“ፀጉራም ውሻ. . .”

Wednesday, 21 December 2016 14:50

 

አለ እያልኩ ልኑር እያስታወስኩኝ

እውነት ሞቶ እንደሆን እንዳታረዱኝ።

            (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁልኝ ወዳጆቼ!?. . . መሰንበት ደግ ነው ብዙ ነገር አይተን፣ ብዙ ነገር ታዝበን እንድንጨዋወት ዕድል ፈጥሯል። እኛ መሰንበት ደጉ ከፈጠረልን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመን ልንጨዋወት ተገናኝተናል። . . . እኔ የምለው ከታቀደለት ጊዜ ዘግይቶም ቢሆን “ጊቤ ሶስት” ፕሮጀክታችን ተጠናቀቀም አይደል? ይህንን ሲሰማ አንድ ወዳጃችን ምን አለ መሰላችሁ? “የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት መጠናቀቅ ለኛ ሳይሆን ለጎረቤቶቻችን በብርሃን መጥለቅለቅ ደስታ ሊፈጥር ይችላል” ሲል ተደምጧል።. . . ግድ የለም ይሄ ፕሮጀክት ለሌሎች ሲዘንብም ቢሆን ለኛ ማካፋቱ አይቀርምና የመብራት እጥረትና ብሶት በመጠኑም ቢሆን ይቀንሳል የሚል ተስፋ አለን።

እኔ የምለው የጎፈረ ነገር አልበዛባችሁም እንዴ?. . . የምሬን እኮ ነው፤ አራዳ ነኝ ባዩ ፀጉሩን ያጎፍራል። ሌላው ሌላው ደግሞ አለ አይደል ሲለው ስልጣኑን ያጎፍራል፣ ወንበሩን ያጎፍራል፤ ደሞዙን ያጎፍራል፤ ዲግሪና ማስተርሱን ያጎፍራል፤ መኪናና ቤቱን ያጎፍራል፤ እኛን በውርጭ እየጨረሰ እርሱ ቦርጩን ያሳብጣል፤ ምን አለፋችሁ በዚህም አላችሁ በዚያ አዲሱም ተመዝጋቢ ሆነ አሮጌው “ነገሩን” ሁሉ አጎፍሮት ቁጭ ነው። . . . ስራ ላይ ግን ዜሮ፤ ይሄን ታዲያ አበው ምን ብለው ይተርታሉ መሰላችሁ? “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት፣ በራብ ይሞት”. . . ቂ.ቂ.ቂ. ደስ አትልም? ይህ የዘመኑ አጎፋሪ ግን በራብ የሚሞት አይመስለኝም። ባይሆን በ“ረሃ” ብዛት ቢሞት ይችል ይሆናል እንጂ።

የምር ግን አለልን፤ እየሰራልን ነው፤ የለውጥ ተስፋችን ነው ያልነው ሰው ሁሉ ወንበሩን ይዞ “ፀጉራም ውሻ” አይነት ነገር ሲሆን አይደብርም?. . . ኧረ በጣም ይደብራል። ተምሯል፤ አገር ይቀይራል፤ ቤተሰብ ይመራል ያልነው ሰው ሁሉ ድግሪውን ይዞ በውስጣዊም ይሁን በውጫዊ ምክንያት ስራ ካልሰራበት ምን ማለት ይቻላል?! “ዲግሪው/ትምህርቱ” ልክ እንደፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት የሞት አይነት ነገር አይመስላችሁም?. . . ሌላው “ፀጉራም ውሻ” የሚመስለኝ ደሞዛችን ነው። ሲጠራና ሲቆጠር ግማሽ ቀበሌ ህዝብ የሚያስተዳድር የሚመስለው ደሞዝ ሁሉ፤ ስንዴና ሽንብራ መግዣ ሆኖ ሲቀር፤ ለሸሚዝና ለሱሪ እጃችንን ሲያሳጥር ምን ይሉታል። ደሞዛችን ሁሉ በብድር አልቆ “አለሽ መስሎሻል ተበልተሸ አልቀሻል”የሚያስተርት ከሆነ ከፀጉራሙ ውሻ በምን ተለየ?

