“አልሸሹም፤ ዞር አሉ”

Wednesday, 08 March 2017 12:02

 

መስታወት አልገዛ እጄ ባዶ ነው፣

በሰው መስታወት ነው ፌቴን የማየው።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንዴት ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . እኛ እንደሆነ “ሲሞላ ጨዋታው ሌላ፤ ሲጎድል አንቀን ልንገድል” የምትለዋን ዜማ እየደጋገምን አለነው። እኔ የምለው ይሄ “ጥልቅ-ተሃድሶ” ምናምን የተባለው ነገር በራሱ በስራችን ላይ መዘዝ ይዞብን መጣም አይደል?. . . እንዲህ ናትና የምሬን እኮ ነው የኛን ስራ ጎልተው “በጥልቅ ተሃድሶ” ሰበብ ስብሰባ ሲያበዙ፤ አይደለም የኛን ጥያቄ ለመመለስ ያቀዱትንም ቢሆን በወጉ ለማድረስ እንዳይቸግራቸው ስጋት አለን።

ኧረ ጎበዝ እንዳንተዛዘብ እየተስተዋለ።. . . ልጁ ልጅቷን ገና በመጀመሪያ የፍቅር ቀጠሮ (ፈረንጆቹ “Blind date” እንደሚሉት መሆኑ ነው) በነገር ያዝጋታል። የሚገባትንም፣ የማይገባትንም፤ የሚያገባትንም የማያገባትንም ነገር እንዲሁ ሲቀባጥር ሰምተው ስታበቃ “እኔ የምለው ይሄን ሁሉ ነገር ለመነጋገር የሚያበቃ ትውውቅ አለን እንዴ?” ከማለቷ ልጁ ሆዬ ምን ቢመልስላት ጥሩ ነው? “የኔ እህት ጠልቀን ከመሄዳችን በፊት ሂሴን ያወረድኩልሽ በጥልቅ ለመታደስ ካለኝ ጥልቅ ፍላጎት ተነስቼ ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ!

ግድ የለም ጎበዝ የሚታዘበን ሰው ስላለ እየተስተዋለ ቢሆን ደግ ነው። . . . ከላይ አድርጉት ተብሎ ስለወረደ ብቻ ስራን ቁጭ አድርጎ በጥልቅ ተሃድሶ ሰበብ ሰውን ማጉላላት “ፌር” አይመስለኝም። . . . እዚህች'ጋ የሙላህ ነስረዲንን ጨዋታ እናምጣ። ነስረዲን አዲስ ከተቀጠረበት መስሪያ ቤት ለሳምንት ያህል ጠፍቶ ይሰነብታል። ልክ ሲመለስ አለቃው ያገኘውና ሳምንቱን ሙሉ የት ጠፍቶ እንደቆየ ይጠይቀዋል። “ጌታዬ በድርጅታችን ትዕዛዝ መሰረት ነው የጠፋሁት” አለቃው ተገርሞ “የምን ትዕዛዝ ነው ከኔ ፍቃድ ውጪ እንድትጠፋ ያደረገህ?” ሲል በጥያቄ ያፋጥጠዋል። ሙላህ ነስረዲን ሲመልስም “የለም ጌታዬ ለአንድ ሳምንት ፈቃድ ፈልጌ ወደእርስዎ ቢሮ በማምራት ላይ ሳለሁ “አድርገው!” የሚለውን የድርጅታችንን መሪ ቃል (መፈክር) አስታወስኩና ሳላስፈቅድህ አደረኩት” ብሎላችሁ እርፍ!

እንግዲህ ጨዋታው ሁሉ በመሰለኝና በደሳለኝ የተሞላ ስለሆነ ለጥፋታችን ምክንያት እየፈለግን መሄድ ነው። . . . ግን ግን ጎበዝ የሚታዘበን ሰው ስላለ እየተስተዋለ ቢሆን ምን ይለናል?. . . የጋራ መኖሪያ ቤት ጉዳይ እንዳስተዛዘበን፣ የስኳር ፕሮጀክት ጉዳይ እንዳስተዛዘበን፣ የኃይል አቅርቦቱ ጉዳይ እንዳስተዛዘበን፣ የመልካም አስተዳደሩ ጉዳይ እንዳስተዛዘበን ይኽው ደግሞ በጥልቀት መታደስም ሰበብ እየሆነ የሚያስተዛዝበን ከሆነ ነገራችን ሁሉ “አልሸሹም ዞር አሉ” አይነት ሆነ ማለት ነው።

