እንደተበላ ዕቁብ. . .

Wednesday, 14 June 2017 12:52

 

እስከዛሬ ድረስ ዳፋ ነበረች

ኧረ ለምን አሁን ጠብ አዝላ መጣች?

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንዴት ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . ሳምንቱ እንዴት አለፈ?. . . እህሳ የብሔራዊ ቡድናችንን ነገር እና የጋናውያንን ግርግር እንዴት አያችሁት? በሞራላችን ላይ ሲረማመዱብን “ኧረ ተው እንከባበር!” የሚል ልባም ቡድን ስናጣ አናሳዝንም? ድክመት ያለበት ሽንፈት አያጣውም፤ “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” እንደማለት ነው። የምር ግን የአምስት ለዜሮ ሽንፈት ለጆሮም ለታሪክም ደስ አይልም።

በየጊዜው ለሽንፈታችን “የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” አይነት አይረቤ ምክንያቶችን ከመደርደር መወጣት ካልቻልን ትዝብት ላይ ይጥለናል። ስሙኝማ ከሰሞኑ አንድ በእግር ኳስ ያበደ ተመልካች ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? “ለኛ እኮ የተፈቀደው በአፍሪካ ዋንጫን መሳተፍ ሳይሆን ማሰፍሰፍ ነው” ብሎላችኋል። የምር ግን በሆነው ባልሆነው እየደነገጥንና እየፈራረጥን ለምክንያት ድርደራ የምንተጋ ከሆነ ምን አለበት ለትንሽ ጊዜ እንኳን በራችንን ዘግተን የቤት ስራችንን ብንሰራ። አለበዛ’ኮ “ምን ያለበት” እየተባለኝ የማንም የጎል ጎተራ ሆነን መቅረታችን ነው።

ሰውዬው የሬስቶራንቱ ቋሚ ደንበኛ ነው። ድንገት ታዲያ ምሳውን ለመብላት ሲገባ የሬስቶራንቱ ወንበሮች በሙሉ በጥንዶች ተሞልቶ ይመለከታል። (እንዲህ ናትና አገራችን በፍቅረኞች ቁጥር ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ አይነት ውጤት አመጣች እንዴ?ቂቂቂ!) በሚል የቁጭት መንፈስ ተነሳስቶ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው? በሬስቶራንቱ መካከል እንደቆመ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ከኪሱ በማውጣት ደወለ። ድምፁንም ከፍ አድርጎ፣ “ወዳጄ አንተ እዛ አገር አማን ብለህ ልጅህን ታጫውታለህ ሚስትህ እዚህ በልጃገረድ “ሙድ” አለሟን እየቀጨችልህ ነው። . . . አዎ ቶሎና በሬስቶራንቱ ውስጥ ከሆነ ሰው ጋር ምሳ እየበላችልህ ነው” ከማለቱ አምስት ሴቶች በጥድፊያ ሬስቶራንቱን ለቀው ሲወጡ ተመለከተ። (አያችሁልኝ እንግዲህ ሰውዬው በፈጠረው የሀሰት ውጅንብር ተደናግጠው አምስት ባለትዳር ሴቶች ሬስቶራንቱን ጥለው እብስ አሉ ማለት አይደለም? ታዲያ እንዲህ አይነቱን “እንትን ያለበት ዝላይ አይችልም” ልንለው አይገባም?)

እናላችሁ የሆነ ማምለጫ መንገድ ካላዘጋጀን በስተቀር በብዙ ነገራችን ድንገት የምንደነግጥ ከሆነ ለዝላይም አንሆንም። አሠራራችንን ካላሻሻልን፣ አሠለጣጠናችንን ካላስተካከልን፣ አመራረጣችንን በብልሃት የተሞላ ካላደረግን፣ ውሳኔያችንን በተግባር ካላሳየን አለ አይደል ውድድሩ ሁሉ እንደተባለ ዕቁብ አይነት እየሆነ ተረስተን መቅረታችን ነው።

የምር ግን ቀድሞ እንደተበላ ዕቁብ ጣል-ጣል የምንደረግበት ሁኔታ እኮ የበዛ አይመስላችሁም?. . . በዚህ ሲሉን በዚያ፤ እንዲህ ሲሉን እንዲያ፤ እንኩ ሲሉን እንኪያ፤ አንድ ሲሉን ሁለት እየመለስን የተሻለ ዕቅድ የምናዘጋጅበት ጊዜ በጣም ይናፍቃል። የሰሞኑ የብሔራዊ ቡድናችን ውጤት መነሻ ሆነን እንጂ በተለያዩ መስኮች ውጤታችን ቀድሞ የሚታወቅና እንደተባለ ዕቁብ ጣል-ጣል እየተደረገ ከሆነ ሰነባብቷል። . . . አለ አይደል ደግሞ የሆነ ስህተት ሲሰራ፤ አላግባብ መሳነፍ ሲመጣ፤ ህመማችን ሌላ መድሃኒቱ ሌላ ሲሆንብኝ፤ ለአቀማመጥ የማይመች ወንበር ሲሰጠን፣ ለአፍ የማይጥም ምግብ ስንበላ፣ ለአይን የማይመች ምስል ስንመለከት፣ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ወሬ ስናደምጥ ደስ አይልም።

