የሙክታር እና ጋትሊን ልብ ያለህ!

Wednesday, 16 August 2017 12:32

 

ያፈሰውም ቢሆን ወርቁን በመዳፉ

ወይም የበተነው ለነፋስ ለዶፉ

ተመልሶ አይመጣም ከተሰናበተ

አዱኛ ብላሹ በቃ ተከተተ።

(“መልክአ ዑመር” - ከተስፋዬ ገሠሠ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... ወደመገባደጃው በተቃረበው የለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ብዙ ነገር ታዝበናል። በተለያዩ ምክንያቶች የውጤት ማሽቆልቆላችን እንደተጠበቀ ሆኖ “ከፍ የማድረጋችንን ያህል ስናፈርጥም ርህራሄ” የሚባል ነገር እንደሌለን ተመልክተናል። አንዳንዴ የሀገራችንን የሩጫ አደጋገፍ ስገመግመው “ወጣ ወጣ እና እንደሸንበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” አይነት ይሆንብኛል። እንደ ሸምበቆ እላይ ሰቅለን፤ ትንሽ ውጤት ሲጠፋ ደግሞ እንደሙቀጫ ለማንከባለል ጊዜ አይወስድብንም።

 

እንደነፍሳችን የምንወዳቸውንና የምንኮራባቸውን አትሌቶች ድንገት ውጤት ጠፋ ብሎ እንዲህ በመንደር እየተከፋፈሉ ከፍ-ዝቅ ማድረግ ቀላል ይደብራል እንዴ። የምሬን እኮ ነው፤ የኛ ከፍ-ከፍ ማድረግ መልሶ ለማፍረጥ ከሆነ ምን ዋጋ አለው። ወርቅ ሲመጣም፤ ወርቅ ሲታጣም “አይዞን” ካልተባባልን አይ መሬት ያለ ሰው ያሉትን ተረት አስተርቶ ያስተዛዝበናልና ግድ የላችሁም እየተስተዋለ።

እናላችሁ የኛ ነገር እቅፍ እና ከፍ እያደረጉ ትንሽ ችግር ሲፈጠር ደግሞ ዝርግፍ አይነት ነገር ከሆነ በጣም ይደብራል። ጐበዝ “ሁሌ ፋሲካ የለም” የምንለው እኮ ለዚህ ነው። ስፖርት ደግሞ በባህሪው መሸነፍም ማሸነፍም ያለበት ሂደት ነው። እናም ምን ለማለት ነው ውጤት ሲመጣ የአበባ እቅፍ፤ ውጤት ሲጠፋ ደግሞ የጅራፍ ግርፍ አይነት ነገር ደስ አይልም። ይልቅዬ ጠዋት እንቅፋት ሆኖ የመታን ድንጋይ ማታም እንዳይደግመን መጠንቀቁ አይከፋም።

 

እንደው ግን ይህ የለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተነሳ አይቀር ምን ታዘብክ አትሉኝም። የ100 ሜትሩ የትራክ ላይ ንጉስ ጀማይካዊው ዩሴን ቦልት በስተመጨረሻው በአሜሪካዊው ጀስቲን ጋትሊን መሸነፉን። መሸነፍም ሆነ ማሸነፍ የስፖርት አንዱ ባህሪይ ነው ተባብለን የለ?... አዎ! ይልቅዬ ምን ደስ አለኝ - አሸናፊው ጋትሊን ከድሉ በኋላ ለጥ ብሎ ለቀድሞው የመስኩ ንጉስ እጅ የነሳበት መንገድ። በርግጥ ይህ ነገር በርካቶችን በዓለም ዙሪያ አነጋግሯል፣ አስገርሟልም። የውድድር ዘመኑን በለንደን ሻምፒዮና በድል ለመደምደም አስቦ የነበረው ዩሴን ቦልት አልተሳካለትም። ግን ደግሞ ከተመልካችም ሆነ ከአሸናፊው (ጀስቲን ጋትሊን) ክብርን አላጣም። (በርግጥ በዕለቱ በርካቶች በአሸናፊው አትሌት ጋትሊን ላይ ሲጮሁበት ተመልክተናል። መቼም ይህ የአበረታች መድሐኒት “ዶፒን” ነገር ከመጣ ጀምሮ ውጤቶች ሁሉ በጥርጣሬ መነፅር መታየታቸው እየተለመደ መጥቷል። ሌላኛው ውድድር ደግሞ አትዮጵያዊው ሙክታር እድሪስ በአንደኛነት ያጠናቀቀው የ5000 ሜትር የሩጫ ውጤት ነው። በዚህም መስክ ላለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት የ10 እና የ5 ሺህ ሜትሮች ባለድል የነበረው እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ በስተመጨረሻ እጅ እንዲሰጥ ተገዷል። ከዚህም ውድድር ውጤት በኋላ ሙክታር እድሪስ ሞ ፋራህን ለማበረታታትና ያለውን ክብር ለመግለፅ ያደረገው ነገር የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።  

 

እናላችሁ ከዚህ ሻምፒዮና ውድድር የሙክታርንና የጋትሊንን ልብ እንዲሰጠን በአንድ በኩል፤ የሞ ፋራህንና የቦልትን አይነት ክብር እንዳያሳጣን ደግሞ በሌላ በኩል በእጅጉ ተመኘሁ። ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ማንን ገደለ?... አድናቆት ለሚገባው አድናቆት መስጠት ማንን ገደለ?... ጭብጨባ ለሚገባው ጭብጨባ መስጠት ማንን ገደለ?... ምስጋና ለሚገባው ምስጋናን መስጠት ማንን ገደለ? ማንንም!

