“ከአፍ የወጣ አፋፍ….”

Wednesday, 26 April 2017 12:22

 

እሣት እፍ ቢሉት ይሰፋል ይነዳል፣

እንትፍ ቢሉበት ይጠፋል ይበርዳል።

ሁለቱም ካንድ አፍ ነው የሚመነጨው

ምላስን በልጓም ስበህ ካልያዝከው

እንኳን ራስህን ታስፈጃለህ ሰው።

(እንዲል ባለቅኔ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ውዶቼ!?... እኔ የምለው የአርሴና የማንቼ ጉዳይ፤ የባርሳና የማድሪድ ነገር እንዴት አከራረማችሁሳ… እንግዲህ ከኑሯችን ዋና-ዋና ጉዳዮች መካከል እግር ኳስ (በተለይም የአውሮፓውያኑ ፍልሚያ) ከሽሮና ከበርበሬ በላይ ወጥሮ ከያዘን ሰነባብቷል ብዬ ነው መጠየቄ።

 

እስቲ ደግሞ ወደዛሬው ትዝብት አዘል ጨዋታችን እንመለስ፤ አበው በተረት ነገር ሲያሳምሩ ምን ይላሉ መሰላችሁ?.... “ከአፍ የወጣ አፋፍ” እናላችሁ ድንገት ከአፋችን የሚወጣው ነገር ሁሉ የሚያመጣው ጣጣ በበዛበት በዚህ ዘመን ዝም ማለቱ ሳይሻል አይቀርም መሰለኝ። በተለይ በማናውቀውና በማያገባን ነገር እንደ እርጐ ዝንብ ከመሬት ተነስተን ጥልቅ ስንል ያስተዛዝባል።   

 

ሰውዬው የሚያወራው የሚሰማለትና ሁለት ፀጉር ያበቀለ ነው። ከጐረቤቱ የሚኖር አንድ ወጣት ደግሞ በስራ አጥነት ይኖር ነበር። ታዲያ ይሄ ትልቅ የሚባል ሰው የወጣቱን ስም በወሬ ያጠፋል። ሌባ ነው ብሎ አስወራበት። ነገሩ በመንደሩ በፍጥነት ከመዛመቱ ባለፈ በቀጣዩ ቀን ጠዋት ፖሊስ ወጣቱ ቤት ድረስ ለመምጣት ይዞት ሄደ። በፖሊስ ምርመራ ግን የወጣቱ ሌብነት ሊረጋገጥ አልቻለም።

 

ፖሊስ የወጣቱን ንፁህነት አረጋግጦ ሲለቀው፤ ወጣቱ ስሜ ጠፋ በሚል በሀሰት ወሬውን የነዛውን ሰውዬ ክስ መሰረተበት። ሰውዬውም የተመሰረተበትን ክስ ለመከታተል ፍርድ ቤት ይቀርባል። በችሎት የተገኘው የመንደሩ ተደማጭ ሰው ችሎት ቀርቦ፣ “ነገሩን እንደቀልድ የተናገርኩት እንጂ ማንንም ለመጉዳት አስቤ ያደረኩት አይደለም” ሲል ለዳኛው አስረዳ። ዳኛውም የሰውዬውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ፣ “መልካም አሁን አንድ ነገር ታደርግ ዘንድ ፍርድ ቤቱ ይፈልጋል። ወጣቱን በሀሰት ሌባ ነው ብለህ ተናግረኸዋል። አንድ ወረቀት ውሰድና ወጣቱን የተናገርካቸውን በሙሉ በዝርዝር ጽፈህ አምጣ” አሉት።

 

በአንድ ወረቀት የፃፈውን ዝርዝር ወሬና የሀሰት ውንጀላ ለዳኛው ሰጣቸው። ዳኛውም ወረቀቱ በኮፒ እንዲባዛ ካደረጉ በኋላ አንድ መቶ ገጾችን በተናጠል በመስጠት፣ “አሁን ወደቤትህ ሂድ፤ በመንገድ ላይ ስትሄድ ግን እነዚህን ወረቀቶች እየጣልክ ሂድ።” በማለት አሰናበተው እና ለቀጣዩ ቀን ውሣኔ በቀጠሮ ተለያዩ።

 

