“እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም!. . .”

Wednesday, 09 August 2017 12:45

 

ገንዘብ መፈጠሩ ለሰው አገልጋይ፣

ሆኖ ሊሰራበት አልነበረም ወይ?

አሁን ግን መስገብገብ በጣም ስለበዛ፣

ሰው ባሪያ እየሆነ ለገንዘብ ተገዛ።

     (ከከበደ ሚካኤል፤ “ታሪክና ምሳሌ- አንድ” መፅሐፍ የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ?!. . . የገንዘብ ነገር ሲነሳ “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” አይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ብዙ ይገጥሙናል። ተደጋግሞ “ብር የሃጢያት ስር ነው” ሲባልም ሰምተናል። እዚህ’ጋ ሙላህ ነስሩዲን የገንዘብ ነገር እንዴት እንደሚያደርገው የምታሳይ አንዲት ወግ በመንደርደሪያዬ እነሆ፡. . . ጨዋታ አዋቂው ነስረዲን  ጋደም ባለበት ድንገት የሚስቱ ወንድም በፍጥነት ወደእሱ ሲመጣ ይመለከታል። ሁኔታው ያላማረው ነስሩዲንም የተኛ ሰው ለመምሰል አይኑን ጨፍኖ ቀረ። የሚስቱ ወንድምም ወደነስረዲን መኝታ ተጠግቶ፣ “ነስሩዲን ተኝተሃል እንዴ?” ሲል ሞቅ ባለድምፅ ጠየቀው። ነስረዲንም ዝም ከምለው ብሎ አይኑን ሳይገልጥ፣ “ለምን ጠየከኝ?” ሲል ስለጥያቄው ማብራሪያ ጠየቀ። “በቅርቡ የምመልስልህ ሶስት መቶ ብር ልታበድረኝ የምትችል ከሆነ አስቀድሜ ምስጋናዬን ልገልጽልህ ፈልጌ ነው” ሲል እጥፍ- ንጥፍ እያለ ብድር ሊጠይቀው መምጣቱን አስረዳው። በዚህን ጊዜ ሙላህ ነስረዲን ምን ቢለው ጥሩ ነው? “እንዲያ ከሆነ መልካም፤ ወደመጀመሪያው ጥያቄህ እንመለሳለን። ተኝተሃል ወይ?” ብለኽኝ ነበር አይደል የጠየከኝ? መልሴም አዎ ተኝቻለሁ! የሚል ይሆናል። በል አሁን ሂድልኝ፤ ልተኛበት” ብሎላችሁ ተከናነበ ይባላል።

በዘመናችን የብር ነገር ሲነሳ እንዲህ ፀባያችን የሚቀያየር ሰዎች በዝተናል።. . . የምር ግን ገንዘብን ያህል የሚያስተዛዝብ ነገር በዓለም ላይ አለ እንዴ?. . . ትዝ አይላችሁም እንዴ ከፈሪሳውያን እና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ ሰዎች ክርስቶስን በንግግሩ ሊጠምዱት አስበው ያቀረቡት ጥያቄ?. . . “ለቄሳር ግብር መስጠት ተፈቅዷልን” ወይስ አልተፈቀደም? ብለው ሲጠይቁት፤ እርሱ ምን አለ? “የቄሳርን ለቄሳር፤ የእግዚያብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት ጥበብ በተሞላበት መንገድ አመለጣቸው። (ማን በከንቱ ይበላል ልጄ? በነገራችን ላይ የግብሩ ግርግር እንዴት ነውሳ የተለወጠ ነገር አለ?). . . እናላችሁ ገንዘብ መፈተኛም መውደቂያም ከሆነ ሰነባብቷል። ቋንቋውም ሆነ የሰው መግባቢያው በብርና ስለብር ብቻ ከሆነም ቆይቷል።

