የግብር ይውጣ ነገር . . .

Wednesday, 26 July 2017 13:34

 

አጀብ!

ባዳራሹ ሙሉ

     ሰው በሰው ሲጠበብ

ተግባር መሬት ወድቆ

     ላፍ እንዴት ይጨብጨብ!

     (“የዘመን ቀለማት” ከተሰኘውና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ካሳተመው “ቅጽ ሁለት” የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ? . . . እንደዘበትም ሱቅ እንደመዝጋትም ምናምን ስናይ አላምን ብለን፤ እንደድንገት የቀን ግምት ግብር የሚባለው ነገር ቀርቶ ባመናችሁበት ክፈሉ ምናምን ሲባል አላምን ብለን ይኸው ደግሞ “አላልኩም-ብያለሁ” ደረጃ ደረስንም አይደል?. . . ያገራችን ሰው ምን ብሎ ይተርታል መሰላችሁ “ሲሮጡ የታጠቁት፤ ሲሮጡ ይፈታል” ልክ አይደል እንዴ?. . . ድሮም እኛ ተናግረን ነበር። የሚሰማን አጣን እንጂ፤ የግብር ይውጣ ስራ ሲሰራ የሚገጥመው ነገር ይኸው ነው። እኔ የምለው ግን አስጠንተንና ጊዜ ወስደን ያመጣው ውጤት ነው አላሉንም ነበር እንዴ?. . . ለነገሩ በሪፖርትና በመሬት ያለ እኛ ዘንድ ልዩነቱ ከሰፋ ሰነባብቷል። የሚባለው ነገር ሌላ የሚደረገው ነገር ሌላ፤ የሚፀድቀው እቅድ ሌላ፤ የሚሰራው ስራ ሌላ፤ ቃል የሚገባው ነገር ሌላ የሚፈፀመው ነገር ሌላ፤ የሚበጀተው በጀት ሌላ አፈፃፀሙ ሌላ እየሆነ ከተቸገርን ቆይተናል።

ገጣሚው እኮ ወዶ አይደለም “ተግባር መሬት ወድቆ፣ ላፍ እንዴት ይጨብጨብ” ያለው. . . የምር- የምር እንነጋገር ከተባለ ነገራችን ሁሉ “ጉራ ብቻ” የሚያዘፍን ከሆነ ሰነባብቷል። በመንደር የሚወራው ስራ እና በወረዳ የሚቀርበው ሪፖርት የተለያየ። በወረዳ የሚሰራውና በክፍለ ከተማ የሚቀርበው ሪፖርት የተለያየ። በክፍለ ከተማ የሚሰራው ስራ እና በከተማ ደረጃ የሚቀርበው ሪፖርት የተለያየ እየሆነ እኮ ሁሉም ተቸግሯል። ይሄን ያለው ደግሞ የአገሪቱ እድሜ ጠገብ ጋዜጣ የሆነው “አዲስ ዘመን” ነው። ሌላስ ምን ቢባል ጥሩ ነው?. . . የሀሰት ሪፖርቶች አስቸግረውኛል፣ ውሸታም አስብለውኛል እኮ ነው የሚለው። እንደውም ቃል-በቃል ምን አለ? “በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት የሚቀርቡ የሀሰት ሪፖርቶች መበራከት አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው” ብሎላችኋል። እናላችሁ ሁሉ ነገር የግብር ይውጣ ሆኖ ሲሰራ የተቋማቱ አለቆች የሚጨነቁት ስለሪፖርቱ እንጂ ስለውጤቱ አይደለም።

በተቃራኒው ደግሞ ላባቸውን ጠብ አድርገው፤ ለፍተውና ደክመው ያገኙትን ውጤት በሪፖርት አድራጊዎች የሚነጠቁ ስንትና ስንት ለፍቶ አዳሪዎች አሉ መሰላችሁ?! ይሄን ጊዜ ታዲያ የአገራችን ሰው ምን ይላል?

