አይቶ እንዳላየ. . .

Wednesday, 22 February 2017 11:50

      ዓይኔ መቼ በራ መቼ ዳነልኝ፣

የሰው ፊት ማየቴ በጣም ደነቀኝ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እህሳ ፆመ ልጓሙን ጠበቅ አድርገን “አብይ-ፆሙን” ጀመርነውም አይደል?. . . ጎሽ እኔ የምለው ግን የአንዳንዶቻችን አያያዝ ፆሙ የሚፈታም አልመስልህ አለኝ እኮ ጎበዝ ምንድነው? ሁሉም ሰው የሃኪም ትዕዛዝ ያለበት ይመስል ለዘመናት በሽሮ ሲያሟሿት የከረማትን ድስት እንዲህ በመያዣ ስም ማቅለጡ ትንሽ “ፌርነት” የጎደለው ይመስላል። ደግሞ አንዳንዶች የሚደንቀው ፆሙን በስጋም በግብረ-ስጋም ለመያዝ ያደረጉት ጥረት ነው። (ለማንኛውም ስጋን እንደስጋት የምትመለከቱት “ቪጂቴሪያን” ትዝብታችሁ ደርሶናልና አፉ ቢሉን። አብይ ፆሙን አጥብቀን እንዳሰርንም ደግሞ አላልተን ለመፍታት አንድዬ የዛው ሰው ይበለን - አቦ!)

ለዛሬ ትዝብት አዘል ጭውውታችንን የምናደምቀው በፍቅር ታሪክ ይሆናል. . . ታሪኳን ስታነቡ በመግቢያችን ያስቀመጥናትን የባለቅኔውን ሃሳብ እየመነዘራችሁ ይሁን!!. . .ሰውዬው በአገሩ አለች የተባለላትን ቆንጆ ሴት በእጁ ያስገባል። ገና ተጋብተው መኖር እንደጀመሩ የቆዳ በሽታ ይከሰትባታል። እጅግ ውብ የነበረችው ሴት ድንገት ፊቷ እየቆሰለ መልኳም እየተቀየረ መጣ። እናም መልኳ ሲቀየር ባሏ እንዳይጠላት መጨነቅ ጀመረች። ችግሯ ተባብሶ፤ የከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ግን ሰውዬው በስራ ምክንያት ከከተማ ወጣ። ከሄደበትም ሲመለስ የመኪና አደጋ ያጋመውና አይነ ስውር ይሆናል። ሁለቱም አዲስ ተጋቢዎች እንደበፊቱ ተቻችለውና ተዋደው መኖራቸውን ቀጠሉ። ምንም እንኳን የሴትየዋ የፊት ቆዳ ከጊዜ ወደጊዜ አደጋው እየተባባሰ ቢመጣም፤ ሰውዬው አያያትምና የውበቷ መርገፍ ለትዳራቸው መፍረስ ስጋት ሳይሆን ቆየ። እናም ሴቲቱ በልቧ “ፈጣሪ ሳይደግስ አይጣላም። ይሄኔ ባለቤቴ የፊቴን መበላሸት ቢያየው ኖሮ፤ ከቀን ወደቀን ፀባዩ ተቀይሮ፤ ትዳራችን በፍቺ ሳይደመደም አይቀርም ነበር።  ነገር ግን ባለቤቴ ድንገት በደረሰበት አደጋ ማየት ባለመቻሉ ይኸውና ትዳራችን አሁንም በፍቅር አለ” ስትል አሰበች።

