“ላም ባልዋለበት. . .”

Wednesday, 06 September 2017 14:12

መስኮቴን ከፍቼ ስቃኘው ዙሪያዬን፣

ቢራቢሮ ማየት ያሰኘዋል አይኔን፤

ዳሩ ምን ዋጋ አለው ቢራቢሮ ቢሉ፣

አንዲት ፅጌረዳ አበባ ሳይተክሉ።

     (ከገጣሚ ሰለሞን ሞገስ “የተገለጡ ዓይኖች” የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ሰውዬው የወረዳ መሪ ለመሆን የምርጫ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ነው አሉ። ውሃም አስገባለሁ፤ መብራትም አስገባለሁ፤ ስኳርም አስልሳለሁ፤ መንገድም አስገነባለሁ ድልድይም አሰራለሁ. . . ወዘተ እያለ በደማቅ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቀበጣጠረ። ሰውዬው ከገባው ቃል ሁሉ ግን የወረዳዋን ነዋሪዎች ግር ያሰኛቸው ወንዝ በሌለበት ድልድይ አሰራለሁ ማለቱ ነበር። ይሁንና ከዓመታት በኋላ መብራቱ ቀርቶ፤ ውሃውም ቀርቶ፤ ስኳሩም ቀርቶ፤ መንገዱም ቀርቶ ድልድዩ ብቻ ተሰርቶ ተጠናቀቀ። እናም በምረቃው ላይ አገረ ገዢው ተገኝተው ድልድዩን ከመረቁ በኋላ ምን ጠየቁ መሰላችሁ? “ድልድዩስ ተሰራ፤ በዚህ አካባቢ ግን አንዳችም የሚፈስ የወንዝ ምልክት አለማየቴ ለምን ይሆን?” ከማለታቸው የወረዳው ተመራጭና ቀደም ብሎ በድለላ ይተዳደር የነበረው ካድሬ ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “ጌታዬ በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ ወንዙን እንሰራዋለን” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ይሄኔ ነው ታዲያ የአገራችን ሰው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሲል የሚተርተው።

ዘንድሮ በብዙ ነገራችን የምንሰራው ሌላ የምንጠብቀው ውጤት ሌላ፤ የምንዘራው ሌላ ለማጨድ የምንጓጓው ሌላ፤ የምንማረው ሌላ የምንመረቀው በሌላ፤ የተነሳንበት ዓላማ ሌላ የምንደርስበት “ኢላማ” ሌላ፤ ለመሆን የምንፈልገው ሌላ የምን ሆነው ዳግም ሌላ፤ አድርጋችኋል ተብለን የሚቀመጠው ደረጃ ሌላ ኑሯችን ያለበት ቁልቁለት ደግሞ ሌላ እየሆነብን ነገራችን ሁሉ የአራምባና ቆቦን ያህል ከተለያየ ሰነባብቷል ማለት ይቻላል።

ለዚያም ነው መሰለኝ ገጣሚው “አበባ ሳንተክል ቢራቢሮ መናፈቃችን” እየጠቃቀሰ በአሽሙር የሚቆነጠን። የምር ግን ዓመታዊ እቅዳችንና የአፈፃፀም ውጤታችን ቢመረመር እኮ ልክ እንደአብዛኛቹ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወጪ በአካፋ፣ ገቢ በማንኪያ፤ አይነት እየሆነ ነገሩ ሁሉ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ስንዳክር መክረማችንን ያሳይ ነበር።

እንደው ሞክሮ መሳሳት ወይም ሳይሳካልን ቢቀር እንኳን ምንም አልነበረም እኮ፤ ሕዝቤ ግን መሞከር የለ፤ መልፋት የለ፤ መጣር የለ ብቻ “ውጤት ተኮር” እየተባለ ነገራችን ሁሉ “ከየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ላይ በማተኮራችን “አቋራጭ ፈላጊዎች” የበዙ አልመሰላችሁም?. . . እናም “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ማለት እኮ ቀላል ተረት አይደለም። እግር ለሌለው ውድ ጫማ ምኑ ነው?. . . አይነ ስውር ለሆነው ሰው ቴሌስኮ ምኑ ነው? በተማረበት ዘርፍ ስራ አጥቶ ስራ የሚፈልግን ሰው ስለስራ ፈጠራ መምከር ምንድነው?. . . መልካም አስተዳደር እንዳልሰፈነ እየታወቀ ነጋ ጠባ ስለመልካም አስተዳደር አስፈላጊነት ብቻ መደስኮስ ከተግባር ውጪ ምን ፋይዳ አለው?. . .ሁሉም ነገራችን “ላም ባልዋለበት” ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው።

