ዓድዋን የኋሊት

Wednesday, 01 March 2017 12:39

 

ዋ!. . . ዓድዋ

ዓድዋ የትላንትናዋ

ይህው ባንቺ ህልውና

በትዝታሽ ብፅዕና

በመስዋት ክንድሽ ዝና

በነፃነት ቅርስሽ ዜና

አበው ተነሱ እንደገና።

. . . ዋ!. . . ያቺ ዓድዋ

ዓድዋ ሩቅዋ

የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

ዓድዋ.  . .

     (ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “እሳት ወይ አበባ”

     የግጥም መፅሐፍ ውስጥ “ዋ!. . . ያቺ ዓድዋ”

     የተሰኘው ግጥም ተቀንጭቦ የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ! . . . እንኳን ለታላቁ የዓድዋ የድል በዓል አደረሰን ብንባባል ቅር የሚለው ያለ አይመስለኝም።. . . እነሆ ዓድዋን የኋሊት. . . የዓድዋ መታሰቢያ በዓልን ስገመግመው ምን ይደንቀኛል መሰላችሁ። እንደው አሁን አሁን ትንሽ “በፌስ ቡክ” መንደር መነቃቃት ባይፈጠር ኖሮ ትልቁ ድላችን “ከውሃ ቀን” እኩል፤ “ከጡት ከማጥባት ቀን” እኩል፤ መከበር ደረጃ ደርሶ እንደነበር ሳስበው እርር ትክን ያደርገኛል። ይልቅዬ ምን ታዘብክ ካላችሁኝ እንቻክሁማ፤ ህዝቤ (በተለይ አብዛኛው ወጣቱ) ዓድዋን አስቦ ከመዋል ይልቅ፤ ጃምቦና ቢራ ከቦ መዋልን የመረጠ ይመስለኛል። ኧረ ጎበዝ ደም ያፈሰሰበትን ቀን በደንብ ብናከብረው ይሻላል።

እናላችሁ በድሉም በበደሉም ላይ ስም እየለጠፉ ታላቁን የዓድዋ ድል በሽርፍራፊ ወሬዎች ማኮስመኑ አያዋጣም። .  . . አንዳንዱማ ከታሪክ እጥረት ይሁን ከአጉል ድፍረት በመነጨ አይታወቅም “የሰሚ- ሰሚ” ያገኘውን በርበሬ የመሰለ ወሬ በፌስ ቡክ በኩል ወደአይናችን ሲወረወር ዝም ማለት አንችልም አቦ!. . . እውነቱን ለመነጋር ዓድዋ ማለት ከፀሎትና ከዱአ በተጨማሪ፤ በአፈርና በአሸዋ ላይ ተዋድቀን ያገኘነው ድል ነው። እናም ይህን ታላቅ መስዋትነት የተከፈለበትን ድል ክብር እንጂ በግርግር ባናሳልፈው መልካም ነው።  

ይልቅዬ ዓድዋን የኋሊት ብለን ስንነሳ የዓድዋን ድል ስለማንኳሰስ የመጀመሪያው ተጠቃሽ ሰው ጄኔራል ባራቲዮሪ ነው። . . . እስቲ ትንሽ ታሪክ፣ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” ከተሰኘው የተክለ ፃዲቅ መኩሪያ መፅሀፍ እንካችሁ። .  . . ከዓድዋ የጦር ግንባር የሸሸው ዤኔራል ባራቲዮሪ የክሪስፒ የግል ወዳጅና የፖለቲካ ጓደኛው፤ በጠቅላይ ጦር አዛዥነቱ ዓድዋ ላይ ድል እንደተመታ በሶስተኛው ቀን በእርሱና ለወገኖቹ መራራ የሆነውን የመሸነፍ ወሬ ለኢጣሊያ መንግስት በቴሌግራም ማስታወቅ ግድ ሆነበት። ሲያስታውቅም ራሱ የነበረበትን የጦር ግንባር ሁኔታ በምን አቅጣጫ አኳኋን ሌሎቹ ዤኔራች ጦርነቱን እንደጀመሩ ገልፆአል። ነገር ግን ራሱ ከመከበብና ከመማረክ ለመዳን ሲል ስለሸሸና የሶስቱን ዤኔራሎች የዳቦ ሚዳን፣ የአሪሞንዲንና የአልቤርቶኒን ፍፃሜ ስለማያውቅ መግለጫው ከዚህ እንደሚከተለው ደበስበስ ያለ ነበር።