 

እዚህ እኛ ዘንድ “የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” የሚለውን አባባል ብቻ ነው የገነባነው። በአንድ ወቅት አንደኛ የነበረ ሰው፤ አሸናፊ የነበረ ሰው፤ መሪ የነበረ ሰው፤ ታላቅ የነበረ ሰው ድንገት ጊዜ ጥሎት ሲወድቅ እኛም የምንጥልበት ክፉ ነገር አናጣም። ስለሰራው መልካም ስራ፤ ስለነበረው መልካም ታሪክ፣ ስለፈፀመው ጀብዱ አንስተን ከማመሰጋገንና ክብርን ከመስጠት ይልቅ ባጐደለው ነገር ላይ እያተኮርን ማቃለልና ማዋረድ መለያችን ሆኗል። እናም በዚህ ጊዜ እንደ ዩሴን ቦልት እና እንደ ሞ ፋራህ  ተሸንፎም ቢሆን፣ እንደ ጀስቲን ጋትሊን እና እንደ ሙክታር እድሪስ ድል ነስቶም ቢሆን የሚያከብር ልብ ያስፈልገናል። የሚንበረከክ ጉልበት ያስፈልገናል። ማድነቅን የሚችል ቀናነት ያስፈልገናል። የኛ ድምቀት ያለፉትን ለማጉላት እንጂ በማፍዘዝ ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። የኛ ክብር የሌሎችን ክብር በማሳነስ ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም። ለምን ቢሉ ለሁሉም ጊዜው ሲደርስ ተነሺም ወዳቂም አለና።

 

በመሆኑም ለሌሎች የምንሰጠው ክብርና አድናቆት ዋጋው ለቀጣይም ትውልድ የሚተርፍ ነው። በርግጥ ሰው የሌለውን ነገር አይሰጥም። እኛ ዘንድ ሰላም ከሌለ ለሌሎችም ሰላም ልንሰጥ አንችልም። እኛ ዘንድ ፍቅር ከሌለ ለሌሎችም ፍቅር ልንሰጥ አንችልም። እኛ ዘንድ ክብር ከሌለ ለሌሎችም ክብር ልንሰጥ አንችልም።… እናም በጊዜው ሁሉም ነገር ይቀየራል። ሞ ፋራህ ለዓመታት አንደኛ ነበር። አሁን ጊዜው የሙክታር ነው። ዮሴን ቦልት ለዓመታት በክብረ ወሰን የታጠረ አንደኝነትን ይዞ ነበር። አሁን ደግሞ ጊዜው የጋትሊን ሆኗል። በሂደት ሙክታርም ሆነ ጋትሊን ይወርዱና ሌላኛው ባለተራ ይተካቸዋል። ነገር ግን ክብርን መሰጣጠት መልመድ እጅግ አስፈላጊ ነው።

 

ትኩረታችን ሚዛናዊ ይሁን። ትኩረታችን አሸናፊው ላይ ብቻ ሳይሆን ተሸናፊውም ላይ፤ ከሳሽ ላይ ብቻም ሳይሆን ተከሳሹም ላይ፤ ሐኪሙ ላይ ብቻ ሳይሆን ታካሚው ላይ፤ መሪው ላይ ብቻ ሳይሆን ተመሪውም ላይ አንደኛው ላይ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛውም ላይ እንዲሆን ያስፈልጋል። ለምን ቢባል አንዱ ያለአንዱ ሊኖር አይችልምና። “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” እንደተባለው መሆኑ ነው። ለማንኛውም እንደ ሙክታር እድሪስ እና ጀስቲን ጋትሊን ላሸነፉት ብቻ ሳይሆን ለተሸነፉትም ክብር የምንሰጥ ያድርገን፤ ለነገሩ ማርኮም ቢሆን ለሰው ልጅ ክብር መስጠት የአባቶቻችን ተግባር ነው። ይህን ማወቅ የፈለገ እምዬ ምኒልክ ከአድዋ ድል በኋላ በምርኮ የያዙዋቸውን ኢጣሊያኖች እንዴት ይንከባከባቸው እንደነበር የዘመናችን ገጣሚ እንዲህ ብሏል፡-

 

ልክ እንደምኒልክ እንደቅድመ-አያቱ

ጥሎ የማይፎክር አዛኝ ለጠላቱ።

ቸር እንሰንብት!!!¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
188 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 419 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us