“ለአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ”

Wednesday, 23 August 2017 12:22

 

የወዳጅ ደንቆሮ ብዙ ነው መዘዙ

እጠቅማለሁ ብሎ ይጎዳል በብዙ።

ከደንቆሮ ወዳጅ ብልሁ ጠላት

ይሻላል ተብሏል ጥንቱን ሲተረት።

     (ከከበደ ሚካኤል፤ “ታሪክና ምሳሌ- አንድ” መፅሐፍ የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . አንዲት ወግ ማሳመሪያ ተረት አለች። “ኧረ በከንቱ ማን ሊሰማ ነው ጩኸቱ” ትላለች። የምር ግን ለስንቱ ነገር በከንቱ ስንጮኽ ከረምን?. . . ብለነው ብለነው የሚሰማን አጥተን፤ ነገሩ ውሎ አድሮ ደድሮና ተከምሮ ሲታይ ጩኸታችንን ቀምቶ የሚያቀልጠው አልበዛም እንዴ? ኧረ የመልካም አስተዳደር ችግር በዝቷል፤ ኧረ የአሰራር ብልሹነት ሰፍኗል፤ ኧረ ማጭበርበር አይሏል፤ ኧረ ኃላፊነትን በሚገባ መወጣት ድሮ ቀርቷል፤ ኧረ የሙስናው  ግዛት ሰፍቷል ስንል ማን ሰማን? ማንም። ይህው አሁን ጩኸት በዝቷል።

ብለነው ብለነው የተወነውን ነገር

ባሏ ዛሬ ሰምቶ ታንቆ ሊሞት ነበር

ያለው ማነው?. . . እናላችሁ ምን ለማለት ነው?. . . እኛ ስንናገረው የፀረ ሰላም ኃይሎች ንግግር ነው እየተባለ። እኛ ስንጠይቅ የፀረ- ልማት ኃይሎች ጥያቄ ነው እየተባለ። እና ስንጮኸ ፀረ መንግስት አላማ ያላቸው ሰዎች ጩኸት ነው እየተባለ ውሎ አድሮ ከእኛ በላይ መጮኽ ሲጀምሩ ምን እንበለው?

የሚቀርበው ሪፖርት የሀሰት ነው ስንል፤ የሚሰጠው ውጤት ውሸት ነው ስንል፤ የተዘረዘረው የኢኮኖሚ እድገት የኑሯችንን ደረጃ የሚገልፅ አይደለም ስንል፤ አስራ ምናምን በመቶ የሚባለው እድገት እንቶ ፈንቶ ነው ስንል የሚሰማን ጠፍቶ ይህው ጊዜ ሁሉን ነገር እንደመስታወት ማሳየት ጀመር መሰለኝ።

እናላችሁ ገጣሚው እንዳሉት “ከደንቆሮ ወዳጅ ብልህ ጠላት ይሻላል” ተብሏልና ጎበዝ በደንቆሮዎች ሪፖርት፣ መላምትና የተንሳፈፈ ውጤት ላይ ተመርኩዘን የምንሰራው ስራ እያስተዛዘበን ነው። እናም አንድ ወዳጄ አዘውትሮ የሚናገራትን ጥቅስ እዚህች ጋ እነሆ፣ “የአይጥ ምስክር ድንቢጥ” ይላል። . . . እኛ ያልነውን ብቻ የሚደግም ባልደረባ፤ እኛ የውደድነውን ብቻ የሚያፀድቅ የስራ አጋር፤ እኛ የተመቸንን ብቻ የሚያሳልፍ ኃላፊ ምን ያደርጋል። ይዘን የመጣነውን እቅድ መዝኖና ፈትሾ፤ አሽቶና አሻሽሎ የሚሰራ ሰው ቢገኝ መልካም ነው። አለበለዚያ ግን የጠቀመን እየመሰለን በቀላሉና ባቋራጩ መንገድ የሚያካልበን ሁሉ እንደደንቆሮው ወዳጅ መዘዙ ብዙ ነው።