በቀጣዩ ቀን ሁሉም ሰው በተሰበሰበበት ከሳሽና ተከሳሽ ፊት ለፊት እንደተፋጠጡ፤ ዳኛው ገብተው በመንበራቸው ተቀመጡ። የዳኛው የመጀመሪያ ንግግር እንዲህ የሚል ነበር፤ “ዛሬ የቅጣት ውሳኔያችንን ከማሰማታችን በፊት አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብሃል። ትናንት ተከሳሽ ሆነህ ስትቀርብ በወጣቱ ላይ በሀሰት የተናገርካቸውን ነገሮች በሙሉ ወረቀት ላይ ጽፈህ በመንገድህ እንድትበትናቸው አዝዤህ ነበር አይደል?” አሉ ዳኛው። ተከሳሹም በአዎንታ መታዘዙንና መፈፀሙን አረጋገጠ። ዳኛው አስከትለው፣ “አሁን ከችሎቱ ወጥተህ ትናንት የበተንካቸውን መቶ ገጾች ሰብስበህ ተመለስ” ሲሉ አዘዙ። ተከሳሹ ግን፣ “ክቡር ዳኛ ይህንን ማድረግ በፍፁም አልችለም። ምክንያቱም ትናንት የበተንኩትን ወረቀት ነፋስ በታትኖ የት እንዳደረሰው ማወቅ አልችልምና ይቅርታ ይደረግልኝ” ሲል ተናገረ።

 

ይህንን ምላሽ የሰሙት ዳኛም የሚከተለውን ተናገሩ፣ “አንተ ባለፈው ጊዜ እንደቀላል የተናገርከው ነገር የዚህን ወጣት እምነት (ታማኝነት) ጥያቄ ውስጥ የጣለ ነበር። እንደቀላል የምንዘራቸው ወሬዎች አንዴ ከኛ ከወጡ በኋላ መመለሻ አይኖራቸውም። ተገቢና ትክክለኛ ያልሆነ ነገር ከመናገር ፀጥ ማለቱ ይሻላል።” ሲሉ በመምከር በተግሳፅ አለፉት የሚል ታሪክ በቅርቡ ማንበቤን አስታውሳለሁ።

 

በሀሰት የሚለጠፍ ውንጀላና በሀሰት የሚሰጥ ማንነት፣ በሀሰት የሚመጣ ዝናና ሀብት ሁሉ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሰጪውንም ተቀባዩንም በእጅጉ መጉዳታቸው የማይቀር ነው። እናም “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ” ነውና ከሀሰትና ከባዶ ወሬ ምላሳችንን ሰብሰብ ማድረጉን መልመድ ይኖርብናል። በተለይ ስለኛ የሚናገረው ሰው የሚታመንና “አንቱ” የምንለው ከሆነ ታማኝነታችን ጥያቄ ውስጥ መግባቱ፤ ስማችንም በከንቱ መጥፋቱ አይቀርም። “ምላስ አጥንት ባይኖራትም አጥንት ትሰብራለች” የሚል ጥቅስ አስታወሳለሁ። ስለነገሮች መልካምነት ብንናገር መልካም ይሆናል ነገር ግን ክፉ-ክፉውን ብቻ የሚዘረግፍ ከሆነ “የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽምና” እየተስተዋለ ጐበዝ!

በተለይ ግን በሀሰት ወንጅሎ፣ በድፍረት ዓይኑን አፍጥጦ ሀሰቱን እውነት ለማስመሰል ከሚደርቅ ሰው አንድዬ ይጠብቀን። እስቲ ደግሞ ለዛሬ ከመሰነባበታችን በፊት ይህቺን ጨዋታ እንካችሁ። … ሰውዬው ቤተ-ክርስትያኗ ለምዕመናኑ መገልገያ ይሆን ዘንድ ካዘጋጃቸው መፅሐፍት መካከል “መዝሙረ-ዳዊት”ን ሰርቆ ይሰወራል። በማግስቱም እንደልማዱ ዳዊት ሊሰርቅ ተመልሶ ይመጣና ማንም ሳያየው ሰተት ብሎ ሲገባ የቤተክርስትያኒቷ ቄስ እክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ ያገኛቸዋል። “ልጄ መሬትና ሰማይ ከመላቀቁ በፊት እዚህ ድረስ አቻኩሎ ያመጣህ ከባድ ጉዳይ ምን ይሆን?” ብለው ቄሱ ጥያቄ ከማቅረባቸው ሌባው ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “አባ ዳዊት ልደግም ነው” ብሎላችሁ እርፍ (ቂ…ቂ…ቂ…) ለማንኛውም በሀሳት ከሚወነጅልም ሆነ ተናግሮ ከሚያናግር ሰው አንድዬ ይጠብቀን አቦ!..... ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
322 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 948 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us