እስቲ እንነጋገር. . .

Wednesday, 19 April 2017 13:00

 

ባለስልጣኖቹ እስኪያስቡበት
መናገራችሁን እንዳትተውት።
(እንዲል ባለቅኔ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ጎበዝ!?. . . በዓለ ትንሳኤው እንዴት አለፈ?. . . መቼም የገበያው ግርግር ለጉድ ነበር። እኔ የምለው ገበያችንን “በነፃ ገበያ” ስም “ሃይ” የሚለው ጠፍቶ ዶሮ ሰባት መቶ ብርት ተሸጠች ሲባል ምንድነው ነገሩ አያስብልም? ኧረ ግድ የላችሁም ጎበዝ ሁሉ ነገራችን በገንዘብ ቋንቋ ላይ ብቻ የተመሰረተ ባይሆን ጥሩ ነው።. . . ከብር በላይ ሥነ-ምግባር በእጅጉ ለማህበራዊ ተግባቦታችን ያስፈልገናል። (የምሬን እኮ ነው የዶሮና የበግ ዋጋ የበሬና የበርበሬን ያህል ሲያቃጥላቸው የሰነበቱትን ቤቱ ይቁጠራቸው)


ይልቅዬ የቅርጫ ስጋውስ ተበላ፤ እርድ የተደረገበትን የልኳንዳ ስጋ ሁሉ ህዝቤ ተጠራጥሮ (በአህያ ነገር ቂም ቋጥሮ ላለማለት እኮ ነው) ሃሜቱ ለጉድ እንደነበር አንዳንድ ወዳጆቼ መታዘባቸውን ነግረውኛል። . . . የምር ግን የዘንድሮውን ፋሲካ የአህያ ወሬ አላደበዘዘውም?. . . (የምር ግን ከሰሞኑ የአህያው ቄራ መዘጋቱን ሰምተናል። እውነት ባረገው፤ እንዲህ ናትና በፋሲካ ሰሞን “ቪጂቴሪያን” አድርጎ የስጋ ስጋቱ ገደለን እኮ ጎበዝ!!!)


የቄራ ስጋዎን የሚያከፋፍለውና በየከተማው የሚታረዱ ከብቶችን የጥራት ሁኔታ እንዲቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው አካል ራሱ “ጎበዝ ራሳችሁን ከአህያው ስጋ ጠብቁ” አይነት ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ መስጠቱን መስማት ነገሩ እንዴት ነው? ሳያስብለን አልቀረም።


የምር ግን ነገራችን ሁሉ በርቀት በርቀት እየሆነ የጥልቀትና የጥራት ነገር ቁልቁል አልወረደባችሁም?. . . አንዳንድ የአራዳ ልጆች “ፍቅርና ትምህርት በርቀት አይሆንም” ሲሉ የሰማዋቸው ይመስለኛል። እውነት ነው አንዳንድ ነገሮቻችን ቅርበታችንንና ተሳትፏችንን ይጠይቃሉ (ታዲያ ተሳትፎ ሲባል በማስመሰል ተሸክፎ የሚደረገውን ማለቴ አይደለም). . . አንዳንድ ፕሮጀክቶች፣ አንዳንድ ግንባታዎች፣ አንዳንድ ስራዎች፣ በቅርበት ክትትልን የሚሹ ናቸው። ስራዎቹን እንዲከታተልና እንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው አካል በሩቁ ሪፖርት እየተቀበለ ብቻ የሚቀጥል ከሆነ ውጤቱ በእጅጉ አስከፊ ነው።. . . እናላችሁ ፍቅራችንና ተግባራችን በቅርበት መታየት አለበት። ስልጣንና ኃላፊነታችን በቅርበት መታየት አለበት። ትምህርታችንና ጥናታችን በውጤት መታየት አለበት። መታመማችን መዳናችን በተግባር መታየት አለበት። መዋደዳችንና መተሳሰባችን በተግባር መገለፅ አለበት አለበለዚያ ግን ነገራችን ሁሉ የይስሙላ ከሆነ በስተመጨረሻ ቁጭቱን አንችለውም።


የዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን በምትከተለው ወግ አድምቀን እንጨርሳለን።. . . ሰውዬው እናቱን በጣም ይወዳቸዋል። ዕለቱ ደግሞ የእናቶች ቀን የሚከበርበት ነው። እናም እርሱ ከሚኖርበት ከተማ በሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለሚገኙት እናቱ ምርጥ የተባለውን አበባ ሊልክላቸው ወሰነ። በከተማው ውስጥ ወዳለው የአበባ መደብር በመግባትም እናቴን ያስደስትልኛል ያለውን አበባ በመምረጥ የድርጅቱ ሰራተኞች ለእናቱ ያደርሱለት ዘንድ የመኖሪያ አድራሻቸውን ተናገረ።


እናቱ ከልጃቸው የተላከላቸው እቅፍ አበባ ሲደርሳቸው የሚሰማቸውን ደስታ እያሰበ ከአበባ መደብሩ ክፍያውን ፈፅሞ ወጣ። መኪናውን አስነስቶ ትንሽ አለፍ እንዳለ ግን አንዲት ልጃገረድ ከመንገዱ ዳር ቆማ በምሬት ስታለቅስ ተመልክቶ መኪናውን አስጠግቶ ቆመ። የልጅቱን የለቅሶ ምክንያት ሲሰማ በጣም ተገረመ። እናቶች የሚታሰቡበትና የሚመሰገኑበት ቀን ላይ ለእናቷ አበባ መግዛት ያልቻለችው ወጣት፤ ለአበባ መግዣ አስር ብር ስለጎደላት ብቻ ነበር እንደዛ ምርር ብላ ታለቅስ የነበረው። ይህን ሁኔተ ለመቀየር አስር ብር አውጥቶ ከመስጠት ባሻገር አብሯት ወደአበባ መሸጫ መደብሩ በመግባት ምርጥ ነው ያለችውን አበባ እንድትወስድ ካደረገ በኋላ ሂሳቡን ከፍሎ እናቷ ወዳሉበት ሊሸኛት ተስማምተው ጉዞ ጀመሩ።


በብዙ ከተጓዙ በኋላ ግን ልጅቱ ከመኖሪያ ቤት ይልቅ መቃብር ስፍራ ስትደርስ እንዲያቆምላት በትህትና ጠየቀችው። ተገርሞ መኪናውን አቆመው። ወጣቷ ከመኪናው ወርዳ ወደእናቷ መቃብር በማምራት ያመጣችውን አበባ አስቀምጣ፤ መቃብሩን በፍቅር ትዳብሰው ጀመር። ለእናቷ ያላትን ፍቅር ገልፃ፤ ከሀዘኗ ተረጋግታ ወደመኪናው ስትመለስ የሰውዬው የመጀመሪያ ጥያቄ፤ “ይሄን ሁሉ ጭንቀት የተጨነቅሽው በህይወት ለሌለች እናትሽ ነው?” ሲል በመደነቅ ጠየቀ። “አዎ! እናቴ በህይወት እያለች ፍቅር መስጠትን አስተምራኛለች። ነገር ግን በሚገባ ፍቅርን ስላልመለስኩላት ይቆጨኛል። አሁን ያንን ቁጭቴን ለማስታገስ ነው ይሄን የማደርገው። በዚህ ላይ ፍቅር እርቀት አይገድበውም” አለችው። በልጅቷ መልስ ልቡ የተነካው ሰውዬውም ወደአበባ መሸጫ መደብሩ ስልክ በመደወል ለእናቱ እንዲያደርሱለት የሰጣቸውን የአደራ መልዕክት ይዘው እንዲጠብቁትና ራሱ በአካል እናቱ ዘንድ መሄድ እንዳለበት ተናግሮ ወደዚያው በረረ።


እናላችሁ እኛም በፍቅርና በኃላፊነት እየበረርን በስፍራው በአካል ተገኝተን ቅርበታችንን፣ ፍቅራችንንና ኃላፊነታችንና የስራ ችሎታችንን ማሳየት ብንችል፤ በቁጭት የሚያንገበግቡን በሪፖርት የቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ባልኖሩ ነበር።. . . ለማንኛውም አሁንም ጊዜ አለን። መልካም የዳግማይ ትንሳኤ ሳምንት ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
288 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 831 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us