“የፈሲታ ተቆጢታ. . .”

Wednesday, 22 March 2017 12:27

 

አንተም አራዳ - እኔም አራዳ

ምን ያጣላናል በሰው በረንዳ

                (እንዳለ ነቄ ሰው)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኔ የምለው በሁሉም ነገር ላይ እኛ ብቻ አራዳ ነን የሚሉ አልበዙባችሁም?. . . የምሬን እኮ ነው። ከምድር እስከጠፈር፣ ከሰፈር እስከ አህጉር ባሉ ነገሮች ሁሉ ራሳቸውን አዋቂና ጠላቂ ለማስመሰል የሚጥሩ ሰዎች ያሳዝኑኛል። ይልቅዬ ስንነቃቃ አለ አይደል፡-

አንተም አራዳ እኔም አራዳ

ምን ያጣላናል በሰው በረንዳ

ተባብለን “ላሽ” ብንባባል ደግ አይመስላችሁም። (ነገሩማ አንዳንድ ነገሮች “ላሽ” (አይቶ እንዳላየ) ለመባባልም የሚቸገሩ አይነቶች ከሆኑ ሰነባብተዋል) የአራዶች ነገር ከተነሳ ላይቀር “እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል” አይነት የአይጦችን ተረት የምታስታውሰኝን የጋብሮቮች ቀልድ እነሆ፡. . . ጤንነት ያልተሰማቸው ጋብሮቫዊቷ ወይዘሮ ቀድሞ የሚያውቋቸውን ዶክተር አውራ መንገድ ላይ ያገኟቸውና፣ “ዶክተርዬ ጤንነት አይሰማኝም። እህል አይበላልኝም፣ ያዞረኛል፣ እባክዎን ይህን ህመም የሚያስታግስልኝ መድሃኒት ይዘዙልኝ” ሲሉ ይለምኗቸዋል። ዶክተሩም ሴትየዋ ወጪ ላለማውጣት የዘየዱት መላ እንደሆነ ስለገባቸው “እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል” በሚል መንፈስ፣ “እሜትዬ ልረዳዎ ዝግጁ ነኝ። ግን ጥቂት ምርመራ ስለሚያስፈልግ ልብስዎን ማውለቅ ይኖርብዎታል” አሏቸው፤ አደባባይ ላይ ማን ልብሱን ያወልቃል? ዶክተሩ “እንዲያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው” አይነት ዘዴን መጠቀማቸው ነው መሰለኝ አራዳ - ለአራዳ ሲነቃቃ እንግዲህ እንደዚህ ነው።

እናላችሁ በሆነው ባልሆነው ብልጣብልጥ የሚሆኑብንን ሰዎች እንዲህ በአቋራጭ መብለጥ ካልቻልን አለቀልን ገሚሱ በቃል፤ ገሚሱ በጉልበት፣ ገሚሱ በስልጣን፤ ገሚሱ በዘመድ ጥላ ስር እየተጠለለ፤ በኛ የዋህነት ላይ የራሱን ብልጣብልጥነት ሊገነባ ሲሞክር ያናድዳል።. . . በዚያ ላይ ደግሞ “የፈሲታ ተቆጢታ” እንዲሉ ስንነቃባቸው ነገሩን በኛ ላይ በማላከክና ለመልስ ምት ለመፍጠን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። አጥፊውም እነሱ፣ ለጣፊውም እነሱ፣ ጠርናፊውም እነሱ፣ ገራፊውም እነሱ ሲሆኑ በጣም ይደብራል አቦ!

ሰውዬው ሴትየዋን ይወዳትና ካላገባሁሽ ሞቼ እገኛለሁ ይላል። ሴትየዋም እሽታዋን ከመስጠቷ በፊት አለ አይደል ጥቂት የቃል ፈተና አይነት ትደረድርለት ጀመር። በመካከል ላይ፤ “ለመሆኑ ከኔ በፊት አግብተህ ታውቃለህ ወይስ አታውቅም?” ከማለቷ ፤ ሰውዬው ፈጠን ብሎ፣ “ሁለቱን ልጆቼን ይንሳኝ አግብቼ አላውቅም” ይላታል። ቀጥሎም እሱም እንደማጣራት በሚመስል መልኩ፣ “ለመሆኑ አንቺስ አግብተሸ ታውቂያለሽ” ሲል ይጠይቃታል። የሰውዬው መልስ ውስጥ ውስጡን ብግን ያደረጋት እሷም ምን ብትለው ጥሩ ነው? “ሁለቱን ባሎቼን ይንሳኝ አግብቼ አላውቅም” ብላላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ ወደው አይስቁ አሉ። (መቼም ይሄን ሲሰማ ሰውዬው ለጥፊ እጁን ማንሳቱ የሚቀር አይመስልም)

