ኑሮ ሲደመር ጥሮ

Wednesday, 15 February 2017 13:27

 

ራስን መቻል ነው፣

    ጥሮ ተጣጥሮ

በወዳጅ በዘመድ፣

   አይገፋም ኑሮ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . አለነው፤ እሰዬው ይሄንንስ ማን አየብን?. . . በዚህ ሽምጥ በሚጋልብ ኑሮ መካከል እውር አሞራን የሚያጎርስ አምላክ እኛንም “የዕለት እንጀራችንን ስጠን” ባልነው መሰረት ባይሰጠን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?. . . ለዛሬ ትዝብታችን የምንጨዋወተው እራስን ስለመቻል ነው።

ይህቺን ሃሳብ የምታጠናክርልኝ መልዕክት እንዲህ ተከትባ በፌስ ቡክ መንደር ላይ ተመልክቻለሁ። “አንዲት ወፍ ስላረፈችበት ዛፍ ቅርንጫፍ መሰበር በፍፁም አትጨነቅም። ምክንያቱም የምትተማመንበት ክንፍ አላትና” ይላል። ይህንን ሃሳብ ደግሞ በግጥም ስናዋዛው እንዲህ እንላለን፤

ሰው እንደው ሸክላ ነው

     ቢወድቅ የሚሰበር፣

በሰው እግር ተውና በራስ

     ክንፍ ብረር።

እውነት ነው በራሳችን መቆም ለብዙዎቻችን ፈተና ነው። ነገር ግን ፍፁም ልናልፈው የምንችለው ፈተና ስለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ራሳችንን የሌሎች ጥገኛ እስካደረግን ድረስ ከባርነት ለመውጣት ያለን ጉልበት በእጅጉ የመነመነ ይሆናል። ሰው በራሱ ከቆመ ከዛሬ አልፎ ለነገውም የሚተርፍ ጉልበት ይኖረዋል። ለዚያም ነው መሰለኝ ከቻይናዊያን መንደር የምትጠቀስ ጥቅስ ተደጋግማ የምትደመጠው፤ “አንድን ሰው ዓሳ ከሰጠኸው ዕለቱን ታኖረዋለህ። ዓሳ እንዴት እንደሚሰገር ካሳየኸው ግን ዘመኑን ታበረታዋለህ” ትላለች። እናላችሁ ኑሮን ጥሮ -ተጣጥሮ እንጂ ሰው ላይ ተንጠልጥሎ ማሳፍ ከባድ ነው።

እዚህች‘ጋ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን ለማጣፈጥ ያህል ከከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሳሌ” መፅሐፍ ውስጥ የምትከተለዋን ወግ እንካችሁ። አበበች በወስከምት ተይዛ የተቀመጠች አንዲት ወፍ ነበረቻት። ወፏም መጥታ ከአበበች እጅ ትመገብ ነበር። አበበችም ወፏን አሁንም አሁንም እያወጣች ትለቃት ነበር። እሷም በወስከምቱ ጫፍ ላይ ወጥታ ትቀመጥ ወይም በክፍሉ ዙሪያ ትበር ነበር። ወፏንም የምትመግባት የነበረችው አበበች ራሷ ነበረች እንጂ ማንም ከእርሷ በቀር ወፏን የሚመግብ አልነበረም።

አንድ ቀን አክስቲቱ የሚያማምሩ አዳዲስ የአሻንጉሊቶች ሳጥን ሰራችና ለአበበች ላከችላት። በአሻንጉሊቶቹም ስትጫወት ደስ አላትና ቀኑን ሁሉ ዋለች። በዚያን ቀን አበበች ወፏን አልመገበቻትም። በማግስቱም ደግሞ አበበችን ለማየት አንዲት ወዳጇ መጣችና የናፍቆታቸውን ሲጫወቱ ምስኪኒቱ ወፍ ምግብ ሳታገኝ ቀረች።

