“እውነትና ንጋት. . .”

Wednesday, 11 January 2017 14:24

 

አቤቱ!

“ኃይል ያንተ ናት” ብዬ

ፀለይኩ አመሰገንኩ

አንተም በመንበርህ ቆየህ ተመለከትኩ

“ከክፉ ሰውረን” ብዬ ስጠይቅህ

ይሄው ዘመን ቆጠርኩ. . .

መልስህን ተነፈግኩ!

     (ከዓለምፀሐይ ወዳጆ - “የማታ እንጀራ” የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . የበዓሉ ግርግር እንዴት አለፈሳ?. . . ይመስገን ከወዳጅ ዘመድ ተገናኝተንበታል። እኔ የምለው ከዶሮ ይልቅ ዘይት ተራ በሰልፈኛ ሲጥለቀለቅ ሰነበተ ምናምን የሚባለው ነገር እውነት ነው እንዴ? ኧረ ግድ የላችም የዚህ ሀገር ገበያ ስኳር እና ዘይት “ምሱ” ነው መሰለኝ ህዝቤ ተሰቃየ እኮ! ታዲያ ለምንድው በርካታ የስኳር ፋብሪካዎች ስራ መጀመራቸውና በርካታ የዘይት ምርቶች ገበያውን ማጥለቅለቃቸው ብቻ ተለይቶ በቲቪና በሬዲዮ የሚለፈፈው፣ ግድ የላችሁም ይዋል ይደር እንጂ እውነትና ንጋት እያደር መውጣቱ አይቀርምና ባንወሻሽ መልካም ነው። (ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም ያለው ማን ነበር?)

እኔ የምለው ነገራችን ሁሉ፤ ችግራችን ሁሉ፤ ማጣታችን ሁሉ፤ አቤቱታችን ሁሉ በስብሰባና በጭብጨባ ብቻ የሚፈታ የሚመስላቸው ሰዎች እየበዙ የመጡ አልመሰላችሁም?. . . የምሬን እኮ ነው፤ የኛ ችግር ሌላ የሚሰጠን መፍትሄ ሌላ፤ የኛ በሽታ ሌላ የሚሰጠን መድሃኒት ሌላ፤ የኛ ጥያቄ ሌላ የሚሰጠን ምላሽ ሌላ፤ እኛ የምንፈልገው ሌላ እነሱ የሚሰጡን ሌላ፤ የሚታቀደው ሌላ የሚተገበረው ሌላ፤ እንደው ምን አለፋችሁ ነገራችን ሁሉ “አራምባና ቆቦ” አልያም “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” አይነት ከሆነ የሰነባበተ ይመስለኛል።

ይሄ ነገር እንድዬም ጋር ሳይደርስ አልቀረም፤ ገጣሚዋ እንዳለችው “ከክፉ ሰውረን” ብለን ጠይቀነው ይህውና ብዙ ዘመን ከክፉ ጋር አለን። . . . ግድ የለም ጎበዝ! አንድዬ በቀጥታና በፍጥነት መልሱን አልሰጠም ማለት ጥያቄያችን (ፀሎታችን) ውድቅ ሆኗል ማለት አይደለም። ይልቅዬ እዚህች'ጋ አንዲት ወዝ ያላት ቅኔ ብንቀኝ ምን ይለናል?

ወንጌል ሰባኪዎች ገልጠው ነገሩን፣

አረመኔዋ ሴት አምና መሞቷን።

እናላችሁ የአንድዬን ነገር ከአምና ጀምረን እንዳመንን በተስፋ አለን ማለቱ ደግ ነው። አለበለዚያማ የዘንድሮ ነገራችን “እውነትና ንጋትን” ያለቀብን መስሏል። ለዚያም ይመስላል ተስፋ ስንቆርጥ የሚከተለውን የምንቃኘው፤

ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ

የዘመኑ ክፋት እንዲህ ሳይፀናብኝ።

እናላችሁ አንድዬ እውነቱንና ንጋቱን ፍንትው አድርጎ ያሳየን እንጂ እኛማ አቤት! በማለት ብቻ ደክሞናል። ማን የማን ወገን እንደሆነ? ማን ምን ያህል “እንደበላ”? ማን ምን ዓይነት ሀብትና ዘመድ እንዳለው፣ ማን የት ቦታ ቤት፣ የት ቦታ ደግሞ መሬት እንዳለው ለማወቅ ተደነጋግሮናል። እናም ከመማረርም ከማማረርም መጀመሪያ አንድዬ ሁሉንም እጃችን ላይ እንዲጥልልን አቤት ብለናል። በቃ! ማን ምን እንደሆነ የለየን ዕለት ግን፤ ያኔ እኛን ነው ማየት፤ እነሱን አያድርገን አቦ! እዚህች'ጋ አንዲት ቆየት ያለች ጨዋታ እናስታውሳለን።

ነገሩ የሆነው በደርግ ዘመን ነው። ሰውዬው አውቶብስ ፌርማታ ላይ ቆሞ የሰፈሩን ባስ እየጠበቀ ሳለ ሌላ ሰው ይመጣል። በፌርማታው ላይ የቆመው ቀጠን ያለ ሰው ድንገት ሳያስበው ጫማው ተረገጠ። ጫማውን የረገጠው ደግሞ ረጅምና ወፍራም ሰው ነበር። በዚህ ጊዜ የተረገጠው ሰውም “ይሄ ሰውዬ የደርግ ባለስልጣን መሆን አለበት እንጂ እንዲህ ረግጦኝ የመቆም ድፍረት አይኖረውም” ሲል አሰበ። እናም የእግሩን ህመም እንደምንም ተቋቁሞ ቀና አለና፣

“ጌታዬ የቀበሌ ሊቀመንበር ነዎት?” ሲል ጠየቀ።

“አይደለሁም” ሰውዬው ቆፍጠን ብሎ መለሰ።

“የአብዮት ጥበቃ ጓድ ነዎት?” አሁንም ጠየቀ።

“አይደለሁም!” ሰውዬው መለሰ።

“እሺ የኢሠፓ አባል ነዎት?” በጭንቅ ሰውዬው አሁንም ይጠይቃል።

“አይደለሁም አልኩ እኮ አትሰማም” ሰውየውም ተናደደ።

“እሺ የደርግ ባለስልጣን ዘመድ ነዎት?” ለመጨረሻ ጊዜ ጠየቀ።

“ኧረ አይደለሁም” በተሰላቸ መንፈስ ሰውዬው መልስ ሰጠ። ይሄን ጊዜ የተረገጠው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው? “ታዲያ ምን አባክ ቆርጦህ ነው እግሬ ላይ ተንፈራጠህ የቆምከው?” አለና ለያዥ ለገላጋይ በሚያስቸግር ፀብ ተጋበዘ ይባላል። . . . እናም እውነትና ንጋቱ የጠራ ቀን (ማን- የማን ወገን እንደሆነ የተረዳን ቀን) እንዲህ ለዱላ ከመጋበዛችን በፊት ግድ የላችሁም ፍትህ ይምጣ!

እናላችሁ ከመሰነባበታችንም በፊት እንዲህ እንላለን፤ “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እና ወደእውነቱና ወደንጋቱ በመቅረብ ላይ ስለምንገኝ በግምገማውም ላይ ይሁን በጥልቅ ተሀድሶ ላይ እውነት እውነቱን ብንነጋገር መልካም ነው። በተረፈ ግን የዓለምፀሐይን ግጥም ደግመን አቤት እያልን “አቤቱን” እንጠይቃን።

     አቤቱ!

“ኃይል ያንተ ናት” ብዬ

ፀለይኩ አመሰገንኩ

አንተም በመንበርህ ቆየህ ተመለከትኩ

“ከክፉ ሰውረን” ብዬ ስጠይቅህ

ይሄው ዘመን ቆጠርኩ. . .

መልስህን ተነፈግኩ!

እናላችሁ አንድዬ ከዘገየ ፍርድ ጠብቆ፤ ለጥያቄያችን መልስ የሚሰጠንን ጊዜ ቶሎ ያምጣልን አቦ!. . . ቸር እንሰንብት። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
479 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 950 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us