“ከመሮጥ ይሻላል ማንጋጠጥ”

Wednesday, 28 December 2016 14:09

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . በአንዳንድ ነገሮቻችን ላይ የሚጠቅመንንም፤ የማይጠቅመንንም “ለኔ-ለኔ” ስንል ነበር። ይኸውና አሁን ደግሞ ድንገት ጉድ ይዞብን ሲመጣ “ወይኔ-ወይኔ?” ማለት ጀምረናል የሚባለው ነገር እውነት ነው እንዴ? ኧረ ግድ የላችሁም ጎበዝ ሁሉንም ነገር በራሳችን ብልጠትና ጉልበት ብቻ የምናሸንፈው ላይሆን ይችላልና፣ “ከመሮጥ ይሻላል ማንጋጠጥ” ይሉትን ብሂል ብንጠቀመው፤ ምን አለበት አልፎ-አልፎ እንኳን “አንድዬን” በመሀከሉ ብናስገባስ?

አለ አይደል አንዳንዴ የአቅማችንን ያህል፤ ላባችንን ጠብ አድርገን፤ ወጥተንና ወርደን የስንቱን ፊት ያየንበት ነገር ላይሳካ ይችላል። ያኔ ታዲያ አስሬ እድላችንን ከማማረር መለስ ብሎ አመጣጣችንን ማየት፤ ተስፋችንን ማደስና “አንድዬ” አንተም ተጨመርበት ማለቱ ሳያዋጣ አይቀርም።

እናላችሁ ልፉ ካላችሁ እንዲሁ ስትዳክሩ ትኖራላችሁ እንጂ ከእፍታው አይደርሳችሁም። ይህን ታዝቦ ይመስለኛል የሀገራችን ሰው

የበሬውን ዋጋ ወስደው ፈረሱ፤

ከኋላ ተነስቶ ቀድሞ በመድረሱ።

ሲል የተቃኘው። ለማንኛውም መዓቱን “ለኛ”፤ ውጤቱን “ለእነሱ” ከሚያደርግ አሰራር አንድዬ ይገላግለን ዘንድ ከመሮጥ ማንጋጠጥን ማስቀደሙ አሪፍ አይመስላችሁም?. . . ከሰሞኑ በታክሲ ትራንስፖርት ውስጥ ያነበብኳትን ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ?. . . “ጠዋት ስትወጣ ፀልይ፤ ማታ ስትገባ አመስግን” ይህ ማለት እኮ ከመሮጥህ በፊት አንጋጥ እንደማለት ነው።

እኔ የምለው ልፋታችን በዝቶ ውጤታችን ጠፍቶ እስከመቼ እንዘልቀዋለን?. . . እንዲህ ናትና እኛ እኮ ይስተካከል ብለን ያለፋንበት መስክ የለም። ዳሩ ምን ያደርጋል መስኩ በሙሉ በወረርሽኝ (ያው ወረርሽኝ ስል ይገባችኋል አይደል፤ በሙስና፤ በዝምድና፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በጥልቅ ባለመታደስ በሚመነጭ ወረርሽኝ ማለቴ ነው ቂ-ቂ-ቂ) ተወሯል። እናላችሁ ኑሮ እየከረረ ሲመጣ ኡኡታው ለኛ፤ እፍታው ደግሞ ለጌቶቻችን እየሆነ ከቀጠለ መፍትሄ የሚሆነው ከመሮጥ ማንጋጠጥ ይመስለኛል።

ሰውዬው በመስሪያ ቤቱ ትጉህ ሰራተኛ ነው። ዳሩ ምን ያደርጋል። ልፋትና ድካም እንጂ እድገትና “ገቢ” የለም። ታዲያ አንድ ቀን ወደመስሪያ ቤታቸው አንድ እንግዳ ይመጣና፣ “የዚህ መስሪያ ቤት ኃላፊው ማነው?” ሲል ይጠይቀዋል።

