You are here:መነሻ ገፅ»tizbitbechewata»Items filtered by date: Wednesday, 16 May 2018 - Sendek NewsPaper
Items filtered by date: Wednesday, 16 May 2018 - Sendek NewsPaper

 

መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጨዋታ በከፍተኛ ረብሻ መቋረጡ ይታወሳል። በእለቱ የወልዋሎ ተጫዋቾችን የቡድን መሪ ዳኛ እያሱ ፈንቴን ከሜዳ ውስጥ እስከ መሮጫ ትራኩ ድረስ እያሯሯጡ ሜዳ ላይ ጥለው ድብደባ በመፈጸም ለጨዋታው መቋረጥ የላቀ አስተዋጽኦ በቪዲዮ ጭምር ታይቶ ዳኛውን ከጥቃት ለመከላከልና ረብሻን ለማረጋጋት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት።
በግጭቱ ላይ በርካታ ተጫዋቾች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፤ ሁለት የመከላከያ ተጫዋቾች ግን ዳኛውን ከጥቃት ለመጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። ከእነርሱም መካከል የፊት መስመር ተጫዋቹ ፍጹም ገ/ማርያምና አማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ ተጠቃሽ ናቸው። በተለይም ደግሞ በእለቱ የመከላከያን ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረው ፍጹም ገብረማርያም ዳኛውን ከጥቃት ለመጠበቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት አሳይቷል።
የቀድሞው የኤሌትሪክና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሮ ደስታውን በመግለጽ ላይ የነበረ ቢሆንም ኛ እያሱ ፈንቴን በመክበብ ጥቃት ሊያደርሱበት እንደሆነ ሲረዳ ደስታውን ትቶ ጸቡን ለማብረድ መሀል መግባትን ነበር የመረጠው። ዳኛውን እንዳይደበደብ መሀል ግብ ሲገላግል ከተጫዋቾች ተገፍትሯል፤ በጭንቅላትም ተገጭ ተመቷል። ፍጹም በወቅቱ ያሳየው ተግባር በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ አድናቆትና ምስጋና አሰጥቶታል።
ከፍጹም በተጨማሪም የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ ሜዳ ውስጥ መልካም ተግባር አሳይቷል። ተጨዋቹ ቡድን ያስመዘገበውን ውጤት በደስታ ከማጣጣምና ረብሻውንም ዳር ሆኖ ከመመልከት ይልቅ ግጭን ለማብረድ ዋና ተሳታፊ መሆንን መርጧል። ረብሻውን ለማብረድና ተጨዋቾችን በማረጋጋት ያሳየው ተግባር ምስጉን አድርታል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ለእነዚህ ተጨዋቾችን ባልተገመተ ሁኔታ ዋጋ የሰጠበትን መግለጫ አሰምቷል። ፌዴሬሽኑ ሁለቱን ተጫዋቾች ላሳዩት መልካም ተግባር ዋጋ በመስጠት በይፋ አመስግኗቸዋል። ምስጋናውም በጹሑፍ እንዲደርሳቸው ወስኗል።
ከመከላከያዎቹ ፍጹምና ዳዊት በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ የወልዋሎው ተስፋዬ ደበበ ዳኛውን ለመከላከል ላደረገው በጎ ተግባር ተመሳሳይ የምስጋና እውቅና ሰጥቶታል።
ፌዴሬሽኑ ባልተለመደ ሁኔታ ለተጫዋቾቹ የምስጋና እውቅና መስጠቱ አስመስግኖታል። ውሳኔው ለተጫዋቾቹ ተግባር እውቅና ከመስጠት ባሻገር ሌሎች ተጫዋቾችም ሊከተሉት የሚገባ መልካም አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑንም መለዕክት የሚያስተላልፍ ነው።
በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ግጭቶች እንዲፈጠሩም እንዳይፈጠሩም በዋናነት ተጫዋቾች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ይህን በማሰብ ለተጨዋቾቹ የሚገባቸውን ይፋዊ ምስጋና ማበርከቱ ያስመሰግነዋል። ወደፊትም አጠናክሮ መቀጠል ቢችል አዎንታዊ ለውጦች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ክፍል ስፖርት

 

የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን በአይነቱ ልዩ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል። መድረኩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለስፖርተኞችና አሰልጣኞች ሙያዊ ስልጠና የሚሰጥበት መሆኑ ተገልጻል።
ስልጠናው ማክሰኞ እለት በወወክማ አዳራሽ የተጀመረ ሲሆን ለአምስት ቀናት የሚቆይ ነው። በሁሉም ቀናት የተለያ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለተሳታፊዎች ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ በተለይም በስፖርታዊ ጨዋነት፣ በህክምና፣ በአመጋገብና በትራፊክ ደህንነት ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው።
ስልጠናውን ከሚሰጡ ባለሞያዎች መካከልም ዶክተር አያሌው ጥላሁን ይገኙበታል። ዶክተር ነጋ ናማጋ በአመጋገብ ላይ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናን በተመለከተ ደግሞ ነርስ ሀያት ከድር እንዲሁም የብስክሌት ስልጠና አሰልጣኝነት ላይ ኢንስትራክተር መላኩ መንግስቱ ይገኙበታል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ረዘነ በየነ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ስፖርኞችና አሰልጣኞች አመራሮችም ጭምር በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የሚያገኙባቸው እንዲሆኑ ያተኮረ ነው።

ክፍል ስፖርት
Wednesday, 16 May 2018 13:45

የውጭ ምንዛሪው ፈተና

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ከተመታ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ እየተባባሰ ሂዶ በአሁኑ ሰዓት ያለው የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ከ 3 ቢሊዮን ዶላር በታች አሽቆልቁሏል። ችግሩ በብዙ መልኩ የተተበተበ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች በሚከተለው መልኩ ዳሰናቸዋል።

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መልሶ ኤክስፖርቱን ሲጎዳው

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለው በኤክስፖርት ገቢውም ጭምር ነው። ወደ ውጪ የሚላኩ የኢትዮጵያ ምርቶች ከማምረቻ ማሽኖች ጀምሮ እስከ ከፊል ያለቀላቸው ምርቶች ድረስ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ከውጪ በመሆኑ የውጪ ምንዛሪ እጥረቱ ኤክስፖርትን በማዳከም ሌላ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የሚፈጥርበት ሁኔታም አለ። በሌላ አነጋጋር የውጭ ምንዛሪ ችግሩ በራሱ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ችግርን ይወልዳል ማለት ነው። እየሆነ ያለውም ይህ ነው።


በተለያዩ የኤክስፖርት ምርት ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከተከተሰው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ምርት አምርተው በኤክስፖርቱ ገበያ መሳተፍ አልቻሉም። በውጪ ገበያ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከተቀባይ ደንበኞቻቸው ጋር በገቡት ውል መሰረት ምርቶቻቸውን በአግባቡና በጊዜ ማቅረብ ካልቻሉ ደግሞ ከገበያ እየወጡ የሚሄዱበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው። ይህም በጊዜ ሂደት የሀገሪቱን የኤክስፖርት ገቢ የበለጠ እየጎዳው የሚሄድ ይሆናል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ

 

የውጭ ባለሀብቶች በአንድ ሀገር መዋዕለ ነዋያቸውን ሲያፈሱ ትርፍ ለመሰብሰብ ነው። በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ የውጭ ባለሀብቶች ኢንቬስት ኢንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸው በዶላር ነው። ለዚህም የተቀመጠላቸው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን አለ። አንድ የውጭ ባለሀብት በዶላር ኢንቬስት የማድረግ ግዴታ ቢኖርበትም ከምርት በኋላ ትርፉን በውጭ ምንዛሪ መንዝሮ የመውሰድ መብቱ ግን የተጠበቀ ነው።


ሆኖም በኢትዮጵያ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋቸውን ያፈሰሱ የውጭ ባለሀብቶች የሚያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ቀይረው ወደ ሀገራቸው መውሰድ የቻሉበት ሁኔታ የለም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የውጭ ባለሀብቶች በተደጋጋሚ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ የቆዩበት ሁኔታም ነበር።


ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ኢንቬስት ያደረጉ የአውሮፓ ባለሀብቶች ህብረት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በባለሀብቶቹ በኩል ከተነሱት ጥያቄዎች መካከለም አንዱ ይሄው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ ነው። ባለሀብቶቹ ትርፋቸውን በዶላር መንዝረው ለመውሰድ ለብሄራዊ ባንክ ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በተገቢው ሁኔታ እየተስተናገዱ አለመሆኑን የገለፁበት ሁኔታ ነበር። በጊዜው ለባለሀበቶቹ የተሰጣቸው ምላሽ በሁለት አቅጣጫ የተመለከተ ነበር። አንደኛው ባለሀብቶቹ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እስኪቃለል ለጥቂት ጊዜ ትዕግስት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ሲሆን ሌላኛው የቀረበው አማራጭ ደግሞ ባለሀብቶቹ በኤክስፖርት ሥራም በመሰማርተው የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ።


የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን ጥያቄ በአግባቡ ለማሳካት በጊዜው ከነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ችግር መሆኑ ተገልፆ ችግሩ በሂደት የሚፈታ በመሆኑ ባለሀብቶቹ እንዲታገሱ የተጠየቀበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ከዚያ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ የበለጠ እየተባባሰ ነበር የሄደው። ሁለተኛው አማራጭ ባለሀብቶቹ ኤክስፖርት በማድረግ የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር የሚለው ነው። ይህ ምላሽ በጊዜው በበርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኩል ቅሬታን የፈጠረበት ሁኔታ ነበር። አንድ የሀገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት መዋዕለ ነዋዩን ሲያፈስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ኤክስፖርት እንዲያደርግ የሚገደድባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም ሁሉም ባለሀብት በዚህ ግዳጅ ውስጥ የሚገባባት አሰራር ግን የለም። ባለሀብቶች ገና ከመጀመሪያው ወደ ኢንቬስትመንት ዘርፉ ሲሰማሩ፤ ዘርፉ ለኤክስፖርት ዘርፍ የተለየ በመሆኑ ሙሉ ምርቶቻቸውን ለኤክስፖርት ገበያ እንዲያውሉ የሚገደዱበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው በርካታ ማበረታቻዎች ከተደረገላቸው በኋላ ነው።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና አላማ የኤክስፖርት ዘርፉን ማሳደግ በመሆኑ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች ከሆኑ መቶ ፐርሰንት ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ የመላክ ግዴታ አለባቸው። እነዚህ ባለሀብቶች ወደዚህ ሥራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት ለማድረግ ቃል ገብተውና ፊርማቸውን አኑረው ነው። በመሆኑም እነዚህ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ልከው የውጭ ምንዛሪ ያስገባሉ፤ከዚህ ገቢ ውስጥም የድርሻቸውን ይወስዳሉ። ሆኖም ከዚህ ውጪ ያሉ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዘርፉ በተለየ ሁኔታ አስገዳጅ ካላደረገውና፤ ባለሀብቱም በውጭ ገበያ የመሳታፍ ፍላጎት ከሌለው በስተቀር በህጉ መሰረት በዶላር ኢንቬስት አድርጎ ትርፉን በዚያው ምንዛሪ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው።


ይሁንና ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጋር በተያያዘ ከተገባው ስምምነትና ከህጉ ውጪ ሁሉም የውጭ ባለሀቶችን ኤክስፖርት አድርጉና ትርፋችሁን በውጭ ምንዛሪ ውሰዱ የሚለው አካሄድ ባለሀብቶች ተጨማሪ የኢንቬስትመንት ሥራን እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ከመሆኑም ባለፈ ሌሎች የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ የሚያደርግ ይሆናል። ይህም ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሀገሪቱን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቬስመንት ፍስት የሚጎዳውም ይሆናል።

 

የኤክስፖርት ማበረታቻውና የውጭ ምንዛሪው ስንክሳር

 

በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርተው በኤክስፖርቱ ዘርፍ ለመስራት የተስማሙ ባለሀብቶች በህጉ መሰረት በርካታ ማበረታቻ ይደረግላቸዋል። ከማበረታቻዎቹ መካከልም የግብር እፎይታ፣ ከውጭ ለሚያሰገቧቸው ማሽኖችና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ መብቶች ተጠቃሚነት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። ባለሀብቶቹ ከሌሎች ባለሀብቶች በተለየ ሁኔታ እነዚህ ማበረታቻዎች ሲደረግላቸው ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት አድርገው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ነው።


ሆኖም በርካታ ባለሀብቶች እነዚህን ማበረታቻዎች ከወሰዱ በኋላ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት አድርጎ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ይልቅ የሀገር ውስጥ ገበያን የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ። ይህ ጉዳይ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደዚሁም በንግድ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳ ቅሬታ ቢሆንም እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ተሰጥቶት አይታይም።

 

የዲያስፖራው ፖለቲካና የውጭ የውጭ ምንዛሪው ፈተና

 

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተደርገው ከሚወሰዱት ምንጮች መካከል አንዱ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚላከው የውጭ ምንዛሪ (remittance) አንዱ ነው። ከንግድ ሚኒስቴርም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከውጭ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ መጠን ኢትዮጵያ በኤክስፖርት ምርት ከምታገኘው ገቢ መብለጥ ችሏል። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ እየጦዘ ከመጣው የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ጋር በተያያዘ የመንግስት የፋይናስ ጉልበት ለማዳከም በሚል የተከፈተ ዘመቻም አለ። ይህ ዘመቻ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የውጭ ምንዛሪ ማዕቀብን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እንዲጥሉ የሚያሳስብ ነው። እንቅስቃሴው በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀንሱ ወይንም መንግስት ኪስ እንዳይገባ ከባንክ ሥርዓት ውጪ ያለውን የመላኪያ ዘዴ እንዲጠቀሙ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ተሰምቷል። ይህ ጥሪ ምን ያህል ግቡን እንደመታ በግልፅ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ይሁንና ምንም አይነት ተፅዕኖን አያመጣም ብሎ መደምደም ግን አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ይሄንኑ ጉዳይ አስመለክተው በቅርቡ በአንድ መድረክ የሚከተለውን ምላሽ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።


“መንግስትን ለማስደንገጥ የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ትክክለኛ መፍትሄ አይደለም። ልጅ ሲያጠፋ የምንቀጣው ራት እየከለከልን አይደለም። እያበላን በድሮው ከሆነ እንቆነጥጣለን በአሁኑ ከሆነ ደግሞ Time out ነው የምንለው። ዲያስፖራ መንግስት ለመቆንጠጥ ዶላር አንልክም ሲሉ። ማነው እየተጎዳ ያለው ሲባል ዝቅተኛ ዶላር የማመንጨት አቅም ያላቸው ነጋዴዎች ናቸው።”

መደበኛ ያልሆነው የንግድ አካሄድና የውጭ ምንዛሬው

 

መንግስት በቂ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ ባልቻለ ቁጥር ነገሮች መደበኛ ያልሆነ አካሄድን መከተላቸው እሙን ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተለይ የጥቁር ገበያ መጠናከር አንዱ መደበኛ ያልሆነው ገበያ ሥርዓት መጠናከር ማሳያ ነው። ከዚህም ባለፈ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ከላኩ በኋላ በመደበኛው የባንክ ሥርዓት የውጭ ምንዛሪን የማያስገቡ ባለሀብቶችም መኖራቸው ይታወቃል።


በብሄራዊ ባንክ ያለው የውጭ ምንዛንረ ወረፋ የሰለቻቸው እንደዚሁም በቂ ከዚህም በኋላ ቢሆን በቂ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ያልቻሉ አስመጪዎች ያላቸው አማራጭ ፊታቸውን ወደ ጥቁር ገበያው በማዞር የዶላር ሸመታን ማካሄድ ነው። ይህም ሁኔታ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ በኩል ያለውን የምንዛሪ ልዩነት የበለጠ እያሰፋው የሚሄድ ይሆናል። ለዚህ ብቸኛው መፍትሄ መንግስት በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ መቻል ብቻ ነው።


