የመልስ ምት

Wednesday, 25 January 2017 13:04

 

እያለሰለሱ ካልያዙት በስተቀር

ካከረሩትማ መበጠሱም አይቀር።

(ድምፃዊ ግዛቸው ተሾመ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... በዓለ ጥምቀቱ እንዴት አለፈ?... መቼም ዘንድሮ ሎሚ ተወዶ ህዝቤ ሁሉ ዓይኑን እና ቃላቱን ብቻ ሲወረውር እንደነበር ከታማኝ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።… ግድየላችሁም ከሁሉም በፊት በምላስ ጠቅ-ጠቅ ተደራርጐ መግባባቱ ውጤት ሳይኖረው አይቀርም - እናንተም ሞክሩት። ይልቅዬ ጥምቀት የምግብ በዓል አይደለም ምናምን ሲባል ሰማው ልበል?... ሕዝቤ ታዲያ ከቤቱ ያስቀረውን በመንገድ ሲሰንቅ ምን እንለዋለን? ለማንኛውም የወረወራችሁም የተወረወረላችሁም እንኳን ዕድል ቀናችሁ ብለናል።

 

ምን ሆነ መሰላችሁ?... ሕዝቤ ታቦት አጅቦ በሚጓዝበት ወቅት ነው። ልጁ ልጅቷን አይቶ ወደዳት። ደጋግሞ ቢጠቅሳትም (የሎሚው ነገር መቼም አልሆነለትም ይሆናል) መልሷ ዝም ሆነ። ለካንስ ልጅት ፀሐዩና ድካሙ በርትቶባት ኖሮ ሻይ ቡና እያለ የሚያሳርፋትን ሰው ትፈልግ ነበር። ይሄ ነገር ያልገባው ወጣቱ ድፍረቱን አሰባስቦ ወደልጅቷ ተጠጋና፣ “ምንድነው አንቺ ጥቅሻ አይገባሽም እንዴ?” ከማለቱ የእርሷ ምላሽ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “ምናለበት አንተስ በዓይንህ ብቻ ከምትጠቅሰኝ በኪስህም ብታናግረኝ” ብላላችሁ እርፍ። (ቂ… ቂ… ቂ… እንግዲህ የአየር ንብረቱ ጣጣ እዚህ ድረስ ፈጣጣ ያደረገን ይመስለኛል ጐበዝ)

 

ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችን አንዲት የአበው ጥቅስ እንካችሁ፣ “ከነገረኛ ሰው ስንቅ አይደባልቁም” ትላለች። እውነት ነው ማን ሰላሙን ያጣል። በሆነው ባልሆነው በነገር ጠቅ-ጠቅ ካልቻልንበት እኮ ተቃጥለን ማለቃችን ነው። ይሄ የነገረኛ ነገር ከተነሳ ላይቀር የምትከተለዋን ጨዋታ እንካችሁ።

 

ጊዜው ቆየት ብሏል። የኛ ሰው ሶቭየት ኅብረት (አሁን ሩሲያ የምንላት መሆኗ ነው) ትምህርቱን ይከታተላል። ታዲያ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ራሻዊያን ምን ያህል ለድንች ፍቅር እንዳላቸው ተገንዝቧል። (በነገራችን ላይ ራሺያ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓልን ተከትሎ የታቦት አጀብ ካለ፤ ከሎሚ ይልቅ ድንች እንደሚወራወሩ አትጠራጠሩ ቂ… ቂ… ቂ…)

 