የገንዘብ ነገር ከተነሳ ስለሀቀኛው ግብር ከፋይ (ስለደሞዝተኛው) እንጨዋወት እስቲ. . . ሰውዬው ደሞዙ ተገፍቶ - ተገፍቶ አድገሃል ተብሎ አምስት ሺህ ብር ይደርሳል። እናም አንዷን ቆንጆ ሊያገባ ይፈልግና ያስማማታል። “እናልሽ ደሞዜ 5000 ብር ነው። በዚህ ደሞዝ አብረን መኖር የምንችል ከመሰለሽ ላገባሽ እፈልጋለሁ” ከማለቱ ልጅቷ ምን ብትለው ጥሩ ነው? “ግድ የለም ተጋብተን መኖር እንችላለን። ግን ያው ያንተ ደሞዝ ብቻ ስለማይበቃ ልክ እንዳንተ አይነት ደሞዝ ያለውን ሌላ ሰው መተዋወቅ ይኖርብኛል” ብላላችሁ እርፍ ቂ- ቂ- ቂ-! (በቃ እኮ የኛ ደሞዝ አኗኗሪ መፈለጊያም ሳትሆን ልትቀር ነው ማለት ነው?. . . ኧረ ተው ግድ የለም ገንዘብ አላፊ ጠፊ ነው ብለን ተናግረናል - ዳሩ የሚሰማን መች ተገኝቶ) ብር ከሌለን መንገዱ ሁሉ የተገደበ አጥር እንደሚሆን ሳይታም የተፈታ ነው። የዘመኑ ቁልፍ ደግሞ ብር ብቻ ሆኗል።. . . ጉዳይ ለማስፈፀም ብር ያስፈልጋል። ፊርማ ለማግኘት ብር ያስፈልጋል፤ ፈቃዱ ለማግኘት ብር ያስፈልጋል፤ ጭራሽ ለመተዋወቅም ብር ያስፈልጋል ሲባል ሰምተናል።

እናላችሁ የብር ነገር በእኛ ዘንድ ግር-ግር መፍጠር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። የምር ግን እኮ የዘንድሮ ደሞዝ “ቁጥር ብቻ” እየሆነ ለሱሪያችን ኪስም፤ ለቆንጆ ሴት “ኪስም” የማይበቃ እየሆነ አስቸገረን እኮ ጎበዝ መላ በሉ እንጂ።

ሰው በገንዘብ ቁጥጥር ስር ምን ያህል እንደወደቀ የምታሳይ የመሰነባበቻ ጨዋታችንን እነሆ ብለናል። . . . ሶስት ጓደኛሞች ለአንድ ቤተክርስትያን ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ስራ ላይ ተጠምደዋል። ሁሉም በጣም እየለፉ መሆናቸውን በመገንዘብ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ለራሳቸው ለማድረግ ይፈልጋሉ። እያንዳንዳቸው ከምዕመናኑ የሰበሰቡትን በርካታ ገንዘብ እንዲያዙ እንደሚከተለው ሃሳብ ያቀርቡ ጀመር።

አንደኛው፤ “እኔ መሬት ላይ ቀለበት እሰራና ገንዘቡን ወደቀለበቱ እበትነዋለሁ። ቀለበቱ ውስጥ የገባው ገንዘብ ለቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ ይሆናል። ከቀለበቱ ውጪ የሆነውን ደግሞ ለራሴ አደርገዋለሁ” ይላል።

ሁለተኛው በበኩሉ፤ “እኔም መሬት ላይ በቀለበት ቅርፅ ክብ ስርቼ ገንዘቡን ወደቀለበቱ እበትነዋለሁ። ወደቀለበቱ የገባው ገንዘብ ለራሴ ሲሆን፤ ከቀለበቱ ውጪ የወደቀው ደግሞ ለቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ ይሆናል” ሲል ተናገረ።

ሶስተኛው ሰው በበኩሉ፤ “የኔ ሃሳብ ከናንተ ፍፁም የተለየ ነው። እኔ የማደርገው የሰበሰብኩትን ገንዘብ በሙሉ አምላክ ዘንድ ወደሰማይ እወረውረዋለሁ። እርሱ የፈለገውን ወስዶ ሲያበቃ ወደመሬት የሚጥለውን ለእኔ እወስደዋለሁ”  ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! (እንዲህናትና ንፉግነት!)

እናላችሁ ጊዜው የእንብላው ብቻ ሆኗል። ቢቻል ሳይነቃ፤ ከተነቃ ደግሞ በትንሽ “ቡጨቃ” ማለትም “እከክልኝ- ልከክልህ” በሚባለው መንገድ በጭፍን መሄድ በርትቷል። ዘንድሮ በአቋራጭ መሄድ እስካልተቻለ ድረስ የኑሮን ግልቢያ መቋቋም የምንችልበት አይመስልም። እናም ከአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ሥራዎች መካከል “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” የምትለዋን ስራ በመገባበዝ የምትከተለዋን ቅኔ ዘርፈን እንሰነባበታለን። . . . ሀብታሙን ያመመው ወረርሽኝ ነው ሲባል፣ ለካስ ሳይታወቅ ምቹ ኑሮ ኑሯል። ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
491 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1013 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us