በጎደለ ሙላ. . .!

Wednesday, 21 June 2017 14:06

 

የማታውቂበትን አጠባ ወርደሽ፣

ህዝቡ ተደነቀ ባጠማዘዝሽ።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ይኸው ደግሞ ዘራፊው የበዛበት የዓመት በጀታችን ከነጎደሎው ፀደቀም አይደል? (ይህን የበጀት ነገር ሁሌ በየዓመቱ ከነጉድለቱ መፅደቅ ያስተዋለ አንድ ወዳጄ ምን ሲል ሰማሁት መሰላችሁ?. . . “የኛ በጀት እኮ በጎደለ ሙላ አይነት የክፍል ፈተና ይመስለኛል” ብሎላችሁ እርፍ) የምር ግን እንዲህ ከብድርም ከእርዳታም ከሚስኪኑ ተቀጣሪ የግብር ከፋይም ሰብስበን ከምናሟላው ዓመታዊ በጀት ላይ ወደ 54 ቢሊዮን ብር የሚጠጋው “ጉድለት አሳይቷል” ሲባል አይደብርም?

ኧረ ተው እንተዛዘን በፀሐይም በጨረቃም እንደው በስም እየተደበቃችሁ አትዝረፉን ተው. . . “መልክ ጥፉን በስም ይደግፉ” የሚሉት የአገራችን አባባል እኮ ያለ ነገር አልተጠቀሰም። የምር- የምር እንነጋገር ከተባለ ስም ያላቸው ዩኒቨርስቲዎች፣ ስም ያላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ስም ያላቸው ኃላፊዎች የህዝቡን ልብ ቀጥ የሚያድርግ ብር እያጎደሉ “አይኔን ግንባር ያድርገው” አይነት ከንቱ መከራከሪያ እያሰሙን እስከመቼ ይዘልቃሉ?. . . (ለነገሩማ የመጠርጠር መብታችንን ተጠቅመን እንጠረጥራለን “ጠርጥር ከገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር” እንዲሉ ነው እንግዲህ. . . የምር ግን እነዚህ በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ብሮችን “እያጎደሉ” ዝም የሚባሉ መስሪያ ቤቶችና ኃላፊዎቻቸውን ሳስብ ምን የሚለው የአገራችን ተረት ትዝ ይለኛል መሰላችሁ? “ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች” እውነቴን እኮ ነው ቂ-ቂ-ቂ!)

እናላችሁ አንዳንዶቹማ የተመደበላቸውን በጀት ከሕግና ከሥርዓት ውጪ በመመዥረጥና ሂሳብ በማጉደል ደንበኛ ሆነው ስንታዘባቸው እውነትም እነዚህ አካላት “ጌቶችን ተማምነው ነው” ማለታችን አልቀረም። እንደው ለእምነቱና ለማዕተቡ መኖር ቢያቅት ለደንቡና ለመመሪያው መገዛት እንዴት ያቅታል ጎበዝ?. . . የስርቆት ነገር ከተነሳ አይቀር የምትከተለዋን ታዋቂ ጨዋታ እንካችሁማ፤ ሰውዬው በተደጋጋሚ በስርቆት ተይዞ ችሎት እየቀረበ ይቀጣል። እናም ለስምንተኛ ጊዜ ከእስር ሲፈታ አሁንም እንደለመደው ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ ይያዝና ያለፈው ጊዜ የቀረበበት ችሎት ይቀርባል። ዳኛው በሰውዬው ሁኔታ ተገርመው፣ “አንተ ሰው በተመሳሳይ ወንጀል እዚህ ችሎት ስትቀርብ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው አይደል?” ይሉታል። ሰውዬው አይኑን አፍጦ በአዎንታ ይመልሳል። “እንግዲህ በተደጋጋሚ ብትታሰርም ልትማር ስላልቻልክ ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣልብህ ወስነናል። ለመሆኑ የቅጣት ማቅለያ አለህ?” ብለው ከመጠየቃቸው በዝርፊያ የተለመደው ሌባ ምን ቢል ጥሩ ነው፣ “ክቡር ፍርድ ቤት እንደሚታወቀው በሀገራችን ደንበኛ ንጉስ ነው። እኔ ደግሞ ለዚህ ችሎት የደንበኛ ያህል ነኝና እንግዲህ ቢቻል በነፃ ካልተቻለ ደግሞ የእስር ጊዜዬን እንዲቀንስልኝ ስል በማክበር እጠይቃለሁ” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ!