ይመጣል የተባለው ለውጥ ቀርቶ ነውጥ ካስከተለማ “አልሸሹም ዞር አሉ” ይታወስ ዘንድ ግድ ይላል። መታደስ ጥሩ ነው። ነገር ግን መታደሳችን እየሰራን እንጂ ሥራ እየወዘፍን ከሆነ ምን ዋጋ አለው? ጎበዝ አራዶች “ኳስ በመሬት” የሚሉት እኮ ይሄን ጊዜ ነው። ሁሉ ነገር በሃሳብና በሰማይ ሲሆን፤ የሚጨበጥ ነገር ሲጠፋ ያኔ “ኳስ በመሬት” እንላለን።

ይልቅዬ ስለስራችን መሞት እንጂ ስለስልጣንና ስለክብራችን ብቻ ስንጨነቅ የምንከፍለውን ዋጋ የምታሳይ አንዲት ወግ ከመሰነባበታችን በፊት እንካችሁ፤. . . ሰውዬው በአለም የታወቀ ቀራፄ ነው። በበርካቶች ዘንድ በሚሰራቸው ቅርፃቅርፆችና ፍፁም ህያው በሚመስሉ ሃውልቶቹ ምክንያት ተወዳጅም ነው። ታዲያ አንድ ቀን በህልሙ መልዓከ ሞት ይመጣና፣ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ እንደሚወስደው ነግሮት፤ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቀው ያስጠነቅቀዋል። በህልሙ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ፍርሃት የገባው ይህ ታላቅ ቀራፂ፤ ፍፁም ራሱን የሚመስሉ ዘጠኝ የሃውልት ቅርፆችን በቤቱ ያቆማል።

መልዓከ ሞት ወደሰፊ ቤቱ በገባ ጊዜ ፍፁም ተመሳሳይነት ያላቸውን የቀራፂውን አካላት የሚመስሉ አስር ሃውልቶች ተመለከተ። መለየት ስላቃተውም በመደነቅ እያያቸው ቆየ። ቆይቶ ቆይቶ የትኛው እውነት፤ የትኛው ደግሞ ሀውልት መሆኑን ለማወቅ ሲቸግረው ወደላከው የሞት አለቃ በመሄድ ያጋጠመውን ሁሉ በዝርዝር ተናገረ። የሞት አለቃውም በሁኔታው ተቆጥቶ ራሱ ቀራፂውን ይዞት ለመምጣት ወደቀራፂው ቤት ሄደ። የመልዓከ ሞትን ሁኔታ በጥንቃቄ ይከታተል የነበረው ጠቢቡ ቀራፂም እንደቀድሞው ሁሉ ምንም አይነት የህያው ስሜትን በማይሰጥ መልኩ፤ ከዘጠኙ ተመሳሳይ ሀውልቶች መካከል አስረኛ ሆኖ ቆመ። ቀራፂውን ከቅርጾቹ፤ ሀውልቶቹን ከባለሀውልቱ መለየት ያቃተው የሞት አለቃም ጥቂት ሲያስብ ቆይቶ፤ አንዳች መላ መጣለት። “አንተ ታላቅ ቀራፂ ሆይ! ሃውልቶችህ ሁሉ ውብ ናቸው፤ ነገር ግን አንደኛው ችግር አለበት” ከማለቱ በስራው ላይ ስለታየው ጉድለት ሰምቶ ዝም ማለት ያልቻለው ቀራፂ ድምፁን ከፍ አድርጎ “የትኛው ነው ስህተት ያለበት ሃውልት?” ሲል ከተመሳሰለበት ወጣ። እናም የሞት አለቃ አንጠልጥሎ ወሰደው።

ሰው እንዲህ በስራው ላይ ታማኝና ኩሩ ሆኖ ለስራው ሲል ይሞታል። እኛም እንደው የምንሞትለት ስራ ባይሆን እንኳን የምንኖርለት ስራ ይኖረን ዘንድ የተሰጠችንን ኃላፊነት በአግባቡ ብንወጣ ምን ይለናል?. . . ስራን ጥሎ፤ ስብሰባን አንጠልጥሎ ብቻ ለውጥ ያመጣ አስተዳደር የለምና። ጎበዝ ቀን ቀን ስሩ ማታ ላይ ባይሆን ለጥልቅ ተሃድሶ ሲባል ተሰብሰቡ!. . . . አለበለዚያ ግን ስራን ጥሎ ሁሌ ስብሰባ ከሆነ ነገራችሁ በመጨረሻም ውጤቱ “አልሸሹም ዞር አሉ” አይነት እንዳይሆን ስጋት አለን። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
338 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1012 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us