አትበል ቀደም - ቀደም

Wednesday, 05 April 2017 12:29

 

መብረር ብቻ አይደለም መኪና መንዳት፣

ገጭ ያለው ከኋላ ምንድነው እዩት።

           (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ?!. . . ዘንድሮ ቀደም - ቀደም ማለት የሚያዋጣም አይነት አይደለም። “ወጣ - ወጣ ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ” እንዲል መሆኑ ነው። ይህውና እንኳን ሰሞኑን አንዳንድ ወዳጆቻችን መኪናቸውን ሲዘውሩ፤ አለ አይደል ቀደም - ቀደም የማለት ባህሪይ ሲታይባቸው ዳር ይዘው መመርመር ጀምረዋል። (የምር ግን ይህቺ ጠጥቶ የማሽከርከርን ነገር ካነሳን አይቀር “መመርመሪያዋ” ለብዙ ነገር የምታገለግል ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር። ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ ከብቃት በታች የሚመሩንም፣ እንዳሻቸው ገበያውን ከፍ ዝቅ የሚያደርጉብን ነጋዴዎችም፤ ሳይገባቸው ሊያስረዱን የሚፈልጉ ካድሬዎችም፣ ባልተጨበጠ ተስፋ የሚሞሉንም ቢገኙ አለ አይደል “መመርመሪያዋን” አፋቸው ላይ እየሰካን ብንፈትሻቸው ኖሮ ብዙ ጉድ የምናይ ይመስለኛል)።

አደም አትበል ቀደም -ቀደም

ትሆናለህ ደም በደም

ከተባለ እኮ በጣም ቆይቷል። ጎበዝ እኛ ዘንድ በተለይ በመኪና አሽከርካሪዎች ዘንድ ያለ ፍጥነት ለፍጥረት ጠንቅ ከሆነ ሰነባብቷል። . . . ኧረ ግድ የላችሁም እሩጫ ይመስል ከምስራቅ አፍሪካ በመኪና አደጋ ግንባር ቀደሞቹ ደረጃ ውስጥ አታስቀምጡን።

የሹፌርና የመፍጠን ነገር ከተነሳ ላይቀር ፕሮፌስር ዳንኤል ቅጣው ከፃፉት “እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ. . .” ከተሰኘ መፅሐፋቸው ውስጥ የምትከተለዋን ትምህርት አዘል መሳጭ ታሪክ እነሆ ብለናል። . . .  ሰውዬው ጠመዝማዛ በበዛበት ተራራ ላይ የስፖርት መኪና መንዳት የሚወድ ነው። በአንድ ወቅት መኪናውን ሽቅብ እያጎነ፣ በጠመዝማዛና መተጣጠፊያዎቹ ጠባብ በሆኑ አቀበት ላይ ይከንፋል። ድንገት ከፊቱ አንድ ትንሽ የቤት መኪና ተንደርድራ መጣችበት። እናም መኪናዋን ታሽከረክር የነበረችው ሴት እንደምንም ብላ ፍጥነቷን ቀንሳ መኪናዋን አንሳጥጣ አበረደች። ሰውዬው ሊደርስባት ጥቂት እንደቀረው አያት። ይሁን እንጂ ሴትየዋ በዚያው ቅፅበት የጋቢናውን መስተዋት አውርዳ “አሳማ” ብላው አለፈች።

ይህ ሰው ትዕግስቱን (ንዴቱን) መቆጣጠር አቃተው። በእርግጥም መስመሩን ይዞ የሚጓዘው እሱ እንጂ እሷ አልነበረችም። “አሳማ” የሚለው ቃል ተምዘግዝጎ በድጋሚ የጆሮ ታቡሩን ደለቀው። የሰውዬው ንዴት ጨመረ። እንደምንም ብሎ ከአንገቱ ወደኋላ በመጠምዘዝና ድምፁን ከፍ በማድረግ “አንቺ ከብት” የሚለውን የቁጣ ቃል ወረወረ። ቃሉ ተራራውን ሰንጥቆ በገደል ማሚቶ ሲስተጋባ የሰማ መሰለው፤ ተሰድቦ እንዳልቀረና ምላሽ እንደሰጣት ተሰማውና በደስታ ፈገግ ብሎ መንገዱን ቀጠለ።

