የደሃና የጌታ ነገር. . .

Wednesday, 18 January 2017 10:04

 

እኔ ድሃ መስሎኝ ተራቁቶ ባየው፣

ለካስ ጌታ ኖሯል የተሰቀለው።

     (እንዲል ባለቅኔ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . እኔ የምለው የምንቦዳደንበት፣ የምንለያይበት፣ የምንለካካበት ነገር የበዛ አልመሰላችሁም?. . . የምሬን እኮ ነው፤ በፈጣሪ አምሳል አንድና እኩል ተደርጎ የተሰራው ሁሉ በምድራዊ ዓይን እንዲህ ልዩነቱ መብዛቱ ይደንቃል። . . . ይልቅ የምድር ነገር ሲነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ የሰሞኑ ብርድ “ምን” ያሳቅፋል የሚባለው አይነት ሆኗልም አይደል። ይኸውና አንዱ ማስታወቂያ ተናጋሪ ከሰሞኑ ምን ሲል ሰማሁት መሰላችሁ. . . የፀሐይዋን ግለት ለመግለፅ ይመስላል። “ዶሮ የምትጥለው እንቁላል ቅቅል ነው” ወይም፣ “በቆሎ ከማሳው ሳይነሳ ጥብስ ነው” አይነት ነገር ሰምተን ፈገግ ብለናል። የሚገርመው ግን የፀሐዩዋን ግለት ያህል ብርዱም አይጣል ሆኗል።

ኢራናዊው ወዳጃችን ሙላህ ነስሩዲን በአንድ ወቅት እንዲህ ብሏል ተብሎ ተጽፏል። ወቅቱ እጅግ ብርዳማ ነበርና አንድ ባለፀጋ አለኝ የሚለውን ልብስ ደራርቦ በመንገድ ይሄዳል። በካኔቴራ ላይ ሸሚዝ፣ በሸሚዝ ላይ ሹራብ፣ በሹራብ ላይ ኮት፣ በኮት ላይ ካፖርት በካፖርት ላይ የአንገት ልብስ የደራረበው ይህ ባለፀጋ ሰው ድንገት ነስሩዲን የለበሰውን ልብስ ሲያይ ደነገጠ።

ወዳጃችን ነስሩዲን አለችኝ የሚላትን ስስ ልብስ ለብሶ፣ አንዳችም የብርድ ስሜት ባለፈጠረበት አኳኋን መንገዱን እየተጓዘ ሳለ፤ ባለፀጋው ያስቆመውና”፣ እኔ የምልህ ነስሩዲን! እኔ ይሄን ሁሉ ልብስ ደራርቤ ይኸውና አሁንም ብርዱ ይሰማኛል። አንተ ግን ይህቺን ትንሽዬ ስስ ልብስ ለብሰህ ምንም አይነት የብርድ ስሜት አይታይብህም ምስጢሩ ምን ይሆን?” ብሎ ይጠይቀዋል። ሙላህ ነሰሩዲን ሲመልስም፣ “ወዳጄ እኔ ያለኝ ልብስ ጥቂት ስለሆኑ ስለብርድ አልጨነቅም። አንተ ግን የምታማርጣቸው በርካታ ልብሶች ስላሉህ፤ ብርድን ስለመከላከል የማሰቡ መብት አለህ። ያ ነው ልዩነታችን” ብሏል። እዚህች'ጋ የመሀሙድ አህመድን ዘፈን እንደማጀቢያ ስንጠቀምባት፤

“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣

ታላቅ ችሎታ ነው” . . . ድመት በአንድ ወቅት “የቱንም ያህል ቢታለብ ለኔ የሚደርሰኝ ያው በገሌ ነው” ብላለች አሉ። ይሄን ጊዜ ተዲያ ባለቅኔው የጠቀሳትን ቅኔ እዚህች'ጋ እንጠቅሳን።

እኔ ድሃ መስሎኝ ተራቁቶ ባየው፣

ለካስ ጌታ ኖሯል የተሰቀለው።

በእጃችን፣ በደጃችን፣ በሻንጣችን፣ በባንካችን፣ በልባችን ያለውን ነገር መጠን ካወቅን አስተሳሰባችንም እንዲሁ ይሆናል። አቅሙን የማያውቅ፣ ልኩን የማያውቅ፣ ያለውን ሀብት የማይረዳ ሰው ግን በእጅጉ ይቸገራል። እናም ድሃ የመሰለን ሁሉ ማን ያውቃል ጌታ ሊሆን ይችላልና አንሳሳት። ድሃ ነው፣ ዋጋ የለውም፣ ገንዘብ የለውም፣ መኪና የለውም፣ ደህና ልብስ እንኳን የለውም ብለን የምናብጠለጥለው ሰው ድንገት አንድ ቀን ጌታ ይሆንና ልዩነታችንን ባናሰፋው ምን ይለናል ጎበዝ!?. . .

እናላችሁ እውነት - እውነቱን መነጋገር ከመደነጋገርም ሆነ ከመተማማት ያድነናልና እውነቷን እንተንፍሳት። ለጌታ ሲሆን ደመቅ፤ ለድሃ ሲሆን ደቀቅ ማድረግ “ፌር” አይደለም። . . . አለበለዚያ ግን ለብርድም ለሙቀትም የማይሆን ልብስ ይዘን በምርጫ ከምንጨናነቅ እውነቷን ተናግሮ የመሸበት ማደር ሳይሻል አይቀርም። እናም ድምጻዊው እንዳለው።

“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው

ታላቅ ችሎታ ነው።”

(የምትለዋን ነገር ማስታወስ ደግ ነው)

የእውነት እቅድ ስናወጣ፤ የሀሰት ዕድሜ ያጥራል ትል ነበር አያቴ። እናም ለክርክርና ለውዝግብ የምናወጣው ጊዜ ይቀንሳል። አይደለም የምናማርጠው ልብስ የምናማርጠው “ውሸት” ካለን የምንከፍለው ዋጋ ብዙ ነው። እዚህች'ጋ አንዲት ጨዋታ አንስተን ትዝብታችንን እናሳምርና እንሰነባበት።

ሰውዬው ወንጀል ፈጽመሐል ተብሎ ፍርድ ቤት ይቀርባል። ዳኛውም መዝገቡን ተመልክተው ሲያበቁ፣ “ጠበቃ አለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል። ተከሳሹም፣ “የለኝም ክቡር ዳኛ” ሲል ይመልሳል። የጉዳዩን ከባድነት ያስተዋሉት ዳኛም፣ “ለመቅጠር አላሰብክም?” ሲሉ ጥያቄያቸውን አስከተሉ። በዚህ ጊዜ ተከሳሹ ምን ቢል ጥሩ ነው? “ምን ይሰራልኛል ክቡር ዳኛ! ያሰብኩት እኮ እውነቱን አብጠርጥሬ ለመናገር ነው።” ብሎላችሁ እርፍ። አያችሁ እውነትን ስትይዙ መንገዱ ቀጥተኛና አጭር ነው። ለማንኛውም ለብርዱም ለግለቱም የሚሆን ነገር አንድዬ አያሳጣን አቦ! ለጌታም ለደሃም የሚበጀውን ጊዜ ያምጣልን!. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
390 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 926 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us