“ቀንዳም በሬ. . .”

Wednesday, 04 January 2017 14:32

 

የተስፋዬ ዛፉ

የተስፋዬ ዛፉ

ሲከረከም ቅርንጫፉ፣

ሥሩ ሲነቃቀል

ሊበጠስ ሲፈነገል፤

ጭላንጭል ስትዳፈን

ብርሃን ዐይኑ ሲከደን፣

አንጥሬ ደርቤ ማቄን

ዘንግቻት እንቁጣጣሼን፣

ዐደይ አበባ ፀደዬን፣

በድቅድቁ ተቀመጥሁኝ

ላለማሰብ እያሰብሁኝ

የልቤን ልበ- ባሻነት ገሰፅኩኝ

ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አረኩኝ፡፡

(ከደበበ ሰይፉ - “ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ” የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እንዴት ነው ሰሞኑን የተጠርጣሪዎቻችን ወሬ የከተማውን አቧራ አጪሰውም አይደል?. . . የምር ግን በሙስና ተጠርጥረው የሚመረመሩት 130 ባለሃብቶችና ባለስልጣናት ብቻ ናቸው? ግድ የላችሁም ቁጥሩ ትንሽ ነው፡፡. . . ጎበዝ አገራችን እኮ ሙሰኞች እንደጉድ የፈሉባት ሆናለች፡፡ ምነው እንኳን ድሮ-ድሮ ጠቅላያችን አንድ እጃችንን ታስረናል እስኪሉ ድረስ መማረራቸውን ተናግረው የለ እንዴ?

ይኸውና ሰሞኑን ባለስልጣናትና ባለሀብቶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው አይነት ወሬ ሲሰማ ህዝቤ ሁሉ “ክውው” አለ፤ ለምን? ሲባል እንዲህ መጨካከን ደረጃ ይደረሳል ብሎ አልጠበቀማ፡፡ “አይጥ በበላ፤ ዳዋ ተመታ” አልነበር እንዴ ድሮ የሚደረገው፤ ለማንኛውም አሁን ላይ አፋችሁን ይዛችሁ ጉድ! ስትሉ ለሰማናችሁ ሰዎች የምትሆን ቅኔ እንካችሁማ፤

ብለነው ብለነው የተወነውን ነገር

ባሏ ዛሬ ሰምቶ ታንቆ ሊሞት ነበር፡፡

እኛ ተወው ብለን ከተናገርን ቆየን እነሱ ይኸው ዛሬ ላይ “ለቀንዳም በሬ በር አትከልክለው ቀንዱ ይከለከለዋል” አይነት ታሪክ እያየን ነው፡፡ ስጋውንም፤ ሳሩንም፣ አጥሩንም አጥንቱንም ሲበላ የከረመ ድልብ ሙሰኛ ሁሉ “ቀንዳም በሬ” ይመስል . . .

እናላችሁ እኛ ዘንድ የቀንድ ነገር ብዙ አለ፡፡ . . . የመልካም አስተዳደር አለመኖር ቀንድ፤ የሙስና ቀንድ፣ የጥቅመኛ ሹመኛ ቀንድ፣ የኢ-ፍትሃዊነት ቀንድ፣ የቁርጠኝነት ማነስ ቀንድ፣ የስግብግብነት ቀንድ ብቻ ምን አለፋችሁ ብዙ-ብዙ ቀንዳሞች አሉን፡፡ ታዲያ ይኸው “ቀንዳቸው” በሀገሪቱ ህዝቦች ልብ ውስጥ አላስገባ ብሏቸው የነሱ ዳፋ እኛ ላይ ሲደፋ አይተናል፤ የፀብ መነሻዎች፣ የግጭት ምክንያቶች ሲሆኑ ታዝበናል።

የምር-የምር እንነጋገር ከተባለ ህዝቡ ከመሪው ቀድሟል፡፡ ዳሩ ግን ሰሚ ያጣ ይመስል ችግሩን ሁሉ ይናገራል እንጂ “አፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጠው የለም” ለዛም ነው ነገራችን ሁሉ እንደሞኝ ለቅሶ-መልሶ መላልሶ አይነት የሚሆነው፡፡ (እኛ ሙሰኛ በዛ እንላለን፤ መንግስትም ከአፋችን ነጥቆ ኧረ ሙሰኞች አስቸገሩኝ ይላል እንጂ ተግባራዊ እርምጃው ላይ የለበትም፤ ማን ያውቃል አሁን ማየት ልንጀምር ይሆናል፡፡)