እናላችሁ በጉደለ ሙላ ከሆነች ዓመታዊ በጀት ላይ በየዓመቱ የኦዲት ሪፖርት ላይ ጉድለት የሚያስመዘግቡ ተቋማትና ኃላፊዎቻቸው አንድ ሊባሉ ይገባቸዋል። አለበለዚያ ግን ራሳቸውን እንደደንበኛ እየቆጠሩ ጨጓራችንን ልጠው ይጨርሱታል። እድገትና ስኬት ይመጣ ዘንድ መልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን መልካም ስነ-ምግባርም እንደሚያስፈልግ የሥነ-መንግስት ምሁራን በበርካታ ንድፈ-ሃሳቦች ያስረዳሉ። ጎበዝ ይግባን እንጂ ሰው ይታዘበኛል፤ ህዝብም ይቆጣብኛል አይባልም እንዴ? ዝም ተብሎ “ይሄን ያህል ሚሊዮን ብር” ጉድለት ተገኝቶበታል ብቻ ተባብለን ወደሚቀጥለው ዓመት ስንሸጋገር በጣም ነው የሚደብረው።

ሰው እኮ በእንቅልፍ ቀርቶ በእውኑ እንዲቃዥ እየተገደደ ነው። ሁለት ጓደኛሞች ናቸው። ጠዋት ላይ ስራ ቦታ ይገናኙና አንደኛው፣ “ስማ ሚስቴ እኮ ሌሊት ስትቃዥ ቀሰቀስኳት፤ ከዚያም ምንድነው የሚያቃዥሽ? ስላት አንድ ሚሊየነር ላግባሽ ሲለኝ አይቼ ነው አለችኝ” ይለዋል። ይሄን ጊዜ ሌላኛው ጓደኛ ምን ቢል ጥሩ ነው፤ “ወንድሜ አንተ እድለኛ ነህ፤ ሚስትህ በእንቅልፍ ልቧ ነው እንዲህ የምትቃዠው የኔዋ እኮ ገና ሳትተኛ ነው እንዲህ አይነቱን ቅዠት የምትጀምረው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ-

እናላችሁ ምን ለማለት ፈልጌ ነው እኛ እድሜ ልካችንን ጥረን ግረን ያላገኘነውን “ሚሊዮን” የሚባል ብር እናንተ በአንድ ቀን እየሰራችሁ “እንትናዬዎቻችንን” ገና ሳይተኙ ቅዠት ውስጥ ጥላችሁብናል።. . .  ግድ የላችሁም ህሊናችን ይስራ፣ መማራችን ይስራ፣ ይሉኝታችን ይስራ እነዚህ አልሰራም ካሉ ደግሞ ፖሊስ ይስራ፣ ፀረ-ሙስና ይስራ፣ ዐቃቤ ህግ ይስራ እና ችሎት አቅርቦ ተከሰው ሲፈርድባቸው እንይ እንጂ ጎበዝ! ይሄን ጉዳይ በተመለከተ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሳይቀር እኮ “ስራችንን በአግባቡ እየሰራን አይደለም” ማለታቸውን በጋዜጣ አንብበናል። እናም እንደምንም ብለን ከምናሟላት በጀት ላይ “የሂሳብ ጉድለት እያሳዩ” ከዓመት ዓመት መዝለቅ እንደማይቻል የሚያሳየን አካል ይምጣልን አቦ!

አለበለዚያማ በየዓመቱ “በጎደለ -ሙላ” ተብሎ ከሚፀድቅ በጀታችን ላይ አንድ ነጥብ ምናምን ሚሊዮን ብር እገሌ የተባለ ድርጅት “ጉድለት አሳይቷል” ምናምን እየተባባልን ብቻ እስከመቼ እንተላለፍ?. . . አለበለዚያ ግን ሳንወድ በግድ “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች” እያልን በጅምላ ሃሜት ውስጥ መገኘታችን አይቀሬ ነው።. . . እስቲ ደግሞ ከጉድለት የፀዳ ሪፖርት የምንሰማበትን ዓመት ያምጣልን አቦ!. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
249 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 927 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us