ታዲያ ኧረ ይሄ ነገር ችግር አለበት ይስተካከል፤ ትክክል አይደለም ምናምን ብላችሁ በቀናነት የተሞላ አስተያየት ስትሰጡ ምን ትላላችሁ መሰላችሁ? “ባክህ አታካብድ ይስተካከል” ኧረ ትዝብት ነው። (እንኳን እዚህ እኛ ሰፈር ይቅርና እላይ አካባቢስ ያሉት “አለቆቻችን” ሂሳቸውን ውጠው አይደል እንዴ ውስኪ የሚጠጡት ጎበዝ ቂ-ቂ-ቂ) እናላችሁ ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ብናካብድም ያምርብናል ያልሆነ ነገር እየተሰራ እንደዜግነታችን በተሰጠን መብት ስንናገር “ኧረ አታካብድ” እያላችሁ ነገሬን ለማቅለል የምትሞክሩ ሰዎች ትዝብት ነው ትርፉ። እናላችሁ በእግር ኳሳችን ጉዳይ ላይ በቁጭት የተሞላ አስተያየት ስንሰጥ፤ “አንድ ቀን እንኳን ኳስ ነክቶ የማያውቅ ሰው እንዴት አስተያየት ይሰጣል?” አይነት የማሸማቀቂያ ነገር አያስፈልግም። እስከመቼ ድረስ የኛ ውጤት እንደተባለ ዕቁብ ጣል -ጣል ተደርጎ ይዘለቃል?

እናላችሁ የተለጠጠ ዕቅድና የተኮማተረ ውጤት በጣም እንደሰለቸን ይታወቅልን። ካልሆነ ደግሞ ሪፖርቶች ሁሉ በሁለት ተከፍለው ይቅረቡልን። ምንና ምን ተብለው ካላችሁ? “የፉጌ” እና “የፍጌ”. . . “የፉጌ ሪፖርት” የሚባለው በውሸት የተሞላ፣ ውጤት አልባ የሆነና ለፉገራ የቀረበ የሪፖርት አይነት ሲሆን፤ “የፍጌ ሪፖርት” የሚባለው ደግሞ ስውር- ቃሉ እንደሚያመለክተው የተፈጋበት፣ የተለፋበት፣ የተሰራበትን የዕቅድ አፈፃፀም በግልፅ የሚያሳየው የሪፖርት አይነት ማለት ነው።

እናላችሁ “በስም የተጣበቀ ጥርስ ቢስቁበት አያደምቅ፣ ቢበሉበት አያደቅ” እንዲሉ ችግራችንን ከመሰረቱ አጥርተንና ተነጋግረን እየሰራን መሄድ እንጂ በሰም እያጣበቅን፤ በቀለም እያደመቅን ብቻ አንዘልቀውም። የኛ ነገር እኮ እንደተባላ ዕቁብ ጣል- ጣል ብቻ ሳይሆን ቀድሞ የሚታወቅ ከሆነ ሰነባብቷል። ገና -ለገና የአንድ ፕሮጀክት ዕቅድ ሲወጣ ማን እንደሚበላው ይታወቃል። ገና ፈተና ሲወጣ ማን እንደሚያልፍ ይታወቃል። ገና ምርጫው ሲጀምር ማን እንደሚያሸንፍ በግልፅ ከታወቀ በቃ እኮ የኛ ነገር “እንደተበላ ዕቁብ” ሆኗል ማለት ነውጎበዝ!?. . .

የሪፖርት ነገር ካነሳን አይቀር የመሰነባበቻ ጨዋታችንን እነሆ፡- ሰውየው የድርጅቱ የገቢ ሁኔታ ሊያስመዘግብ ይፈልግና፣ “ከመካከላችሁ ሁለት አይነት የገቢ ማሳወቂያ መዝገቦችን ማዘጋጀት የሚችል ሰው አለ?” ሲል አዲስ ከተመዘገቡት ሰራተኞች መካከል በቋሚነት ለመስራት የፈለገ አንድ ወጣት ፈጠን ብሎ፤ “ጌታዬ እኔ ሶስት አይነት መዝገቦችን ማዘጋጀት እችላለሁ” በማለት ተናገረ። ኃላፊው ተገርሞ “እንዴት ነው ሶስት አይነት የምታዘጋጀው?” ከማለቱ ወጣቱ ቀልጠፍጠፍ ብሎ ማስረዳት ጀመረ። “የመጀመሪያው የገቢ ማሳወቂያ መዝገብ ከድርጅቱ ስር ለማይጠፉ ባለአክስዮኖች የሚዘጋጅ ነው። ይህ ምንም ውሸት የሌለበት መዝገብ ይሆናል። ሁለተኛው መዝገብ ደግሞ ድርጅቱ አካባቢ ደርሶ ለማያውቅ ባለአክስዮን የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ይህ ዝቅተኛ ትርፍ የሚሰፍርበት ይሆናል። ሶስተኛው መዝገብ ደግሞ ለግብር ሰብሳቢና ተቆጣጣሪው መ/ቤት የሚዘጋጅና በእርግጠኝነት ኪሳራን የሚያሳይ ይሆናል ብሎላችሁ እርፍ። እንዲህ ነው እንግዲህ የፉጌ እና የፍጌ ሪፖርት ማለት። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
267 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 919 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us