እናላችሁ በየመስኩ አሉ ስንላቸው “ፀጉራም ውሻ” መስለው ጉድ ያደረጉን በዝተዋልና ትዝብት ነው ትርፉ።. . . ሳይሰሩ ሳይለፉ፣ ደሞዝ የሚልፉ፣ በቀብድ የሚቆልፉ፣ ብዙ የሚለፈልፉ ሰዎች ትዝብት ነው ትርፉ በሚል “ፀጉራም ውሾች” ብለናቸዋል። እስቲ ደግሞ ጥሮ ግሮ ውጤት ስለማግኘት የምትሰብክ አንዲት ቆየት ያለች ታሪክ እዚህች'ጋ ላስታውስ።

በጥንት ዘመን ነው አሉ። ንጉሱ የሀገሩን ጠቢባን አስጠርቶ ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ የሚችለው ካለፈው ትውልድ የተቀሰመ ጥበብን ፅፈው እንዲያመጡለት አዘዛቸው። ጠቢባኑም ከብዙ ልፋትና ምክክር በኋላ ለመጪው ትውልድ ይጠቅማል ያሉትን ሃሳብ በብዙ ቅፅ መፅሐፍት አዘጋጅተው ለንጉሱ አቀረቡለት።

ንጉሱ ግን ጠቢባኑ ያቀረቡለት ብዛት ያላቸው መፅሐፍት ለመጪው ትውልድ ጊዜን የሚሻሙ ናቸው ብሎ በማሰብ አሳጥረው እንዲያቀርቧቸው በድጋሚ ያዛል። ጠቢባኑም በንጉሱ ትዕዛዝ መሰረት ከብዙ ልፋትና ትጋት በኋላ ለመጪው ትውልድ መልካም ይሆናል ያሉትን ሃሳብ በአንድ መፅሐፍ አዘጋጅተው ያቀርባሉ። አሁንም ንጉሱ መፅሐፉ በዝቷል በሚል “እስቲ አንድ ምርጥ ምዕራፍ መርጣችሁ ስጡኝ” አላቸው። ጠቢባኑ የንጉሱን ትዕዛዝ ለመፈፀም መፅሐፉን በአንድ ገፅ ጨምቀው አቀረቡለት። ሆኖም ግን ንጉሱ ይህን አንድ ገፅ ቢሆን ይረዝማል በማለቱ በስተመጨረሻ አንድ ጠንካራ ኃይለ ቃል ያለው አረፍተ ነገር እንዲያመጡለት ያዛቸዋል። ጠቢባኑም ካለፈው ትውልድ የቀሰሙትንና ለመጪውም ትውልድ ይሆናል ያሉትን አንድ አረፍተ ነገር እንዲህ በማለት በፅሁፍ ያሰፍራሉ፣ “ነፃ ምሳ የሚባል ነገር የለም” ይህ ማለት ሳይለፉ ሳይደክሙ፤ በማስመሰል ብቻ ውጤት ማግኘት ከንቱ ነው እንደማለት መሆኑ ነው ጎበዝ!

እኔ የምለው ለቱሪስትና ለዲያስፖራ ጭራቸውን የሚነሰንሱ (ቀሚሳቸውን ለማለት ድፍረቱን አጥቼ እንደሆነ ይታወቅልኝ) አልበዙባችሁም? እስቲ ትንሽ ውጪ ሀገር ቆይታችሁ ኑ ያኔ ነው የሀበሻን ፀባይ መመልከት። እንዲህ ናትና ጎበዝ ውጪ ሀገር ደርሶ የመጣ ሰው ለወጪ ምን ያህል ጠንቃቃ እንደሆነ ካልገባን በጣም ተሸውደናል ማለት ነው። በተለይ አንዳንድ “ዲያስፖራዎችን” እና አንዳንድ ቱሪስቶችን (በተለይ ነጮችን) ከመሬት ተነስተን ዶላር ጭነው መጥተዋል ብሎ ማመን በኋላ ትዝብት ላይ ጥሎ “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት በረሃብ ይሞት” ይሉን ተረት ሊያስተርተን ይችላል።