እናላችሁ ይህ የእኛ ሰው ታዲያ አንድ ቀን ምሳ ላይ አጥንት ያለው ስጋ ይቀርብለትና እያጣጣመ አጥንቱን እንደ አርሞኒካ መጋጡን ይቀጥላል። ከፊት ለፊቱ ተቀምጦ የነበረ አንድ ራሺያዊ የሀበሻውን የአጥንት አጋጋጥና አቆረጣጠም ሲመለከት ደነቀው። ተደንቆም አላበቃ የሚከተለውን ጠየቀው፤ “እኔ የምልህ እናንተ ሀበሾች አጥንት እንዲህ የምትግጡና የምትቆረጣጥሙ ከሆነ በሀገራችሁ የውሻ ቀለቡ ምንድነው?” ብሎ ከማለቱ የኛ ዘር ጐመንዘር ምን ቢመልስለት ጥሩ ነው? “በእኛ ሀገር የውሻ ቀለብ ድንች ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ… ቂ… ቂ…! … እንዲህ ነን እንግዲህ የመልስ ምት ስንሰጥ።

 

እሾህን በእሾህ እንዲሉ ነገረኛ ሰው ካጋጠመን በነገር ጠቅ-ጠቅ መግጠም ግድ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል። ባልና ሚስቱ በነገር መነታረክ ከጀማመሩ ሰነባብተዋል። ታዲያ አንድ ቀን ድንገት ሚስት በፈገግታ ተሞልታ ትመጣና “ይኸውልህ ቀለበትህን ውሰድልኝ ሌላ ሰው አግኝቻለሁ” ከማለቷ ከአፏ ነጥቆ፣ “የሰውዬውን ስምና አድራሻ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?” ሲል ጠየቃት። ሚስት ሆዬ በሚያስቀና ፌዝ ውስጥ ሆና፣ “ለምን ልትገልብኝ ነው?” ስትል ጠየቀችው፤ ባል ሆዬ የዋዛ ሰው አልነበረም ለካ ምን ቢላት ጥሩ ነው? “ኸረ ምን በወጣኝ ቀለበቱን ልሸጥለት ፈልጌ ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ… ቂ… ቂ… ! እንዲህ ነው እንግዲህ በነገር ጠቅ-ጠቅ ጨዋታ ማለት።

 

እናላችሁ “ከነገረኛ ሰው ስንቅ አይደባልቁም” እንዲሉ ብንጠነቀቅም ገፍተው ከመጡብን ግን ምላሻችንን አዘጋጅተን በተጠንቀቅ መጠበቁ አይከፋም። ለምን ቢባል ድምፃዊው እንዳለው፤

 

እያለሳለሱ ካልያዙት በስተቀር

ካከረሩትማ መበጠሱም አይቀር

 

 

ተብሏልና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም። ድንገት ግን ከነገረኛ ሰው ጋር ስንቃችን ከተደባለቀ የአፀፋ ምላሻችን ምን መሆን እንዳለበት በተዘዋዋሪ ከምታመላክት ወግ ጋር እንገናኝ። ጨዋታዋን ያኘናት “እንቅልፍ ለምኔ” ከተሰኘችው ከብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል መጽሐፍ ነው። መጽሐፏ የአንድ ወታደርና ተማሪን ታሪክ እንዲህ ትተርካለች።

 

አንድ ወታደር ሰጋር ፈረስ ጭኖ፣ ጠመንዣውን አንግቶ በጐዳና ሲገሰግስ፤ አንድ ተማሪ ደበሎውን ለብሶ ልብሱን በአኮፋዳው ቋጥሮ ሲሄድ ደረሰበት። በዚህም ጊዜ ወታደሩ ተማሪውን፣ “ተሜ ምን ይዘሃል? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ብሎ ቢጠይቀው፤ “ጥጥ መሳይ መዝኜ ለእናቴ መውሰዴ ነው” አለው። ወታደሩ በሰጋር ፈረሱ ላይ እንደተቆናጠጠ ሲገማሸር፤ ተማሪው ብቻውን እንዳይሆን እየተከታተለው ሲሄዱ ውለው መሸባቸውና ወታደሩ፤ እዚህም “እባካችሁ አሳድሩኝ”፤ እዚያም “እባካችሁ አሳድሩኝ” እያለ በየቤቱ ሲለምን እሺ የሚለው አጣ። ተማሪው ግን የክት ልብሱን ከአኮፋዳው አውጥቶ ለብሶ ጥምጥሙን ጠመጠመና፤ “በእንተ ስሟ ለማርያም፣ ስለቸሩ እግዚአብሔር የመሸብኝ እንግዳ አሳድሩኝ” ብሎ ለመናቸው። እነዚያም ሰዎች ወዲያው አባቴ ይምጡ ብለው አስገቡና ጐዝጉዘው የሰንጋ ቁርበት በአልጋው ላይ አንጥፈው፤ ጠላውን ከማጀት ቀድተው፤ እንጀራውን ከሌማት በገበታ አድርገው ግብር ሰሩና ማዕድ ይባርኩልን ብለው አስባርከው እራታቸውን በመልካም አድርገው ተጋበዙ።