ከዚህ ባለፈ በአንድ ሀገር ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ሀብት በሚኖርበት ወቅት በባለሀብቶቹ በኩል በራስ መተማመን ስለማይኖር በብር የሚገኘውን ገቢ በውጭ ምንዛሪ ቀይሮ በውጭ ባንክ የማስቀመጥ ሁኔታም ይከሰታል። በሙስና ተጎጂ የሆኑ ሀገራት አንዱ የውጭ ምንዛሪ ድርቀት ይህ ነው። ይህ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ሀብት በዘረፋ ከመገኘቱ ባለፈ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ቋሚ ሀብቱ ለሀገር ተጨማሪ ጉዳትን የሚያስከትለው በገንዘብ ማሸሻነት የሚያገለግል መሆኑ ነው። ይህ ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው እነዚህ የገንዘብ ማሸሺያ የሆኑ የንግድ ተቋማት አንዳች አይነት እርምጃ ሲወሰድባቸው ብቻ ነው።


በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲከሰት የሚያስከትላቸው ችግሮች ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ናቸው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢንቨስትመንትን ይጎዳል፣ የንግድ ሚዛንን ያዛባል፣በውጭ እዳ ክፍያ ላይ የራሱን የሆነ ተፀዕኖን ያሳድራል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት ፈተናዎች መካከልም ይሄው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ አንዱ ነው። ዶክተር አቢይ በቅርቡ እንደተናገሩት የፈተናው መፍትሄ ዓመታትን የሚፈጅ ነው።

ክፍል ኢኮኖሚ

 

የአትሌች መፍለቂያ በሆነችው ግን ደግሞ ብዙዎችን የሚያሳትፉ የሩጫ መድረኮችን በማዘጋጀት የማትታወቀው በቆጂ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የ5 ኪ.ሜ. ህዝባዊ የጎዳና ላይ ሩጫ ይካሔዳል። የሩጫው ዋና አላማ አሳሳቢው የአለማችን የአየር ንብረት ላይ ግንዛቤ መፍጠርና ለስፖርተኞች አማራጭ የውድድር መድረክ ማዘጋጀት እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።


የውድድሩ አዘጋጅ ጭላሎ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ከተለያዩ ተባባሪ አካላት ጋር የሚያዘጋጀው የሩጫ መድረኩ የፊታችን ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በቆጂ ከተማ ላይ የሚካሔድ ሲሆን፤ ‹‹አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ›› በሚል መሪ ቃልንም ያነገበ ነው።


‹‹የአለም ሙቀት መጨመር በአትሌቶች ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ግንዛቤ የመፍጠር አላማ ያገበ ነው›› ያሉት አዘጋጆቹ፤ ‹‹ዶፒንግ እንጸየፍ›› በሚል ቃልም በተከለከለ አበረታች መድሀኒት ዙሪያ መልዕክት እንሚተላለፍም አስታውቀዋል።
በሩጫው እለት ተሳታፊዎች ችግኞችን ይዘው በመሮጥና መጨረሻ ላይም ችግኞቹን በመትከል አካባቢ ጥበቃና ደህንነት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። በመድረኩ ላይ ከከተማዋ ተሳታፊዎች በተጨማሪ ስመ ጥር አትሌቶችና አሰልጣኞች፣ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ይገኛሉ ተብሏል።

ክፍል ስፖርት

 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ22ኛ ሳምንት መርሀግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም የመከላከያ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ በከፍተኛ ረብሻ መቋረጡ ይታወሳል። በእለቱ የወልዋሎ ተጫዋቾችና የቡድን መሪ የመከላከያን 2ለ1 መሪነት ያረጋገጠች ግብን ባጸደቁት ዳኛው እያሱ ፈንቴ ላይ አካላዊ ጥቃት በመፈጸማቸው ጨዋታው የተቋረጠው። ለረብሻውን ለጨዋታው መቋረጥ መንስኤ በሆኑ አካላት ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል። የቅጣት ውሳኔን ተከትሎም የተለያዩ አስቴየቶች በመሰንዘር ላይ ናቸው።


ፌዴሬሽኑ ባስተላለፈው ቅጣት መሰረት በእለቱ ዳኛውን ሜዳ ውስጥ ገብተው በማሯሯጥና መሬት ላይ በመጣል ድብደባ የፈጸሙት የወልዋሎ ክለብ የቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረጸድቅ ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እድሜ ልክ ታግደዋል። ግለሰቡ ተጨማሪ 20ሺ ብር ቅጣትም የተጣለባቸው ሲሆን፤ ገንዘቡንም ክለቡ እንዲከፍል ተብሏል።


በክለቡ ላይም 250ሺ ብር ቅጣት የተላለፈ ሲሆን፤ በሶስት ግብ በፎርፌ ተሸንፎ ነጥቡ ለመከላከያ እንዲመዘገብ ወስኗል። ከዚህ በተጨማሪም በክለቡ ተጨዋቾች ላይም ፌዴሬሽኑ የገንዘብና የጨዋታ እገዳ ቅጣት አስተላልፏል። የክለቡ ተጨዋቾች የሆኑት በረከት አማረ፣ አለምነህ ግርማ፣ አስሪ አልማዲ ማናዬ ፋንቱና በረከት ተሰማ ዳኛውን በማሯሯጥና የድብደባ ሙከራ በማድረግ ከእግር ኳስ ተሳትፎ የ6ወር እገዳ እና የ10.000 ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል። ሌላኛው የክለቡ ተጨዋች የሆነው ዋለልኝ ገብሬ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ዳኛውን በመደብደቡ ለ2አመት እገዳ 15.000 ብር ቅጣት እንደተጣለበት ታውቋል።

ክፍል ስፖርት

 

በብሩክ አያሌው

የኢፌዴሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ) ደርጊቱ በወንጀል ከስ አቅራቢነት የሚያሰቀጣው እና ከስድስት ወር እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት የሚሆነው ጥፋተኛው ጉዳት ያደረሰው በመርዝ ወይም በገዳይ መሳሪያ ወይም የአካል ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ሌላ መሳሪያ በመጠቀም እንደሆነ ነው በማለት ይደነግጋል።

በዚህ ድንጋጌ አተገባበር ዙሪያ ብዙ ጊዜ በፍ/ቤቶች አካባቢ የአተረጓጎም ልዩነት ይስተዋላል።በአንድ በኩል አጥፊው ድርጊቱን ሲፈጽም መሳሪያ ከተጠቀመ የደረሰው ጉዳት ግምት ዉስጥ ሳይገባ በዚህ ድንጋጌ ስር ሊከሰስ እና ሊቀጣ ይገባል የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ አጥፊው ድርጊቱን የፈጸመው መሳሪያ ተጠቅሞ ቢሆንም እንኳን በተጎጂው ላይ የደረሰ ጉዳት ከሌለ መሳሪያዉን በመጠቀሙ ብቻ በዚህ ድንጋጌ ስር ተከሶ ሊቀጣ ይገባል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል።

የመጀመሪያውን አቋም የሚደግፉት ተከራካሪዎች የሚያቀርቡት ምክንያት አጥፊው መሳሪያውን ተጠቅሞ ድርጊቱን ከፈጸመ የደረሰው ጉዳት ይነስም ይብዛም ድርጊቱን ሲፈጽም ጉዳት የማድረስ ሀሳብ አለው የሚል ነው።መከራከሪያቸውን ሲያጠናክሩም ጉዳት አልደረሰም ከተባለም ቢያንስ በሙከራ ሊከሰስ ይገባል ይላሉ።ሙከራ ሲባል በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27(1-3) ትርጉሙና ዝርዝር ነገሮቹ የተገለጸ ሲሆን አንድ ሰው ወንጀል ለማድረግ ጀምሮ የወንጀል ድርጊቱን እስከመጨረሻው ድረስ ያልተከታተለ ወይም ለመከታተል ያልቻለ እንደሆነ ወይም የወንጀሉ ድርጊት እንዲፈጸም እስከ መጨረሻው ድረስ ተከታትሎ የሚፈልገውን ዉጤት ለማግኘት ያልቻለ እንደሆነ በመሞከሩ ብቻ ጥፋተኛ ተብሎ ወንጀሉ ቢፈጸም ኖሮ ሊቀጣ በሚችልበት ድንጋጌ የሚቀጣበት የህግ መርህ ነው። በመሳሪያ በመጠቀም ድብደባ ተፈጽሞ አጥፊው በድርጊቱ ያደረሰው ጉዳት ባይኖርም ድርጊቱን ሲፈጽም መሳሪያ መጠቀሙ በመሳሪያው ጉዳት የማድረስ ሀሳብ ስላለው ያሰበውን ውጤት ባያገኝ አንኳን በመሞከሩ ብቻ በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር ተከሶ መቀጣት አለበት ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላን ሰው በዱላ ጭንቅላቱን ቢመታውና በተመታው ሰው ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት ባይኖር ደብዳቢው በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር ያለውን ድርጊት ለመፈጸም ሞክሯል ተብሎ በዚሁ ድንጋጌ ስር ያለውን ቅጣት መቀጣት አለበት ማለት ነው።