ሞት አይቀርምና ከዓመታት የፍቅር ኑሮ በኋላ ሴትየው አረፈች። በዚህም ሰውዬው በሃዘን በጣም ተጎዳ። የሁለቱ ፍቅር ገኖ በሚታወቅበት በዚያ ከተማ መቆየት ያልፈለገው ይህ ሰው፤ ጓዙን ጠቅልሎ ወደሌላ ሀገር ለመሄድ ተነሳ። ነገር ግን የከተማውን ሰው ሁሉ ያስገረመ አንዳች ነገር ተከሰተ። አጋጥሞት በነበረ አደጋ ለረጅም ጊዜ አይነ ስውር ሆኖ የቆየውና ያለባለቤቱ እርዳታ ከቦታ- ቦታ የማይንቀሳቀሰው ሰው በነፃነት በከተማው ጎዳና ላይ ሲራመድ ታየ። ይህንን ተዓምር ያስተዋለ አንድ የከተማው ነዋሪ ስሙን ጠርቶ፣ “ለመሆኑ አይነ ስውር ሆነህ ያለባለቤትህ መሪነት የማትንቀሳቀስ የነበርከው ሰው እንዴት ብለህ ነው ያለመሪ እንዲህ በቀላሉ የምትሄደው?” ሲል ጠየቀው። ሰውዬውም ሲመልስ፤ “በእውነቱ በደረሰብኝ አደጋ የዓይን ብርሃኔን እንዳጣሁ ያስመሰልኩት ውሸቴን ነው። ምክንያቱም ባለቤቴ የቆዳ ህመሙ የፊቷን ገፅታ ክፉኛ ሲቀይረው ከሚሰማት ህመም በላይ በውበቴ የተማረከው ባለቤቴ የመልኬን መበላሸት አይቶ ይጠላኝ ይሆናል በሚል የሚሰማት ስቃይ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል አስቤ ያደረኩት ነገር ነው። ትዳራችንን በቃል ኪዳን አስረን ስንጀምረው ጀምሮ እርሷ ጥሩና ቆንጆ ሚስት ነበረች። እናም እስከዕለተ ሞቷ የሚገባትን ደስታ ልሰጣት ሞክሬያለሁ” አለው ይባላል።

አንዳንዴ ለሌሎች ደስታ ስንል ብቻ ነገሮችን አይተን እንዳላየን፤ ሰምተን እንዳልሰማን ሆነን ማለፉ ደግ ሳይሆን አይቀርም። የሰውን ስህተት እንፈልግ ብለን ከተነሳን፤ ዘጠና ዘጠኝ ከሚደርሰው ትክክለኝነታቸው ይልቅ አንዷ ስህተት ላይ ልናተኩር እንችላለን። ለራሳችንም ሰላም፤ ለሌሎችም ደስታ ሲባል አንዳንዴም ቢሆን ብንተላለፍ ምን አለበት ጎበዝ!? . . . የኛ አለመስማት ደስታ የሚፈጥርላቸው ከሆነ፤ የኛ አለማየት ደስታ የሚፈጥርላቸው ከሆነ፤ የኛ አለማወቅ ደስታን የሚፈጥርላቸው ከሆነ፤ የኛ ዝም ማለት ደስታን የሚሰጣቸው ከሆነ ምን አለበት አንዳንዴ እንኳን ሰምተን እንዳልሰማን፣ አይተን እንዳላየን መምሰልን ለወዳጆቻችን ብንቸራቸው።

እናላችሁ ወቅቱ የአብይ ፆም በመሆኑ ለወዳጆቻችን አልያም ለሌሎች ደስታና ሰላም ስንልም ቢሆን አይቶ እንዳላየ ወይም ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን እስቲ ደስታን እንፍጠር።. . . ነገር ግን ለሌሎች ደስታ ስንል አይነት እንዳላየ፤ ሰምተን እንዳልሰማ መሆናችንን እንደጅልነት ቆጥረው በክፉ ከሚያተርፉ ሰዎች ደግሞ ራሳችንን መጠበቅ እንዳለብን መዘንጋት የለበትም።. . . በተረፈ ግን እንዲህ ለፍቅር ሲባል የተከፈለን መስዋትነት በምድር አልበቃው ሲል ለሰማይ ያበደራልና እንደመምህርና ገጣሚው ደበበ ሰይፉ “ተይው እንተወው.  . .” መባባል ሳይሻል አይቀርም። . . . ጎበዝ ግድ የለም አንዳችን ለሌላችን ሰላም ሲባል “ተውት እንተወው” መባባልን እንወቅበት.  . .

ተይው እንተወው

ተይው እንተወው.  . .

የዘመን ቃፊሩን ማለፍ አልቻልንና

ይህ ዓለም ጥበቱ አለመጠነንና፤

ተይው እንተወው፣. . .

ውጥኑ ግብ ይሁን

ጅማሬው ፍፃሜ

ቅፅበቷ ሙሉ ዕድሜሽ

ወቅቷ ዘላለሜ።

     (ከደበበ ሰይፉ፤ “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” (የብርሃን ፍቅር ቅፅ )

የግጥም መድብል የተወሰደ)

መልካም ሳምንት፤ እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!!!  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
424 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 914 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us