“የፊሽካ ያለህ!”

Wednesday, 29 March 2017 12:27

 

ቶሎ ቶሎ ሂጂ ወንበዴው ሳይጠና

ከዚህ ስፍራ ቀረሽ አትባይምና።

                (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ዛሬ የምንጨዋወተው ብዙ ነገር አለ። (የሴቶችን ጉዳይ ጨምሮ ማለቴ ነው). . .  እንዴት ነው ጎበዝ!. . . የሴትን ጉዳይ ወንድ ሲያነሳው በአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከቱን ተወት እንጂ። አለ አይደል፡-

“አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ፣

ጉች- ጉች ያለጡት አንድም ቀን ሳላይ”።

በሚሉት ወገን በኩል አይደለንም።. . . ቁም ነገር እኮ ነው። ሁሌ ስለሴት ልጅ መነሻና መቀመጫ ብቻ ከመነጋገር አንዳንዴም ደፈር አንዳንዴም መረር እያደረጉ ጠንካራ ጉዳዮችን ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል።

ይኸውና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን አልፎ - አልፎ የሚሰሙ የሴት ልጅ የጥቃት አይነቶች አፍ የሚያስዙ ሆነዋል። ይህቺ ከስብሰባ ቦታ የማታልፍና ሁሌ የምትደንቀኝ አነጋገር ምን መሰለቻችሁ? “ሴት ልጅ ማለት እኮ እናትም፣ ሚስትም፣ ልጅም እህትም ናት!” ምንድነው ነገሩ ጎበዝ! ለእኛ ይሄ መቼ ጠፋን? ችግሩ ያለው በሆነ ባልሆነው ሴቶችን ወደኋላ ስንጎትታቸው ነው። (እዚህችጋ አንድ ወዳጄ ምን እንዳለ ለጨዋታ ማዋዣነት ልጥቀስማ፤ “እኛ ወንጆች ሴቶችን ወደኋላ ነው የምንጎትታቸው ወደፊት እንዲቀድሙን ዐድሉን የምንሰጣቸው ግን “መቀመጫቸውን” ለማየት ሲሆን ብቻ ነው” ብሎላችሁ እርፍ).  . ኧረ ግድ የለም ጎበዝ እየተስተዋለ።

እናላችሁ ምን ለማለት ፈልጌ ነው የሴቶች ጉዳይ አሁንም ብዙ መስራት ያለበት ይመስለኛል። ይህን ያስባለኝ ምን መሰላችሁ?. . . ከሰሞኑ በሸገር ኤፍ ኤም የቅዳሜ ጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም ላይ ቀርበው የነበሩት የህግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር አሪፍ ቁምነገር አስጨብጠውናል። . . .. ከተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ግን አንዲት ጨዋታቸው በብዙ የምትመነዘር ሆና አገኘኋት። ነገሩ ምን መሰላችሁ? በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሴቶችን ጥቃት ለማስቀረት በተካሄደ ዘመቻ መሳካት “ፊሽካ” የራሷን አስተዋፅኦ ተወጥታለች አሉ። እንዴት በሉ መልስ አለን።. . . በተቀናጀ የሴቶች ጥቃት መከላከል ላይ ያተኮረ ማህበር ተቋቋመ። የዚህ ማህበር አባል የሆኑ ሚስቶች ሁሉ በምስጢር የሚጠቀሙበት “ፊሽካ” ይሰጣቸዋል። ወደቤታቸው (ወደ መንደራቸው) ሲመለሱ አንድ ወንድ ጥቃት ለማድረስ ቢሞክር ፊሽካቸውን ላጥ አድርገው መንፋት ነው። ያኔ ሴቷ ሁሉ ከያለችበት እየተሯሯጠች “ማነው? ምንድነው?” በሚል ለመከላከል ትደርሳለች ማለት ነው። (የድረሱልኝ መጥሪያ ደወል መሆኑ ነው)

ይህን የደቡብ አፍሪካውያን ሴቶች መላ ለኛም በየመስኩ ሳያስፈልገን አይቀርም። የምሬን እኮ ነው። ኢ-ፍትሃዊነት ሲያጋጥመን፣ ጡንቸኛ ሲበረታብን፣ አስተዳደራዊ በደል ሲደርስብን፣ ኑሮ እርር- ምርር ሲያደርገን ላጥ የምናደርገው “ፊሽካ” እና አለው ብሎ የሚደርስልን ወገን ቢኖረን መልካም አይደል? እዚህች’ጋ ታዲያ ቅኔዋን እንደግማታለን፡-

ቶሎ-ቶሎ ሂጂ ወንበዴው ሳይጠና

ከዚህ ቦታ ቀረሽ አትባይምና።

እናላችሁ ባለቅኔው እንዳለው “ወንበዴው” አስተሳሰባችን ካልተስተካከለ፤ “ወንበዴው” ወንድነታችን ካልተሞረደ፤ “ወንበዴው” ስሜታዊነታችን ካልሰከነ፤ “ወንበዴው” ሴትን መመልከቻ መነፅራችን ካልተለወጠ በስተቀር “ከዚህ ስፍራ ቀረሽ አትበይምና (በአካልም በመንፈስም ቆንጆ) የምንላቸው ዓይነት ሴቶችን ከህይወት መንገድ ላይ ማስቀረታችን የማይቀር ነው። . . . እንደደቡብ አፍሪካውያኑ ጎልቶና ተግባብቶ የሚነፋ ፊሽካ ባይኖራቸውም የኛው ሀገር ሴቶች እህ ብለን ብንሰማቸው የሚነፋት ስንት የበደልና የመከራ ጉድ አለ መሰላችሁ።

በኢትዮጵያ ታሪክ አቤቱታዋ ከተሰማላት ሴት መካከል በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ብቅ ያለችው አበራሽ ትገኝበታለች። በዘመኑ አፄ ቴዎድሮስ እናቷን፣ አባቷን፣ እህትና ወንድሟን በእሳት ያቃጠሉባት ይህቺ ሴት፤ ፍትህ ቢጎድልባትና በደል ቢበረታባት እንዲህ ብላ በምሬት አልቅሳለች አሉ፡-

ሺ ፈረስ በኋላ ሺ ፈረስ በፊቱ

ሺ ነፍጥ በኋላው ሺ ነፍጥ በፊቱ

ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ።

በሸዋ በትግሬ የተቀመጣችሁ

በጎጃም በላስታ የተቀመጣችሁ

አንድ ዛላ በርበሬ መንቀል ቸግሯችሁ

አቃጥሎ ለብልቦ ቆጥቁጦ ፈጃችሁ።

ይህን የሰሙት አፄ ቴዎድሮስ በነገሯ ቢናደዱም የደረሰባትን ችግር አስተውለው ይቅርታ በማድረግ ብዙ ብርና አሽከር እንደሰጧትም በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ለማንኛውም በሴቶች ጥቃት ላይ ስንጮህ የሚሰማ ህብረተሰብና መሪ ያስፈልገናልና ሁላችንም የፌሽካ ያለህ! እንበል። እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
561 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1050 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us