ሁለተኛውን አቋም የሚደግፉት ደግሞ አጥፊው በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር ጥፋተኛ ነው ለማለት ድርጊቱን የፈጸመው ጉዳት ሊያደርስ በሚችል መሳሪያ ሆኖ፣ሊታይ የሚችል ጉዳት ካደረሰ እንዲሁም የደረሰው ጉዳት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 560 ስር የተገጸው የእጅ እልፊት ጉዳት ወይም በአንቀጽ 555 ስር የተገለጸው ከባድ የአካል ጉዳት ውጭ ከሆነ ነው በሚል ይከራከራሉ።እኔም የዚህ አቋም ደጋፊ ስሆን ይሄንን ክርክር ለማጠናከር የሚከተሉትን መከራከሪያዎችን አቀርባለሁ

1. የወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ከአንቀጽ 556(1) ጋር ተያይዞ መተርጎም ይኖርበታል። በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(1) ላይ ጥፋተኛው በአንቀጽ 555 ከተገጸው ከባድ የአካል ጉዳት ውጪ የሆነ ጉዳት ካደረስ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል።አከራካሪው የወንጀል ህግ ድንጋጌም ከአንቀጽ 556(1) የቀጠለ ሲሆን ሁለቱ ድንጋጌዎች ተያይዘው ሲተረጎሙ አጥፊው ሊቀጣ የሚችለው በንዑስ ቁጥር አንድ ላይ የተገለጸውን ጉዳት በመሳሪያ ከፈጸመው ብቻ ነው።ይሄ ማለት መሳሪያ ከመጠቀሙ ባሻገር ያደረሰው ጉዳት ሊኖር ይገባል ማለት ነው።ድንጋጌው በዚህ አግባብ ካልተተረጎመ አና የመጀመሪያውን አቋም የሚደግፉት ሰዎች አንደሚሉት ከተተረጎመ አጥፊው መሳሪያ ስለተጠቀመ ብቻ የደረሰ ጉዳት ሳይኖር በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(1) ላይ ከተቀመጠው ቅጣት የከበደ ቅጣት ከ6 ወር ያላነሰ ቀላል እስራት ይቀጣል ማለት ነው።ይሄ ማለት ደግሞ መሳሪያ ሳይጠቀም የአካል ጉዳት ያደረሰ አጥፊ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ተቀጥቶ፣ መሳሪያ ተጠቅሞ ጥፋት ፈጽሞ ጉዳት ሳያደርስ ከ6ወር ያላነሰ ቀላል እስራት ሊቀጣ ነው ማለት ነው።

2. የወንጀል ህጉ ሊደርስበት ካሰበው ግብ እና ከህግ አውጭው ሀሳብ አኳያ መተርጎም ያስፈልጋል (የወንጀል ህግ አንቀጽ 3/4/)።ይሄ ሲባል በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ላይ ህግ አወጪው አጥፈው መሳሪያ በመጠቀሙ ከፍ ያለ ቅጣት እንደሚቀጣ ያስቀመጠው መሳሪያ መጠቀሙን ብቻ ለመቅጣት ሳይሆን አጥፊው መሳሪያ ተጠቅሞ ድብደባ ከፈጸመ በተበዳዩ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ያደርሳል በሚል ግምት ነው።ድርጊቱ በመሳሪያ ተፈጽሞ የደረሰ

ጉዳት ከሌለ ወይም የደረሰው ጉዳት የእጅ እልፊት ከሆነ በአንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር የተገለጸውን ቅጣት መቅጣት የህግ አውጭው አላማ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም።

3. በሙከራ መጠየቅ አለበት የሚለውን መከራከሪያ በተመለከተ አጥፊው ድርጊቱን ፈጽሞ ውጤቱን ስላገኘ ድርጊቱ በሙከራ የቀረ ነው ማለት አያስችልም። አጥፊው ድርጊቱን ሲፈጽምም ሃሳቡ ጉዳት ለማድረስ ስለመሆኑ ማወቅ አይቻልም። ስለሆነም ይሄ መከራከሪያ ብዙም የሚያስኬድ አይደለም።ለምሳሌ አጥፊው በኤርገንዶ ጫማ ወርውሮ ሰው ቢደበድብ እና የደረሰ ጉዳት ባይኖር የተወረወረው ጫማ በራሱ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል አይደለም። በዚህ ጊዜ ጉዳት የማድረስ ሀሳብ አለው ማለት አይቻልም።

ሲጠቃለል አጥፊው መሳሪያ ተጠቅሞ ድብደባ ፈጽሞ የደረሰ ጉዳት ከሌለ በወንጀል ህግ አንቀጽ 560(1) ስር ከሚጠየቅ በስተቀር በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር መጠየቁ ተገቢነት የለውም።

ክፍል ምልከታ

 

ኪዳኔ መካሻ (የህግ ባለሞያ)

ሊያውም ሁለቴ ነዋ። ሕገመንግስት ህዝቡ መብቶቹን ለመንግስት እንዲያስተዳድረው አሳልፎ ሲሰጥ የሚዋዋለው ማህበራዊ ውል ነው።


የሀገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ በመሆኑ ከሌሎች ሕጎች የተለየ ክብደት አለው። የሚሻሻለውም በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ የማሻሻያ ስነስርአቶችን በተከተለ መንገድ ነው። የተማማልንበት ቃል ኪዳናችን ነውና ከሌሎች ሕጎች የበለጠ መከበርና መታፈር አለበት።


ለዚህም ነው ብዙዎቻችን ሕገመንግስት የሚለውን ቃል ከግለሰባዊም ሆነ ከሌሎች የመብት እና የግዴታ ጉዳዮች ጋር የምናያይዘውና እንዲከበር የምንፈልገው።


ለዚህም ነው እኛ ሳንሰማ፣ ሳንወያይበት እና ድምፅ ሳንሰጥበት ሕገመንግስታዊውን ስርአት ሳይከተል ተሻሽሏል ብንባል ለማመን የሚከብደን።


እውነታው ግን አዎ ተሻሽሏል ሊያውም ሁለት ጊዜ የሚል ነው።


ይህን ብዙዎቻችን የማናውቀውን እውነታ ያረጋገጠልን ፤በወሎ ዩንቨርስቲ የሕግ መምህሩ እረዳት ፕሮፌሰር አቶ ዘላለም እሸቱ በሀረማያ ዩንቨርስቲ የሕግ መፅሄት ላይ በ 2007 ዓ.ም ባሳተመው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ነው። “ሕገመንግስታዊ ያልሆኑ የሕገ መንግስታዊ ማሻሻሎች በኢትዮጵያ” የሚለው የህግ መምህሩ የአቶ ዘላለም ፅሁፍ፣ የተጠቀሱት ማሻሻያዎች ሕገመንግስታዊነት ላይ ሙያዊ ፍተሻና ማብራሪያ ሰጥቶባቸዋል። እኔ ደግሞ ጥናታዊ ፅሁፋን ዋነኛ ነጥቦች በአጭሩ እነሆ ብያለሁ።


የመጀመሪያው ማሻሻያ በ1989 ዓ.ም በፌደራሉ መንግስትና በክልል መንግስታት የጋራ የግብር ስልጣንን በሚደነግገው በአንቀፅ 98 ላይ የተደረገው ነው።