ሰውዬው ድንገት ከየት እንደመጣው ባልታወቀ ገንዘብ አዲስ መኪና ገዛ፡፤ እናም የሆዱን በሆዱ ይዞ አዲሷን መኪና እንዲባርኩለት ወደነፍስ አባቱ ዘንድ ይሄዳል። ቄሱም እያቅማሙም ቢሆን ከባረኩለት በኋላ ምን ቢሉት ጥሩ ነው? “ልጄ ይሄ ቡራኬ ግን በሰዓት ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ስትነዳ ላይሰራ ይችላል” ብለውላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ሰው እኮ በቅኔ መጠቃጠቅ ከጀመረ ሰነባብቷል።

እናላችሁ የውሸት አጨብጫቢ፣ የውሸት አድናቂ፣ የውሸት ስራ ፈፃሚ፣ የውሸት ሪፖርት አቅራቢ፣ የውሸት ዘጋቢና የውሸት አጃቢ ከሚኖር የምር ቢቀርብን ይሻለናል። ለምን ቢባል “ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል” ነውና። . . . ሰውዬውን ባንወደውም የሚወደድ ሀሳብ ካለው ብንቀበለው ምን አለበት?. . . ሰውዬውን ብንጠላውም የሚወደድ ሃሳብ ካለው ብንወድለት ምን አለበት?. . . ሰውዬውን ባናውቀውም የሚያስተዋውቀን አዲስ ሃሳብ ካመጣ ብንቀበለው ምን አለበት?. . . ሰውዬው “የእገሌ ድርጅት” አባል ቢሆንም ያመጣው ዕቅድ ግን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ከሆነ ብንቀበለው ምን አለበት? ምንም! ነገር ግን የተበለጥን ከመሰለን እና “ኢጓችንን” ማሸነፍ ካቃተን ሁሉ ነገር የከንቱ ከንቱ መሆኑ አይቀርም።

እናት ልጇ ስቅስቅ እያለ ሲያለቅስ ትደርሳለች። “አንተ ልጅ ምን ሆነህ ነው የምታቅሰው?” እናት ጠየቀች። “አባዬ በመዶሻ ሚስማር እመታለሁ ብሎ በመሳቱ ጣቱን ስለመታው” ልጅ ማልቀሱን ሳያቋርጥ ለናቱ ጥያቄ መልስ ሰጠ። እናትም በመልሱ ተገርማ፣ “እና ይሄ ያስቃል እንጂ ያስለቅሳል እንዴ?” ከማለቷ ልጁ ምን ቢመልስላት ጥሩ ነው?” ስለሳኩማ ነው “በኩርኩም ብሎኝ” አሁን እያለቀስኩ ያለሁት” ብሎላችሁ እርፍ።

እናላችሁ ይህቺን ጨዋታ ባሰብኩ ቁጥር “እውነቱንማ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ብለው ሆድ ይፍጀው የሚሉ ሰዎች ውልብ ይሉብኛል። . . . ለማንኛውም ያወቅነው እውነት ስንናገር እንደ ፀረ ሰላምና፣ እንደፀረ ልማትና እንደፀረ መንግስት ከመተያየት ይልቅ አለ አይደል “ከደንቆሮ ወዳጅ ብልህ ጠላት ይሻላል” በሚለው ቢያዝልን መልካም ነው። አለበለዚያ ግን እኛም ስንጮህ እናንተም ሰምቶ እንዳልሰማ ስትሆኑ (አረቦቹ እንደሚሉት “ውሾቹ ይጮኻሉ ግመሉ ግን ይሄዳል”) ከተባባልን እኛም ደክሞናልና “ኧረ በከንቱ፣ ማን ሊሰማ ነው ጩኸቱ” ብለን የአንድዬን ጊዜ መጠበቃችን አይቀርም። ጩኸታችንን የሚሰማ ጆሮ ይስጣችሁ አቦ!. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
243 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 957 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us