“ፀሐይ ወይስ ጨረቃ?”

Wednesday, 05 July 2017 12:37

 

ከወንዝዋ ዳርቻ ሐመልማልዋ መሃል

በትካዜ ምርኩዝ ባሳብ ተውጠሃል!

ተጠንቀቅ አዚምዋ ያዞርብህና

ዥው አድርጐ ጥሎ ያሰምጥሃልና።

(“መልክአ ዑመር” - ከተስፋዬ ገሠሠ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... እኔ የምለው ምንድነው እሱ ነገራችን ሁሉ ጥድፊያ በዛው እኮ። አለ አይደል እበላለሁ ሲባልም መበላት እንዳለ እየተስተዋለ ቢሆን ምን ነበረበት?... የምሬን እኮ ነው። በተረት እንደተነገረችን የእንስራ ውስጥ እንቁራሪት የሆን ይመስል ሰማዩን ባየነው ልክ ብቻ ባንመዝነው ምን አለበት?... ጥድፊያው ለበጎ ነገር ቢሆን እኮ መልካም ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል እየተሞዳሞድን ሲመስለን፤ የሆነች ቡጬ ያለባት ሲመስለን፤ የሆነ ቤትና መኪና የምናገኝ ሲመስለን አድርጉ የተባልነውን ለምን ብሎ የመጠየቅ ሞራል የሚያንሰን እየበዛን ይመስላል። የአገራችን ሰው ደግሞ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” የሚለው ወዶ እንዳይመስላችሁ።

 

እናላችሁ ለኔ እንጂ ለሌላው ምን አገባኝ፤ ለቤቴ እንጂ ለጐረቤቴ ምን አሳሰበኝ፤ ለአጥሬ እንጂ ስለመንደሬ ምንጨነቀኝ የምንል የምንበዛ ከሆነ ችግሩ “የፈራሁት ነገር መጣ-ድሆ-ድሆ” እንደተባለው አይነት መሆኑ አይቀርም። ሰው ሆነን ከኛ አልፈን ለሌሎችም መትረፍና ማሰብ እስካልቻልን ሙሉ ሰው ሆነናል ለማለት ይከብደኛል። ሰው ሙሉ ሲሆን ደግሞ ከራሱ ባሻገር፣ ከቤቱ ባሻገር፣ ከአጥሩ ባሻገር፣ ከመንደሩ ባሻገር፣ ከክፍለ ከተማው ባሻገር ከከተማው ባሻገር፣ በክልሉ ባሻገር እንዲሁም ከአገሩ ባሻገር ማሰብ ይጀምራል። ያኔ ትልቁንና ዋናውን ነገር ያስተውላል ማለት ነው።

 

አንዳንድ ሰው የደፍ-የደፉን ብቻ እየያ ሲንደፋደፍ ስንትና ስንት ለዓለም የሚበቃ ነገር ያመልጠዋል መሰላችሁ። ዋናውን ነገር ዋና ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሁለት ህፃናት መምህራቸው የሰጣቸውን የቤት ስራ እየተነጋገሩበት ነው። “ለመሆኑ ከፀሐይና ከጨረቃ ማንን ይበልጣል መረጥክ?” ይጠይቃል አንደኛው። “ፀሐይን ነዋ” ይመልሳል ሌላኛው። “አየህ ፀሐይ እኮ ብርሃን ከመስጠት ባለፈ ሙቀት አላት” ከማለቱ ቀዳሚው ጠያቂ ምን ቢል ጥሩ ነው? “ሞኝ አትሁን እኔ የመረጥኩት ጨረቃን ነው። ለምን ቢባል ፀሐይ አውቃ በቀን እየወጣች ነው እንደዚህ የምትደምቀው ጨረቃ ግን እኛ በጨለማ እንዳንደናበር ስትል በሌሊት ታበራልናለች” ሲል መለሰ። ጐበዝ የጨረቃን የብርሃን ምንጭ መመርመሩ አይከፋም። አለበለዚያ ግን “በሬ ሆይ - ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” የሚያስብል አስተዛዛቢ ሀሳብ ማቅረብ በኋላ ጉድ ያደርገናል። ጨረቃ ትደምቅ ዘንድ ፀሐይ አስፈላጊ መሆኗን ማወቅ ያስፈልጋል። እኛ ዛሬ እንዲህ የራሳችን ማንነት እንዲኖረን ትናንት አባቶቻችን በጋራ የከፈሉልን ዋጋ እንዳለ ሊታወቅ ይገባል። ተማሪዎች የተሳካላቸው ዶክተሮች፣ መሃንዲሶች፣ ፓይለቶች፣ መሪዎች ይሆኑ ዘንድ መምህራኖቻቸውና ወላጆቻቸው ብዙ እንደደከሙባቸው ሊታወቅ ይገባል።

