የጥሎ ማለፍ ዘመን. . .

Wednesday, 08 February 2017 14:59

የቀጠሮ ሰልፎች

እንጀራዬ ደርቆ ስጪኝ ብላት ወጡን

በጦም ልታበላኝ ዐርብ አለችኝ ቁርጡን።

     (ከገጣሚ ዮሃንስ ሞላ “የብርሃን ሰበዞች” ከተሰኘ

የግጥም መድብል ውስጥ ተቀንጭቦ የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እንዴት ነው ነገሩ ከግራም ከቀኝም እኛን ለመጣል የሚፈታተነን በዛ እኮ።. . . የምር ግን “ወደፊተናም አታግባን” ማለቱን ዘነጋነው መሰል እንጃልን ፈተናችንም፤ በዝቷል። እኔ የምለው የአፍሪካውያኑ መሪዎች ጉባኤ በሰላም ተጠናቀቀም አይደል? (ላመቱ ያድርሰን ተባብለን አንመራረቅ ነገር ጭንቅ ነው። በተለይ ለከተማችን የትራንስፖርት ለተሳፋሪዎችና ለታታሪ ሰራተኞች አስቸጋሪ እንደነበር ሁላችንም ታዝበናል። የምር ግን ያን ሰሞን የዓመት ፈቃድ ብንወስድ ኖሮ ደግ ነበር)

ይልቅዬ ስለአፍሪካ መሪዎች ካነሳን አይቀር፤ ስለአፍሪካ ትራፊኮችም ትንሽ ብንቦጭቅ ምን ይለናል?. . . ቡጨቃዋን ያገኘዋት ደግሞ ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ከፃፈው “የፒያሳ ልጅ” መፅሐፍ ላይ ነው። ጨዋታዋ እንዲህ ትላለች፤. . . አፍሪካ ውስጥ መንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም ወደየትኛውም አገር ስሄድ ወዳጆች ስላሉኝና የህዝቦቹም የዋህነት ችግሩን ያስረሳል። የኑሮ ችግር ሁሉም ዘንድ ተመሳሳይ ነው። ቀልዱም ያንኑ ያህል ነው። የትራፊክ ፖሊስ ታሪክ ግን ተወርቶ አያልቅም። የኮንጎ ሲንሻሳዎቹን የሚያህል የለም። አንዱ አንድ ቀን መኪና ያስቆምና መንጃ ፈቃዱን ይጠይቀዋል። ሁሉንም ካረጋገጠ በኋላ፣ “ይሄስ ምንድነው?”ሲል “ሙዚቃ ማጫወቻ ነው” በማለት ነጂው ይመልሳል። “ይሄ ተሽከርካሪ ዳንስ ቤት ስለሆነ ቀረጥ መክፈል አለብህ” ብሎት ጉርሻውን ተቀበለው ይባላል። አንዱ ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት ከተመረመረ በኋላ፣ “የተወለድኩበትን ማስረጃ አምጣ” ተብሏል። አፍሪካ ውስጥ የችግር መከላከያ ቀልድ ነው። ከማልቀስና ከማዘኑ መሳቁ መድሃኒት ይሆናል። (ገፅ ÷228)

ይህቺ ጨዋታ አፍሪካዊ እንደመሆናችን መጠን እኛም ዘንድ ትሰራለች። ከትራፊክ ፖሊሶች ውጪ ባሉ የስራ መስኮች ባለጉዳይና (ተገልጋይን) በጉርሻና በጥቅሻ ማጫወቱ የተለመደ ነው። የሚያስተዛዝበው ግን ለመብላት (ለሙስና) ሲሉ ብቻ የማይሆን ጥያቄ የሚጠይቄ ሰዎች ከገጠሟችሁ ነው። እዚህች’ጋ አንዲት ቆየት ያለች ጨዋታ ብቅ አለች። ሰውዬው ሰራተኛ አወዳድሮ ለመቅጠር ፈተና እየሰጠ ነው። የሚፈለገው አንድ ሰው ብቻ ሲሆን፤ ለፈተና የቀረቡት ደግሞ አንድ ጎረምሳና አንዲት ቆንጅዬ ልጅ ነበሩ። ታዲያ ከሁለቱ በሴቲቱ ውበት ፈተና የገባው ቀጣሪው ወንዱን ጥሎ፤ ሴቷን አንጠልጥሎ ለማሳለፍ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበላቸው።

