ታማኝ ሌቦች

Wednesday, 03 May 2017 12:25

 

እኔ እየመከርኩህ አንተ እየተቆጣህ

ለኔም መቀመጫ ላንተም መቆሚያ አጣህ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ውዶቼ!?. . . እኔ የምለው ሁሉ ነገር በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሆነ አይደል? እዚህ አገር ደግሞ ለየት የሚለው ክፉውንም ደጉንም እየተማመኑ ምንም እንዳልተፈጠረ መተላለፉ ነው። ትልቅ ስህተት እየተሰራ፣ ትልቅ ሙስና እየተሰራ፣ አይን ያወጣ ዝርፊያና ውሸት እያየንና እየሰማን ይቅርታ የሚጠይቅ የለ እንዲያው የሚቀጣ የለ ዝም- ዝም ሲባል ምን ትሉታላችሁ?. . . እናላችሁ በተለይ መንግስት ጋር ሲሆን፤ የመልካም አስተዳደር ችግር አለብን ይባልና ቀጥሎ ዝም።. . . የአመለካከት ችግር እንዳለ ደርሰንበታል ይባልና ማን ሊጠየቅ ይሆን? ብለን ስንጠብቅ ዝም።. . . በዘመድ አዝማድ የተገመደ የሙስና ሰንሰለት አለ እንባልና ሰንሰለቱ ተበጥሶ፤ ማን ሊታሰር ይሆን ብለን ስንጠብቅ ዝም።. . . በቃ ምን አለፋችሁ የኛ ነገር በሃጢያቱ ላይ እየተማመንም በቅጣቱ ነገር ላይ ግን ከዝምታ በቀር የለንበትም።

ሰውዬው ስለትንሹ ልጁ ጎበዝነትና ታታሪነት አብዝቶ ለጎረቤቱ እየተናገረ ነው። “ቤተሰቡን የሚረዳ ታማኝና ግልጽ ልጅ በመሆኑ በጣም ነው የምኮራበት” ይላል አባት፤ ስለልጁ በኩራት ሲገልጽ። ድንገት ታዲያ ስለጉብዝናውና ስለታማኝነቱ ሲተረክለት የነበረው ልጅ ከውጪ ይገባል። በእጁም ዶሮ አንጠልጥሎ ነበር።

“ዶሮዋን ከየት አመጣሃት?” አባት ጠየቀ።

“ሰርቄአት ነው አባዬ” ልጁ በልበሙሉነት መለሰ። ይሄኔ አባት ወደጎረቤታቸው በኩራት ዞር ብለው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “አየኸው ይሄን ጎበዝ ልጅ ቢሰርቅ እንኳን አይዋሸኝም” ብለውላችሁ እርፍ (ቂ.ቂ.ቂ ወደው አይስቁ አሉ!)

እናላችሁ የኛም ነገር እንዲሁ ነው። ባለስልጣናቱ ይሳሳታሉ ነገር ግን ከሂስና ግለ ሂስ የዘለለ ነገር የለም። ስንት ፕሮጀክቶች ተገትረው ሲቀሩ፤ ስንት አሰራሮች ተግባራዊ ሳይደረጉ ሲቀሩ፤ በከተማው ሙሉ በሙስና ሀሜት ሲታመሱ እየዋሉ ጥሩ ሰርተዋል ከመባባል ያለፈ አንዳችም የምርመራም ሆነ የእርምጃ አይነት አይተን አናውቅም።

እጃችንን በሙስና ተይዘን ለመንግስታዊ አስተዳደር አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ ብንጠፈርም “የኛ ሰዎች እኮ ቢሰርቁም እንኳን ግልፅ ናቸው” ተባብለን ከመተላለፍ ውጪ ወፍ የለም። ለሀገርና ለወገን ይጠቅማሉ በተባሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ስም ብሩ ወጥቶ ቀልጦ ሲቀር ከመጠያየቅና ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ተማምነን እና “ታማኝ ሌቦችን” ደባብቀን መቀጠል ስራችን ሆኗል።

አሁን- አሁን እንደውም የሙስና ወንጀል ከመስራት ይልቅ መስራታቸውን በግልፅ አምነው ይቅርታ የማይጠይቁ አባላት ወየውላቸው። ጎበዝ እኛ ዘንድ እኮ ይቅርታ ማለት ለቀጣይ ዝርፊያ መዘጋጀት ማለት ይመስላል። .  . . እናላችሁ እየተማመንን ነገር ግን ሳንጠያየቅ የምናልፍበት አካሄድ መጨረሻው ገደል መሆኑን መጠርጠር ይኖርብናል። እናም የታማኝ ሌቦች ነገር ይጣራልን!. . .