በዚያው ቅፅበት ወደፊት ለፊቱ እየነዳ ጋራውን እንደተጠመዘዘ ግን አይኖቹን ከጎለጎለና አስፋልት ላይ ከቆመ አሳማ ጋር ተላተመ። አሳማውን ገጨው። አሳማውን ገደለው። . . . ሴትየዋ የቻለችውን ያህል ተጣጥራ “አሳማ” ስትለው ዝርዝር ነገሩን ለመጨረስ የሚያበቃ ጊዜ ስላልነበራት ነበር። “አሳማ ከፊትህ አለ ተጠንቀቅ” ልትል ነበር። ይሁን እንጂ በሰውየው የልቡና ውቅር ውስጥ ለዘመናት የኖረው “የሰደበህን ስደብ፣ ዓይን ለዓይን፣ ጥርስ ለጥርስ” በሚል የአስተሳሰብ ሞዴል ውስጥ ነበርና ፈጥኖ ወደተግባር ያዋለው ይሄንኑ ነው፤ ይሉናል ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፡፤ (የተሰመረባት የኔ ናት) እኛም እንላለን አሽከርክር ረጋ ብለህ፣ አትቸኩል ትደርሳለህ ዘና ብለን - አለበለዚያ ግን ልክ እንደአደም ትሆናለህ ደም -በደም አለቀ።

አንዳንዴ ስንቸኩል ከመዳረሻችን ሳንደርስ ልንሰናከልባቸው የምንችልባቸው ምክንያቶች አብዛኞቹ በራሳችን ጥፋት የሚመጡ ናቸው። እናም መሪ ስንይዝ ትንሽ ዞር ይልብናል መሰለኝ ቶሎ ግንፍል - ግንፍል፤ ወዲያው ስድብ - ስድብ ይለናል። እናላችሁ ይሄ “መመርመሪያ” የሚሉት ነገር ጠጥተው መኪናቸውን ወደጦር መሳሪያነት ከሚቀይሩ አሽከርካሪዎች ጥፋት ትንሽም ቢሆን ጋብ ሳያደርግልን አይቀርም።

አነጋገራችን ማንነታችንን እንደሚያሳይ ሁሉ፤ መስጠት ወይም መንፈጋችን ስብእናችንን እንደሚያሳይ ሁሉ፤ መማር ማጥናታችን በፈተና ወቅት እንደሚገለጥ ሁሉ፤ መሳብ መጎተታችን አቅማችንን እንደሚያሳይ ሁሉ፤ የአነዳድ ፍጥነታችንም አደራረሳችን ይወስንልናል።

እስቲ አሁን ደግሞ ከመሰነባበታችን በፊት ከሰሞኑ ከፌስ ቡክ መንደር ተለጥፋ ያነበብኳትን ወግ እንካችሁ . . . አንድ መንገደኛ ለብቻው ጉዞ ይጀምራል። ጥቂት እንደተጓዘም በመንገዱ ሌላ ሰው ያጋጥመዋል። የሚጓዝበትን ቦታ ርቀት አያውቅ ኖሮ ከመንገዱ ያገኘውን እንግዳ ሰው እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፤ “ቀጥሎ ያለው ከተማ ለመድረስ ምንያህል ጊዜ ይወስድብኛል?. . . ነገር ግን እንግዳው መንገደኛ ለጥያቄው ምንም አይነት መልስ ሳይሰጥ ጉዞውን ቀጠለ። አቅጣጫቸው አንድ ቢሆንም ሳይነጋገሩ በዝምታ ይጓዙ ነበር።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ቅድም ጥያቄ የቀረበለት መንገደኛ ወደጠያቂው ዞር ብሎ፤ “ቀጣዩ ከተማ ለመድረስ አንድ ሰዓት ይፈጅብሃል” አለው። በነገሩ የተገረመው የቅድሙ ጠያቂ፤ “ታዲያ ቅድም ስጠይቅህ ለምን አልመለስክልኝም? በማለት ደግሞ ጠየቀ። ያገኘው መልስም፤ “ቅድምማ የጉዞ ፍጥነትህንና የእርምጃህን ልክ አላውቀውም ነበር” አለው ይባላል።

ሰው ሁሉ እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም። በፍጥነት መፎካከሩ ዋጋ ያስከፍለናል፤ በቁመት መወዳደሩ ሞኝ ያስብለናል፤ በብቃት መወዳደሩ ትጉ ያሰኘናል። እናም ሁሉም እንደመስኩ እንጂ እንዳመጣለት አይፍጠን፤ አይቸኩል። በተለይ በመኪና ጥድፊያ ህይወትን፣ አካልንና ንብረትን ይነጥቃል ቀደም - ቀደም ማለት ባናበዛ ይመረጣል። . . . እስከ ሳምንት ቸር እንሰንብት!!!     ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
324 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 893 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us