 

የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ፣

ከኋላ ተነስቶ ቀድሞ በመደረሱ።

እኛ እንደበሬም እንደገበሬም ሆነን እንለፋለን እነ አጅሬ በአቋራጭ ይመጡና የኛን ውጤት እያስመዘገቡ በእድገት ጎዳና ላይ ይረማመዳሉ። ለፍቶ መና ከመሆን ወይም አመድ አፋሽ ከመባል አንድዬ ይሰውራችሁ አቦ!. . . የምር ግን እናንተ ለፍታችሁ ሌሎች ሲበሉባችሁ አያናድድም?

እስቲ ደግሞ ከመሰነባበታችን በፊት ይህቺን ጨዋታ እንካችሁ፤. . . ሰውዬው እንግሊዛዊ ነው። በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ወደፈረንሳይ ሀገር ይሄድና ንግግር እንዲያደርግ ይጋበዛል። በጉባኤው ላይ ረጅም ደቂቃዎችን የወሰደ ንግግር ቢያደርግም በስተመጨረሻ ከመድረክ ሲወርድ ማንም ሰው አላጨበጨበለትም ነበር። ከእርሱ ቀጥሎ ግን መድረኩን የተቆጣጠረችው ውብ ወጣት የእርሱን ያህል ጊዜ የሚፈጅ ንግግር አድርጋ ከመጨረሷ አዳራሹ በሞቀ ጭብጨባ ተናጋ። በሁኔታው የተደነቀው እንግሊዛዊ ታዲያ ለኔ ሳይጨበጨብ ለእሷ እንዲህ መጨብጨቡ ነውር ነው በሚል ስሜት፤ አጠገቡ ወዳለው ሰው ጠጋ ብሎ፣ “ለኔ ጊዜ አንድም ያላጨበጨቡት ሰዎች ለዚህች ወጣት ሴት ጊዜ ይሄን ያህል ጭብጨባውን ያዥጎደጎዱት ምን ብትናገር ነው ባክህ?” ብሎ ይጠይቃል። መላሹም “ወዳጄ ወጣቷ እኮ ያንተን ንግግር ነው ያስተረጎመችው” ብሎላችሁ እርፍ። ዋናው ተናጋሪ ቁጭ ብሎ ላስተርጓሚ የምታጨበጭብ አለም ስትገጥማችሁ ምን ታደርጋላችሁ?

እናላችሁ “ተግባር መሬት ወድቆ ለአፍ የሚጨበጨብበት” ዘመን ላይ ደርሰናልና የውሸት ሪፖርትና የውሸት ግምት የሚያመጣውን ጣጣ ልብ ብላችሁ ታዘቡልኝማ። . . . የምር ግን እኮ የአንዳንድ ተቋማት ሪፖርትና የሥራ አፈፃፀም በንፅፅር ሲታይ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ይሉትን አባባል በደንብ ነው የሚያስታውሳችሁ። ሴትየዋ “በሂውማን ሄር” ተውባና በኮስሞቲክስ ደምቃና ተደባብቃ የሚያውቃት ወዳጇ አንድ ቀን በተፈጥሮዋ (ሳትኳኳል) ቢያገኛት ምን አለ መሠላችሁ? “አንቺም እንደበርካታ የመንግስት ተቋማት ሪፖርቶች እውነተኛ መልክሽ እና በሜካፕ የሚለው ገፅሽ ይህን ያህል መለያየቱ ያስገርማል” ብሎላችሁ እርፍ። እናላችሁ አንድዬ ብቻ በተግባር ዜሮ ሆኖ በሪፖርት ተቆንዝሮ ከሚቀርብ ተቋማዊ አሰራር አገራችንን ይጠብቅልን አቦ . . . ከግብር ይውጣ አሰራርም እንዲሁ አለበለዚያ ግን እንዲህ እንላለን. . .

 

 

መጣላት ከሰው ጋር

ምንም አልተስማማን

ኡ-ኡ ብለን ስንጮህ

ጆሮ ያለው ይስማን።

(አርቲስት መሐሙድ አህመድ)

ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
222 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 997 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us