ለደግነት ጊዜ ቢኖረን

Wednesday, 28 June 2017 11:55

 

አይደለም (የዘወትር ምጤ)

አይደለም ለክብረት ለነዋይ ተዳምሮ

አይደለም ለሹመት ለተጫፍሮ ኑሮ

አይደለም ለዝና ለጠፊ ውሎ አድሮ…

ለትሁት ህይወት ነው፣ እኔ መሯሯጤ

በዘልማድ መንገድ ጉዞ አለመምረጤ፤

ደቂቀ ብርሃንን

ውበት ፍቅር- እውነትን

ለመገላገል ነው፣ የዘወትር ምጤ።

ይኸው ነው መስቀሌ

ይኸው ነው አክሊሌ

ይኸው ነው ድክመቴ

ይኸው ነው ብርታቴ።

(ከደበበ ሰይፉ፤ለራስ የተፃፈ ደብዳቤየተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... ምናለበት እንደው እንዲህ፤ እንደባለቅኔው የዘወትር ምጣችን እውነትን ተናግሮ የመሸበት ለማደር ቢሆን ብዬ አስባለሁ።… የምር ዘመኑን ታዝባችሁልኝ ከሆነ ለተንኰል፣ ለራስ ምቾት፣ ለጥፋትና ለከበርቻቻ የሚሆን ጊዜም ገንዘብም የተትረፈረፈው መብዛቱን ያሳየናል። በአንፃሩ ደግሞ ለመልካም ነገር፣ ለወዳጅነትና ለቅንነት የሚሆን ጊዜም ገንዘብም ሲጠፋን በእጅጉ ያሳዝናል። … የምሬን እኮ ነው ምናለበት ለሴራ ያለንን ጊዜ ያህል ለስራ ቢኖረን? ለነገር ያለንን ጊዜ ያህል ለመመካከር ቢኖረን? ለማጉደል ያለንን ጊዜ ያህል ለመሙላት ቢኖረን እስቲ ምን ነበረበት?

 

ሰውዬው በአንድ የሥነ-መለኮት ኮሌጅ ውስጥ ተማሪ ነው። የዓመቱ መጨረሻ ሲደርስ መምህሩ በክፍል ውስጥ ላሉት ተማሪዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ባዶ ወረቀት በመስጠት የሚከተለውን ጥያቄ በሰሌዳ ላይ ይፅፋሉ። ጥያቄው “በ30 ደቂቃ ውስጥ የፈጣሪን እና የሰይጣንን ባህሪያቶች በዝርዝር ፃፉ” የሚል ነበር። … ተማሪው የቀረበለትን ጥያቄ በሚገባ ተገንዝቦ መልሱን መፃፍ ጀመረ። “አምላክ ፍቅር ነው።… አምላክ መሀሪ ነው።… አምላክ ቸር ነው።… አምላክ አዳኝ ነው….” ወዘተ በማለት በትጋት ስለፈጣሪ ብቻ ሲዘረዝር የተሰጠው 30 ደቂቃ አበቃ። በዚህ ጊዜ ስለሰይጣን እንዲፅፍበት የተሰጠውን ባዶ ወረቀት አነሳና በትልቁ ምን ቢፅፉበት ጥሩ ነው? “ለሰይጣን ጊዜ የለኝም” ብሎላችሁ እርፍ! ይሞታል እንዴ?

 

የምር ግን እንዲህ ለመልካሙ ነገር፣ ለሚበጀው ነገር፣ ለሚጠቅመን ነገር፣ ለፍቅርና ለምክር፣ ለትብብርና ለአንድነት የሚሆን ጊዜ ቢኖረን ምን ነበረበት?... ግርም የሚለው እኮ ለፀሎት ጊዜ የሌለው ሰው ለሀሜት ከየት እንደሚያመጣው ነው። ለስራ ጊዜ የሌለው ሰው ለስወራ (ለስሪያ አላልኩም ደግሞ) ጊዜ እንዴት እንደሚያገኝ ነው። ለማስታረቅ ጊዜ የሌለው ሰው ዘሎ ለማነቅ ብርታትን ከየት እንደሚያመጣው ይገርማል። ለመማር ጊዜ ያልነበረው ሁሉ ስራ ለማባረር ጊዜ ሲተርፈው፤ ነገሩን ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ያስብልበታል። ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ለመኮትኮት፣ ለማጨድና ለመውቃት ጊዜ የሌለው ሰው ሁሉ ለመብላት ጊዜው በሽ ነው። (“ለወቀጣው ጊዜ ማንም ሰው ሳይመጣ፤ ለእንብላ ለእንጠጣ ከያለበት መጣ እንደማለት መሆኑ ነው።)