“ቅዳሜ ዓድዋ ያለውን የሸዋ ጦር እንደወጉ ጦሩን ከሶስት ላይ ከፍዬ አንዱን ተጠባባቂ አድርጌ አንዲዋጉ አዘዝሁ. . . የግራው ጦር ወደፊት ቀድሞ መቸገሩን ስለሰማሁ የዳቦርሚዳ ጦር እንደረዳ ትዕዛዝ አስተላለፍሁ. . . በዓድዋ በኩል ጦርነቱ ተማሙቆ ነበር። በሌላውም በኩል በድፍረት ወደፊት እየተዥጎደጎዱ የሚዋጉት የጠላት ወታደሮች ለማገድ ስላልተቻለ ሁሉም ሊበላሽ ቻለ. . . ከዚያ ወደተነሳንበት ወደሳውሪያና ወደ ሰሜን ሁሉም ፊቱን መልሶ ሰፊ መተላለፊያ እየፈለገ ሄደ። . . . ከኔም ጋር ኤሌናና ቫሌንዛና ወደ አዲቀይህ መጥተዋል። የዳቦርሚዳ ወሬ የለኝም። የአርሞንዲንና የአልቤርቶኒን ሁኔታም አላወቅም። ወሬውም የተለየ ነው. . . ስለመፍረሳችን አደገኛ ሁኔታም የሚቀርበው ሃሳብ የለኝም። የተዋጉትን የነጭ ወታደሮች እንደገና አዘጋጅቶ ለማዋጋት ግን አይቻልም።

የጥቁሩም ወታደር የበለጠ ተዘበራርቋል፣ ሞራላቸው እንደነጮቹ ተበጥብጧል። በዚህ ፈንታ የጠላቶቻችንና የሽፍቶቹ ሞራል ከፍ ብሏል። የአዲግራት ምሽግ በማይሸነፉ ሽፍቶች ስለተከበበ ምሽጉን ለቀው እንዲወጡ ማዘዝ የሚቻል አይመስለኝም። ዛሬ ሌሊቱን ወደ ሰገነይቲና ወደ አስመራ እሄዳለሁ። በዚህ ጊዜ ነገ ጧት አስመራ የሚገባው ላምቤርቲ የቅኙን አገር አስተዳደር ይዞ ከመንግስቱ ጋር ይፃፃፋል።” ባራቲዮሪ

አያችሁልኝ አይደል ጄኔራል ባራቲዮሪ እንኳን ድላችንን ለማንኳሰስና ጥላሸት ለመቀባት ያሳየውን ትጋት.  . . ግድ የለም ጎበዝ! ቀደምት አባቶቻችን ህይወት የገበሩበትን የዛሬ ነፃነት ዋጋ ብንሰጠው ይበጀናል። (ኧረ ጎበዝ እኛም እኮ “ስፖንሰር” የሚያደርገን አጥተን እንጂ ልክ እንደ” ሮዛ ፓርክስ” አለምን የሚያስደምሙ የመቶ ባለታሪኮችን ገድል መተረክ እንችል ነበር)

ለማንኛውም ባለቅኔው እንዳለው ዓድዋ ማለት “የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥጓዋ፣ ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ” ናትና ከዘመናችን በደል ይልቅ ለአንድም ቀን ቢሆን ከኛ አልፎ ለጥቁሮችም ማነቃቂያ የሆነውን የድል ታሪካችንን ከፍ ብናደርገው ምን ይለናል?. . . ምንም! በመጨረሻም ምን ለማለት ፈልጌ ነው መሰላችሁ?. . . ታላቁን ድል ከማንኳሰስ ይልቅ ታሪክን የኋሊት ብሎ ታሪክን መዳሰስ ሳይሻለን አይቀርም። አለበለዚያ ግን ከታሪክ ይልቅ ታሪኩ የሚባል ሰው ብቻ ጠይቀን፤ ከድንበር ይልቅ ድንበሩ የሚባል ሰውን ብቻ ጠብቀን፣ እያወቅን፤ ከመብራት ይልቅ መብራቱ የሚባልን ሰው ለይተን፤ ከወንዝ ይልቅ ሺወንዙ የሚባል ሰው ተዋውቀን ብቻ ከቀጠልን የትም የምንደርስ አይመስለኝም። በተረፈ እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
330 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 893 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us