እንደመጨረሻ ቀን መኖር

Wednesday, 15 March 2017 12:32

 

መጨረሻ ያለው በቅርብ የሚያግድ

ውስጥ ለውስጥ የለም የሚያስኬድ መንገድ

*      *      *

ያዳም ልጆች ሁሉ ምንድን ያደርጋሉ

አንድ ባንድ ለመሄድ ይሽቀዳደማሉ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . ዛሬ በህይወት ለመኖር የተሰጠን የመጨረሻ ቀን እንደሆነ ብናስብ የሚፈጠረውን ነገር አስባችሁታል?. . . ብዙ ዕቅዶች ቢኖሩንም፤ ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩንም፤ ብዙ ስራዎች ቢቀሩንም እስቲ እንደው ዛሬ የመጨረሻ ቀን እንደሆነ እናስበው። ያኔ ምናልባት ለውጥ ለሚያስፈልጋት ዓለማችን “ወርቃማውን ሕግ” እንጀምር ይሆናል።

ዛሬን እንደመጨረሻ ቀን መኖር ስንጀምር ምናልባት አንዳንድ ወዳጆቻችን በጠዋት ተነስተው ወደቤተክርስትያን ወይም ወደቤተ መስጂድ ማቅናታቸው አይቀርም። (ምንም እንኳን ቃሉ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” ቢልም ዛሬ የጭንቅ ቀን ነውና ወደፈጣሪ ፊቱን የሚያዞር አይጠፋም)

የተቀየሙትን ይቅርታ የሚጠይቅ፣ ያስቀየሙትን ደግሞ ይቅር የሚል ሰው የሚበዛው ዛሬ የመጨረሻ ቀናችን ሲሆን ነው። አንዳንድ ተንኮለኛም ደግሞ አይጠፋም። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል መንፈስ ተነሳስቶ፤ የመጨረሻዋን ቀን ሴራ መጠንሰሻ ወይም ቂም በቀል መዝሪያ አድርጎት ሊያልፍ ይጣደፍ ይሆናል።

አንጋፋው ደራሲ ከበደ ሚካኤል እንዳሉት፤

ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም።   

የምንል ሰዎች መብዛታችንም አይቀርም። . . . በዚህች አጭር የመኖሪያ ዕድሜያችን በጎ በጎውን ሰርቶ ለማለፍ ዘመን እንደመጨረሻ ቀን እየቆጠሩ መኖር ደግ ይመስላል። ዛሬ የመጨረሻ ቀናችን እንደሆነ ብናውቅ ኖሮ አይደለም ሮሮ ስራ አናሳድርም ነበር። እውነቱን ለመናገር ከዛሬ አሳልፈን የማናውቀው ነገ ውስጥ ስንቶቻችን “ስንት ነገር” አስቀምጠናል። እርግጥ ነው የሰው ልጅ ከትላንት ትዝታው ሲከተለው ለነገረው ደግሞ ተስፋው ይቆየዋል። ነገር ግን ነገን በሰላምና በመልካም ሁኔታ ለመኖር ዛሬ የምንሰራው ስራ ወሳኝነት እንዳለው ማንም አይጠረጥርም። ሰው የዘራውን ያጭዳል እንዲል መፅሐፉ መሆኑ ነው።

ሰውዬው ለብዙ ዓመታት በአናጢነት ሙያ ተሰማርተው አገልግለዋል። አሁን ላይ ብዙ ከመስራታቸው ብዛት ደክመዋልና ድርጅታቸው በጡረታ እንዲያሰናብታቸው ፈልጉ። ይህንንም ሀሳባቸውን ለቀጣሪያቸው ይነግሩታል። በርካታ ዓመታትን በድርጅቱ ውስጥ በመስራታቸውና በጡረታ የመሰናበቻ ጊዜያቸው በመድረሱ ቀጣሪያቸው በእጅጉ ያዝናል። ነገር ግን አንድ የመጨረሻ ውለታ እንዲውሉለት ይጠይቃል። “ምናልባትም አሁን በድርጅታችን ውስጥ ሆነው የሚሰሩት ቤት የመጨረሻ ሊሆን ይችላል” ሲል፤ ስራቸውን እንዲጀምሩ ሁሉን ነገር አሟልቶ አቀረበላቸው። የሚገነቡት ቤት ለእርሱ መሆኑን አስታውቆ ምናልባትም ከስራ ከወጡ በኋላ በዚህ ቤት ውስጥ ሲኖር የእርሳቸውን ስራ እያደነቀ እንደሚያመሰግናቸው ነገራቸው። ያም ሆኖ ሰውዬው ልባቸው ስራ ከመስራት ይልቅ እረፍት ወስደው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስለሚያሳልፉት ጊዜ ብቻ በማሰብ ስለተጠመዱ ሌሎች ባለሙያዎችን አስተባብረው የሰሩት ቤት እንደነገሩ ነበር። ከዲዛይኑ ጀምሮ የተጣለው መሰረትም ሆነ የተጠቀሙባቸው የግንባታ ዕቃዎች ቀላልና ረጅም ዕድሜ የሌላቸው ወይም አይረቤ የሚባሉ ዓይነት ነበሩ።

