እያቀዱ መልፋት. . .

Wednesday, 10 May 2017 13:13

 

ትልቅ ትልቅ ዳቦ በእጃችሁ ይዛችሁ፤

ምነው እናንተ ጌቶች ትጋመጣላችሁ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ውዶቼ!?. . . ለዛሬ ቀደዳ ላይ አተኩረን በትዝብት እንጨዋወታለን።. . . አበው ሲተርቱ “ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል” ይላሉ፤ እውነት ነው። በተለይ አሁን ላይ ያለ ሰው መቅደድ የዘወትር ስራው ይመስላል። ኧረ እንደውም እኛ ዘንድ ከቀዳዳ አልፎ የቡጨቃ ዘመን ላይ ደርሰናል መሰለኝ። ይባስ ብሎ ለቡጨቃ እንዲመቸን ያልሆነ ፕሮጀክት እያፀደቅን በለው ማለት ልማድ ሆኖብናል። አንዳንዴ ሳስበው ውጤቱን እያወቅነው በከንቱ ለመልፋት እቅድ የምናወጣ ሁሉ ሳያስመስልብን አልቀረም ጎበዝ!

ሁሉነገር ሙሉ ሆኖ፤ ሁሉ ነገር በበር በደጃችን እያለ ከመቀደድና ከመቧጨቅ ተላቀን አናውቅም። በእጃችን ያለውን በሚገባ መጠቀም ትተን በሌሎች ነገር ላይ ስንባላና ስንቧጨቅ እነሆ መሽቶ ይነጋል፤ ነግቶም ይመሻል። ልክ ስራ እንደፈታው መነኩሴ ከፈረሱ ጋሪውን እያስቀደምን በብዙ መቸገራችንን ሳትታዘቡ የቀራችሁ አይመስለኝም።

እነዚህች’ጋ አንዲት ጨዋታ ትዝ አለችኝ። አንቱ የተባሉ የከተማው አስተዳዳሪ ናቸው። በክብር ወደተጠሩበት የድልድይ ምርቃት መጡና በሰዎች ታጅበው የተገነባውን ድልድይ እያደነቁ መረቁ። በኋላ ላይ ነገሩን በትኩረት ሲመለከቱት ቆዩና አጠገባቸው ወዳለ ሰው ዘወር ብለው፣ “ለመሆኑ ወንዙ የታል?” ብለው ጠየቁት። ያገኙት ምላሽ፣ “ጌታዬ እሱማ በመጪው አምስት ዓመት ዕቅዳችን ውስጥ ተካቷል እኮ” ብሎላችሁ እርፍ። . . . እንዲህ አይደል ታዲያ ቆብ ቀዶ መስፋት ማለት?. . . ወይም ደግሞ እያቀዱ መልፋት ማለት ይህ ይመስለኛል።

ሰርተን ውጤቱን መጠበቅ ሲገባን፤ ውጤቱን እያወቅን እንሰራለን። አጥንተን መፈተን ሲገባን ተፈትነን ማጥናት እንጀምራለን፤ ተምረን መመረቅ ሲገባን ተመርቀን መማር እንጀምራለን፤ ነግደን ማትረፍ ሲገባን አትርፈን እንነግዳለን፣ በተለይ ደግሞ በአፍሪካዊያን ፖለቲከኞች ዘንድ ተመርጠን ስልጣን መያዝ ሲገባን ስልጣን ይዘን እንመረጣለን። ሁሉ ነገር እኛ ዘንድ የተገላቢጦሽ ይመስላል። እናም በስተመጨረሻ በእጃችን ያለው ዳቦ ቀርቶ መገማመጥ እንጀምራለን።

በከንቱና በንትርክ የምናጠፋውን የመሰለ የሚያሳዝን ጊዜ የለም። ሰው እስቲ የእርሱ ባልሆነና ለማይጠቅመው ነገር ሲጋጭ አይገርማችሁም።. . . ለምሳሌ ሁለት መላጦች ማበጠሪያ ለማግኘት ያሳዩትን ፍልሚያ የሚተርከውን ተረት በአይነ-ህሊናችሁ ሳሉልኝማ። ውሃ ለሌለው ባዶ ጀሪካን እንደመታገል፤ ውሃ በድስት እንደመጥበስ ምን የሚያስቅ እና የሚያሳቅቅ ነገር አለ? እያቀዱ መልማት ማለት እንዲህ ነው እንግዲህ። . . . ለማናችንም ስለማይጠቅም ነገር ግን ሁላችንንም ስለሚያናክስ ነገር ሳስብ አንዲት ጨዋታ ብቅ አለችልኝ።

ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ከፈተና ክፍል እንደወጡ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ሳይወጡ መቧቀስ ይጀምራሉ። በመሀል አንድ ገላጋይ ይገባና “አንተም-ተው፤ አንተም ተው” ብሎ ይገላግላቸዋል። አስከትሎም በምን ምክንያት እንደተጣሉ መጠየቅ ይጀምራል። አንደኛው ታዲያ ፈጠን ብሎ ይመልሳል፣ “ይሄ ደደብ በፈተና ወረቀቱ ላይ ምንም መልስ ሳይሰራ ስሙን ብቻ ፅፎ መስጠቱ አናዶኝ እኮ ነው” ከማለቱ ገላጋዩ በአነጋገሩ ተገርሞ፤ “እና ታዲያ መልሱን ካላወቀ ስሙን ብቻ ፅፎ መስጠቱ ምን ችግር አለው?” ብሎ ጥያቄ ከመሰንዘሩ ያገኘው ምላሽ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “ምን ችግር አለው? ትቀልዳለህ እንዴ! እኔም እኮ ስሜን ብቻ ፅፌ ነው የሰጠሁት። አስተማሪው ወረቀታችንን ሲያየው የተኮራረጅን ቢመስለውስ?” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ!

እናላችሁ ባለቅኔው እንዳለው በእጃችን ብዙ በረከት እያለ፤ በእጃችን ብዙ ዕድል እያለ፤ በእጃችን ጥዑም ዳቦ እያለ የሌለውን ዘለን ስንገምጥ ዘመናችን ክፉ እናደርገዋለን።. . . ከመጎራረስ ይልቅ መቦቃቀስ በመካከላችን ስለምን እንደሚያብብ ግራ ይገባኛል። ለዛም ይሆናል ቴዲ አፍሮ “ከፊት የነበርነው ከሰው ኋላ ቀርተን” በሚል መንፈስ ንቁ የሚለን። ምርጥ- ምርጥ ዳቦ፣ ዕድል፣ ሀብትና በረከት በእጃችን ቢኖርም የኛንም ሳንበላ የሌላውንም ሳናስበላ እንዲሁ በነገር ስንጎነታተል፤ ትልቁ ዳቦ ሊጥ እየሆነ ያሳለፍነው ጊዜ ብዙ ይመስለኛል። እናም እንደባለቅኔው እንጠይቃለን።

ትልቅ ትልቅ ዳቦ በእጃችሁ ይዛችሁ፤

ምነው እናንተ ጌቶች ትጋመጣላችሁ?

የምር ግን የምንገማመጥበት ከንቱ ምክንያት አይደንቃችሁም? ከሀገር አልፎ ለአለም የሚበቃ ሀብት ይዘን እርስ- በእርሳችን መሳደዳችን በጣም ነው የሚያሳዝነው።. . . “የማን ቤት ተንዶ የማን ቤት ይቆማል” የሚል አጉል ንትርክና ትግል ውስጥ የሚከተን ከራሳችን አልፈን ማየት ሲያቅተንና አንድነታችን ላይ ማተኮር ሲሳነን ብቻ ይመስለኛል።

   እናላችሁ ስንትና ስንት የምንሰራው የሀገር ስራ እያለብን፤ በከንቱ ቆባችንን እየቀደድን የምንሰፋ ከሆነ፤ በከንቱ እያቀድን የምንለፋ ከሆነ ምን ዋጋ አለው?. . . ስንት የምንገነባው ወንዝ ወለድ ድልድይ እያለን ድልድይ ገንብተን ከጨረስን በኋላ ወንዙን መፈለግ ምን ይሉታል?. . . ባልገባንና ባላወቅነው ጥያቄና መልስ በከንቱ ከምንቧቀስ አንዳችን ሌላችንን እያረምንና እያገዝን፤ በትብብርና በአንድነት መኖር ብንችል የት በደረስን ነበር።. . . ብቻ አንድዬ ከመናከስ፣ ከመቧጨቅና ከመጋመጥ አውጥቶ ለተስፋ ዘመን ያድርሰን አቦ!. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
310 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 84 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us