቀጨ። የምር ግን አንድዬ ነስቶ ሲሰጥ እንጂ ሰጥቶ ሲነሳ እንዴት ያማል መሰላችሁ።

እዚህች'ጋ አንዲት የቱርካውያን ተረት ትዝ አለችኝ። ፈጣሪ ደሃን ለማስደሰት ከፈለገ መጀመሪያ አህያው ይሰውርበታል። ከዚያም ደሃ ሆዬ አህያዬ ጠፋ እያለ በፍለጋ ሲዋትት፤ ፈጣሪ እስቲ ይህንን ደሃ ላስደስተው ይልና ድንገት አህያውን ከፊቱ ገጭ ያደርግለታል። ይሄኔ የኔ ብጤው ደሃ የጠፋበትን የራሱን አህያ ስላገኘ እየተደሰተና እየፈነጠዘ አምላኩን አመስግኖ ወደቤቱ ይገባል። እንዲህ ነው የኛ “ስታይል” . . . የሚገባንንም፣ የራሳችን የሆነውንም፣ የከፈልንበትንም፣ በስማችን የሚጠራውንም ነገር ድንገት ተነጥቀን ሲሰጠን መፈንጠዝ የኛ የምስኪኖቹ ተግባር ሆኗል። . . . ለምሳሌ ሰሞኑን ምን ታዘብኩ መሰላችሁ? . . . ከሰሞኑ የተዘጋው የፌስ ቡክ በር ገና በጥቂቱ ገርበብ ከማለቱ ህዝቤ ሁሉ አጥፊውንም አልሚውንም እያመሰገነ፤ “እቱ ያገሬ ልጅ እንደምን ከርመሻል? የኔ ልብ በሃሳብ ይዋልልሻል” አይነት ሰላምታውን ተለዋውጧል።. . . እናም የሚገባንን ነገር ነጥቀው መልሰው በመስጠት ደስታችንን እያበዙት “እንዲህ ነው የኛ ስታይል” ያሰኙን ይዘዋል።

እናላችሁ ሰው ደስታውን ያገኝ ዘንድ ልክ እንደኛ የራሱንና የሚገባውን ነገር ማጣት አለበት እንዴ?. . . በርካታ ለኛ የሚገቡንን ነገሮች አጥተን መልሰን ስናገኝ የሚፈጠርብን ደስታ ምን የሚሉት እንደሆነ መግለፅ ይቸግራል። ለምሳሌ ልናገኝ የሚገባው የምንከፍልበት ውሃ፣ መብራት፣ ስኳርና ዘይት ድንገት ከቤትም ከገበያም ጠፉ ስንባል ማመልከቻችንን በኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በኩል አቤት ከማለት በዘለለ እንደመብት ጠይቀን እናውቃለን? አናውቅም! ምክንያቱም ማን እንደሚጠየቅና ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት እንኳን በቅጡ አናውቅም። አፍሪካ ውስጥ እኮ አለቅነት እንጂ ተጠያቂነት ወዴት እንዳለ አይታወቅም። ለምን ቢባል “እንዲህ ነው የኛ ስታይል” እናም የራሳችንን (የሚገባንን) ነገር ወይም መብታችንን ተነጥቀን፤ ተጨንቀን እንቆይና ድንገት “ሰጪው አካል” ሲመልስልን እልል እያልን እናመሰግናለን። ይህ የመንጠቅና የመስጠት የደስታ ቀመር ይቀጥላል፤ ለምን ቢባል እንዲህ ነው የኛ “ስታይል”! (አጥቶ ማግኘት ነው የኛ የደስታ ቀመር)

እስቲ ደግሞ ትዝብታችንን ከማጠናቀቃችን በፊት የምትከተለዋን ተረት ልተርክላችሁ። ሰውዬው ሃብት ሞልቶ የተረፈው አይነት ነው። ሆኖም ግን የደስታን ጣዕም አጥቶ ነበርና በቦርሳ ሙሉ ገንዘብ ተሸክሞ ደስታን ፍለጋ ከከተማ ከተማ ይንከራተታል። ታዲያ በመንገዱ አንድ ሰው ያገኘውና ምን ይዞ? ወዴት እየሄደ? እንደሆነ ይጠይቀዋል። ሰውዬውም በቦርሳው ሙሉ ገንዘብ መያዙንና ያጣውን ደስታ ፍለጋ ከቀናት ጀምሮ ለማግኘት እየተንከራተተ ቢሆንም የፈለገውን ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል።

በባለሀብቱ የደስታ ፍለጋ ሃሳብ የተገረመው ሰውም ድንገት የሰውዬውን በገንዘብ የታጨቀ ቦርሳ መንትፎት ይሮጣል። ባለሀብትም በገጠመው ዝርፊያ ደንግጦ ዘራፊውን ያራውጠው ጀመር። ቦርሳውን የያዘው ሰው በፍጥነት ይተጣጠፍና ከዓይኑ እንደመሰወር ብሎ ቦርሳውን ከመንገዱ ዳር በማስቀመጥ የሰውዬውን ሁኔታ ተደብቆ መመልከት ይጀምራል። የተነጠቀው ባለሀብትም የተሰረቀውን ቦርሳ ድንገት በመንገዱ ላይ በማግኘቱ ተደስቶ ንብረቱን በደረቱ በማቀፍ አምላኩን እያመሰገነ ደስታውን ሲገልጽ ታየው። ይሄኔ ነጣቂው ሰው ከተደበቀበት ብቅ ብሎ “አየህ ወዳጄ ደስታ ማለት ይሄ  ነው፤ የሚያስፈልግህን ነገር አጥተህ/ተነጥቀህ መልስህ ማግኘት!” አለው ይባላል።

እናላችሁ የሚገባንን እየነጠቀ ደስታችንን ከሚያዛባ፤ ራሱን የመብት ሰጪና ነሺ አድርጎ “እንዲህ ነው የኛ ስታይል” ከሚል ተሟዛዥ አንድዬ ይሰውረን አቦ!. . . አፍሪካ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ ውጤቱን የማትክድበት፣ እፍርታሞች የማይበዙበት፣ ልጆቿ የሚተጋገዙበት፣ መንግስታቱ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆኑ ሰሚም የሚሆኑበት ዘመን ይመጣ ዘንድ እንመኛለን. . . ቸር እንሰንብት!!!  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
507 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 995 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us