ሰጪ እና ተቀባይ

Thursday, 13 July 2017 14:38

 

ሰነፍ አውደልዳዩ ወጥቶ ተጋለጠ

ከስራ መለኪያው እየተጨበጠ።

ሰነፍ ሰው ራቁቱን  ይተኛል

ልብስ ካጣ  ምን ያደርጋል?

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኔ የምለው ክረምቱም እንደገቢዎች ግምት ተቆልሎ መጣብን አይደል? እኛ ይኸው ሰኔ በከንቱ አለፈ ምናምን ብለን ሳንጨርስ ከተማችንን የተቀደደች መርከብ አስመስሏት ቁጭ።. . . ይልቅዬ ፀሐይንም ዝናብንም በሚገባ የምንጠቀምበት ጥበብ አያሳጣን። ባለቅኔው እንዳለው ስንፍናን የሚጠላ ልብ አያሳጣን፤ ያኔ ክረምት ህይወት ይሆንልናል።

ሰውዬው እጅግ ሲበዛ ሰነፍ ነው። የራሱን ምግብ ለማግኘት ሁሌም ቢሆን ሳይሰራና ሳይለፋ እጁን አጣጥፎ እንዲሆንለት ይፈልጋል። ይህ ዓለም ደግሞ እንደሚታወቀው ትንሽም ቢሆን ካልደከሙ ዕድለኛ ካልሆኑ በስተቀር ጠብ የሚል ነገር የለውም። እናም አንድ ቀን የሚበላ ነገር ፍለጋ በመንቀሳቀስ ላይ ሳለ የደረሰ የፍራፍሬ እርሻ ተመለከተ። አካባቢውን ቃኘት -ቃኘት ሲያደርግ ማንም ሰው አልነበረም። ድንገት ወደእርሻው ቅጥር ዘሎ በመግባት ከአንድ ዛፍ ላይ የሚበላውን ፍሬ ለማውረድ በኃይል መነቅነቅ ሲጀምር የእርሻው ባለቤት የሆነው ገበሬ ተመለከተው። በንዴት የተሞላው ገበሬ በእጁ ዱላ ይዞ ወደእርሱ ሲሮጥ የተመለከተው ሰነፉ ሰው እግሬ አውጪኝ ብሎ ተፈተለከ።

ከእርሻው አጥር ባሻገር ወዳለ ጫካ በመግባት ራሱን ከገበሬው ለመደበቅ ፈለገ። ለጥቂት ደቂቃዎችም ድምጹን አጥፍቶ በጫካው ውስጥ ከተደበቀ በኋላ ምንም አይነት ድምጽ አለመኖሩን አስተውሎ ጉዞውን ለመቀጠል ተነሳ። ድንገት ግን ከጫካው በመውጣት ላይ ሳለ ለማመን የሚከብድ ነገር ተመለከተ። አንድ ቀበሮ በመሬቱ ላይ በዝግታ ይጎተታል። ቀበሮው በተፈጥሮው ይሁን በአደጋ (አይታወቅም) ሁለት እግሮች ብቻ ያሉት ነበር። ይህን ሲመለከት ሰነፉ ሰው “ይህ ቀበሮ ሁለት እግር ብቻ እያለው አድኖ መብላትም ሆነ ከጠላቶቹ ማምለጥ ሳይችል፤ እንዴት ብሎ በጫካ ውስጥ በዚህ መልኩ መኖር ቻለ?” ሲል ራሱን ጠየቀ።

ወዲያው ደግሞ ሌላ አስገራሚ ነገር ተመለከተ። በአፉ ሙዳ ስጋ ያንጠለጠለ አንድ አንበሳ ወደቀበሮው መጣ። በጫካው ውስጥ ያሉ ሌሎች እንስሳት ፈርተው ሲፈረጥጡ የተመለከተው ይህ ሰው፤ በድንጋጤ ተውጦ አጠገቡ ካለ ትልቅ ዛፍ ላይ በመውጣት የሚሆነውን ነገር ሁሉ አንድ በአንድ መመልከት ጀመረ። ማምለጥ አቅቶት የሚጎተተው ተኩላ ብቻውን ሲቀር አንበሳው በአፉ የያዘውን ስጋ አጠገቡ አስቀመጠለት። ቀበሮ አንበሳ ያመጣትን ስጋ አጣጥሞ መብላት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሰነፉ ሰው ባየው ነገር ተገርሞ የፈጣሪን ተዓምር አደነቀ። በልቡም “እውር አሞራ መጋቢ አምላክ መኖሩን” እያስታወሰ ፈገግ አለ።