እናላችሁ ያልተሳካውን እንደተሳካ፤ ያልተገኘውን እንደተገኘ፤ ያልተበለውን እንደተበላ፤ ያልተሰራውን እንደተሰራ፤ እንድናምንላቸው ሽንጣቸውን ገትረው የሚወተውቱን በየቦታው ሞልተዋል። የነዚህን አይነት የፈሲታ ተቆጢታዎች ነገር ስናነሳ. . . ለትዝብት አዘል ጨዋታችን ማሳረጊያ የሚሆነው የሚከተለው ቆየት ያለ ተረት ነው።

አንበሳና ጅብ በአንድነት ይኖራሉ። አያ አንበሳ በሬ ሲኖረው፤ ጅብ ደግሞ ላም አላት። ሁለቱም ከብቶቻቸውን ግጦሽ አሰማርተው፤ አግደውና ሰብስበው ሲኖሩ ቀናት ያልፋሉ። ከብዙ ቀናት በኋላ ጅብ የሚያሳድጋት ላም ጥጃ ትወልዳለች። ነገር ግን አያ አንበሳ ጥጃው የተወለደው ከኔ በሬ ነው ሲል ሙግት ይገጥማሉ። እናም የዱር አራዊቱ በሙሉ ተጠርተው “የወለደው የአንበሳው በሬ ነው ወይስ የጅብ ላም?” በሚለው ጉዳይ ላይ ለፍርድና ለምስክርነት ይቀርባሉ። የአያ አንበሳን ነገር ፍለጋ ያጤኑት አራዊቱ በሙሉ በሀሰት ምስክርነትና ፍርደ ገምድልነት እየተነሱ፣ “ጥጃው የተወለደው ከበሬው ስለሆነ ንብረትነቱ የአንበሳ ነው” ሲሉ በአንድ ድምጽ ይመሰክራሉ።

ከአራዊቱ ሁሉ ወደኋላ ቀርታ የደረሰችው ጦጢትም፣ “ጥጃ የሚወልደው በሬ ነው ወይስ ላም!” በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ከመስጠቷ በፊት አንበሳ በጥያቄ ያጣድፋታል። . . .” ለመሆኑ እስካሁን የት ቆይተሸ ነው ጦጢት?” አንበሳ በቁጣ ተሞልቶ ጠየቀ። አያ አንበሶ እዛ ሰፈር መሬት ተቀዶ እየሰፉሁኝ ነው የቆየሁት” ስትል መለሰች። አንበሳ በጦጢት መልስ ተገርሞ፤ “አንቺ ውሸታም ለመሆኑ ከመቼ ጀምሮ ነው መሬት ተቀዶ የሚሰፋው?” ከማለቱ ጦጢት ፈጠን ብላ ምን ብትል ጥሩ ነው? “አያ አንበሳ አንተስ ከመቼ ጀምሮ ነው በሬ የሚወልደው?” ብለው እብስ አለች ይባላል።

ለማንኛውም በብዙ ነገር እየተነቃቃን ስለማንናገር ብቻ እንደማናውቅ ተደርጎ ባይወስድብን መልካም ነው።. . . እንደነቃን ሲያውቁ እኛን ሊያንቁ የሚሯሯጡ አሉ ብለን እንጂ ስንት ነገር በሆዳችን አለ መሰላችሁ። እናላችሁ በየመስኩ ብልጣብልጥ የሆነችሁ የመሰላችሁ ሁሉ።

አንተም አራዳ እኔም አራዳ

ምን ያጣላናል በሰው በረንዳ።

ስትባሉ ይግባችሁ እስቲ . . . አንድዬ ብቻ “ከፈሲታ ተቆጢታዎች” ይሰውረን አቦ. . . እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!!!  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
324 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 895 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us