“ታጋሽ ሰው ውሃ በወንፊት ይቀዳል፤. . .”

Thursday, 28 September 2017 14:38

 

በክፋት በዛቻ ጡጫ

ወገኔ ግራ ተጋብቶ፣

ትዕግስቱን አትንሳኝ ይላል

ከፍርሃቱ ተፈቶ።

እንበል እንጂ ግድ የለም፤

ትዕግስት ፍራቻ አይደለም።

ታግሶ ያለፈ ይበልጣል

ውሃ በወንፊት ይጠጣል።

     (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!. . . እኔ የምለው ድሮ-ድሮ “ትዕግስት ፍራቻ አይምሰልህ!” ይሏት አይነት ራስን ማስከበሪያ ዛቻ ነገር ነበረችም አይደል?. . . ይህውና ዘንድሮ የማንም አቦሬ አፍ- ዝም ብሎ እየተከፈተብን ስንቸገር ትዝ አለችን እኮ። . . . የምር ግን ዘንድሮ “ትዕግስት” የሚሉት ነገር በእህቶቻችን “ስምምነት” ላይ ብቻ የሚታይ ቅርስ ከሆነ የቆየ አልመሰላችሁም። . . . “አደም አትበል ቀደም ቀደም- ትሆናለህ ደም- በደም” የተባባልነው እኮ “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” የሚለውን በአፅንኦት ለማስተማር ነበር።

የትዕግስት መኖሪያ ከጠፋብን ቆይቷል። በተለይ መኪና በሚጋልቡ ሾፌሮች ዘንድ የትዕግስት አስፈላጊነት ደረጃዋ ከወረደ ሰነባብቷል። እኔ የምለው ግን የመኪና መሪ ሲይዙ ባህሪያቸው የሚለውጥበትና “አንቱ” ያልናቸው ሰዎች “አንተ” ሆነው የሚቀሉበት ምስጢር አልገባኝም። . . . ሰሞኑን በአንድ ታክሲ ውስጥ እየተጓዝኩ ነው። ወጣቷ ለሁለት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲሙ መንገድ ሶስት ብር ለረዳቱ ሰጠችው። ቆየት ብላ የሃያ አምስት ሳንቲሟን መልስ ስትጠይቀው ረዳቱ ምን አላት መሰላችሁ፣ “አጠራቅመሽ 40/60ን ትሰሪበት መስሎሽ ከሆነ እንኪ” ሲል በመብቷ ላይ አላገጠ። ዝርዝር አጥቼ ነው የለ፤ እረስቼው ነው ይቅርታ የለ ዘሎ ዝርጠጣ ምንድነው?. . .  ልጅት ታዲያ ሴት አንበሳ ኖራ “አንተስ ስራና ልመናን ቀላቅለህ የኛን ሳንቲም ከምትቆራርጥ ምናለ ብትመልስልን” ብላ ታክሲውን ሳቅ አርከፈከፈችበት።

ይሄን አይነቱ እንካ - ሶላንቲያ ተፋፍሞ ወደዱላ ሊቀየር ምንም አልቀረውም ነበር። አንድ አባት መሀል ገብተው ነገሩን እንዲበርድ ባያደርጉት ኖሮ. . . እና ምን ልላችሁ ነው? ይቅርታ የለ፤ ልክ ነሽ የለ፤ መቻቻል ብሎ ነገር የለ፤ በቃ ምላስ እንዳመጣ መመራረግ የታክሲዎችን ያልተፃፈ የአሰራር ፈሊጥ ይመስላል። ደግሞ እኮ የሚገርማችሁ ይሄንን የሃያ አምስት ሳንቲም ጭቅጭቅ ያስነሳው ታክሲ ውስጥ የተለጠፈ ጥቅስ ምን ይላል መሰላችሁ?