ፈጣሪ እርሱን ተማምነው ለሚጠብቁት ፍጡራን አንዳች መጋቢ ወይም ምግብ እንደሚሰጣቸው፤ ተስፋ ላጡ ተስፋ እንደሚሆናቸው፣ ደስተኛ ላልሆኑ ደስታን እንደሚያላብሳቸው፣ ምግብ ላጡም አጉራሽ እንደሚልክላቸው በፅኑ የተረዳው ሰነፉ ሰው አንድ ነገር ብልጭ አለለት። ፈጣሪ ለእሱም አንዳች መጋቢ/ ምግብ እንዲሁ በተቀመጠበት እንደሚሰጠው አስቦ፤ ከዚያ ጫካ በመውጣት ራቅ ወዳለ አካባቢ ሄደ። ከሚያውቁት ሰዎች እርቆና ተነጥሎ ለሰዓታት ብሎም ለቀናት መንገድ መንገዱን እየተመለከተ የሚመግበውን ሰው ቢጠብቅም ምንም ነገር አላገኘም።

ርሃቡን መቋቋም ሲያቅተው ተነስቶ ወደከተማው መሄድ ጀመረ። በመንገዱም አንድ በዕድሜ የገፉ ብልህ ሰው አገኘ። ባለፉት ቀናት ያጋጠሙትን ነገሮችና ጠብቆ ያጣውን ነገር ሁሉ ለአዛውንቱ አጫወታቸው። አዛውንቱም ከአንድ ትልቅ ዛፍ ስር አስቀምጠው በመጀመሪያ ምግብና ውሃ በመስጠት ከርሃቡ እንዲያገግም አደረጉት። ምግቡን በልቶና ውሃውን ጠጥቶ ሲያበቃ አዛውንቱን ካመሰገነ በኋላ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው። “እኔ የምለው አባቴ!. . . ፈጣሪ ያንን ምስኪን ሁለት እግር ብቻ ያለውን ቀበሮ በአንበሳ በኩል ሲቀለብ አሳይቶኝ ምነው እኔ ፍጡሩን እንዲህ ጨከነብኝ?” ጥያቄውን በፅሞና ያደመጡት ብልሁ አዛውንትም “እውነት ነው አንተ እንዳልከው ፈጣሪ ለሁሉም ፍጡራን የራሱ ዓላማ አለው። አንተም ፈጣሪ ተዓምሩን ከሚገልፅባቸው ሰዎች አንዱ ነህ። ለዛም ነው የምስኪኑን ቀበሮ እና የለጋሱን አንበሳ ታሪክ በአይንህ እንድትመለከት የተደረገው። ነገር ግን ልጄ አንተ ፈጣሪ ያሳየህን ምልክት በተሳሳተ መንገድ ተርጉመሀዋል። ፈጣሪ አንተ እንደቀበሮው ሳይሆን እንደአንበሳው እንድትሆን ነው የሚፈልገው።፡ ሰጪ እንድትሆን እንጂ ተቀባይ እንድትሆን አይደለም። ብርቱ እንድትሆን እንጂ ሰነፍ እንድትሆን አይደለም። አንተ ደካሞችን የምትረዳ እንድትሆን እንጂ የምትረዳ እንድትሆን ፈጣሪ አላማው አይደለም” አሉት።

እናላችሁ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ላይ ብናተኩር፤ ከማስጨነቅ ይልቅ ማሳቅ ላይ ብናተኩር፤ ከመበደል ይልቅ የበደሉንን ይቅር ማለት ላይ ብናተኩር፤ ከስንፍና ይልቅ ብርታት ላይ ብናተኩር፣ ከዝምድና ይልቅ በሃቅ፣ ከመተዋወቅ ይልቅ በዕውቀት ስራችንን መስራት ብንችል ከእኛም አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ በረከትና አቅም ስላለን እርሱን ብንጠቀምበት ምን ይለናል?. . . እኔ የምለው በታማኝነት፣ በቅንነትና በቅልጥፍና እናገለግላለን ምናምን የሚባለው ነገር በማስታወቂያና በመፈክር ላይ ብቻ የቀረ ነገር ሆነ ማለት ነው?. . . ለማንኛውም ጫናው ከከበደብን ግብርና ዝናብ አንድዬ የማናልፍበትን ብርታት አይንፈገን አቦ! ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
211 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 877 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us