“ቁርጡን ያወቀ ሰው. . .”

Wednesday, 15 November 2017 12:45

 

በአቤል አዳም

ፍርድ እንዳያዛባ አንዱ በሌላው

ለምን ትላላችሁ ታሪክ አይወቅ     ሰው።

(እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ያበጠው ይፈንዳ ብሎ ቁርጣችንን የሚነግረን ሰው እንዲህ እንጣ?. . . እኛ እዚህ ቲማቲም ቁርጥ አጥተን እነሱ እዚያ ታናሽና ታላቅ እየቆረጡ ቁርጣችንን የሚነግረን ሰው ቢጠፋ አይፈረድም። አንዲት ራስ መሆን የምትችልና አንጀት የምታርስ ጥቅስ ከሰሞኑ አንብቤ በጣም ነው የወደድኳት። ምን ትላለች መሠላችሁ?. . . “ቁርጡን ያወቀ ሰው ምርጫ ይኖረዋል” ደስ አትልም?

ጎበዝ እኛ እኮ በየመስኩ በሚሰጠን አጓጉል ተስፋ ላይ ተንተርሰን፤ መሬት በማይረግጥ ዕቅድ ሀሳባችን ተወጥሮ አለቅን እኮ። (ይሄኔ ታዲያ “ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይበላ ኖሮ. . .” የምትለው አገረኛ አባባል ትውስ ይለኝና፤ እነዚህ ሰዎች በእውናችን የተስፋ ቅቤ እየበሉን ይሆን እንዴ? ስል እጠይቃለሁ) እናም ምርጫችንን እናስተካክል ዘንድ ቁርጡ ቢነገረን ጥሩ ነው።. . . ሰውዬው በአስገራሚ ሁኔታ ጎበዝ ሯጭ ይሆናል። ታዲያ ቀደም ሲል በቡጢኛነቱ (በቦክሰኛነቱ) የሚያውቁት ሰዎች “እንዴት ተደርጎ ነው ከጡጫ ወደ ሩጫ የመጣው?” ብለው ይጠይቁታል። ታዲያ ታሪኩን ስንመረምር የምናገኘው እውነት በሳቅ የሚያንፈረፍር ነው። ይህ ታላቅ አትሌት በአንድ ወቅት ቦክስ ሊወዳደር ወደመድረክ ከመውጣቱ በፊት ከተጋጣሚው ጋር ይገናኛል። (ያው በቦክሰኞች አለም ፉከራና ቀረርቶ የሚመስል ተጋጣሚን የማስፈራሪያ የስነ-ልቦና ጦርነት መኖሩ ይታወቃል።) ያን ጊዜ አሁን አትሌት የሆነው ሰው ተጋጣሚውን፣ “ላረጋግጥልህ የምወደው ነገር ቢኖር እነዚህን ጓንቶቼን አጥልቄያቸው የተወለድኩ ቦክሰኛ መሆኔን ነው” ከማለቱ ተጋጣሚው ሆዬ ምን ቢለው ጥሩ ነው?. . . “እኔ ደግሞ ላረጋግጥልህ የምፈልገው ነገር፤ ጓንቱን አጥልቀህ እንተወለድክ ሁሉ ከነጓንቱ ወደመቃብርህ ለመሸኘት መዘጋጀቴን ነው” ብሎ በፉከራ ቡጢ ድንገት ቢጠልዘው  የዛሬው አትሌት ከመወዳደሪያ ስፍራው “እግሬ አውጪኝ” ብሎ ፈትለክ አለ። ይህውና ከዚያን ጊዜ በኋላ ከጡጫ ይልቅ ሩጫ እንደሚያዋጣው አረጋግጦ ባለድል መሆን ችሏል።

እናላችሁ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? ወይ እንደማንችል አልያም ደግሞ እንደማይችል እንዲህ ቁርጣችንን የሚነገረን ስናገኝ ምርጫችንን ማስተካከል የምንችልበት ዕድል ይኖረናል ማለት ነው። ልጁ ከልጅቷ የሆነ ነገር ጀማምሮታል። ዳሩ ምን ያደርጋል ልጅቱ ጊዜም ቦታም ልትሰጠው አልቻለችም። ይሄን ጊዜ ልጁ ለጓደኛዋ ምን ቢላት ጥሩ ነው? “እኔ እኮ እሷ ተመችታኝ እንጂ አማራጭ አጥቼ መሰላት እንዴ? ንገሪያት የጨረታ ሳጥኔ አልተዘጋም አብረን መሆን ካልቻልን ቁርጡን ትንገረኝ” ብሎ የይርዳው ጤናውን ዘፈን ጋበዛት አሉ።

