መጠበቅ እና ማስጠበቅ

Wednesday, 19 July 2017 13:21

 

በአረንጓዴው መብራት ሄዱ ገሰገሱ፣

በቢጫውም መብራት ስንቶች የት ደረሱ?

ታሳዝነኛለች አንዲት አገርማ

በቀዩ መብራት ላይ የቀረችው ቆማ።

     (“ፅሞና እና ጩኸት” ከተሰኘው የሰለሞን ሞገስ የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እህሳ የአርባ ስልሳው እና የቀን ገቢ ግምቱ ነገር እንዴት አክርሟችኋል?. . . እኛ እንደው ኑሯችን ሁሉ ቀይ መብራት ላይ እንደተገተረ መኪና ቆሞ የቀረ መስሏል። አስራ አንድ በመቶ ዕድገት የለ፤ የኑሮ መሻሻል የለ፤ ነገሩ እንዴት ነው ብለን ብንጠይቅ መልስ የሚሰጠን ሰው የለ።. . .የምር ግን ከልባችን አዝነንለት በምን በኩል እንርዳው፤ ምስኪን ሰው እኮ ነው ያልነው ሁሉ እኛን እያዘናጋ በአረንጓዴ ዘመድና ስልጣን በኩል አይናችን እያየ ሲተኮስ መመልከቱ ምን ይሉታል? . . . እኛ ለዘይትና ለስኳር በራሽን ካርድ ስንጋፋ “ምስኪን ሰው ነው” ያልነው የ40/60 ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ሲመጣ ትዝብት ነው ትርፉ ከማለት ውጪ ምን ይባላል?. . . አንድዬ ብቻ የበይ ተመልካች ከመሆን ያድነን አቦ።

አንዲት የድሮ ተረት እዚህች’ጋ ትታወሳለች።. . . አንበሳ ሆዬ እድሜው ገፍቶ፤ ጉልበቱ ደክሞ እንደልቡ ተሯሩጦ አድኖ መብላት የሚሳነው ደረጃ ይደርሳል። መቼም እርጅና ቢኖርም ሆድ አይቀርምና የሚበላውን አድኖ የማግኘት አቅሙ ቢያንስበትም መላ መዘየዱን ግን አላጣውም። አሞኛል በሚል ሰበብ በዋሻው ውስጥ ተኝቶ እርሱን ለመጠየቅ የሚመጡትን እንስሳት ለመብላት አስቦ፤ መታመሙን ያውጃል።

“ታሟል” መባሉን ሰምተው አንበሳን ለመጠየቅ በየዋህነት ወደዋሻው የገቡት እንደአጋዘን፣ ተኩላ፣ ሚዳቆ፣ የሜዳ አህያ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔና የመሣሠሉት የዱር እንስሳት ከገቡበት ሳይመለሱ ይቀራል። ይህን ሁኔታ በሚገባ ያስተዋለችው ጦጢት ግን አንበሳን ከመጠየቅ ወደኋላ አላለችም። ነገር ግን የጥየቃ ዘዴዋን ለውጥ በማድረግ ከዋሻው በር ላይ በመቀመጥ “አያ አንበሶ ጤንነት እንዴት ነው፤ ተሻለህ?” ስትል ጠየቀችው። ጠርጣሪነት ግራ አጋብቶት፣ “ምን ጤነኝነት አለ ብለሽ ነው፤ ኧረ እንደውም ከትላንቱ ዛሬ ብሶብኛል። ምነው ግን ከበሩ ገባ ብለሽ በደንብ አትጠይቂኝም እሳ!?” ይላታል።

ይህን ጊዜ ጦጢትም፣ “የለም አያ አንበሶ አንተን ለመጠየቅ ወደዋሻው የገቡት እንስሳት ዱካዎች ሁሉ ሲገቡ እንጂ ሲወጡ አልተመለከትኩም። እናም እኔም ገብቼ ከመብላት ይልቅ አልጠየቀችኝም እንዳትል ይኸው መጥቻለሁ። ለመሆኑ “እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል” የሚሉትን ተረት ታውቀዋለህ?” ስትል የአንበሳን ወጥመድ እንደነቃችበት ነገረችው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሌሎች እንስሳት ወደአንበሳ ዋሻ እንዳይገቡና እንዳይጠይቁት ጦጢት በማስታወቋ፤ ሁሉም ከበር እየተመለሰ አንበሳም የሚበላው አጥቶ ሞተ ይባላል።

እናላችሁ ስንቶቻችን ሳይገባን ተበላን መሰላችሁ? የሚረባና የማይረባ ምክንያት እየደረደሩ ጊዜያችንን የሚበሉ፤ ገንዘባችንን የሚበሉ፤ ቁጠባችንን የሚበሉ፤ ተስፋችንን የሚበሉ፤ ዕቅዳችንን እየበሉ ስንቶች የራሳቸውን እድሜ እንዳስቀጠሉ ፈጣሪ ይወቀው. . . እኛ ግን ይኸውና ቀዩ መብራት ላይ እንደተተከልን ፈቀቅ ሳንል አለነው።

እኛ ይለወጣል፣ ይሻሻላል፣ ይስተካከላል በሚል ተስፋ ከዛሬ ነገን ስንጠብቅ “የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” በሚል ተልካሻ ምክንያት ብቻ የስንቶቻችን ተስፋ በስንቶቹ ራስ ወዳዶች ሜዳ ቀረ መሰላችሁ?. . . ሁሉም ዋሻውን ሰርቶ እኛን ሊበላ ያሰፈሰፈ እንደሚጠበቅ ደርሰንበታል።. . . እናም ወደዋሻው የሚገባ እንጂ የሚወጣ ዱካ የለምና ጎበዝ ጠንቀቅ ማለቱ ሳያዋጣ አይቀርም። በዚህ ዘመን ትልቁም ትንሹም እንብላው እንጂ እናባላው የሚያውቅም አይመሰልም። . . . ለዛሬም ለነገም ትሆነናለች ያልናትን ተስፋ እየገዘገዙ ብዙዎች በኛ ላይ ተንጠላጥለው የራሳቸውን ቤት ከገዙ ከእንግዲህ ምን ቀረ ይባላል?. . . በአካፋ ሲታፈስ በማንኪያ እንኳን እንድንቀምስ አለመደረጉ “ፌር” አይደለም። ማን ነበር እንኳን “ሆድ ከሀገር ይሰፋል” ሲባል ሰምቶ “ለዛ ነዋ የእነእገሌ ሆድ የማይሞላው” ብሎ ያሽሟጠጠው?

አትስጋ ይሉኛል እንደምን አልሰጋ፣

ተዱር እያደርኩኝ ተሸክሜ ስጋ።

እንዲል ባለቅኔ ስንቶች ያሰፈሰፉበት ስጋ ይዘን፣ ተስፋ ይዘን፣ ዕቅድ ይዘን፣ መስራት እየቻልን ዘመድና ማዕረግ በማጣታችን ብቻ ስንቶች ስጋት እንደጨረስን አንድዬ ይወቀው።. . . እናላችሁ መልካሙን አስተዳደርና መልካሙን ጊዜ በመጠበቅና በማስጠበቅ ናፍቆት እየማቀቅን እንደሆነ አለቆቻችን ቢረዱት ምን አለበት። እናም የተሻለ ነገን ስንጠብቅ ምን ያህል እንደተጎዳን ለመጠቆም ያህል እንዲህ ተቀኝተን እንሰነባበታለን።

ትመጫለሽ ብዬ ሳይ ማዶ -ሳይ ማዶ

የልጅነት አይኔ ሟሟ እንደበረዶ።

ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
188 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 975 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us