 

እናላችሁ አሁን - አሁን በሀገራችን ሁሉ ነገር ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ ውጤቱን እንዳይሆን አድርጐ ያስቀምጥልን ይዟል። ባለቅኔው እንዳለው ጊዜያዊ ውበት፤ ጊዜያዊ ስልጣን፤ ጊዜያዊ ሀብት እያማለለን ዥው አድርጐ ሊጥለን እየተዘጋጀ ነውና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም። እናም ዕቅዳችንንም፣ ማርቀቃችንንም፤ ማፅደቃችንንም፣ ማወጃችንንም ሰከን ባለ መንፈስና በተረጋጋ መንገድ ብናደርገው ምን አለበት?... ሲሆን ትንሽ ተነጋግረን እና ተረዳድተን ነገሩ ገብቶን ቢሆን ጥሩ ነው። አለበለዚያ ግን ነገራችን ሁሉ በጥድፊያ ከቀጠለ “ሲሮጡ የታጠቁት፣ ሲሮጡ ይፈታል” መሆኑ አይቀርም። ለማንኛውም አይጦች በድመቶች የሚዶለትባቸውን ሰምተው ምን አንዳሉ ታስታውሳላችሁ አይደል? “እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል” ነው ያሉት ቂ… ቂ… ቂ!

 

እናላችሁ ምን ለማለት ፈልጌ ነው?... ሰውዬው ድንገት ወደሴትየዋ ቤት ይገባና “ይቅርታ እመቤቴ ፒያኖዎትን ልቃኘው ነው የመጣሁት” ይላል። ሴትዬዋም ተገርመው፣ “ግን እኮ እኔ በፍፁም እንድትቃኝልኝ አልጠራውህም” ከማለታቸው ባለሙያው ምን ቢል ጥሩ ነው? “ትክክል ነዎት እመቤቴ! የጠሩኝ እኮ ስልት በሌለው ሙዚቃ ጆሯችን ደነቆረ ያሉ ጐረቤቶችዎ ናቸው” ብሎላችሁ እርፍ… እንዲህ ነው እንግዲህ ችግራችንን እኛ ማወቅ ሲሳነን ጠቋሚ አያሳጣን ማለት።

 

የኑሯችን ቅኝት መበላሸቱን፣ የአስተዳደራችን ቅኝት መበላሸቱን፣ የኃላፊነት ቅኝቱ መበላሸቱን፣ የፍትህ ቅኝቱ መበላሸቱንና የፖለቲካ ቅኝቱ መበላሸቱን፣ የትዳር ቅኝቱ መበላሸቱን እኛው ማወቅ ከተሳነን አንድዬ ሐኪም የሚጠራ ጐረቤት አያሳጣን አቦ!...

በተረፈ ግን በሆነ-ባልሆነው እየተዋከብን ትኩረታችን ሁሉ ከአንድ ነገር ጋር ከተያያዘ ችግር አለ ማለት ነው። የጋራ ነገራችንን፤ በጋራ እና በመነጋገር እናድርገው እንጂ የምን ችኩል-ችኩል ነው? እናላችሁ አንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ እንዳለው

 

ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፣

ፍቅሬ-ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም።

 

በሉ እንግዲህ የአስተሳሰብ ቅኝታችን ተስተካክሎ፤ የጨረቃ ድምቀት መንስኤ የሆነችውን “ፀሐይ” የምናስተውልበት ልቦና ይስጠን አቦ… ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
233 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1079 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us