ሁለተኛው ደግሞ በ1997ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበትን የ 10 አመት የጊዜ ሰሌዳ የሚደነግገው አንቀፅ 103(5) ላይ እንዳስፈላጊነቱ በሁለቱ ም/ቤቶች የጋራ ውሳኔ የጊዜ ሰሌዳው እንዲራዘም ያደረገው ማሻሻያ ነው።


ይህ ማሻሻያ የተደረገበት ምክንያት የ1997 ምርጫ እና የቆጠራው በዚያው አመት ተደርበው በመዋላቸው የተነሳ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ተብሎ መሆኑን ፅሁፉ ይጠቅሳል።


ሁለቱም ማሻሻያዎች ሕገመንግስቱን የጣሱበት ምክንያት ሕገመንግስቱ ላይ የተቀመጡትን የማሻሻያ ስርአቶች ባለማክበራቸው ነው።


ህዝብ ያልተወያየባቸውና እንዲሻሻሉ ያልወሰነባቸው በመሆናቸው፤ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ባለመውጣታቸው፤ ከማሻሻያው በሁዋላ በታተሙ የሕገመንግስቱ ቅጂዎች ላይ ባለመታተማቸው እና በሌሎችም ጥናቱ ላይ በዝርዝር በተጠቀሱ ምክንያቶች እንደሆነ አቶ ዘላለም በምርምር ፅሁፋቸው ውስጥ ጠቅሰዋል።


በተጨማሪም እንዲህ አይነት ስርአቱን ያልተከተሉ ማሻሻያዎች ህገመንግስቱን በዘፈቀደ ለሚጥሱ ማሻሻያዎች እንደሚያጋልጡ ጠቅሰዋል።


ሕገመንግስታዊነትን የመተርጎም ስልጣኑ የተሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ቤት ቢሆንም በማሻሻያዎቹ ውስጥ ም/ቤቱም ተሳታፊ ስለነበር፥ ገለልተኛ ሆኖ የራሱን ውሳኔ መርምሮ ሊወስን ስለማይችልና ፍ/ቤቶችም ጉዳዩን የመዳኘት ስልጣን ስለሌላቸው፤ ገለልተኛ የሆነ የሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤት አይነት ተቋም መኖር እንዳለበት ጥናቱ ጠቁሟል።

 

(DIRETUBE)
..

ክፍል ምልከታ

 

ንጉሴ ረዳኢ www.abyssinialaw.com

1. የመዘዋወር ነፃነት አለም አቀፋዊ አንድምታው

 

የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ከሚያገኛቸው አያሌ የተፈጥሮ መብቶች ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የሰው ልጆችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ከሐይማኖት፤ ከባህል እና ከሌሎች የተፈጥሮ ህግጋት ጀምርን ስንመለከተው ፅኑ መሰረት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። በአለማችን ታሪክ ይህ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት በአንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች ላይ ተገድቦ የነበረ ቢሆንም በአብዛኛው ግን ሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸው ሲከበር ቆይቷል። ይሄንን ተፈጥሮአዊ መብት በመጠቀም የተለያዩ የአውሮፓ ሰዎች አዲስ ግኝትን፤ የመካከለኛውና የሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ደግሞ ንግድን በማጧጧፍ ለሀገራቸው እና ለአህጉራቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አበርክተዋል። ይህንን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ማግና ካርታ (Magna Carta) አይነት ጥንታዊ ሰነዶች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን አውጀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በታላቋ ሮም የነገሱ አብዛኛው ነገስታት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነትን ሲያከብሩ መቆየታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።


ይሁን እንጅ አለማችን በታሪኳ ካጋጠሟት ጠባሳ ታሪክ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሁለተኛው የአለም ጦርነት እና ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ እጅግ አስከፊ የመብት ጥሰቶች መካከል ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ይጠቀሳል። አንድ ችግር ሲፈጠር ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ወይም መንገድ ማበጀት የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪው በመሆኑ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የተፈጠሩ የመብት ጥሰቶችን በማስመልከት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው ነበር። ከተወሰዱ እርመጃዎች መካከል አለም አቀፍ የሰበዓዊ መብት ተቋማትን መመሰረትና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ። በዚህም መሰረት በተቋም ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲቋቋም በሰብዓዊ መብት ሰነድ ደረጃ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant on Civil and Political Rights) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13[1] ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት እውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል። በተለይ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት በአንቀፅ 12 ላይ በመርህ ደረጃ ይህ መብት ገደቦች የሌሉበት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በህግ በተደነገጉ ቀድመ ሁኔታዎች አማካኝነት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ከብሔራዊ ደህነት፤ ከህዝብ ሞራል እና ጤና ጋር የሚያያዙ ናቸው። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ የሚወጣ ህግ ከአድሎ ነፃ የሆነ እና የትኛውንም ህዝብ በተለይ የሚጎዳበት አግባብ ሊኖር እንደማይገባው ይደነግጋል። በአጠቃላይ አለማችን አሁን በደረሰችበት የአእምሮ ማሰብ አድማስ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የሰው ልጅ ከተሰጡ መሰረታዊ መብቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ከመሆኑ አንፃር የአለማችን የህግ ሰዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ ማለት ይቻላል። በመሆኑም በአለም አቀፍ የልማዳዊ ህግ መስፈርቶች መሰረት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የአለም አቀፍ የልማድ ህግነት ደረጃ ደርሷል ማለት እንችላለን። በመሆኑም ማነኛውም ሀገር፤ በሀገር ውስጥ ያለ አስተዳደራዊ ክልል እንዲሁም ማነኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ይህንን መብት የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለበት።
 
2.  ኢትዮጵያ የመዘዋወር ነፃነትን እንዴት ትመለከተዋለች?
 
የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ከሌሎች መብቶች በተሻለ ሲከበር እንደነበር ማየት እንችላለን። ከኦሮሞ የጉድፈቻ ባህል ጀምረን እስከ አማራ እና ትግራይ የእንግዳ ተቀባይነት ልማድ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ከህግ አልፎ ህብረተሳባዊ መሰረት እንዳለው እንረዳለን። ከዚህ በተጨማሪ በአብዛኛው የኢትዮጵታ ክፍሎች የሚታወቀው “ቤቱ ስትሄድ የሚጮህ ውሻ ብቻ ነው” የሚለው አባባል ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የህዝቡ የቆየ ባህል እንደሆነ ያስረዳናል። በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ ለአካባቢው አዲስ የሆነ በተለምዶ አጠራሩ ፀጉረ ልውጥ ወደ ቀየው ሲሄድ የተለየ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ለማወቅ የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ክፍል አንደ ጊዜ መጎብኘት በቂ ነው። በተናጠል ከሚደረገው መዘዋወር በተለየ በሀገራችን በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የተነሳ በተከሰቱ የቡድን የህዝብ ዝውውሮች በተሳካ ሁኔታ ተፈፅመው አንዱ ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር በአሁኑ ሰዓት ለመለየት እስከሚያስቸግር ድረስ ተዋህደው እየኖሩ ይገኛሉ።ይሄንን የኑሮ ዘይቤ በሚያጠናክር ሁኔታ የሚነገር “ሩቅ ካለ ዘመዴ ጎረቤት ያለ ባእድ ይሻለኛል”  የሚለው አባባል እንግዳን ተቀብለው አብረው ከሚኖሩ ህዝቦች በዘለለ በማያውቁት ቀየ በመሄድ ጎጇቸውን የሚቀለሱ ህዝቦች ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያላቸውን ተላምዶ የመኖር ባህል ያሳየናል። በመሆኑም በህግ የተሰጠው ትርጓሜ በቀጣይ የሚታይ ሲሆን በማህበረሳዊ አንድምታው ስናየው በኢትዮጵያ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንደ ባህል የሚታይ ልማድ ነው። 


በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር የመዘዋወር ነፃነትን ስንመለከተው በሰነድ ማስረጃ የተደገፈ የመዘዋወር ነፃነት የሚገድብ ታሪካዊ ክስተት ለማግኘት ያስቸግራል። በተቃሪኒው የኢትዮጵያ ያለፉት መንግስታት በተለያዩ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክናያቶች ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አንድን ህዝብ ከአንድ አካባቢ አንስተው ወደ ሌላ አካባቢ መወሰድ የተለመደ አሰራር ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የመዘዋወር ነፃነትን ወጥ በሆነ መንገድ ተቀብላው እንደቆየች የባህል እና መንግስታዊ አሰራሮች ያስረዱናል። 
 