 

ጭቅጭቁን ትተን ምነው ብንፋቀር

ሁሉም ቅርብ ወራጅ ነው ከፈጣሪ በቀር።

ኧረ ግድ የላችሁም ትዕግስት ፍራቻ አይደለም እና እርስ- በእርሳችን በትዕግስት እንተላለፍ። እውነቱን ለመናገር የትዕግስት ዋጋ ብዙ ነው። አንዳንድ ቀለም ቀመስ ወዳጆቻችን እኮ ወደው አይደለም “ትዕግስት ዘሯ መራራ፤ ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ነው” የሚሉን። . . . አበውስ ሲተርቱ “የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል” ማለታቸው ቀላል ነው እንዴ?. . . ስለመታገስና ስለትዕግስት ባሰብኩ ጊዜ አንዲት ድንቅ የምትለኝ አነጋገር አለች። “ታጋሽ ሰው ውሃ በወንፊት ይዞ መሄድ ይቻላል። ዋናው ነገር ውሃው በረዶ እስኪሆን መጠበቁ ነው” ትላለች።

ማመናጨቅና ቁጣ የዘመኑ ምልክት እስኪመስሉ ድረስ እርዳታቸውን የጠየቅናቸው ሁሉ፤ አገልግሎታቸውን ፈልገን ደጃቸው የደረስን ሁሉ፤ መሪነታቸውን ፈልገን አቅጣጫ የጠየቅናቸው ሁሉ፤ ያወሩት ነገር አልገባ ያለን መሆኑን የገለጽንላቸው ሁሉ እየተነሱ በቁጣ የሚደነፉብን ለምን እንደሆነ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው። . . . ምናለ በትዕግስት ተነጋግረን ብንረዳዳ? “መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች” የምትለዋ የታላቁ መጽሐፍ ጥቅስ እኮ ቀላል መፍትሄ እንዳትመስላችሁ። ባይቻል እንኳን አለመቻሉን በለዘበ መንፈስ የሚያስረዳን ስናገኝ መልካም ነው። አለመቻሉንም፣ አለመሆኑንም፣ የጠየቅነው ነገር አለመኖሩንም ሆነ አለመፈፀሙን በሰከነ መንፈስ የሚያስረዳ ሰው ማግኘትም በራሱ መታደል ነው።

“ከታገሱት ሁሉም ያልፋል” ማለትስ ቀላል ሃይለ-ቃል ነው እንዴ?. . . በፍፁም አይደለም! ህይወት እንደው የክብ ሩጫ ናት። ህፃኑ ሲጎረምስ፤ ጎረምሳው ይጎለምሳል፤ ጎልማሳው ሲያረጅ፣ ያረጀው ደግሞ ወደማይቀረው ሞት ይሄዳል። አንዱ ሲሞት ደግሞ ሌላው ይወለዳል። ህይወት እንግዲህ የክብ ሩጫ ናት የምንለው ለዚህ ነው። . . . በሌላም በኩል ስንመለከተው በትዕግስት ጊዜውን ከጠበቅን እንዲህም ሲሆን ልናይ እችላለን። ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ ሲመጣ አሶች ትላትሎችን ይመገባሉ። ውሃው በደረቀ ጊዜ ደግሞ የተገላቢጦሽ ይሆንና ትላትሎቹ አሶቹን ይበሏቸዋል። እናም ምን ለማለት ነው ከታገስን የኛ ጊዜ መምጣቱ አይቀርምና ስለክፋትና ስለቁጣ ባንጣደፍ ሳይሻል አይቀርም። ለምን ቢሉ ታጋሽ ሰው ውሃ በወንፊት ይቀዳልና።

እናላችሁ ትዕግስት ፍራቻ አይደለምና ትዕግስታችንን ተላብሰን ብንስተናገድ ምን ይመስላችኋል?. . . “ታጋሽ ሰው ውሃ በወንፊት መያዝ ይችላል፤ ዋናው ነገር ውሃው በረዶ እስኪሆን መጠበቁ ላይ ነው” የምትለዋን አባባል እስቲ በጋብሮቮው ቀልድ አሟጠናት እንሰነባበት።

አንድ ጋብሮቮው መንገድ ዳር ብርድ እያንዘፈዘረው እንደተቀመጠ ሌላ ሰው ይመጣል። “በዚህ አንዘፍዛፊ ብርድ እመንገድ ዳር ምን ገተረህ ጃል?” ብሎ ቢጠይቀው የጋብሮቮው መልስ ምን ሆነ? “ከግሮሰሪ የገዛሁት የብራዲ ጠርሙስ ለተሰበረብኝ፤ የፈሰሰው መጠጥ እንደበረዶ እስኪጋገርልኝ እየጠበቅሁ ነው” ብሎላችሁ እርፍ። . . . አንድዬ ብቻ ከግልምጫና ከጡጫ የራቀ፤ በትዕግስትና በመልካምነት የታጨቀ ዕድሜን አይንፈገን አቦ. . . ቸር እንሰንብት!!!    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
347 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 87 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us