ወደትምህርት ቤት የምንልካቸው ልጆች የተሻለ ይማራሉ፤ ሥነምግባር ያውቃሉ፤ መታዘዝን ይለምዳሉ ብለን ዘርዝረን ሳናበቃ የእሳት ልጅ አመድ ሆነው ቁጭ ሲሉ ምን ይባላል? ምንም!. . . ልጁ ብዙ ብር በሚከፈልበት ትምህርት ቤት እየተማረ ነው። ይሄኔ አባቱን እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል።

ልጅ፡- “አባዬ አንተን የፈጠረህ እግዚአብሔር ነው አይደል?”

አባት፡- “አዎ የኔ ልጅ”

ልጅ፡- “እኔንም የፈጠረኝ እርሱ ነው?”

አባት፡- “በትክክል!”

ልጅ፡- “አፈጣጠሩን እያሻሻለ ነው በለኛ” ብሎላችሁ ቁጭ!

እንግዲህ የትውልዱ መንገድ ይሄን ይመስላል። እኛ ለፍሬ እንዘራዋለን - እርሱ ለጥሬ እየሆነ ነገራችንን ሁሉ “ላም ባልዋለበት” አስመስሎታል። አንድዬ ብቻ ልብ ይስጠን!

ከዚህ ቀደም ተጨዋውተናትም ቢሆን ለዛሬ ወጋችን ግድ የለም እንድገማት፤ ሙላህ ኑስሩዲን ከቤቱ በራፍ ላይ ካለ የመንገድ መብራት ስር አንዳች ነገር በመፈለግ ተጠምዷል። ይሄን ተግባሩን የተመለከተ አንድ የነስሩዲን ጎረቤትም ጠጋ ይልና “ወዳጄ ኑስሩዲን ምን ጠፍቶህ ነው የምትፈልገው?” ሲል ይጠይቀዋል። “የጣት ቀለበቴ ወድቆብኝ እየፈለኩት ነው” ነስሩዲን ይመልሳል። በጠፋው ዕቃ ክፉኛ የደነገጠው የነስሩዲን ጎረቤትም ፍለጋውን ተቀላቅሎ ለብዙ ደቂቃዎች በመንገዱ መብራት ብልጭ የሚል ወርቅ ይፈልግ ጀመር። ትንሽ ቆየት ብሎ ግን ጎረቤትየው፣ “ለመሆኑ የጣት ቀለበትህን እዚህ ስለመጣልህ እርግጠኛ ነህ?” ሲል ይጠይቃል። ለዚህ ጊዜ ሙላህ ኑስሩዲን ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “ለነገሩማ የጣት ቀለበቴ የጠፋብኝ በመኝታ ክፍሌ ውስጥ ነው።” ጎረቤቱ ተገርሞም፤ ተናዶም፣ “ታዲያ እዚህ ስለምን ትፈልገዋለህ?” ሲል ከመጠየቁ ያገኘው ምላሽ ይበልጥ ጨጓራ የሚልጥ ሆኖ እናገኘዋለን። ነስሩዲን እንዲህ አለ፤ “ምክንያቱም መኝታ ቤቴ ውስጥ መብራት የለም። እዚህ ደግሞ እንደምታየው የመንገድ መብራት ስላለ እዚህ ብፈልገው ይሻላል ብዬ ነው” ብሎላችሁ እርፍ. . . ይሄንን አይነቱን ተግባር ነው ታዲያ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” የምንለው።

ለማንኛውም በምናቅደው ልክ ከሰራን፤ በምንናገረው ልክ ከኖርን፤ በምንማረው ልክ ካጠናን፤ በምንገባው ቃል ልክ ታማኝነታችንን ካሳየን፤ ልንደርስ ባሰብንበት ግብ ልክ ካለፋን የማይመጣ ውጤት የለምና እንበርታ!. . .። እናም መጪው አዲስ ዓመት በልካችን አቅደን በልካችን የምንሰራበት፤ የዘራነውን የምናጭድበት የተመኘነውን የምናገኝነበት ይሆን ዘንድ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቃሚዎች ከመሆን አንድዬ ይሰውረን አቦ!. . . ቸር እንሰንብት!!!   

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
176 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 81 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us