ጎበዝ የኛ ሀገር መዝረፍ እኮ ለእርሾ የሚቀርለትም አይደለም። ታዝባችሁልኝ ከሆነ ሙስናው በራሱ የመቶ ፐርሰንት ደረጃ ደርሷል። አንዳንዶች በግልፅ እንደተናገሩት እናጠፋዋለን ያልነው ሙስና እኛኑ እያጠፋን መሆኑን እወቁልን። ከመሰረት ድንጋያቸው በስተቀር ተጀምረው የተጠናቁ ፕሮጀክቶች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። በትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ይጣላል፤ ት/ቤቱ ግን አይገነባም። ለሆስፒታል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ይጣላል፤ ሆስፒታሉ ግን የለም። ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ይጣላል፤ ስኳር ፋብሪካው ግን የለም። የቤት ግንባታ መሠረቱ ይጣላል፤ ቤቱ ግን የለም።. . . በኋላ ላይ ነገሩ ሲጣራ ታማኝ ናቸው ያልናቸው “እነእንትና” መቶ በመቶ የግንባታውን በጀት ላጥ አድርገው ኑሯቸውን ሲያሞቁ ልንመለከት እንችላለን። ያኔ ታዲያ በውስጥ መስመር ተማምነንና ይቅርታ ተጠያይቀን መተላለፍ እንጂ እንደስራቸው መቀጣጣት ብሎ ነገር የለም።

አንድ የአገራችን መሀንዲስ ነው አሉ፤ ከጎረቤት ሀገር ኬኒያ የተመደበ መሀንዲስ ጋር በጋራ በመሆን ለትምህርታዊ ስልጠና ወደቻይና ይላካል። ሁለቱም መሃንዲሶች ስልጠናቸውን አገባደው ሲመለሱ ገና በመጀመሪያዎቹ ቀናት አንደኛው የአንደኛውን ቤተሰብ ይጎበኛሉ። ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ድንገት ኢትዮጵያዊው መሃዲስ ለስራ ጉዳይ ወደኬኒያ ይሄዳል።

ኬኒያዊው መሀንዲስ ቤት ሲደርስ፤ ከባለፈው በእጅጉ ኑሮው ተመንድጎ፤ ቤቱ ተቀይሮ የሃብት ደረጃው በእጅጉ ከፍ ብሎ ጠበቀው። “እንዴት በዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ኑሮህ ከስር መሰረቱ ተቀየረ ጃል?” ሲል ኢትዮጵያዊው መሀንዲስ በመገረም ጠየቀው። ኬኒያዊው መሃንዲስም የሰራቸውን ፕሮጀክቶች እያስጎበኘው፤ “እዛ’ጋ ያለው ድልድይ ይታይሃል?. . . ከሱ ላይ 30 በመቶ አንስቼለታሁ።. . . ይሄ ትልቅ ህንፃ ይታይሃል ከዚህም ላይ 50 በመቶ አንስቼለታሁ። መንግስት ከሚያስገነባቸውም ሪልስቴቶች እንዲሁ 50 በመቶ አንስቼለታለሁ። ሌሎችም ያልነገርኩህ ስራዎች አሉ” እያለ የሠራውን ሙስና ይዘረዝርለታል።

ከዓመት በኋላ ኬኒያዊው በበኩሉ ወደኢትዮጵያ ሲመጣ የጓደኛውን ቤት ሲመለከት ተገርሞ “እንዴት ነው ለውጥህ ፈጣን ሆነብኝሳ?” ከማለቱ ያገኘው ምላሽ ምን ቢሆነ ጥሩ ነው? “የኔ ጌታ ብዙ ፕሮጀክቶችን ሰርቼ ያፈራሁት ሀብት ነው። ተመልከት እዛ’ጋ ያለውን ህንፃ” ሲለው ኬኒያዊው ህንጻ አልታይ ይለውና “የቱ ህንጻ?” ሲል ይጠይቃል። “አየህ እዛ’ጋ ህንፃ ሊሰራ ታስቦ ነበር። እኔ መቶ ፐርሰንቱን ወሰድኩት። . . . ተመልከት ደግሞ እዛ’ጋ ያለውን ድልድይ” ከማለቱ አሁንም ኬኒያዊው መሃንዲስ ግራ ተጋብቶ “የምን ድልድይ ነው የምታሳየኝ። የለም እኮ” ከማለቱ ኢትዮጵያዊው፣ “አዎ እዚያ’ጋ ድልድይ ይሰራል ተብሎ ነበር መቶ ፐርሰንቱን ወሰድኩት” እያለ መዘርዘሩን ቀጠለ ይባላል።

እናላችሁ ጎበዝ እንዲህ በግልፅና አይን ባወጣ መልኩ እየሞሰስን ይቅር መታሰሩ፤ ይቅር መገረፉ ጮክ ብሎ የሚቆጣ አካል እንኳን ሲታጣ በጣም ይደብራል።. . . ለማንኛውም በግልፅነት ስም፤ በታማኝነት ስም፤ በአባልነት ስም፤ ጥረን -ግረን የፈጠርነው ሀብት ነው በሚል ስም መዘራረፉ ቢበቃ ምን ይመስላችኋል? (እዚህች’ጋ በመግባያችን ያሰፈርናትን የባለቅኔውን ነገር ደገም አድርጓት)

እኔ እየመከርኩህ አንተ እየተቆጣህ

ለኔም መቀመጫ ላንተም መቆሚያ አጣህ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

አዎ!!! . . . እስከ ሳምንት ቸር እንሰንብት አቦ!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
364 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 923 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us