“ቅድሚያ ለሴት ስለሚሰጥ የመጀመሪያው ጥያቄ ላንቺ ነው” አለ ፈገግ ብሎ፤ ልጅቷም የዋዛ አልነበረችም ፈገግታዋን ከእርሱ እጥፍ አድርጋ “እሺ የፈለከውን ጠይቀኝ” አለችው። (በነገራችን ላይ ይህቺ “የፈለከውን ጠይቀኝ” አባባሏ ለትንኮሳም የምትጋብዝ አይነት ሆና ተገኝታችና እናንተዬዎች የፈለግነውን እንድንጠይቃችሁ የልብ- ልብ አትስጡን አቦ!) ጠያቂው ጥያቄውን “ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በግምት ስንት ደርሷል?” ሲል ለልጅቱ አቀረበ። እሷም “በግምት 100 ሚሊዮን ደርሷል” ከማለቷ ትክክል በማለት ፊቱን ወደወንዱ አዙሮ ምን ቢጠይቀው ጥሩ ነው? “የ100 ሚሊዮኖቹን ኢትዮጵያውያን ሙሉ ስም በፍጥነት ጥራልኝ” ብሎት እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! (ሊበሏት ያሰቧትን . . .)

እናላችሁ እኛን ለመጣል የማይቆረጥ ገመድ፣ የማይቆፈር መንገድ የለም። ብቻ ግን ፈተናውን አብዝተው እኛን ከነፍስም ከስጋም ለማራቆት ለሚሹ ሰዎች ሁሉ የገጣሚውን ቅኔ ተውሰን እንዲህ እንላለን፣

 

እንጀራዬ ደርቆ ስጪኝ ብላት ወጡን፣

በጦም ልታበላኝ አርብ አለችኝ ቁርጡን።

የምር ግን በኛ ውድቀት ጊዜ የሚገዙ፣ በኛ ውድቀት ገንዘብ የሚያግዙ፣ በኛ ውድቀት ያሻቸውን የሚያፈሱ ሰዎች በየመስኩ የበዙ አልመሰላችሁም?. . .ኧረ ጎበዝ ግድ የለም እየተዛዘንን። በሆነ ባልሆነው እኛን ለመብላት ሲባል ብቻ ፈተናችንን “በግምት ስንት ነው” እና “ስማቸውን ጥራ” ዓይነት አታድርጉብን አቦ!. . . እናላችሁ ዘመናችንን በትዝብት አይን ስንገመግመው ጥሎ ማለፍ እንጂ ተባብሮ ማለፍ (ከፍ ማለት) የማይታሰብ የሆነበት ይመስላል።

እናም ዘመኑ የጥሎ ማለፍና የአቋራጭ ፈላጊዎች መሆኑን የምታሳይ የመጨረሻ ጨዋታ እንካችሁ። የአንድ ድርጅት ባለቤት የሂሳብ ባለሙያዎችን ለመቅጠር አስቦ፣ “ለመሆኑ ከመካከላችሁ ሁለት አይነት የገቢ ማሳወቂያ መዝገቦችን ማዘጋጀት የሚችል ሰው አለ?” ሲል ጠየቀ። ይሄኔ አንዱ ቀልጠፍ ብሎ፣ “እኔ ሶስት ዐይነት ማዘጋጀት እችላለሁ” ሲል መለሰ። ኃላፊው በመገረም “ሶስት አይነት ስትል ምን ማለትህ ነው?” ሲል ጠየቀ። “የመጀመሪያው ከድርጅቱ ስር ለማይጠፉ ባለአክስዮኖች ሲሆን፤ እውነተኛውን ትርፍ ያመለክታል። ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቱ አካባቢ ደርሶ ለማያውቅ ባአክሲዮን የሚዘጋጅ ይሆንና አነስተኛ ትርፍ የሚያሳይ ይሆናል። ሶስተኛው ደግሞ ለግብር ተቆጣጣሪው መ/ቤት የሚዘጋጅ መዝገብ ሲሆን በእርግጠኝነት ኪሳራን የሚያሳይ ተደርጎ ይዘጋጃል” ሲል መለሰ ይባላል። ጎበዝ አያችሁ አይደል ዘመኑ የቱን ያህል የሴራና የጥሎ ማለፍ ደረጃ እንደደረሰ?! ግብርና ታክስ መሰወር ሀገርን መጉዳት መሆኑን ያለማስተዋል? . . . ለማንኛውም አንድዬ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚያስብ ልበ-ሰፊ ወዳጅ አያሳጣን አቦ! ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
354 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1091 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us