“ይሉኝታ እና ጥቅም”

Wednesday, 08 November 2017 19:27

 

ይሉኝታና ፍቅር አብረው አይሄዱም

ጨዋታሽ ናፈቀኝ አትበይኝ ዝም።
ነይ ቶሎ- ነይቶሎ ድረሽ ባፋጣኝ
እያንገበገበ ፍቅርሽ አመመኝ።

                  (ድምጻዊ ነዋይ ደበበ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኔስ አለው - አለው ለዛሬ እንደምንም፣ እግዜር የሰጠውን ሰው አልችል አይልም ያለው ማን ነበር?. . . የምር ግን የይሉኝታና የጥቅም ነገር እኮ የአይንና ናጫን ያህል የማይገጥም ነው። መፅሐፉስ ቢሆን “ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻልም” ያለው ወዶ መሰላችሁ እንዴ?. . . አስቡት እስቲ ብድር ልትጠይቁት የደወላችሁለት ሰውዬ ድንገት እናንተ በደወላችሁለት ስልክ በኩል የራሱን ችግር አስቀድሞ ብድር ቢጠይቃችሁ ምን ትሉታላችሁ? (በይሉኝታ ዝም!)


ለማንኛውም ይሉኝታ እና ጥቅም ማለት ውሃ እና ዘይት እንደሆነ አትርሱ። አልያም አንዳንድ ያራዳ ልጆች እንደሚያስቡት እሳትና ጭድ ሊሆንም ይችላል። ከውርደት ሁሉ የከፋው ውርደት ወዳጆች/ በሰዎች ፊት መዋረድ ነው። ይህ ነገር እውነት ነው በተለይ ሀበሻ ሰው ፊት ገመናውን ለመሸፋፈን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለምን ቢሉ ክብር የሚሏት ነገር አለቻ። (ሀበሻ እኮ “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ብሎ እስከመተረት የደረሰ ነው ጎበዝ!)


እስቲ ለመነሻ ያህል “ይሉኝታ እና ጥቅም” የእሳትና ጭድነት ማሳያ የምትሆን ጨዋታ እንካችሁ። . . . ወጣቱ በኮሌጁ ቤተመጽሐፍት ውስጥ በጣም ከሚወዳት ቆንጆ ሴት አጠገብ ይደርስና ድንገት ወደጆሮዋ ጠጋ ብሎ፣ “ይቅርታ የኔ ቆንጆ አጠገብሽ መቀመጥ እችላለሁ?” ሲል ድምጹን ዝቅ አድርጎ ጠየቃት። (“ውይይይ ወንዶች ግን የምትፈልጉትን እስክታገኙ ድረስ እጥፍ ዘርጋ ማለትን ስትወዱ” ያለችው ልጅ እዚህ’ጋ ትዝ አለችኝ ቂ-ቂ-ቂ-!). . . እናላችሁ ልጅት ሆዬ ድምጿን የቤተመፅሐፍቱ ተገልጋይ ሁሉ እንዲሰማ ከፍ አድርጋ፣ “ይቅርታ እኔ ካንተ ጋር ማደር አልችልም” ከማለቷ የሁሉም ተማሪ አይን ወደወጣቱ አፈጠጡ። “ይሉኝታ እና ጥቅም” አብረው አይሄዱምና ሊበላት ያሰባት “እንትናዬ” ድንገት ያላሰበውን ውርጅብኝ ስታወርድበት፤ በመደንገጡ ከአካባቢው ራቅ ብሎ ይቀመጥ ዘንድ ተገደደ።


