የመተዛዘል ነገር. . .

Wednesday, 17 May 2017 12:40

 

ልጄ በምሽቱ አትጀምር አዝመራ

በጊዜ ነው እኮ ስራ የሚሰራ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ውዶቼ!?. . . ይኸውና ስንቱን ስናይና ስንሰማ፤ ስንቱን ስንታዘበው ሳምንቱ አለፈ። . . . ይኸውና ደግሞ በፈተና ዘመን ሲሲቲቪ ከሰሞኑ አንድ አጃይብ የሚያሰኝ የፈተና ወሬ አሰደምጦናል። ነገሩ እንዲህ ነው፤ በያዝነው ዓመት ወደኮሌጅ ለመግባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለፈተና ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አስራ ሁለቱ ውጤታቸው ስለተበላሸባቸው ራሳቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ አጥፍተዋል። ለምን ሲባል ፈተናው በሕይወታቸው የሞት ሽረት ሳይሆን እንዳልቀረ ገማቾች ተናግረዋል።

እኔ የምለው ከውጤቱ እኮ ትጋቱ መቅደም አለበት።  “የነ ቶሎ-ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰምበሌጥ” እና “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” የተሰኙ አገር በቀል ተረቶችን የሚያስታውሱ ሁኔታዎች ከበረከቱ እኮ የነበሮች መጨረሻ እንዲሁ አማራሪ መሆኑ አይቀርም።. . . ያም ሆኖ ከፈተና መውደቅ ማለት ከህይወት መሰናበት አይደለምና ይሄን ያህል የጨከነ ውሳኔ በራስ ላይ መወሰን በፍፁም አይገባም። ይኸው እኮ ከወደ ቻይና አካባቢ የተሰማው ወሬ መፈተንን መማር፣ መማርን ደግሞ መፈተን ያስመሰለ ሰው ታሪክ ሰምተናል። ሰውየው ለሃምሳ አንደኛ ጊዜ ትምህርት ቤት ገብቶ የማጠቃለያ ፈተናውን ለመውሰድ ስለመቀመጡ የተሰማው ዜና በርካቶችን አስገርሟል።

ለማንኛውም ጎበዝ ስራችንን በጊዜ መስራት እንጂ “የነቶሎ-ቶሎ ቤትን” እና “የእነሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱን” ተረት የሚያስታውስ ስራ እየሰሩ መልካም ውጤት መጠበቅ ዘበት ነው። አባት ሳለ አጊጥ ጀንበር ሳለች እሩጥ አይደል የሚባለው?

እዚህች’ጋ የትምህርት ነገር ከተነሳ ላይቀር አንዲት ቆየት ያለች ጨዋታ እንካችሁ።. . . ነገርዬው የሆነው የመሠረተ- ትምህርት ታውጆ፤ ያልተማረ ይማር፤ የተማረ ደግሞ ያስተምር በተባለበት ወቅት ነው። ታዲያ ሁሉም ተማሪ በሆነበት በዚህ ጊዜ በዕድሜ ትንሽ ገፋ ያሉ ባልና ሚስት መሠረተ-ትምህርቱን በአንድ ክፍል ውስጥ ይያያዙታል። የማጥናት ጊዜ አልነበራቸውምና፤ እንዲሁም ትኩረታቸው ያን ያህል ስለነበር እነዚህ ባልና ሚስቶች ትምህርቱ አልገባ ይላቸዋል። ማቋረጥ ደግሞ በፍፁም የማይታሰብ ነገር ሆነባቸው። በየሳምንቱ በሚሰጠው ፈተና ጭንቅ ጥብብ ይላቸዋል። ምንም እንኳን ውጤታቸው እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም መማራቸውን አላቋረጡም።

ድንገት ግን ሚስትዬው በውጤታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት ይጀምራሉ። እያደርም ከክፍላቸው አንደኛ ይወጣሉ። ባል በሚስታቸው ውጤት ተገርመው መላውን ለመጠየቅ ይሰናዱና፣ “አንችዬ እንዴት ነው ቀለሙን በአንዴ ጠጥተሸው የዕውቀት ብርሃኑን ተላበሺው እኮ ዘዴሽ ምንድነው?” ብለው ቢጠይቁም ሚስት አልናገርም ብላ ትቋጥራለች። (ያሁን ዘመን ሰው መቼም ምስጢር ከመቋጠር ይልቅ ብር መቋጠር ላይ ነው የሚያተኩረው አይደል?)

