መቶ እንደአንድ ብር. . .

Wednesday, 01 February 2017 13:47

 

ያንዱን ጎጆ አንደኛው አይቶ ሲያንኳስሰው

ሁሉም ተናናቀ ማንይሆን ትልቅ ሰው

ጀንበር ጥልቅ አለች አንዱባንዱ ሲስቅ

ከሰዎች መካከል ማንይሆናል ትልቅ

መቧጨቅ መናከስ ሆኗል የሰው ጣጣ

አቤቱ ጌታዬ ደጉን ዘመን አምጣ

      (አንጋፋው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እነሆ ገዥዎቻችን ሲሰበሰቡ እኛ ደግሞ እንደደጋሽ ሽር - ብትን ስንል ሰነበትናት አይደል?. . . እኔ የምለው የትራንስፖርትን መጨናነቅ ስመለከት ምን እንዳሰብኩ ታውቃላችሁ? በቃ መሪዎቻችን ሲሰበሰቡ (ሲሰሩ) እና በዓመት እንኳን እንድናርፍ ቢደረግ ምን ይለናል?. . . በነገራችን ላይ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባን ስናስታውስ የጋምቢያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ ትዝ አሉኝ!. . . ምነው እንኳን ስልጣን አለቅም ብለው በምርጫ ያሸነፏቸውን ሰውዬ በጡጫ ወደጎረቤት ሀገር እንዲኮበልሉ አድርገውም አልነበር?. . . ይህውና አንድዬ ቀን ቆጥሮ “እነሱ ሲሄዱ እኛ ተቀያሪ” አይነት ታሪክ ሰሪ አደረጋቸው አይደል?. . . ግራ የገባኝ ነገር ያህያ ጃሜህ ስልጣን ልቀቁ ሲባሉ አገር ለቀው የመውጣታቸው ነገር ነው። (ቂ.ቂ.ቂ ለጠላቴ ብለህ ጉድጓድ አርቀህ አትቆፍር ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና ማለት ይሄኔ ነው። ጃሜህ ምን እንደቆፈሩ ማን ያውቃል?)

እናላችሁ ያገራችን ሰው እንደሚለው “እግዜር ሲጥል፣ እናትም አታነሳም” ማለት እንዲህ ነው። ጃሜህን እግዜር ጥሏቸው ነው መሰለኝ ጦራቸውም ሊያነሳቸው ሳይችል ቀርቷል። ይልቅዬ ስማችን እንደመቶ ብር ስራችን እንደአንድ ብር አክሎ ተዋርዶ-ከመውረድ አንድዬ ይሰውረንማ። (ይህቺ ምርቃት በሙሉ ቀልባቸው እዚህ እኛ ዘንድ ለተሰበሰቡት አፍሪካውያን መሪዎች ባስተርጓሚ በኩል እንደደረሳቸው ይደረግልን አቦ!)

እኔ የምለው የምር ግን ዘንድሮ በየመስኩ “ስማቸው መቶ ብር ስራቸው አንድ ብር” የሆኑ ሰዎች አልበዙባችሁም?. . . ለዛ እኮ ነው ጉዳያችንን ይፈፅሙልናል ያልናቸው ባለወንበሮች ሁሉ በሆነ ባልሆነ ያለአቅማችን “እጅመንሻ” እየጠየቁ ጉዳችንን እያፈሉት . . . ግን ትዝብት ነው ትርፉ።

ይሄ የአቅም አለመመጣጠን (መቶ ብር መስሎ አንድ ብር አክሎ የመታየቱ) ነገር ማለቴ ነው፤ በተለይ በፌስ-ቡክ መንደር የበረታ ነው። ትልቅ ነው ያላችሁት “እንትናዬ” መልኩን አሳምሮና “የትምሮ” ደረጃውን እንደሰባ ደረጃ ቆልሎ ሲያበቃ፤ አለ አይደል ወርዶ የአራተኛ ክፍል አይነት የቀለለ ሀሳብ ሲያነሳባችሁ ስም መቶ ብር -ስራ አንድ ብር ይሉት አነጋገር ከች ነው የሚልባችሁ።