በጥድፊያና እንደነገሩ የገነቡትን ቤት እንዳጠናቀቁ ቀጣሪያቸውን ጠርተው “እነሆ ቤትህ” አሉት። የቤቱን መጠናቀቅ ገና ከውጭ ሆኖ የተመለከተው ቀጣሪም በፍጥነት ያዘጋጀውን አንድ ወረቀት ወጣ አድርጎ በመፈረም ለሰውዬው ሰጣቸው። ወረቀቱ እንዲህ ይላል፤ “ይህ እርስዎ ለበርካታ ዓመታት በድርጅታችን ውስጥ በማበርከትዎ የተሰጠኦ ስጦታ ነው”. . . በስጦታው እጅግ የደነገጡት ዕድሜ ጠገቡ አናፂ በቁጭት ስሜት ሆነው “ምናለበት ቀደም ብዬ ለኔ መሆኑን ባውቅ የተሻለ አድርጌ በተመረጡ ጥሬ ዕቃዎች እገነባው አልነበረም” ሲሉ በሃሳብ ተብሰከሰኩ።

ይሄ ነው ታዲያ የታላቁን ደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ማፈንዳት፤

ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖም

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም

በዚህ ታሪክ ውስጥ ምን እንደታየኝ ታውቃላችሁ?  የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ መሠረት የሆነው “ወርቃማው ሕግ” እንዲህ ይላል፣ “በአንተ ላይ ሊፈፀም የማትፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አትፈፅም” ይላል።. . . ለኛ ጥሩ ቤት የምንፈልግ ከሆነ ምናልባት ለሌሎችም ጥሩ ቤት ብንሰራ (ይህቺ አሽሙር የአዲስ አበባ ቤቶች በተለይም የኮንዶሚንየም ግንባታ ላይ የሚሳተፉት ሁሉ እንደሚመለከት ልብ ይባልልኝ) ለኛ ጥሩ ስራ፣ ለኛ ጥሩ ደሞዝ፣ ለኛ ጥሩ መኪና፣  ለኛ ጥሩ ወንበር የምንፈልግ ከሆነ ምናለ ለሌሎችም እንዲደርስ ከልባችን ብንሰራ?. . . ጎበዝ ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው።

እናላችሁ ዛሬን ልክ እንደመጨረሻ ቀን ስንኖር፤ ለሌሎች መልካምን በማሰብና መልካምን በመስራት ቢሆን ዓለማችን እንዴት የተሻለች ትሆን ነበር! . . . ማን ያውቃል ምላሹን ከምድር ብናጣው በሰማይ እናገኘው ይሆናልና ዛሬን እንደመጨረሻ የበጎነት ቀን እየቆጠርን ብንኖር ይበጀናል። ደግሞም ዛሬ የመጨረሻ ቀናችን ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለን። ሕይወታችን በማንኛውም ደቂቃ ተሰባሪ ሸክላ ናትና፣ ሕይወታችን በፈጣሪያችን እጅ ነውና አዲሱን ቀን ሁሌም ቢሆን እንደመጨረሻ ቀን እያዩ በጎነትን ማሳረፍ ይገባል። በመጨረሻም በሰሞነኛው የቆሻሻ መደርመስ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች “ነፍስ ይማር!” ለቀረነው ደግሞ ልብ እና መፅናናትን ይስጠን አቦ! ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
413 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1054 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us