የዕድሜና የፍጥነት ገደብ - በአፍሪካ

Wednesday, 04 October 2017 12:59

 

ፍቅር ማደሪያ አጣ

ካልተረጋገጥን አንተላለፍም?

ካልተጠላለፍን አንረማመድም?

ካልተዘላለፍን አንነጋገርም?

ሰው በመሆን ሚዛን አንከባበርም?

ሰው በመሆን ጸጋ አንነባበብም?

ካልተነካከስን ወይ ካልተጠፋፋን

ካልተጎሻሸምን ወይ ካልተገፋፋን

ምነው ግን መሄጃው

መንገዱ እሚጠፋን?

        (“የተገለጡ ዓይኖች” ከተሰኘው የገጣሚ ሰለሞን ሞገስ መፅሐፍ የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!. . . በቃ እንደው እኛ አፍሪካውያን በስልጣን ነገር የሙጥኝ ማለታችን እንዲህ ወንበር እስከሚወረወር እና እስኪሰበር ድረስ አይን አውጥቶ አረፈው?. . . ወይ የስልጣን ነገር፤ አንዳንዴ ሳስበው ፀሐፊው እንዳለው “ዋናው ነገር ስልጣንን መያዙ ሳይሆን፤ በስልጣን ላይ መሰልጠኑ ነው” የሚሻለው።. . . ምነው እንኳን በዚህ ሰሞን ለሰላሳ አንድ ዓመታት ኡጋንዳን ሰጥ-ለጥ አድርገው የመሯት ዩሬ ሙሴቬኒ እራሳቸው ላፀደቁት ህገ- መንግስት መገዛት አቅቷቸው፤ “እድሳት ልግባ” በማለታቸውም አይደል እንዴ ፓርላማ ውስጥ “ሪሲሊንግ” የተመለከትነው። እውነቱን ለመናገር ድብድቡ ምክንያታዊ ነው ማለት ይቻላል። እንደው በሰለጠነ መንገድ ሀሳብን ለማይቀበል መሪ (ፓርቲ) አንዳንዴም እንዲህ በቡጢ መግባባት ከተቻለ መሞከሩ አይከፋም መሰለኝ (ቂ-ቂ-ቂ)

እናላችሁ “ከአፍ ሲያመልጥ፤ እራስ ሲመለጥ” አይታወቅም ያሉ የመሠሉት የኡጋንዳ ፓርላማ አባላት ሰውዬው አሁን ላይ 73 ዓመታቸው በመሆኑ እንደ ህገመንግስቱ አንድ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደር ሰው ዕድሜው ከ75 ዓመት ማለፍ የለበትም የምትለዋን ሀረግ አሻሽለው ለ2021 (እ.ኤ.አ) የምርጫ ፉክክር ሙሴቬኒን ሊያደርሷቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል። “ከአይሆንም- ይሆናል” ጭቅጭቅ አልፎ የወንበር መወራወር ደረጃ እስኪደርሱ ተመልክተናል። (አይ -አፍሪካውያን መሪዎች ራሳቸው ለፃፉትና ላጸደቁት ህገ መንግስት መገዛት ሲያቅታቸው ምን ይባላል?

የዮሪ ሙሴቬኒን የዕድሜ ነገር ስመለከት በቅርቡ በቲቪና በሬዲዮ ከሚተዋወቁ የትራፊክ አደጋ ማስታወቂያዎች መካከል “የፍጥነት ወሰኑ 30 የሆነው በምክንያት ነው” አይነት ኃይለ-ቃል ተደጋግሞ የሚሰማበት ማስታወቂያ ትውስ አለኝ። . . . እናም ምን ለማለት ነው? ለአፍሪካውያን መሪዎች እንዲህ ቁርጥ ያለ የዕድሜ ወሰን ሲቀመጥ “ያለምክንያት አይደለም” (ያው እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ጨዋዎች ነን፤ ወንበር እስከመወራወር አንድረስም። ዳሩ እንወራወርስ ብንል ፍልጥ ይዘን ካልገባን በስተቀር የፓርላማችን መቀመጫ እንደው ሲያምረን ይቀራል። ቂ-ቂ-ቂ!. . . የኡጋንዳዎቹን በወንበር መወራወር የተመለከተ አንድ ወዳጄ ተደንቆ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “እዚህ እኛ ዘንድ በቅጡ ቃላት መወራወር ዳገት ሆኖብናል እነዚህ ሰዎች ወንበር እንደካርታ ሲማዘዙ መመልከት ያስቀናል” ብሎኝ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ!)

እኔ የምለው ግን አፍሪካውያን መሪዎች ዝም ብለው ተጨማሪ ዕድል እየተሰጣቸው ሲቀጥሉ ጊዜ የሰሞኑ የቢራ ዕጣ ፍለጋ - “በድጋሚ ይሞክሩ” አይነት ዕድል አላበዙትም ብላችሁ ነው?. . . እስቲ እዚህች’ጋ አንዲት ጨዋታ እንካችሁ። ሴትየዋ በባሏ ላይ ሌላ አይነት ልምምድ ጀምራ ኖሮ ምነው አንድዬ በደፋልኝ አይነት ስለት አስገብታለች። ታዲያ ዛሬ ድንገት ባልዬ ከውጪ እንደገባ፣ “ይሄንን ሾፌር ላባርረው ይገባል” ሲል በመደንፋት ሲናገር ሚስት እንደደነገጠ መስላ፣ “ምነው?” ከማለቷ ባል ሲመልስ፣ “ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ አጋጭቶ በአደጋ ሊገለኝ ነበር እኮ” ብሎ ስሞታውን ከማቅረቡ ሚስትየው ምን ብትለው ጥሩ ነው? “አይ አታባረው ባይሆን አንድ የመጨረሻ ዕድል ስጠው” ብላላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ምን ማለቷ ነው? አንዴ እስኪጨርስህ ጠብቀው ማለቷ እኮ ነው ጓዶች!

አንድ ዕድል ስጠው ማለት? ይግደልህ ማለት ነው?. . . እናላችሁ አፍሪካ ውስጥ አንድ እድል ለመሪዎቻችን እየሰጠን ከተፈቀደው ዕድሜና ፍጥነት በላይ እንጋልባችሁ የሚሉን የበዙ ይመስለኛል። ለማንኛውም የስልጣን ገደብ ባይኖር እንኳን የዕድሜ ገደብ ልጓም መኖሩ ጥሩ ነው። የፍጥነት ገደብም ቢኖር እንደዛው።

ህዝቤ በአግባቡ ኑሮን ሳያጣጥማት፤ አነስተኛዋን በህይወት የመቆያ ዕድሜ ሲለማመን እየተመለከትን የአፍሪካ መሪዎች ግን በስልጣን ላይ ብቻ የሶስት ዲጂት ዕድሜን ለመቆየት ሲጣጣሩ ማየት ትንሽ “ፌር” ነገር አይመስልም። . . . እናላችሁ ለስልጣንም ሆነ ለፍጥነቱ ገደብ ቢኖረው መልካም ነው። አለበለዚያ ግን ኡጋንዳዎች በወንበር መወራወር እንደጀመሩት ሁሉ እያደር በድንጋይ ሊሆን ይችላልና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም። እንደትራፊክ አደጋው ሁሉ የስልጣንንም አደጋ ለመከላከል “30 የሆነው በምክንያት ነው” የምንልባትን ዘመን ያምጣልን አቦ! . . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
264 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 170 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us