ጎበዝ “አመል- ያወጣል ከመሀል” እንዲሉ የግለሰቦች፣ የአስተዳደርም ሆነ የተቋውሞ አመልና አሰራር ካልተሻሻለ በስተቀር ከመሀል የሚያወጣው ጉድ አያጣውም፡፡ እዚህች'ጋ ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችን ማዋዣ ትሆነን ዘንድ ከከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሳሌ” ሁለተኛ መፅሐፍ ውስጥ የምትከተለዋን እንካችሁ፤

የንጉስ ግምጃ ቤት ሆኖ የሚሰራ አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም የንጉሱን ገንዘብ እየሰረቀ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ ሀብት ሰብስቦ ነበር፡፡ ኋላም ከንጉሱ ዘንድ ቀርቦ፤ “ከእንግዲህ ወዲያ እየነገድሁ ለመኖር አስቤያለሁና ግርማዊነትዎ ፈቅደው ቢያሰናብቱኝ እወድ ነበር” ብሎ ለመነ፡፡  ንጉሱም መልሱን በኋላ እሰጥሃለው አለውና አሰናበተው፡፡ እርሱም ከወጣ በኋላ የእሱ ተቆጣጣሪ ሆኖ የሚሰራውን ሰው አስጠርቶ፣” ይህ ግምጃ ቤት (ሰራተኛ) ስራውን በትክክል ይሰራል ወይ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ተቆጣጣሪውም የጎደለውን ገንዘብ ሁሉ በመዝገቡ አመልክቶ፤ የሰረቀውን የገንዘብ ልክ ለንጉሱ አስረዳው፡፡

ንገሱ ከዚህ በኋላ ግምጃ ቤቱን አስጠርቶ እንዲህ አለው፡፡ አንድ ሰው ከእለታት አንድ ቀን ከገበታው ላይ አንድ ጠርሙስ ወተት አስቀምጦ ሳይወትፈው ረስቶት፤ ትቶት ሄደ፡፡ አንድ ቀን እባብ በጠርሙሱ አፍ ገብቶ ወተቱን ሁሉ ጭልጥ አድርጎ ጠጣው፡፡ ከጠጣው በኋላ በዚያው በጠርሙሱ አፍ ተመልሶ ሊወጣ ቢሞክር ሰውነቱ በጣም ደነደነና የጠርሙሱ አፍ አላስወጣህ አለው፡፡ ምን ቢታገል ለመውጣት የማይችል ሆነበት፡፡

እንግዲህ እንዳንተ ሃሳብ ይህ እባብ ከጠርሙሱ ውስጥ ለመውጣት እንዲችል ምን ማድረግ ይገባዋል ብሎ ጠየቀው፡፡ (ሰውየውም) የጠጣውን ወተት ሁሉ መመለስ ያሻዋል፤ ይህን ያደረገ እንደሆነ ሰውነቱ እንደቀድሞው ተመልሶ ይቀጥንና የጠርሙሱ አፍ ያስወጣዋል፡፡ አለዚያ ግን ለመውጣት አይችልም፣ ብሎ ግምጃ ቤቱ ለንጉሱ መለሰለት፡፡ ንጉሱም ያንተም ነገር እንዲሁ ያለ ነው ብሎ በምሳሌ አስረዳው ይባላል፡፡

እናላችሁ አንዳንድ አለቆች፤ አንዳንድ ሹመኞች፣ አንዳንድ ባለሀብቶች፤ አንዳንድ ባለስልጣናትም እንዲሁ ናቸው፡፡ የሙስና፣ የብልሹ አሰራር፣ በጥልቀት ያለመታደስ፣ የአገልጋይነት ስሜት ማጣታቸው ሁሉ ተደማምሮ ያገኙትን ይጨልጡና “ልባቸው ይሰባል” ያኔ ታዲያ ወደህዝቡ የልብ ጓዳ እንዳይገቡ ስራቸው ቀንድ ሆኖባቸው ይከለክላቸዋል፡፡ በዚያም ነው “ቀንዳም በሬን በር አትከልክለው ቀንዱ ይከለክለዋል” የሚባለው፡፡

ለማንኛውም ዘንድሮ ደፋር እና ቀጥተኛ የመፍትሄ ሃሳቦችን በተግባር አስደግፎ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ፤ ወተት እንደመጠጠው እባብ፤ የህዝብን ላብና ደም የመጠጡ ግለሰቦችም ይኖራሉና መወጫው እንዳይጠባቸው ከወዲሁ ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡ ቀንዳቸውን በበራችን ልክ ያርጉልን አቦ! ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
496 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 979 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us