3.  የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከቱ ህጎች በአሁኗ ኢትዮጵያ
 
ከላይ የተመለከትነው ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ እውነታ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ነፍስ ዘርቶ እንዲሄድና ተፈፃሚ እንዲሆን በህግ አግባብ መውጣት ይኖርበታል። ይሄንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ የተለያዩ ህጎችን ሲያወጣ የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ድንጋጌዎችን በማካተት እና የመዘዋወር ነፃነት የሚመለከቱ አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረም የመጀመሪያውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ጥረት አድርጓል። በመሰረቱ የአንድን ሃገር በአንድ ጉዳይ ላይ ያላትን የህግ አቋም ስንመለከት ከሀገሪቱ የበላይ ከሆነው ህግ መጀመር የተለመደ ነው። በዚህም መሰረት በ1995 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት ስናየው የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከት ድንጋጌ አካቷል። በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 32(1) መሰረት ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው። በዚህ አንቀፅ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ በመረጠው በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር ነፃነት ሲኖረው ከዚህም በላይ ይህ ግለሰብ በተዘዋወርበት አካባቢ በተመቸው ቦታ ላይ መኖሪያውን መስርቶ የመኖር ነፃነት ተሰጥቶታል። ከዚህ አንቀፅ ጋር በተያያዘ የሕገ-መንግስቱ ሌላው ድንጋጌ አንቀፅ 41(1) እንደሚገልፀው ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማነኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው። ከዚህ አንቀፅ እንደምንረዳው ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የትኛውም አካባቢዎች በመሄድ የፈለገውን ስራ በመመረጥ የመስራት መብት እንዳለው ነው። በመሆኑም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 31 እና 41 መሰረት ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፈቃድ በመረጠው የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በመሄድ መኖሪያውን የመመስረት እና በፈለገው ሙያ ላይ የመሰማራት መብት አለው። ከሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ስንወጣ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን እናገኛለን። እነዚህ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 9(4) መሰረት የሀገሪቱ ህግ አካል በመሆናቸው ኢትዮጵያ እነዚህን ስምምነቶች የማክበር ግዴታ አለባት። ከላይ እንደተመለከትነው የመዘዋወር ነፃነትን በሚመለከት ከወጡ እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መካከል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant on Civil and Political Rights) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13 ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት እውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ካፀደቀችው ሕገ-መንግስት በዘለለ በፈረመችው (ባትፈርመው እንኳን የአለም አቀፍ የልማዳዊ ህግነት ደረጃን በደረሱት) የመዘዋወር ነፃነትን በሚመለከቱት እነዚህን አለም አቀፍ ስምምነቶችን የማክበር ግዴታ አለባት።  


በመርህ ደረጃ አንድ ህግ ሲዎጣ የወጣውን ህግ ተፈፃሚነቱን ለማረጋግጥ እንዲያስችል ህጉ የሰጠውን መብት ጥሰው በተገኙ አካላት ላይ ቅጣት ማስቀመጥ የተለመደ ነው። በዚህ መሰረት ስንመለከተው የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ማነኛውንም ጥሰት የፈጠረ አካል ላይ የወንጀል ቅጣት እንደሚጠብቀው በ2004 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ ያስረዳናል። በዚህ የወንጀል ህግ አንቀፅ 607 መሰረት ማንም ሰው በሕግ ሥልጣን ሳይኖረው ሌላው ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በነፃ እንዳይዘዋወር የከለከለ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም መቀጮ እንደሚቀጣ በመግለፅ ጥፋቱን የፈፀመው የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ ግን ጉዳዩ በአንቀፅ 407 መሰረት እንደሚታይ ይገልፃል። የወንጀል ህጉ አንቀፅ 407 ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን የሚመለከት ሲሆን እንደቀረበው ጉዳይ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከ 15 ዓመት ከባድ ቅጣት ሊደርስ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ እንደቀረበው ማስረጃና ጉዳዩ ከተፈፀመበት ሁኔታ አንፃር ጉዳዩን ዘር ማጥፋትን ወደ ሚመለከተው አንቀፅ 269 (ሐ) መሰረት የሚታይበት የህግ አግባብ ተቀምጧል። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ባለው የኢትዮጵያ ህግ አንፃር የመዘዋወር ነፃነት በህግ ሙሉ ለሙሉ እውቅና የተሰጠው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ይሄንን ነፃነት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መገደብ ከቀላል እስራት እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ የወንጀል ሃላፊነትን ያስከትላል።
 
4. በክልል የተገደበው የመዘዋወር ነፃነት
 
የአለም አቀፍ ህግ ሙህራን አንድ ሃገር ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የሚጠበቅባትን ደረጃዎች ያስቀምጣሉ። ከእነዚህ ደረጃዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የህግ ማእቀፍ መዘርጋት ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ግን ተቋማትን መመስረትና ሌሎች የወጣውን ህግ የሚያስፈፅሙ እርምጃዎች መውሰድ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ህግ ማውጣት የሚያወሩትን ላውራ (talking the talk) የሚባል ዋስትና የሌለው እርምጃ በመሆኑ ሌሎች የወጣውን ህግ በትክክል የሚያስተገብሩ እርምጃዎች (walking the talk) መውሰድ በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዘንድ ትኩረት ሲሰጥበት ቆይቷል።ሐገራችን ኢትዮጵያ ከቀድሞ መንግስታት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የመፈረም ችግር ሳይታይባት ቆይቷል። ይሁን እንጅ በየጊዜው ከሚከሰቱ ችግሮች እንደምንረዳው እነዚህ የሚዎጡ ህጎችና የሚፈረሙ ስምምነቶች በተለይ በአስፈፃሚ አካላት ተነበው የማያውቁ በአልፎ ሂያጅ ብቻ ለትምህርትነት የሚያገለግሉ ሰነዶች ሁነው ቆይተዋል። የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ጉዳዩን ይበልጥ የሚያወሳሰብ እና ከላይ ያየናቸውን የወግ እና የባህል ሁኔታዎችን ጥያቄ ውስጥ ባስገባ መልኩ መከሰት የጀመረው የመብት ጥሰት በተለይም ሀገሪቱ የፌደራል ስርዓትን መከተል ጀምሬያለሁ ባለች ማግስት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም አካባቢዎች በቋንቋ እና በተለያዩ ማንነቶች መሰረት በክልል ከመከፋፈላቸው ጋር ተያይዞ በተለያየ አጋጣሚዎች የመዘዋወር ነፃነት ትልቅ እክል ሲገጥመው ቆይቷል። በተለይም የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢ ቤት ንብረታቸው እየተቀማና እየተቃጠለ፤ አለፍ ሲልም ህፃናትና አዛውንት ሳይቀሩ ሲገደሉ እና ሲፈናቀሉ መቆየታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች መረጃዎች ቀረበው ተሸፋፍነው አልፈዋል። ይህ የአማራ ተወላጆች ላይ ብቻ ሲፈፀም የነበረው የመፈናቀል እና የመዘዋወር ነፃነትን የመነጠቅ ድርጊት ባለፉት አራት እና አምስት አመታት አድማሱን አስፍቶ በኦሮሞ እና በትግራይ ተወላጆች ላይም ተፈፅሟል። ይሁን እንጅ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው የመፈናቀል እና የመዘዋወር ነፃነትን የመነጠቅ ወንጀል እንደሌሎች ሁሉ በጊዜ እና በቦታ የተገደበ እና ጊዜያዊ አለመሆኑን በዚህ አመት ተፈፀሙትን ሁነቶች ብቻ መመልከት ይበቃናል። በተለይ ከሰሞኑን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በቦሎ ዲዴሳ ቀበሌ መስተዳደር ተፃፈ ተብሎ የተሰራጨውን ደብዳቤ እና ከክልሉ ተፈናቅለው ባህርዳር የሚገኙትን ህፃናት፤ አዛውንቶች እና ሴቶችን ስንመለከት ጉዳዩ በቶሎ የህግ እርማት ካልተሰጠው ለሃገሪቱ ህልውናን የሚፈታተን ሁኔታ ይፈጥራል። የፁሁፉ አላማ አይደለም እንጅ የተለያዩ በሀገሪቱ በግልፅ የተፈፀሙ የመንቀሳቀስ መብትን የሚጥሱ ሁኔታዎችን መዘርዘር ይቻል ነበር።