ወይ እሺ በይ

ወይ እምቢ በይ

በመግደርደር ሰው አትግደይ።

ቁርጡን - ቁርጡን

ቁርጡን - ንገሪኝ እባክሽን።

የምር ግን በሆነ ባልሆነው በመልካም አስተዳደር ችግር ከምንሰቃይ፣ አለ አይደል? በቃ አልቻልንበትም የሚሉና ቁርጡን የሚነግሩን አስተዳዳሪዎች ብናገኝ ይሄ ሁሉ የኑሮ ውድነት ይናድብን ነበር?. . .። በየቢሮው፣ በየፌዴሬሽኑ፣ በየክፍለከተማው፣ በየወረዳው ከአቅም በታች (አቅም የሌላቸው ሆነው አቅም እንዳለው “አክት” የሚያደርጉ ሰዎች ከበዙ ምን ማድረግ ይችላል?). . . ለማንኛውም በየመስኩ አንችልም በቃን የሚሉ ሰዎች ከተገኙ እኛም ቁርጡን እንዳወቀ ሰው ምርጫችንን እናስተካክላለን።

“ቁርጡን ያወቀ ሰው ምርጫ ይኖረዋል” የምትለዋን ጥቅስ ባነበብኩ ጊዜ “ጨቋኞች” የሚሰጡንን ምርጫ እያሰብኩ የምትከተለዋን የአለቃ ገብረሃና ጨዋታ ወዲህ አልኩ።. . . በአንድ ወቅት ወታደር አለቃ ዘንድ እንግዳ ሆኖ ይመጣል። በዘመኑ በሆነ-ባልሆነው መቻያ እየተባለ ወታደር በየቤቱ “በእንግድነት ስም” እየገባ ብዙ የግፍና የብልግና ስራ ይሰራ ነበር። ታዲያ ወደአለቃ ገብርሃና ቤት የመጣውም ወታደር ይህን አምጣ፤ ያንን ድገም ሲላቸው ቆይቶ ሚስታቸው ማዘንጊያን ይጎመዣል። ወታደር ሆዬ አለቃን፣ “የበቅሎ ሳር ያምጡ” ሲል አዘዛቸው። አለቃም ነገሩ ገብቷቸው ኖሮ፣ “እሺ ማዘንጊያ ገመድ ይዘሽ ነይ!” ከማታቸው ወታደሩ በቁጣ ተሞልቶ፣ “ለምን እሷ እዚሁ ቆይታ እንጀራ ትጋግር ወጥም ትስራ እንጂ” አላቸው። አለቃም፣ “የለም ትምጣ! እኔ ሳጭድ እሷ ትታቀፋለች” አሉ። ያም ሆኖ ወታደሩ ፈርጠም ብሎ “በጊዜ መሄዱ ይሻልዎታል” በማለቱ ለአጨዳ ይሄዳሉ። ከዚያ ወዲህ የሆነውን የሚያውቅ የለም። አለቃም አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዳሉ ባለቤታቸውን ከማኩረፍ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም።

እናላችሁ ቁርጡን ያወቀ ሰው እና ምርጫ ያለው ሰው እንደመሆን የተሻለ ነገር የለም። በቀቢፀ ተስፋ ከምትሞሉን፣ በፕሮፖጋንዳ ከምታምሱ፣ በአጉል ይሆናልና ይሳካል ከተስፋ ማማ ላይ ከምትሰቅሉን ግድ የላችሁም ቁርጣችንን ንገሩን። ያኔ ምርጫችንን እናስተካክላለን። እንደማይፈፀም ተስፋ ልብን የሚሰብር ነገር የለም ያለው ማን ነበር? አጉል ተስፋ እንደሸምበቆ መደገፊያ ነው። ድንገት ይሰበራል። ተሰብሮም ከመጣሉም በላይ እኛኑ መልሶ ሊወጋን ይችላል። እናም ቁርጡን ያወቀ ሰው ምርጫ አያጣምና እስቲ ጣፋጭ ከሚመስል ውሸት የሚመረውን እውነት አሳዩን። . . . ቸር እንሰንብት!!! 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
512 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 922 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us