ጣፋጭ አቃጣዮች!

Wednesday, 30 August 2017 13:09

 

ሥነ-ህይወት

እጅግም አትጣፍጥ-እጅግም አትምረር

ከቻልክ አመጣጥነው - ሁለቱንም ነገር

ይልቅ ሁን ሚጥሚጣ - ወይ ደግሞ በርበሬ

“ጣፋጭ አቃጣይ” ነው - የሚወደድ ዛሬ።

(© በርናባስ ከበደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... ምነውሳ ከዚህም ከዚያም መንደር ነገር የሚደረድርና እሣት የሚያቀጣጥለው በዛ እኮ!... የምሬን ነው፤ ሰውዬው በዓለም የፍልስፍና መዝገብ ውስጥ ቁጥር አንድ ተጠቃሽ ነው። የወጣቶችን አዕምሮ በአቴንስ አደባባዮች ላይ መፍታትና ማፍታታት ያወቀም ጭምር ነው። ታዲያ ይህ በበርካቶች ዘንድ የሚወደድና ብዙ ተከታዮችም ያሉት ፈላስፋ በቤቱና በአስፋልቱ ሲታይ የተለያየ ሰው ነበር። በጠዋት ከቤቱ እየወጣ ተመስጦ በማሰብና ፍልስፍናዊ ጥልቅ አስተሳሰቦቹን ለሌሎች ሲያጋራ፤ እንዲሁም በአንድ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ጋር ሲወያይና ሲከራከር ውሎ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቱ ይገባል። ቤት የምትጠብቀው “አለቃው” (ሚስቱ መሆኗ ነው) ግን በነገር እሣት ተሞልታ የምትጠብቀው አርድ አንቀጥቅጥ ክፉ ሴት እንደነበረች በታሪኩ ሰፍሯል። እናም የሚያውቁት ሰዎች ምናለበት ከዚህች ጨቅጫቃ ሴትዮ ተለያይተህ ህይወትህን በነፃነት መኖር ብትጀምር የሚል ሀሳብ ሲያቀርቡለት ምን መለሰ መሰላችሁ? “የሷ ባህሪይ ነው እኔን ከቤት እያስወጣ የአደባባይ ፈላስፋ ያደረገኝ” ብሎላችሁ እርፍ ቂ… ቂ… ቂ… (ይሄኔ ነው ታዲያ ገጣሚው እንዳለው ዘመኑ የሚፈልገው “ጣፋጭ አቃጣይ ነው” እንድንል የሚያስገድደን አይሆንም?) … ይህ ፈላስፋ አከል አድርጐም እንዲህ ብሏል፤ “ትዕግስት ጥሩ ነው። እሣትን መታገስ የቻለ በብርድ ውስጥ መኖር ይችላል” ይህ ባለታሪክ ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ነው።

 

እናላችሁ በግራም በቀኝም አናዳጅና አቃጣዮች በዝተው፤ ነገር ቆርጠው ሲቀጥሉ እየታዘብን አለነው። እናም ያለልክ መናደድ መንገብገቡ ጨጓራን ከማሳጣቱ በቀር ምን ጥቅም ይኖረዋል። አንዲት የፈረንጆች አባባል ትውስ አለችኝ። በግርድፉ ስንተረጉማት እንዲህ ትላለች፤ “በነገሮች ላይ ሁሉ ብስጭትና ንዴት ምንም መፍትሄ አይሆንም። እንዲያውም ምንም ነገር ከመገንባት ይልቅ በንዴት ጊዜ የነበረንም መልካም ነገር ሁሉ ይፈራርሳል” ትላለች። እና ምን ለማለት ነው?... ሌላው ቢቀር ያስገነባነው ቤትና ፎቅ ባይፈርስ እንኳን በደህና ጊዜ ጠግነን ያቆየነው ጤነኛው ጨጓራችን በመላላጥ ብዛት እኛን እንዳያፈርሰን ስንል አቃጣዮቻችንን ማጣፈጫ አድርገን ወስደናቸዋል እንላለን።

 

ለነገሩማ ሀበሻ የሚያቃጥል ነገር እንደሚወድ የታወቀ ነው። ለዚህም ምስክርና ምሳሌ ጥቀስ ካላችሁኝ የበርበሬና የሚጥሚጣ ወዳጅነቱን መመልከቱ በቂ ነው። (አንዳንድ ሰው ግን አይገርማችሁም በርበሬ እየበላ በቃሪያ ሲያጣጥም ምን ይባላል?) አንዲት እናት “ይሄ ልጅ አቃጥሎ ሊደፋኝ ነው” ብላ የገዛ ልጇን ስታማርር ከሰማችሁ በእርግጠኝነት ይሄንን ልጇን ከሌሎቹ ልጆች በተለየ ትወደዋለች ማለት ነው። ለምን ከተባለ ዘንድሮ የሚወደደው “ጣፋጭ አቃጣዩ ነውና” ነው መልሴ። እናላችሁ ዘንድሮ የሚያቃጥለን ኑሮ እየከበደ ቢመጣም እኛም የግዳችንን ወደነው ኑሮን የሙጥኝ እንዳልን አዲሱ ዓመት ደረሰ ማለት ነው።

 

ከሁሉም-ከሁሉም በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ አንዲት ተናገራት የተባችው ነገር በ“ጥበብ አንድ” መፅሐፍ ላይ ተከትባ ማንበቤ ትዝ ትለኛለች። ፈላስፋው እንዲህ ይላል፣ “ባለስልጣን ማለት የራሱን ፍላጐት መቆጣጠር የማይችል፣ ነገር ግን የህዝብን ፍላጐት መቆጣጠር የሚፈልግ ሰው ማለት ነው”… እንዲህ ልክ-ልካችንን እንነጋገር እንጂ ጐበዝ። ይኸውና ከሰሞኑ ስንቱ ወደ እስር ቤት የተወረወረውስ የኛን መሠረታዊ ፍላጐት ተቆጣጥሮ የራሱን ልቅ ፍላጐት ሲያራውጥም አይደል እንዴ?... “አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል” ያሉት አባባል እዚህች’ጋ መታወስ ይኖርበታል። በቀላሉ ማግኘት የሚገባንን ተንገላተንና ብዙ ውጣ ውረድ አይተን ስናገኘው ደስ ይለናል። ለምን ቢባል ድካማችን ሁሉ እንደጣፋጭ አቃጣይ ይወደዳልና ነው።... የቺክስ ነገር ቢሆን ትንሽ አንከራተውን ካልሆነ እንዲህ በቀላሉ የሚገኘውን “በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል” ብለንስ አይደል እንዴ የሚያንከራትተንን ፍለጋ ስንሮጥ የምንታየው።

 

እናላችሁ መቼም እኛም እርም አያውቀን ከበደሉን ጋር፣ መሠረታዊ ፍላጐታችንን ካሳጡን ጋር፣ የመናገር መብት ሰጥተው ከማያናግሩን ጋር፣ እያወቅናቸው ከማያውቁን ጋር አብረን መኖራችንን ቀጥለናል። ለምን ቢባል “ዘንድሮ የሚወደደው ጣፋጭ አቃጣዩ ነውና”… ከመሰነባበታችን በፊት ግን እስቲ ደግሞ ፊት-ለፊት ያቃተንን በቅኔ ተናግረነው ይውጣልንሳ…

 

አሸር-ባሸር በልቶ ሆዴን ከማለት፣

ጦም ውሎ ጦም አድሮ ጥሩ መሸመት።  

   

ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
283 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 435 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us