መተላለፍ እንጂ መጠላለፍን ምን አመጣው?

Wednesday, 11 October 2017 13:22

 

ልቤ ቂም አርግዞ፣
ውስጤ ተወጥሮ፣ ሆዴ ተሰቅዞ፣
አምጪ - አምጪ በጭንቅ ብወልደው፣
አዋላጁን ሁላ ደም-በደም አረገው።
(“ምጥ” በሚል ርዕስ ተፅፎ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ካሳተመው
“የዘመን ቀለማት” የግጥም መድብል የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!. . . እህሳ ከሰሞኑ የምንሰማው ነገር ሁሉ ደስ የሚልም አልሆን ብሏል። እኛ በየፌስ ቡኩ ፎቶ እየለቀቅን፣ በየአውቶቡሱ ለታላላቆቻችን ቦታ እየለቀቅን፣ በሰፈራ ምክንያት ተወልደን ካደግንበት ሰፈር ቤት እየለቀቅን፣ የተሻለ ደሞዝ ፍለጋ ብለን ስራ እየለቀቅን ስንገላበጥ ያዩ “ጌቶቻችን” ስልጣን በቃኝ ብለው መልቀቅ መጀመራቸው ያልተለመደ በመሆኑ ትንሽ ሳያስደነግጠን አልቀረም አይደል?. . . የባህሪይ ለውጥ ይሉሃል እንዲህ ነው።


ገጣሚዋ እንዳለችው ዘመን ቀያሪ ይሆንልናል ብለን፤ በጭንቅ የምንወልደው ሁሉ አዋላጁን ደም-በደም እንዳያደርገው ስጋት አለን ጎበዝ! . . . አለ አይደል የምናየው ነገር ሁሉ ደስ የማይልና የተገላቢጦሽ እየሆነ፤ እንደዘመነኛው ድምጻዊ ነገራችን ሁሉ “ያ ሌላ - ይሄ ሌላ” የሚያስብል ይመስላል። . . . ለማንኛውም የቀዘቀዘውን ሞቅ፤ የገነፈለውን በረድ የምናደርግበት ጥበቡን አንድዬ ይስጠን እንጂ ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮችማ ከበውናል። . . . የሆነው ሆኖ ልባችን ቂም ሳያረግዝ፤ ለመፍትሄ የሚሆን ነገር ብቻ የምንፈልግበት ቀና ልቦና ያስፈልገናል። የቱን ጥለን-የትኛውን ደግሞ አንጠልጥለን መትረፍ እንዳለብን በግልፅ የገባን አይመስልም።. . . እናላችሁ በሆነ ባልሆነው በነገር ከመጠቃጠቅ፣ ከመጠላለፍ ምናለበት በትዕግስት ብንተላለፍ የሚያስብል ብዙ ነገር እየደጋገመን ነው።


መቼም የጨነቀው ሰው መካሪውን ሁሉ ይሰማ ዘንድ ግድ ነው። ለዚያም እኮ ነው የጨነቀው ሰው ምን ያህል ግራ እንደሚገባው ለማሳየት አበው፤ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” የሚሉት።. . . እዚህች’ጋ አንዲት ትዝብት አዘል ጨዋታችንን የምታደምቅ ወግ እንካችሁ። ሰውዬው በጠና ይታመምና ከባህል ሀኪም እስከዘመናዊ ሆስፒታል ቢመላለስ ለበሽታው ፈውስ የሚሰጠው ያጣል። በዚህ ጊዜ ጭንቀቱን የተመለከቱ ወዳጆቹ “እስኪ ጠበል ሂድበት” ይሉታል። ሳይሻለኝ አይቀርም ይልና በማግስቱ በጠዋት ወደተባለው ጠበል ቦታ ይሄዳል። እዛም ሲደርስ ሰዎች እንዲህ ይሉታል፣ “በሙሉ ልብህ ካመንክ ይህ ጠበል ይፈውስሃል። ነገር ግን ጠበሉ ይፋጃልም። እንዲፈውስህ ከፈለክ ቢፈጅህም ቻል አድርገህ “እሰይ- እሰይ” ማለት አለብህ። አለበለዚያ ግን “ፈጀኝ -ፈጀኝ” የምትል ከሆነ አይፈውስህም ብለው ምክር ይሰጡታል።