“በእውነቱ የዚህ መ/ቤት ኃላፊ እንደአርስዎ አመጣጥ ይለያያል” በማለት ሊያብራራ ሲሞክር ግራ የተጋባው እንግዳ፣ “ቆይ ይሄ መስሪያ ቤት ያለው ኃላፊ ስንት ነው?” ከማለቱ ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “ጌታዬ አመጣጥዎ ለምስጋና ከሆነ የአለቃችን ቢሮ ያውልዎት፤ ነገር ግን አመጣጥዎ ለወቀሳ ከሆነ እኔ አለውልዎት” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ-! . . ይህቺ ናት ጨዋታ እንግዲህ ለወቀሳ ጊዜ ወደኛ፤ ለምስጋና ጊዜ ወደነሱ ማለት እንዲህ ነው።

ለማንኛውም “ከመሮጥ ይበልጣል ማንጋጠጥ” ተብሏልና ከመሯሯጣችን በፊት ውጤቱ ያምር ዘንድ ማንጋጠጥን እናስቀድማለን። አለበለዚያማ ባላሰብነው መንገድ ልንበላ እንችላለን። እስቲ አሁን ደግሞ አንዲት ተረት ለመሰነባበቻ እንካችሁ።

በአንድ ወቅት አንበሳ፣ ጅብ፣ ቀበሮ፣ ነብር፣ ተኩላና አህያ በጋራ ምግባቸውን ፍለጋ መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። (ሁሉም ተሯሩጠው እንጂ አንጋጠው አልጀመሩም) በመሆኑም ቀኑን ሙሉ ምግብ ቢፈልጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ቀኑ መሸ። በመጨረሻም ለእረፍት ይሆን ዘንድ አንድ ዛፍ ስር ተሰብስበው ቁጭ አሉ።

በእረፍታቸው ላይ ሳሉም ድንገት ቀበሮ ከመካከላቸው ይነሳና፣ “አንድ ሃሳብ አለኝ። ዛሬ በጋራ ሙሉ ቀን ምግብ ብንፈልግም ማግኘት አልቻልንም። እንደሚመስለኝ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ከመካከላችን አንዱ ከባድ ኃጢያት ሰርቷል ማለት ነው። ስለዚህ ፍቃደኛ ከሆናችሁ እያንዳንዳችን እየተነሳን ከዚህ ቀደም የሰራነውን ከባድ ኃጢያት እንናዘዛለን” ሲል ተናገረ። በቀበሮ ሃሳብ ሁሉም ተስማምቶ፤ የኃጢያት ኑዛዜው ተጀመረ።

በቅድሚያ የአራዊቱ ንጉስ አንበሳ ተነሳና፣ “አንድ ቀን አንዲት ጊደር ከመንጋው ተነጥላ የሰው ማሳ ውስጥ ገብታ ስትበላ አገኘኋትና ለሌሎች ጊደሮች መማሪያ ትሆን ዘንድ ዘነጣጥዬ በልቻታለሁ። ይህ ኃጢያት ነው የምትሉ ከሆነ ፍርዳችሁን እቀበላለሁ፣” ሲል ተናዘዘ። እንስሳቱም በሙሉ ድምፅ “ አይ ይሄማ ምንም ኃጢያት አይባልም ሌሎች ከስህተቱ እንዲማሩ ማድረግ ነው” ብለው መልስ ሰጡ።

በመቀጠልም ነብር ተነሳና፣ “አንድ ቀን አንድ ወጠጤ ፍየል መሳሪያ ከታጠቀ እረኛ ጋር ስለሆነ ምላሱን አውጥቶብኝና ሰድቦኝ ሄደ። በማግስቱም የእሱን መንታ ወንድም ወጠጤ ፍየል ቅጠል ሲለቃቅም አገኘሁትና ዘነጣጥዬ በላሁት። ይህ ተግባሬ ኃጢያት ነው ካላችሁ ፍርዴን እቀበላለሁ” ሲል ተናዘዘ። በዚህ ጊዜ ተኩላ ፈጠን ብሎ፣ “ይሄ ኃጢያት አይባልም። ምናልባትም ኃጢያት የሚሆነው የሰደበህን ወጠጤ ፍየል ሳትበቀለው ብትቀር ነበር” ሲል ተናገረ።