በመሆኑም ሀገሪቱን የሚያስተዳድራት አካል የሚከተሉትን ጥያቄዎች ተመልክቶ አስፈላጊውን መልስ በመስጠት መፍትሄ ማምጣት ይኖርበታል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት አንድ ግለሰብ ከሚኖርበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ እንዳይሰራ በሚከለክል መልኩ በክልል መስተዳድሮች የማፈናቀል ስራ ሲሰራ በተዘረጋው የህግ ማእቀፍ አማካኝነት አጥፊዎች ወደ ህግ እንዲይቀርቡ የማይደረግበት ምክናያት ምንድን ነው? በተለይም የክልል መስተዳድሮች በክልል የመስራት መብትን ለዚህ ክልል ተወላጅ ብቻ በመቁጠር የተለያየ ግፎችን እና ወንጀል ሲሰሩ ጉዳዩ የሚመለከተው አቃቤ ህግ ለምን ዝምታን መረጠ? እነዚህን ጉዳዮች እልባት ይሰጣሉ ተብለው የተቀመጡት የሕገ-መንግስቱና የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች በዳኞችችን ተነበው በአጥፊዎች ላይ የሚበየኑት መቸ ይሆን? በተለይም በአሁኑ ሰዓት እንኳን መፈናቀልን የሰፈር ፀብን በተለያየ ማስረጃ በሚያዝበት ወቅት የማስረጃ ጥያቄ እንደ ችግር ሊነሳ አይችልም። እንደዛ ከሆነ በሽህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በሽብርተኘነት የሚከስ አቃቢ ህግ እንዴት በግልፅ ወንጀል የሰራን የክልል ባለስልጣን ለመጠየቅ ወኔ አጣ? የትላንት አምራች ዜጎች ዛሬ ተፈናቅለው ሸራ ዘርግተው በየጎዳናው የወደቁ ለማን አቤት ይበሉ? በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች የሚታዩ ማስረጃዎችን እንደ በቂ ጥርጣሬ በመውሰድ ምርመራ ለመጀመር የሚስችለውን የፖሊስ ወኔ ማን ሰለበው? በአጠቃላይ ጥያቄው ህግ ይከበር ነው! ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ስራቸውን ይስሩ! ወንጀለኞች ወደ ህግ ይቅረቡ። አሁንም በዙ ነፍሶች መልስን ይሻሉ። ጉዳዩን በተዳፈነ ቁጥር እያበጠ ስለሚሄድ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ እየተገባ ነው።  
 
በህዝቦቿ እኩልነት የምታምን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!   

ክፍል የኔ ሃሳብ
Wednesday, 16 May 2018 13:36

ሰውና ስብሐት

 

ጥያቄ፡- አጠቃላይ ሰው ለአንተ ምንድነው?


“እንግዲህ መጻህፍቱ ይነግሩናል እንጂ እግዚአብሔርን በውል አናውቀውም። አላሸተትነውም፣ አልዳሰስነውም፣ እንግዲህ የእሱን ተአምራት የምንመለከተው በሰው ነው። ሰው እግዚአብሔር እስኪገኝ የምድር ላይ ተለዋዋጭ አምላክ ነው ብትፈልግ። ከሰውም ደሞ ሴት። ወንድ ትንሽ ሙቀት ከሰጣት እሷ ለመፍጠሩ ትበቃለች። እናት ብቻ ሳይሆን ሚስትም የምትሆነው ያቺው ሴት ነች። ልጅ ሆና ህይወት የምትቀጥለው በሷ ነው። ታዲያ እንዴት ከፈጠረች፣ ህይወት እንዲቀጥል ካደረገች አምላክ አትሆን? የወንድ ሥራ ዓለምን ማስተዳደር ብቻ ነው አጋፋሪነት። ሕይወት የሴት ናት።


ጥያቄ፡- ይቺ ገለፃህ ሩቅ ምሥራቅ ያለ የሕይወት ምንጭን የማምለክ ሥርዓት አስታወሰኝ። ከሚወልደውና ከሚወስድበት ብልት በላይ አምላክ የለም ይላሉ። አኗኗራቸውም ይሄንኑ ይከተላል። ለመሆኑ የእነሱ፣ የሩቅ ምሥራቆቹ አኗኗር አስቀንቶህ አያውቅም።


“አያስቀናኝም! ለምን ያስቀናኛል? ሩቅ ሆነው በጣም ደስ ይላሉ። ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል ወደ ምዕራብ በኩል ያለው የደመናዎቹና የተራራዎቹ ቀለም ወደ ፅጌረዳ ማዘንበሉ በጣም ደስ ይልሃል። በቃ ከሱ ጋር ትቆያለህ። ግን እንደሱ በሆንኩ አትልም። የእነሱም የህይወት አተያይ እንደዛ ነው። እዛ ተወልጄ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር። እዚህ መወለዴ ግን ያ ቀረብኝ አያሰኘኝም። ከሩቅ ማየት በቂ ነው። እዚህ ላይ ነው ደግሞ የአባትህ የእናት ተፅዕኖ ጎልቶ የሚታየው። በምንም መንገድ፣ እንደገና መወለድ ቢቻል ከነድህነቱ፣ ከነጉድለቱ ወላጆቼ መልሰው ቢወልዱኝ ነው የምመርጠው። ሌላ ወላጅ ጥበብ የሚያውቅ፣ በቦቅስ የአለም አንደኛ የሆነ አልፈልግም።”


ጥያቄ፡- ጥያቄውን ከአንተ አንጻር አይቼ ነው ያነሳሁት። ወደ ሩቅ ምሥራቅ የተለየ እምነት ብቻ ሳይሆን አኗኗርም አለ። ሲያሻቸው ራቁታቸውን ይሄዳሉ (እንደ ማሃቬራ)፣ የተገለጠላቸውን ያስተምራሉ፣ ያልተስማማቸውን ይነቅፋሉ… እዚህ መፅሐፍ ፅፈህ ከ30 ዓመት በላይ እንዲታተም አልተፈቀደልህም። ፍላጎትህን፣ ምኞትህንም ባሰኘህ ሁኔታ እንዳትገልጽ ኅብረተሰቡ ክልከላ ጥሎብሃል። እነዚህ ገደቦች አቅጣጫ ስተህ እንድትፈስ የሚያደርግ አመፅ ሊፈጥሩብህና ሌሎችን የመሆን ምኞት ሊያሳድሩብህ ይችላሉ በሚል ነው።


“ሰዎቹ በሚጥሉት ክልከላ ታዛዥ የሆነ ባህርይ ያለው ይታዘዛቸዋል እንጂ እኔኮ ታዝዤያቸውም አላውቅም። ግን እንደ መንግሥቱ ገዳሙ “ያው አፈርሳቸዋለሁ!” እያልኩ በአደባባይ አላውጅም። ደንብ፣ ህግ ብትል እኔ በጣጥሼ ነው የምሄደው። ሰው እስካልጎዳሁ ድረስ ይሄ ህግ ለህዝቡ፣ ለሃገሩ ያስፈልጋል፣ ያለሱ እንዴት እንኖራን የሚባልበት ካልሆነ አልታዘዘውም። እግዜር ከፈለገ በኋላ የሚቀጣኝ ከሆነም (አይመስለኝም እንጂ) ይቅጣኝ ከፈለገ። አሁን እኔ ሙሴ እንዲህ አታድርግ አሉኝና ምኔ ናቸው? ምኔም አይደሉም። ስትወድደው ነው፤ ካልወደድከው ምንህም አይደል። ቅድም እንደ ተጨዋወትነው ነው። ሰው ለጊዜውም ቢሆን ፊት ለፊቴ የሚያየው፣ የሚዳስሰው፣ የሚጨብጠው ፈጣሪው ወላጁ ነው። ግን ደግሞ ካልተመቸው ለእሱም ጠላት ሆኖ “አጥፋኝ ወይ ላጥፋህ” ይለዋል። እንዲያ ነው።”
ስብሐት ገ/እግዚአብሔር - ህይወትና ክህሎት በአለማየሁ ገላጋይ