ሰውዬው የተሰጠውን ምክር በልቡ አኑሮ ወደ መጠመቂያው ይገባል። ሰዎቹ እንዳሉትም ጠበሉ ይፋጃል። ፈጀኝ- ፈጀኝ እንዳይል ፈውሱን ይፈልገዋል። እናም ከበሽታው መዳኑን እያሰበ፤ ነገር ግን ደግሞ ሁኔታውንም እየታዘበ “እሰይ- ፈጀኝ!. . . እሰይ ፈጀኝ!” አለ ይባላል። መቼም የጨነቀው እንዲህ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ቢያወጣም አይፈረድበትም።


እናላችሁ አንድ አዲስ ቀን በተጨመረልን ቁጥር የምናየውና የምንሰማው ሁሉ በልባችን የቋጠርናትን ቂም የሚያንጸባርቅ ሳይሆን አይቀርም ጥፋት በዝቷል። ልባችን በቅናት ከተወጠረ “ገጣሚዋ” እንዳለችው በጭንቃችን ጊዜ የደረሱልንን አዋላጆች ሁሉ ደም-በደም እንዳያደርጋቸው ያሰጋል። . . . በቅንነት ብንተላለፍ፤ በአንድነት እና በሰላም ብንተቃቀፍ፤ በመቻቻል መንፈስ ሆነን ብንተቻች ሳይሻለን አይቀርም። በትዕግስት ተቻችሎ መተላለፍን ያህል ነገር፤ መንገድ የመሰጣጣትን ያህል ትልቅ ነገር የለምና በዚህ የጭንቅ ወቅት “የማርያም መንገድ” የሚሰጠን ልበ-ሰፊ ሰው (መሪ) ያስፈልገናል። አለበለዚያ ግን ተኮራርፈን፣ ተጠላልፈን፣ ተዘጋግተን እንኳን በአንድ አገር በአንድ ትዳር ውስጥ መኖር ይከብደናል።. . . “የእልህ በር ሳይዘጋ ያድራል” የሚሏትን ተረት የምታስታውሰኝን አንዲት የጋብሮቮዎች ጨዋታ እንካችሁ ከመሰነባበቴ በፊት። . . . ሁለት ጋብሮቭ ሾፌሮች ጠባብ መንገድ ላይ ስለተገናኝ፤ አንደኛው የግድ መኪናውን ወደኋላ አንቀሳቅሶ የሌለውን መኪና ማሳለፍ ሊኖርበት ሆነ። ነገር ግን ወደኋላ በመንቀሳቀስ ቅንጣት ነዳጅ ማቃጠልን ሁለቱም አልፈቀዱምና አንዳቸውም ሳይንቀሳቀሱ ቀሩ። በዚህም መሀል አንደኛው ሾፌር “ቆይ አሁን ቁርጡን ሲያውቅ መንገዱን ይለቅልኝ የለ” ብሎ በማሰብ ጋዜጣ ዘርግቶ ማንበቡን ጀመረ።


ይሄኔ ነገሩ የገባው ሁለተኛው ሾፌርም ከእርሱ የባሰ ነበርና ምን ቢለው ጥሩ ነው? “ይቅርታ የኔ ወንድም ጋዜጣውን አንብበህ ስትጨርሰው ታውሰኛለህ” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ . . . እናላችሁ ዘንድሮ ከመተላለፍ ይልቅ መቆላለፍ የሚቀናበት አካሄድ በዝቷል። ቅንነት እየጎደለን፤ በልባችንም ቂም እያረገዝን ነው መሰል ምርመራ ሳያስፈልገን አይቀርም። ለዛም ሳይሆን አይቀርም የዘመናችን ወጣት ድምጻዊ፡-


“ካልተጣላ በቀር ካልራቀ ከነፍሱ፣
ደህና ዋል አይሆንም ለደህና እደር መልሱ።


ሲል “ያሌላ- ይሄ ሌላን” ያቀነቀነው . . . ለማንኛውም ቂማችንን አራግፈን፣ መጠላለፋችንን ትተን፤ የምንተላለፍበትን የተሻለ አኗኗር የምናይበትን ጊዜ አንድዬ በቅርቡ ያሳየን አቦ! ለወንበሩም፣ ለትዳሩም፣ ለስራውም፣ ለትምህርቱም፣ ለሩጫውም፣ ለኳሱም፣ ለመሄዱም፣ ለመቆሙም መተላለፍ እንጂ መጠላለፍን ምን አመጣው?. . . በሚያልፍ ጊዜ ውስጥ ከመጠላለፍ ይሰውረን።. . . ቸር እንሰንብት

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
404 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 924 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us