“እኔ ብዙም ንግግር አላበዛም” ሲል ጀመረ ቀጣዩ ተናጋሪ የሆነው ጅብ፤ “አንድ ቀን አንድ ያረጀ ፈረስ በመንገድ ላይ ስለተገናኘን ብቻ ሲያየኝ ደነገጠ። በዚህም ተናድጄ በልቼዋለሁ። ምክንያቱም እኛ እንስሳት ወንድማማቾች ሆነን ሳለ እኔን ሲያይ መደንገጥ አልነበረበትም ከሚል ተነስቼ ነው። ይሄ ተግባሬ ኃጢያት ነው ካላችሁ ፍረዱብኝ” አለ። አንበሳም ፍርዱን ሲሰጥ፣ “ይሄ ኃጢያት አይባልም። እንደውም ኃጢያተኛው ፈረሱ ነው። እንዴት አንተን የመሰለ የዋህና ደግ እንስሳ አይቶ ይደነግጣል?” ሲል በጥያቄ መልስ ሰጠ።

ተኩላ በበኩሉ፣ “እኔ ከአንድ ገበሬ ቤት አይብ ሰርቄ በልቻለሁ። ልሰርቅ የቻልኩትም አስቤበት ሳይሆን፤ በመንገዴ ሳልፍ ስለሸተተኝና የቤቱም በር ክፍት ሆኖ አንድም ሰው ዝር አለማለቱ አደፋፍሮኝ ነው። ይህ ተግባሬ ከባድ ኃጢያት ነው የምትሉ ከሆነ ፍርዱን አሁኑኑ እቀበላለሁ” ሲል ተናዘዘ። በዚህ ጊዜ የአራዊቱ ንጉስ አንበሳ፣ “ኃጢያት የሚሆነው የእንስሳት አምላክ የሰጠህን ክፍት ቤት አልፈህ ብትሄድ ነበር” በማለት አስረዳና ወደመጨረሻዋ ተናጋሪ አህያ ፊቱን አዙሮ ተቀመጠ። . . . ከመካከላቸው አንድ እንስሳ  ኃጢያተኛ ተብሎ ለመብላት ያሰፈሰፉ ሁሉ ወደአህያ ሲመለከቱ እርሷ በልቧ፣ “ጉልበቴ ሆይ! አውጣኝ አውጣኝ ስትል፤ እነርሱ ደግሞ በልባቸው ጌታችን ሆይ አብላን - አብላን እያሉ ነበር። “እኔ አንድ ቀን ጭነት ተጭኜ በመንገድ ስሄድ” ስትል ጀመረች አህያ ኑዛዜዋን፤ “ታዲያ በመንገድ እያለፍኩ ሳለ ችም ችም ብሎ የበቀለ ሳር በመንገዱ ዳር በማየቴ አሳሳኝና አንድ ሁለቴ ጋጥ-ጋጥ አድርጌ አልፌያለሁ። ይሄ ኃጢያት ከተባለ ፍረዱብኝ” ከማለቷ ተኩላው ከተቀመጠበት በፍጥነት በመነሳት፣ “አንቺ ደፋር በስራ ሰዓት ለሆድሽ ስትንሰፈሰፊ በሰራሽው ኃጢያት ነዋ እኛ ዛሬ ቀኑን ሙሉ ምግብ ሳናገኝ የቀረነው” ሲል ደነፋ። አንበሳም ቀጠለ፣ “አንቺ ሆዳም አህያ ለሁለት ጉንጭ ሳር ብለሽ የተከበረውን የሰው ልጅ ጊዜ ታቃጥያለሽ” አለ። ይሄንን አንበሳውን ንግግር ተከትሎ ሁሉም እንስሳት አህያን ኃጢያተኛ አደረጓት። እናም እየተቀባበሉ ዘነጣጥለው ምግባቸው አደረጓት።

አያችሁ ጎበዝ ቀን ፊቱን ያዞረ ዕለት እንዲህ ነው፤ ጉልበት ካላቸው ጋር ያለአቻ ገጥሞ ከመልፋት ይልቅ ማንጋጠጥ ይበልጣል ያልነውም ለዚሁ ነው። “አውጣኝ ያለው ወጣ፣ አብላኝ ያለው በላ” ያለው ማን ነበር? እናም ጎበዝ ልፋት ጥሩ ነው። መልፋትም ለውጤት መደገፊያ ነው።  ነገር ግን “ከማይረባ ጉልበት ልብ አርጉልኝ” ማለት እንደሚያዋጣ ሁሉ፤ “ከመሮጥም ይሻላል ቅድሚያ ማንጋጠጥ” ቸር እንሰንብት!!! 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
520 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 923 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us