አንቱ ያልናቸው ሰዎች ድንገት አንተ ሆነው ቀለው ሲገኙ፤ ችግር ፈቺ ይሆናሉ ያልናቸው ሰዎች ችግር አመንጪ ሲሆኑ፤ እኛን አስተባባሪ ይሆናሉ ያልናቸው ሰዎች ይባስ ብለው እኛን ሰባባሪ ከሆኑ ምን ዋጋ አለው ስማቸው መቶ ብር ስራቸው አንድ ብር አይነት ሆነው ተገኝተዋል ማለት ነው።

የአንዳንድ መስሪያ ቤቶች እቅድና ሪፖርትም እንዲሁ “በስም በመቶ ብር - በተግባር አንድ ብር” የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው። መሳጭና አስደንጋጭ ዕቅዶች ወጥተው፤ ከመሬት የራቁ ሪፖርቶች ተነበው ስንሰማ አለ አይደል ይሄ ነገር በስም መቶ ብር በተግባር አንድ ብር አይነት ነው ብለን ያለፍናቸው ስንት ጉዶች አሉን። እዚህች'ጋ አንዲት አገረኛ ብሒል ትዝ አለችኝ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” ትላለች። የኛ ነገር ሪፖርቱ ሁሉ፣ ስብሰባው ሁሉ፣ ዕቅዱ ሁሉ፣ ስኬቱ ሁሉ፣  ብዙ ጊዜ በስም እና በቁጥር ተደግፎ የሚኖር ይመስለኛል። ታዲያ ነገሩ አልገጥም ያላቸው ታዛቢዎች በሽሙጥ ምን ይላሉ መሰላችሁ? “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ቂ-ቂ-ቂ!

በፖለቲካው መስክ አንቱ ያልናቸው፣ በሃይማኖቶች ማማ ላይ ያስቀመጥናቸው፤ በህይወታችን ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆኑ አምነን የፈቀድንላቸው ሰዎች አለ አይደል ያለቦታቸው ወርደውና እምነታችንን በልተው ስናገኛቸው ነገራቸው ሁሉ፣ “በስም መቶብር- በተግባር አንድ ብር” አይነት ትዝብት ላይ መውደቃቸው ሃቅ ነው።

እስቲ ደግሞ ከመሰነባበታችን በፊት “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራልን” የምታስታውስ ታሪክ እንካችሁ. . . ሰውዬው ልጁን ስነ-ምግባር እያስተማረ ስለመሆኑ በኩራት ይናገራል። አንድ ቀን ጓደኛው ወደቤቱ ሲመጣ፣ “ልጄ እኮ ጎበዝ ሆኗል። ስነስርዓት ያለውና የሃይማኖታችንንም ህግጋት ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው። የቱ ተግባር ወደ ሲኦል እንደሚያስገባና የቱ ተግባር ደግሞ ወደገነት እንደሚያስገባ ጠንቅቆ እንዲያውቅ አድርጌዋለሁ” ብሎ በኩራት በመናገር ላይ ሳለ ድንገት ልጁ ከውጪ ሮጦ ይገባል። ይሄን ጊዜ ይለቅጥ ተጋኖ፤ ዝናውን ሲያደምጥ የቆየው የአባቱ ጓደኛ ወደልጁ ጠጋ ብሎ፣ “ለመሆኑ ወደመንግስት ሰማያት ለመግባት ምን ያስፈልገናል?” ብሎ ጥያቄውን ሳይጨርስ፤ ልጅዬው ፈጠን ብሎ ምን ቢመልስለት ጥሩ ነው? “ወደገነት ለመግባት በዋነኝነት የሚያስፈልገን ነገር ሞት ብቻ ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ!

እናላችሁ እንደመቶብር ይዘናቸው፤ እንደመቶብር አስበናቸው፤ እንደመቶ ብር ጠብቀናቸው፤ ነገረ ስራቸው ሁሉ እንደ አንድ ብር ከሆኑ ሰዎች አንድዬ ይጠብቀን አቦ!. . . ቸር እንሰንብት  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
391 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 531 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us