የባንኩ እና የ“ቡኩ”

Wednesday, 07 June 2017 14:09

ትልቁን አጎዛ ሸጠችው ለብር፣

ትንሽ ለምድ አመጣች የሚቆረቁር።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንዴት ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . መቼም ሰው ነን እና መሳሳታችን አይቀርም። ግን ደግ አለ አይደል አንዳንዴ የምንሳሳትበት መንገድ አልያም ስህተታችንን የምንሸፍንበት መንገድ አስቂኝም አስተዛዛቢም ይሆናል። እንካችሁ ጨዋታ . . . ሰውየው በመኪና ስርቆት እጅ ከፍንጅ ተይዞ ፍርድ ቤት ይቀርባል። ጉዳዩን የሚከታተሉት የችሎቱ ዳኛ ሰረቀ ወደተባለው ተከሳሽ እየተመለከቱ፣ “በመሆኑ መኪናውን ለመስረቅ ምንድነው ያነሳሳህ?” ብለው የማጣሪያ ጥያቄ ሰነዘሩ። ይሄኔ ተከሳሹ ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “ጌታዬ መኪናው ቆሞ የነበረው መቃብር ቦታ አጠገብ በመሆኑ ባለቤቱ የሞተ መስሎኝ ነው መኪናውን የሰረኩት” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ!

ዘንድሮ ነገራችን ሁሉ እንደባንኩ እና እንደቡኩ እየተለያየ ያስቸግረን ይዟል። በባንኩ ያለው ሂሳባችን ሌላ በቡካችን የተመዘገበው ሂሳባችን ሌላ ሆኖ ሲገኝ ግር ይላል አይደል?. . . አንድ ወዳጃችን ምን ሆነ መሰላችሁ? የሆነች የገቢ አጥሩ ከፍ ባለች ጊዜ ለመጦሪያም ይሁን ለመኖሪያ ይጠቅመኛል በሚል ያገኘውን ገንዘብ ሰብስቦ ወደባንክ ይሄዳል።. . . (ወዳጄ ዘንድሮ እኮ ብር ከማጠራቀም በሰማይ ላይ ዳመና ማጠራቀም ይቀላል። ምን እኮ የዘንድሮ ብር የሚከንፍበት ነገር አብሮት ያለ ይመስል። ሲመጣ እንደኤሊ ሲሄድ እንደ ጥንቸል ሆኖ አስቸገርን እኮ!)

ገንዘቡን ባንክ አስገብቶ፤ የባንክ ደብተሩን እንደአሜሪካ ቪዛ ኪሱ ከቶ ወደቤቱ ይመለሳል። ታዲያላችሁ ውሎ ሲያድር የኑሮ ጥያቄ ይበረታበትና የተሰጠውን የክፍያ ካርድ (ኢ.ቲ.ኤም ካርድ) እያጎረሰ ብሩን ይመዠርጣል። ሰነባብቶ ታዲያ ድንገት የባንክ ደብተሩን (ቡኩን ማለቴ ነው) ከፊት አድርጎ ሲመለከት፤ ከሃያ ስድስት ሺህ ብሩ ጋር ይፋጠጣል። ኧረ ምን አባቱ ፈታ ልበልበት ብሎ ብሩን ለማውጣት የክፍያ ካርዱን ይዞ አስር ሺህ ብር ቢጠይቅ “ማሽኑ” ዝም። . . . ወዳጃችን “ይህቺን ይወዳል፤ ብሬን ተበላሁ” በሚል መንፈስ ብሩን ወዳስገባበት ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ሄዶ አገር ይያዝልኝ አለ።