ከደቂቃዎች በኋላ ታዲያ ያቺ ወጣቱን ያሸማቀቃቸው ቆንጆ ጥናቷን እንዳጠናቀቀች ወደልጁ ሄደችና፣ “አየህ እኔ የሥነ -ልቦና (ሳይኮሎጂ) ተማሪ ነኝ። ወጣት ወንዶች ምን እንደሚያስቡ አውቃለሁ” ስትል ወደጆሮው ተጠግታ አንሾካሾከች። በዚህ ጊዜ ወጣቱም ብድሩን ሊመልስ እንደተዘጋጀ ሁሉ ድምጹን ከፍ አድርጎ፣ “እንዴ ቅድም ምንድነው ያልሽኝ? ለአንድ ጊዜ አዳር ነው ሶስት መቶ ብር የጠየቅሺኝ? በጣም ውድ ነው። ይቅርብኝ አልፈልግሽም” ከማለቱ በቤተ መጽሐፍቱ ያሉት ዓይኖች ሁሉ ወጣቷ ላይ አፈጠጡ። በዚህ ጊዜም ወጣቱ ወደልጅቱ ጆሮ ጠጋ ብሎ፣ “አየሽ እኔ ደግሞ የህግ ተማሪ ነኝ። ሰዎችን እንዴት ወንጀለኛ ማድረግ እንደምችል ጠንቅቄ አውቃለሁ” ብሏት ወጣ። . . . አንድዬ ብቻ በሰው ፊት ከመውረድም ከመዋረድም ይጠብቀን አቦ!. . . “በሰፈሩት ቁና መስፈር አይቀርም” ማለት እንዲህ ነው።


እናላችሁ በስንቱ ነገራችን እንደ ይሉኝታ እና ጥቅም ሁሉ አብረውን የማይሄዱ ነገሮች ያጋጥሙናል መሰላችሁ። ምሳሌ ጥቅስ ካላችሁኝ መዘርዘር እችላለሁ። ለእግር ኳስ ያለን ጥልቅ ፍቅር እና የእግር ኳሳችን ደረጃ የይሉኝታና ጥቅም ያህል አብሮን የማይሄድ ነው።


የመሪዎቻችን የመምራት አቅምና የኛ አስተዳዳሪዋ ጥያቄ ብዛት የይሉኝታና የጥቅም ያህል አብሮ የማይሄድ ነው። የምንሰራው ስራ እና የሚከፈለን ደሞዝ (ብዙዎች የደሞዛችን ነገር ከኑሮ ጋር ሲነፃፀር የጥንቸልና የኤሊን ያህል እንደሆነባቸው ሰምተናል) እናም ስራችንና ደሞዛችን የይሉኝታና ጥቅም ያህል አብሮ አይሄድም። አልፎ- አልፎም ሀሳባችን (ዕቅዳችን) እና ተግባራችን የይሉኝታና የጥቅም ያህል የማይገጥም ነው። (በነገራችን ላይ ይህ የዕቅድና ተግባር ውጤት በተለይ የመንግስት ተቋማት ጋር ሲደርስ ይብስበታል።)


እናላችሁ እዚህ እኛ ዘንድ ብዙ ነገሮች የይሉኝታ እና የጥቅም ያህል የማይገጥሙ ከሆኑ ሰነባብተዋል። የበዛ ይሉኝታ ቢስ ከመሆን፤ የበዛ ጥቅመኛ ከመሆንም አንድዬ ይጠብቀን አቦ!. . . እነሆ የመሰነባበቻ ጨዋታ. . . ነገርዬው “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ወይም ደግሞ “የሌባ አይነደረቅ” የሚሉትን ሀገርኛ አባባሎች ያስታውሳችኋል። የድርጅቱ ኃላፊ ወደቢሮው ድንገት ሲገባ ፀሐፊው ከአንድ ሰራተኛው ጋር ተቃቅፋ ሲሳሳሙ ይደርሳል። ኃላፊውም በነገሩ ተቆጥቶ፣ “ስማ አንተ ደሞዝ የምከፍልህ እኮ ለዚህ ስራህ አይደለም” ከማለቱ ሰራተኛው ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “አውቃለሁ ጌታዬ! ይሄ በትርፍ ሰዓቴ የምሰጠው አገልግሎት ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! . . . እንደ አይንን በጨው ታጥቦ መጋፈጥ እንጂ አይቻልም እኮ።


የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “በታሪክና ምሳሌ” ቀዳሚ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ የምትል ውብ ግጥም ትነበባለች፤ ለመሰናበቻ እንዲሆናችሁ እንካችሁ. . .


ባለም ላይ ተሰርቶ በብዙ ጥበብ፣
ማዕረግ የሚባለው የደረጃ ግንብ።
በዚህ በሚያዳግት ባቀበት መንገድ፣
ግማሹ ሲወጣ ግማሹ ሲወርድ፤
ከወደዳር ቆሞ ማስተዋሉን ሳይተው፤
ምንኛ ደስ ይላል ለተመለከተው።


ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
1725 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1042 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us