 

እናላችሁ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየቢሮውና በየኃላፊው ጠረጴዛ ላይ በርካታ ጉዳዮች ተደርድረው በቅንነትና በኃላፊነት ካለመስራት ብቻ የሚንገላቱ ዜጐች ብዙ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል።… አንዳንድ ኃላፊዎችና መስሪያ ቤቶች እኮ ለስራ ጊዜ የላቸውም እንዴ? ብላችሁ እንድትጠይቁ የሚያስገድዷችሁ ናቸው። “ህዝቡን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል” ባዩ ሁላ፤ “የመልካም አስተዳደር ሳንካዎችን እንሰባብራለን” ሲል በየስብሰባው የሚፎክረው ሁላ፤ “መቶ በመቶ ችግር ፈቺ ሀሳቦችን እንተገብራለን” ባዩ ሁሉ፤ “በጥልቀት ታድሰናል” የተባለው ሁሉ፤ “በአዲስ መልክ ስራ ጀምረናል” ባዩ ሁላ ከመድረክ እንደወረደ ወደ ስራ ከመሄድ ይልቅ ውጥንቅጥ ወደበዛበት አላስፈላጊ ቢሮክራሱ እየተመለሱ ስንቶቻችን ተቸግረናል መሰላችሁ። (እንዲህ አይነቶቹን ነው እንግዲህ የሀገራችን ሰው “ታጥቦ ጭቃ” የሚላቸው። ቂ.. ቂ.. ቂ..) ለክፉ ነገር የተትረፈረፈ ጊዜያችንን ግማሹን እንኳን ለበጎ ብንጠቀምበት የዚህች ሀገር እድገት አይደለም አስራ አንድ በመቶ ሃያ አንድም መድረስ በቻለ ነበር።

 

እስቲ ደግሞ ለዛሬ ከመሰነባበታችን በፊት የወዳጃችንን ሙላህ ነስረዲንን “ታኮ” መሆን የምትችል ወግ እነሆ። … ሙላህ ነስረዲን በሚኖርበት ሀገር ፈላጭ፤ ቆራጭ የነበረው ንጉስ ወደቤተ መንግስቱ ያስጠራውና፣ “ለመሆኑ እኔ ስሞት ገነት ነው ገሃነም የምገባው?” ሲል ቀጥተኛ ጥያቄ ያቀርብለታል። ሙላህም ምንም ሳያንገራግር “የምትገባው ገሀነም መሆኑ አያጠራጥርም” ሲል ይመልሳል። በሙላህ መልስ በእጅጉ የተናደደው ንጉስም፣ “ለመሆኑ ገሃነም እንደምገባ እንዴት እርግጠኛ መሆን ቻልክ?” ሲል ይጠይቀዋል። “አየህ ንጉስ ሆይ! አንተ ለአመታት ባልሰሩት ወንጀልና ሀጢያት በግፍ አሰቃይተህ የገደልካቸው ሰዎች ሁሉ ገነትን በማጨናነቃቸው ገነት ሙሉ ነው። ነገር ግን አትስጋ በገሃነም የክብር ቦታን አዘጋጅተውልሃል” ሲል መለሰለት ይባላላ። …. እናም ምን ለማለት ነው። ለምድሩ እንኳን ባይሆን ለሰማዩ ሲባል። ለመልካም ነገር ጊዜያችንን ሰጥተን ብንሰራ ምን አለበት? እስቲ እንደው ለደግነት እንጂ ለክፋት፤ ለመልካምነት እንጂ ለጥፋት ጊዜ የለንም የምንል ያደረገን አቦ!... የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤልን አንጋፋ ስንኞች እዚህ’ጋ ማስታወሱ አይከፋም።

 

ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም።

 

ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
272 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 918 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us