የባንኩ ሰዎችም ችግሩን አድምጠው፤ ተረጋግቶ እንዲቀመጥ ከጋበዙት በኋላ ተፍ- ተፍ ማለት ጀመሩ። ጥቂት ቆይተው በስሙ የተዘመገቡ ደረሰኞችን ይዘው በመምጣት፣ “ጌታዬ በዚህ በዚህ ቀን በክፍያ ካርድዎ በኩል ይሄን ያህል ገንዘብ አውጥተዋል። አላወጡም?” ወዳጃችን በሚጠቅሱት ቀናት ሁሉ ብር ማውጣቱን ሲያስታውስ እፍረት ተሰማው። ለካንስ በክፍያ ካርዱ “ማሽኑን” ብር ሲጠይቀው ከርሞ፤ ያስቀመጠው ገንዘብ ተመናምኖ ኖሯል። እናላችሁ ወዳጃችን ገና ሲያስገባ የነበረውን የብር መጠን ከቡኩ ላይ ተመለከተ እንጂ ያወጣውን ገንዘብ ዘንግቶት ነበር። ይሄኔ ነው እንግዲህ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ማለት”። በባንኩ ያስቀመጠው ብር ሌላ፤ በቡኩ የቀረው ብር ሌላ ሆነ ማለትም አይደል?. . . (አስቡት እስቲ በኪሳችሁ ያለው አስር ብር ሆኖ የቆጠረው “ቢል” ሰባ ብር ቢሆን ምን ይውጣችኋል?)

እንደው ግን የብር ነገር ከተነሳ አይቀር ብርርር አድርጎ ጨረሰን እኮ፤. . . ይባስ ብሎ ደግሞ ባለቅኔው እንዳለው ብር ወዳድ እየሆን አጎዛ ሸጠን ለምድ የምናመጣ ከንቱዎች እየበዛን ከመጣን ሰንበትበት ብለናል። አንዳንዴ ሳስበው ያለን ዕውቀትና የያዝነው ዲግሪ፤ የነበረን ተሳትፎና የተሰጠን የምስክር ወረቀት፤ የሚከፈለን ደሞዝ እና የምንሰራው ስራ፤ ያለን ስልጣንና የምንወስነው ውሳኔ አልመጣጠን ሲሉኝ ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? የባንኩ ሌላ የቡኩ ሌላ አይነት ነገር ነው። . . . እናላችሁ ለራሳችን እያተረፍን መስሎን ከሌሎች እናጎላለን፤ ለራሳችን እየሞላን መስሎን የሌሎችን እያፈሰስን ነው። በሆዳችን የያዝነው ቂም፣ በቀል፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል ሲሆን በፊታችን ላይ የሚታየው ደግሞ በአስመሳይነት የተሞላ ቅንነት፣ ደስተኛና መልካምነት ነው። ይሄ ታዲያ የባንኩ ሌላ የቡኩ ሌላ የምንለውን ጉዳይ አያሳየንም ብላችሁ ነው?. . . የባለቅኔውን ትዝብት እንካችሁ፡-

 

ትልቁን አጎዛ ሸጠችው ለብር፣

ትንሽ ለምድ አመጣች የሚቆረቁር።

እናላችሁ በባካችን ተቀማጭ ሂሳብ እና በቡካችን “ቁጥር” መካከል ያለውን ልዩነት ማስታወስ አልያም ማስተካከሉን ከዘነጋን ትርፉ ትዝብት ላይ መውደቅ ነው። የታሪክም ክፍተት እንዲሁ ነው። በመካከል ላይ ያሉ ታሪኮችን በማወቅ ወይም ባለማወቅ የረሳን እንደሆን፤ ጎዶሏችንን ፍለጋ አደባባይ መወጣታችን አይቀርም። ለማንኛውም በባንኩ እና የቡኩ አቅም ይመጣጠን ዘንድ በክፍያ ካርድ (ኢ-ቲ-ኤም የምናወጣውም ይመዝገብልን።) . . . አንድዬ ብቻ የባንኩን፤ የስራችንንና የደሞዛችንን፤ የስልጣናችንን እና የውሳኔያችንን፤ የዕቅዳችንን እና የውጤታችንን ልክ እና የቡኩን የምናመጣጥንበትና የምናስታውስበት ህሊና ይስጠን አቦ. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
263 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 926 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us