ሂደት ሰወር፤ ውጤት ተኮር!

Wednesday, 13 September 2017 12:26

 

ዓለማዊ ምኞት ልብን ስቅል አርጎ

ይነሳል እፎይታ

ሲለማም ላንዳፍታ፣ ቢጠፋም ባንዳፍታ

በበረሃ ’ሸዋ  እንዳረፈ በረድ፣

ተቁለጭልጮ ጭልጥ፣ ብን ይላል እንዳመድ።

(ከአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ “መልክአ ዑመር” የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እነሆ መስከረም ጠባ፤ አዲስ ዓመት ሆነ። እስኪ ደግሞ ቸር የምናይበት መልካሙን የምንሰራበት ዓመት ያድርግልን አቦ! ውጤቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ሂደቱ ላይም የምናተኩር ያደርገን። መቼም እንደአምናና ካቻምናው “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” በሚል ብቻ ውጤት ተኮር (ያውም በሪፖርት ብቻ የሚታይ ውጤት የምናተኩር) ሆነን ስንት ነገር ማጣታችንን እንደሀገር ሳትታዘቡ አልቀራችሁም።

ውጤቱን ከሂደቱ ነጥሎ ማየት መዘዙ ብዙ ነው። ያልተለፋበትን፣ ያልተደከመበትን፣ ያልተጣረበትን ውጤት እንዲያው ባቋራጭ ለማግኘት መሟሟቱ በጣም ያስተዛዝባል። እናም በብዙ መልኩ አሰራራችን ሁሉ ሂደት ሰወር፤ ውጤት ተኮር በሚል ብቻ ከተቃኘ ነገራችን ሁሉ ከንቱ ነው።

እንካችሁማ ጨዋታ፤ ተማሪው በመምህሩ እየተጠየቀ ነው። መምህር “ለመሆኑ ወደ መንግስተ-ሰማያት ለመግባት ምን ማድረግ አለብን?” ይጠይቃሉ። ጮሌው ተማሪም ሲመልስ ምን አለ መሠላችሁ? “መሞት አለብን!” እርፍ ነው እንግዲህ. . . እናላችሁ መልካም ስራ መስራት አለብን የለ፣ የጽድቁን መንገድ መያዝ አለብን ብሎ ነገር የለ- ዘው ብሎ መሞት ብቻ መንግስተ-ሰማያት እንደሚያስገባን ማመን ከጀመርን ችግር አለ ማለት ነው። ምክንያቱም ከውጤቱ በላይ ሂደቱ ወሳኝ ነውና።

አንዳንድ ሰው አጋጥሟችሁ አያውቅም እድሜው ለአቅመ አዳም ደርሶ፤ ሁሉ ነገር ሙሉ ሁሉ ነገር ዝግጁ ሆኖለት  ሲያበቃ “ቆይ ግን ለምን አታገባም?” ስትሉት ምን ይላችኋል መሰላችሁ?. . . “ዘንድሮ ሴት እንጂ ሚስት የሚሆን ሰው የታለና?” ሲል ያፈጥባችኋል። ዳሩ ምን ደርጋል ይሄ ሰው አንድም ቀን በፍቅር የቀረባትም ሆነች ለትዳር የጠየቃት ሴት የለችም። እናም ሂደቱን ሳያስቡ ውጤቱ ላይ ማተኮር ምን ዋጋ አለው?