ታዲያ አንድ ቀን ሁለቱ ባልና  ሚስት ቤታቸው ተቀምጠው ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ሳለ የወቅቱ ርዕሰ-ብሔር ኮሎኔል መንግስት ኃ/ማርያም ብቅ ብለው ንግግር ያደርጋሉ። በንግግራቸው መካከልም አፅንኦት ሰጥተው፤ እየደጋገሙ “ከእንግዲህ በምንም መንገድ ተዛዝለን መቀጠል አንችልም። ራሳችንን መቻል አለብን ጓዶች!” ይላሉ። ይሄኔ ባል ልባቸው እስኪፈርስ ከትከት ብለው ይስቃሉ። ይሄኔ ሚስትም ነገሩ እንደታወቀባቸው ገብቷቸው ሳቅ ብለው፣ “ምን ላድርግ አንተ ግን አታደርገውም” ይሏቸዋል። ባልም፣ “አይይ አሁንማ ጓድ ሊቀመንበር አንተዛዘልም ብለው መመሪያ ሰጥተውበታል እንዴት እችላለሁ ይብላኝልሽ ላንቺ እንጂ” አሏቸው። ለካንስ ሚስት ሲጨንቃቸው የመጨረሻ ልጃቸውን በከረሜላ እያባበሉ አዝለውት መሠረተ -ትምህርት በመግባት የፈተናውን መልስ የሚኮርጁት ከህጻኑ ኖሯል።

እናላችሁ አንዳንዴ ጊዜው በዋዛ ፈዛዛ ያልፍና የግድ በምንወጠርበት ጊዜ በከረሜላ (በጉርሻ) እየታለልን የምንተዛዘልበት ወቅት ይመጣል። የምር ግን በየመስኩ እንደተዛዘልን አይደል እንዴ በጀት ተከፍቶ፤ በጀት የሚዘጋው? እውነት - እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እኮ እዚህ አገር ብዙ ስራ የሚሰራው ጊዜው ካለፈና ከረፈደ በኋላ ወይ ግደለኝ ወይ አድነኝ በሚመስል መተዛዘልና ውትወታ ነው።. . . በተለይ- በተለይ በአቋራጭና በአማላጅ የሚሰራውን ስራ ስትመለከቱ እነዚህ ሰዎች ስራው ግዳጅ ሆኖባቸው ነው ወይንስ መተዛዘል ለምዶባቸው? ያስብላችኋል።

እናላችሁ ስንት ነገር እየሰማን እንዳልሰማ፤ እያየን እንዳላየ ሆነን ማለፋችን የመተዛዘል ባህላችን የቱን ያህል እንዳደገ የሚያሳይ ይመስለኛል።. . . እኛው እየተሠረቅን፣ እኛው እየተሠቃየን፣ እኛው እየተቸገርን እኛው እየተሸከምን እስከመቼ እንተዛዘል ጎበዝ!. . . “አውቀሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” እንባባላለን ደግሞ፤ የምር ግን አካፋን “አካፋ”፤ ዶማንም “ዶማ” እየተባባልን መቀጠሉ አይሻለንም?. . .” ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ እኛም በጊዜ ዘመናችንን በእውነትና በግልጽነት ውብ ብናደርጋት ምን ይለናል? ምንም። ከመሰነባበታችን በፊት ባለቅኔውን እናስታውሳለን፡-

ልጄ በምሽቱ አትጀምር አዝመራ

በጊዜ ነው እኮ ስራ የሚሰራ።

     (እንዲል ባለቅኔ)  እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
348 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 892 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us