 

ያ ወታደር ግን ፈረሱን ይዞ ከደጅ ተቀምጦ ነበርና ተማሪው ባለቤቶቹን አሽከሬ እደጅ ከብት ይዞ ተቀምጧልና አስገቡልኝ አላቸው። ባለቤቱም ተነስቶ ወጥቶ ፈረሱን ተቀብሎ አስገብቶ ለሰውዬው የተማሪውን ትርፍራፊ እንዲበላ ሰጠው። ከራትም በኋላ ተማሪውን በመልካም ከተነጠፈ አልጋ ላይ አስተኙት። ወታደሩ ግን በአሽከር ደንብ ተማሪው ከተኛበት ቤት ከማደያው ላይ ትንሽ ደሳሳ (የሚነጠፍ ነገር) ተሰጠውና ያቺን አንጥፎ ከዚያ ከደረቀ መሬት ላይ ተኛ።

 

ከዚህ በኋላ ሰው ሁሉ እንቅልፍ ሲወስደው ወታደሩ ሌሊት ከተኛበት ተነሳና ተማሪው እንደዚህ የተከበረው በዚህ በልብሱ አይደል? ብሎ ከምድጃ የግራር ጉልጥምት ተዳፍኖ ነበርና የዚያን የተማሪ ልብስ በዚያ በእሣት እዚያም-እዚያም እየለኰሰ ብስትስት አድርጐ ተመልሶ ተኛ። ተማሪው ግን ይህን ሁሉ ሲሰራ ተከናንቦ ያይ ነበርና ወታደሩ እንቅልፍ ሲወስደው ጠብቆ የሰጋር ፈረሱን ለንጨጭ በጩቤ ሙልጭ አድርጐ ቆረጠና ተመልሶ ተኛ።

 

ማለዳ ሲነጋጋ ቀደም ብሎ ተነስቶ ያንን በእሣት የተቃጠለ ልብሱን ለብሶ በዚያ በወታደር ፈረስ ፊት ለፊት ቆሞ ዳዊት ይደግም ጀመር። ያም ወታደር ከእንቅልፉ እንደተነሳ መጣና የፈረሱን ለንጨጭ መገልፈፍ ሳያይ “ደብተራ ልብስህን ምን እንደዚህ አቃጠለው?” አለው። በዚህ ጊዜ ተማሪው እንዳላየ ሰው፣ “ውይ-ውይ ለካ ያንተ ፈረስ የሚስቀው የኔን ልብስ መቃጠል እያየ ኖሯልን” ብሎ መለሰለት ወታደሩም ቀና ብሎ ቢያይ ፈረሱን ጥርሱን አግጦ ስላገኘው ራሱን ይዞ ጮኸ ይባለል።

 

እናላችሁ ከነገረኛ ሰው ጋር ስንቃችንን ስንደባልቅ - ጠቅ ሲያደርገን እንዲህ ጠቅ ማድረግ ካልቻልን ይደብራል። የሰውን ልብስ ማቃጠል ብቻ ሳይሆን፤ የኛም ጥርስ ሊረግፍ፤ አልያም ድዳችን ሊገፈፍ ይችላልና ጐበዝ ለመልስ ምት ተዘጋጅቶ መጠበቁ ሳይሻለን አይቀርም። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
706 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 933 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us