አንዳንዶች ደግሞ አሉላችሁ “ፈረንጅ” ባዩ ቁጥር የብር ክምር እንጂ የችግር ዘር ትውስ የማይላቸው። ጎበዝ. . . የፈረንጅም ባዶ ኪስ መኖሩ እየተስተዋለ እንጂ። ፈረንጅ የማይቸግረውና ፈረንጅ የማይዋሽ ለሚመስለው ሰው ሁሉ የምትከተለዋን አስተዛዛቢ ጨዋታ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም።

ለስራ ይሁን ለስለላ አልያም ለጉብኝት በቅጡ ያልተለየ ፈረንጅ የሰለለ እግሩን በቁምጣ ውስጥ እያወዛወዘ ከኤርፖርት ይወጣል። አንድን ባለታክሲ ጠርቶም ወደአንድ ታዋቂ ሆቴል እንዲያደርሰው ተስማምተው ጉዞ ይጀመራል።

ፈረንጅም በመንገድ ላይ ሳሉ አንድ ትልቅ ህንፃ ይመለከትና “ለመሆኑ ይህን ህንፃ ገንብታችሁ ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባችሁ?” ሲል የታክሲ ሾፌሩን ይጠይቀዋል። “ጌታዬ ከአስር ዓመት በላይ ፈጅቷል” ሾፌሩ ይመልሳል። “በእውነት አትረቡም እኛ ሀገር ቢሆን በ10 ወር ነበር ተሰርቶ የሚጠናቀቀው” ይላል ፈረንጁ። ጥቂት አለፍ እንዳሉ አሁንም ፈረንጁ አንድ የሚያምር ህንፃ ይመለከትና “ይሄኛውስ ስንት ዓመት ነው የፈጀባችሁ?” ሲል ይጠይቀዋል። ሾፌሩም ላለመሸነፍና ሀገርን ላለማዋረድ ብሎ፣ “ይሄኛው እንኳን በአምስት ዓመት ውስጥ ነው ተገንብቶ የተጠናቀቀው” ሲል ይመልሳል። ፈረንጁም ጉረኛ ብጤ ሳይሆን አይቀርም፣ “ይሄ እኛ ሀገር ቢሆን በ5 ወር ውስጥ ነበር የሚጠናቀቀው” ሲል ይቀደዳል። በዚህ ጊዜ ሾፌሩ እንደመናደድም እንደመጠቃትም ያለ ስሜት ይሰማውና የምን እንግዳ ተቀባይነት ነው ይሄ ውሸታም ፈረንጅ ቆይ እሰራለታለሁ እያለ ወደሆቴሉ መዳረሻ ሲቀርቡ፤ አሁንም ፈረንጁ ትልቅ ስታዲየም ይመለከትና “ለመሆኑ ይሄን ስታዲየም በስንት ጊዜ ውስጥ ነው ገንብታችሁ ያጠናቀቃችሁት?” ሲል ይጠይቀዋል። ይሄኔ ሾፌሩ በንዴት ቱግ ብሎ፣ “እውነቱን ለመናገር አላወኩም። ምክንያቱም ጠዋት በዚህ ሳልፍ ስታዲየሙ አልነበረም፤ አሁን  ነው ያየሁት” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ

እናላችሁ ነገራችን ሁሉ፤ ስልጣናችን ሁሉ፣ ገንዘባችን ሁሉ፣ ትምህርታችን ሁሉ፣ ሰውነታችን ሁሉ፣ ትዳራችን ሁሉ፣ ደረጃችን ሁሉ አለ በተባለበት ቦታ ካልተገኘ ምን ዋጋ አለው? አለ ያልነው ነገር ሁሉ ድንገት ከጠፋ፤ ያጠበብነው ልዩነት ሁሉ ድንገት ከሰፋ፤ የሞላነው ነገር ሁሉ ድንገት ከተደፋ አለ አይደል አበው እንደሚሉት “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት በርሃብ ይሞት” እንዲሉ ሆኖ መቅረቱ ነው።. . . በተረፈ ግን አንድዬ አለ ብለነው ከሚጠፋ፣ ሞላ ብለነው ከሚደፋ ነገር ሁሉ ይሰውረን አቦ!. . . በስተመጨረሻም የባለቅኔውን ስንኞች እንካችሁ. . .

አለ እያልኩ ልኑር እያስታወስኩኝ

እውነት ሞቶ እንደሆን እንዳታረዱኝ።

ቸር እንሰንብት!!!  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
536 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 948 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us