እናላችሁ ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ሚስት ሳይፈልጉ፤ አንዲት ቆንጆ ሳያባብሉ፣ ልዘርጋልሽ፣ ልነጠፍልሽ ሳይወጣቸው፣ ለሻይ ቡና የሚሆን ጊዜ የሌላቸው ሰዎች ድንገት እየተነሱ “ዘንድሮ ሴት እንጂ ሚስት የሚሆን ሰው የታለና!” ማለት ከጀመሩ ነገር ተበላሸ ማለት ነው። ለምን ቢባል ሚስት ለማግኘት ሂደትን እንጂ “ውጤት ተኮር” አካሄድን መከተል የትም አያደርስምና።

አሪፍ ውጤት የሚፈልግ ተማሪ ወጥሮ ማጥናትና ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው። ነገር ግን እንደው በደፈናው “ውጤት ተኮር” እየተሆነ ሳይለፉና ሳይደከሙ አንደኛ ለመውጣት መሻት የውጤቱን እውነተኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥለው ይሆናል። ግማሽ በመቶ ሳይጥሩ መቶ በመቶ ውጤት መጠበቅ ምን የሚሉት ምኞት ነው? ዘንድሮ መቼም ቢ.ፒ. አርን አንሻፈን እየተጠቀምንበት ከሂደቱ ይልቅ ውጤቱ ይሻላል እያልን ከስንት ነገራችን በአቆራራጭ ደላሎች እጅ ወደቀ መሰላችሁ።

አባቶች “ቀልደኛ ገበሬ በሰኔ ይሞታል” የሚሏት ተረት አለች። እውነት ነው ማረስና መለስለስ የገበሬ ተግባር ነው። ቀጥሎ መዝራት መኮትኮትና ሲበቅልም ምርቱን ማፈስ (ማጨድ) የተገባ ነው። ነገር ግን ሳያርሱ፣ ሳይዘሩ፣ ሳያጭዱም እንዲያው ዝም ብሎ ምርት መጠበቅ፤ ሂደቱን ትቶ ውጤቱን ማለት ምን ዋጋ አለው?

የአገራችን ታሪክ፣ አንድነትና ባህል እዚህ ደረጃ የደረሰበትን ይህ ትውልድ ማወቅ አለበት። አባቶቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ የወጡትን ዳገትና የወረዱትን ቁልቁለት ከታሪክ ካልተረዳን፤ የተሰው ወገኖቻችንን “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጽናት የወደቁትን ቀደምቶች ልፋት ካላደነቅን “ታላቋን ኢትዮጵያ” መቀበል እጅግ ይከብደናል። የአሁኗ ኢትዮጵያ የአባቶቻችን የትግልና የመስዋዕትነት ውጤት ናት። ዳሩ ግን ይሄን ባለመረዳት አገራችን በቅርቡ የተሰራች የሚያስመስሉ “ውጤት ተኮራሞች” ብዙ ናቸው። እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች “ሂደት ሰወር”፤ ውጤት ተኮር ልንላቸው እንችላለን።

በቤተሰብ ደረጃም ቢሆን ልጆቻችን አሁን ያላቸው ጥሩ ነገር ሁሉ እንዴት እንደመጣ ቢያውቁት ዋጋውና ክብሩ ከፍ ማለቱ አይቀርም። የሚኖሩበት ቤት፣ የሚተኙበት አልጋ፣ የሚለብሱት ልብስና የሚማሩበት አሪፍ ትምህርት ቤት ሁሉ ወላጆች ጥረው ግረው፣ ለፍተው በሚያመጡት ገንዘብ የተገኘ መሆኑን ልጆች ማወቅ አለባቸው። አለበለዚያ ግን ልጆች በእጃቸው ባለው ምቹ ነገር ላይ ብቻ ካተኮሩ ነገሩን ሁሉ አቅልለውት “በእጃቸው ያለን ወርቅ እንደመዳብ ሊቆጥሩት ይችላሉ”. . . ይህም በመሆኑ ውጤት ለማግኘት፤ የተሻለ እርቀት ለመሄድ፤ ቋሚና ቀጣይነት ያለው ስራን ለመስራት፤ በሰሩት ስራ እርካታና ደስታን ለማግኘት ሲባል፤ ከውጤቱ ባልተናነሰ ሂደቱም ቢተኮርበት መልካም መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው። መልካም አዲስ ዓመት . . .ቸር እንሰንብት!!!   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
223 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1037 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us