አበበችም ከወዳጇ ጋር ቀኑን በአሻንጉሊቶች ሳጥን ሲጫወቱ ዋሉ። በሶስተኛው ቀን ግን አበበች አሻንጉሊቶቹን ሰልችታቸው ኖሮ ከወፊቱ ጋር ልትጫወት ሄደች። አንዳች ፍሬም ልትሰጣት ወደወስከምቱ ቀረበች፤ ነገር ግን ያቺ ምስኪን ወፍ ሙታ በወስከምቱ ውስጥ ተጋድማ ተገኘች። ምክንያቱም ምግብ ስላጣች ነው። በስተመጨረሻም በጫካ ውስጥ ጥራ ግራ ምግቧን የምትበላ ወፍ የተቀኘችውን ደራሲው እንዲህ አስቀምጠውታል።

የጌቶች አዳራሽ ምን ያደርግልኛል፤

በጠባብን ጎጅዬ መኖር ይሻለኛል።

እናላችሁ ጎበዝ እንዲህ የሰው እጅ የምንጠብቅና፣ በሰው ትከሻ ላይ የምንጣበቅ ከሆነ ዋጋም አይኖረንም። ደግሞ በራሳችን ተፍጨርጭረን ከመስራት ይልቅ ሁሉንም ነገር ከሌላ ሰው የምንጠብቅ ከሆነ ውጤቱም ደስታውም ከኛ የራቀ ይሆናል። ይህን አስተውሎ ይመስላል ታላቁ እንግሊዛዊ ደራሲ ዊሊያም ሼክስፐር፣ “ሁልጊዜ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም ከማንም ሰው ምንም ስለማልጠብቅ፤ ጥበቃ ብዙ ጊዜ ጎጂ ነውና” ይለናል።

ጎበዝ ስንት ነገር ያለቅጥ ታቅዶልን፤ እኛም ያለቅጥ ተስፋ አድርገን ይኽው ሀዘናችንን ታቅፈን የለም እንዴ?. . . ይኽውና እንኳን የኮንደሚኒየም ነገር ከስንት ነገራችን ላይ ይቅር ብለን ቆጥበንና ቆጣጥበን ስንፍጨረጨር አይደለም እንዴ መንግስታችን “ወገቤን” ብሎ ኩም ያደረገን። (አሁንማ ኮንደሚኒየም ከመጠበቅ “ሪልስቴት” መግዛቱ ሳይሻለን አይቀርም፡፤ ቂ-ቂ-ቂ! ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኑን ማለት ይሄኔ ነው) እኛማ ስንት ነገር ጠብቀን ነበር። ገበያችን ይጨምራል ብለን ጠብቀን፣ ኑሯችን ይሻሻላል ብለን ጠብቀን፣ አቤቱታችን ሁሉ መልስ ያገኛል ብለን ጠብቀን፤ ሙሰኞች ሁሉ ተጠራርገው ይታሰራሉ ብለን ጠብቀን፤ የመልካም አስተዳደር ችግር ሁሉ በጥልቅ ተሃድሶ ይቀለበሳል ብለን ጠበቅን. . . በቃ ምን አለፋችሁ ብዙ ነገር ጠብቀን ነበር። ግን. . . ይቅር!

በዚህ አጋጣሚ ግን አንድ መልዕክት አለን። አንዳንድ ዘመድ አለን የሚሉ፤ ገንዘብ አለን የሚሉ፤ ስልጣን አለን የሚሉ፤ ጉልበት አለን የሚሉ . . . ወዘተ ሁሉ ድንገት የሚከሰተው ነገር አይታወቅምና ለክፉም ለደጉም ቢሆን “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የምወትለዋን የአበው ጥቅስ ልብ ያድርጉልን አቦ!. . . እናም ራስን መቻል ነው እንጂ እንደፓራሳይት ተለጥፎና ተንጠልጥሎ አይዘለቅም። የዘመናችን ባለቅኔ በመግቢያችን ላይ የተቀኛትን ግጥም እንደመዝጊያም እነሆ፡-

ራስን መቻል ነው

     ጥሮ ተጣጥሮ፣

በወዳጅ በዘመድ

     አይገፋም ኑሮ።

                  ቸር እንሰንብት!!!  

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
510 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 891 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us