 

ክፍል አንዳንድ

 

በግብፅ አሌክሳንደሪያ ከተማ ከሜይ 8 እስከ ሜይ 11 2018 በምስራቅ አፍሪካ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች ውስጥ ለሚገኙ ጋዜጠኞች የሚዲያ ስልጠና ተሰጥቶ ነበር። ስልጠናውን ያዘጋጁት የሲውድን ዓለም ዓቀፍ የውሃ ኢንስቲትዩት (SIWI) እና በዩኔስኮ ሥር የሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የውኃ ትብብር ማዕከል (ICWC) ከናይል ተፋሰስ የአቅም ግንባታ ኔትዎርክ (NBCBN)ጋር በመተባበር ነው።

የስልጠናው ዓላማ፣ ጋዜጠኞች በናይል ተፋሰስ ሀገሮች የሚገኘውን የውሃ ሃብት ተያይዞ ለሕብረተሰቡ የሚያቀርቡት ዘገባ ከአድልዖ ከወገንተኝነት የፀዳ እና በሳይንስ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አቅማቸውን በመገንባት ማገዝ ነው። እንዲሁም፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ለምሳሌ ከውሃ ከአካባቢ ለውጥ ጋር በተያያዘ በምስራቅ አፍሪካ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ በጋዜጠኞች ግንኙነትና ትብብር እንዲኖራቸው ማመቻቸት ነው። በተጨማሪም፣ በተፋሰሱ ዙሪያ በሳይንስ የተደገፈ መረጃ ስለአካባቢ ስለአየር ንብረት ለውጥ፣ ስለውሃ ለጋዜጠኞች ማቅረብ ነው። በተፋሰሱ ሀገሮች ውስጥ ያሉ የመስኖ ሥራዎችን በመጎብኘት መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

ስልጠናው አንድ ቀን ሙሉ ፋዩም በተባለ ሥፍራ የሚገኙ የመስኖ ሥራዎችን መጎብኘትን ያካተተ ነበር። የተቀሩትን ጊዜያት አሌክሳንደሪያ በሚገኘው በሲውዲን ኢንስቲትዩት ውስጥ የተከናወነ ነው። በርከት ያሉ የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ውይይቶች ተደርጎባቸዋል። ጋዜጠኞችም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስቻለ ስልጠና ነበር።

ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶች መካከል፤ ከሲውዲን ዓለም ዓቀፍ የውሃ ኢንስቲትዩት ከመጡት ባለሙያዎች ወ/ሮ ማሪያ ቪንክ “Introduction to the role of media in fostering regional/transboundary cooperation”፤ ዶክተር ፊሊያ ሬሰቲያኒ “Water cooperation and benefit sharing in a regional context”፤ ሚስተር ማትስ ኤሪክሰን “A global outlook on water for development and examples on hydroclimatic hazards in Asia” ያቀረቡ ሲሆን እነዚህን የጥናት ሰነዶችን የተለያዩ አብነቶችን በማቅረብ በጥሩ ሁኔታ አቅርበዋል።

ሌላው በዶክተር ኬቨን ዊለር፤ “The immediate implications of the GERD and the need for upstream-downstream cooperation.” “The long-term costs and benefits of infrastructure to mitigate hydro-climatic risks.” በሚል ርዕስ የቀረቡ የጥናት ውጤቶች ናቸው። የዶክተሩ ሳይንሳዊ መረጃዎች በጣም የጠለቁና ገለልተኛ በመሆናቸው የስልጠናው ማሰሪያ ተደርጎ የተወሰደ ነው።

ሌላው፣ በርካታ ጠቃሚ መረጃ የተገኘበት እንዲሁም መረጃ አልባ አወዛጋቢ ትንተና ያቀረቡት የግብፅ ዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ ናቸው። ያቀረቧቸው የጥናት ወረቀቶች፣ “Climate change and expected impact on water resources in the Nile from hydro climatic hazards (Floods, droughts, etc) Hydro climatic hazards”
& “
Water for agriculture – a basin wide perspective on agriculture-based economy and basis for livelihoods in the eastern Nile basin countries “ & “Impact on life and livelihoods in the basin including forced migration.” የሚሉ ናቸው። በስልጠናው የተለየ አቀራረብ እና አተያያት የነበረው በአቶ ወንድወሰን ሰዒድ የቀረበው ፣“ Emotion, the Nile and the Media.” የሚለው የጥናት ወረቀት ነው።

 

በዚህ ጽሁፍ ሁሉንም የስልጠና የምርምር ሰነዶች ማቅረብ አይቻልም። ከቀረቡት ጥናቶች መካከል በተለይ የዶክተር ኬቨን ዊለር እና የዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ በወፍ በረር ለመመልከት እንሞክራለን።

ዶክተር ኬቨን ዊለር በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪና መምህር ናቸው። ለዶክትሬት ዲግሪያቸው የማሟያ የጥናት ሥራቸውን ያደረጉት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ ላይ ነበር፤ ጨርሰውም ተመርቀዋል።

ዶክተር ኬቨን የጥናት ወረቀታቸውን ሲያቀርቡ የአካዳሚ ጥናት መለያ ባሕሪዎችን አስቀምጠው ነው። ይኸውም፣ በራሱ ሀሳብ የሚመራ፤ ነፃ ትንተና ምርመር (independent analysis)፤ በጣም ተባባሪ (highly collaborative)፤ ለሌሎች አስቻይ አማራጮችን ከግምት እንዲወስዱ የሚያቀርብ (provide possible approaches for others to consider (consultants, ministries, TNC) ነው ሲሉ አስምረው ነበር የጀመሩት።

ዶክተር ኬቨን በሰጡት ሙያዊ ትንተናዎች በተለይ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ጋር በተያያዘ በሳይንሳዊ ቀመር ከማስደገፋቸው በላይ በጉዳዩ ላይ ያላቸው በራስ መተማመን የሁላችንም ቀልብ የሳበ ነበር። በተለይ በግብፅ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል በሚደረጉ ድርድሮች ከመግባባት መድረስ አልቻሉም ከሚባለው ጉዳይ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚሞላበት አግባብ መሆኑ በስፋት ተዘግቧል።

ዶክተር ኬቨን በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናታቸውን ተመስርተው እንዳስቀመጡት፣ በመጀመሪያ ዓመት በጣም ትንሽ የውሃ መጠን በግድቡ በመያዝ ወደ ሥራ ለመግባት እያለቁ ያሉትን ተርባይን 9 እና 10 ለመሞከር ይውላል። በሁለተኛው አመት በግድቡ በሚያዘው ውሃ ሁሉንም ተርባይኖች ለመሞከር በሚያስችል መጠን ውሃ በግድቡ እንዲገባና እንዲያዝ ይደረጋል። በተቀረው አመታት 640 ሜትር ከፍታ ያለውን የህዳሴውን ግድብ ለመሙላት ይውላል ብለዋል። እንደዶክተሩ ገለፃ ግድቡን ለመሙላት ቢያንስ አምስት ዓመት ያስፈልጋል። ይህ የሚወሰነው እንደዝናብ መጠኑ ነው ብለዋል።

ዶክተር ኬቨን ለሰልጣኞች ቁልፍ ነጥቦች ብለው አስቀምጠዋል። ዶክተሩ ጥናታቸውን በአሰረጂነት አቅርበው፣ ኢትዮጵያ ተጋፊ (aggressively) በሆነ መልኩ ግድቡን የመሙላት እቅድ የላትም፤ ኢትዮጵያ እንደዝናቡ መጠን ለመሙላት ፈቃደኛ ናት፤ ሁሉም ነገሮች አሁን በድርድር ላይ ናቸው ብለዋል።

“የህዳሴው ግድብ ውሃ ሲሞላ አደጋ አይኖረውም?” ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶክተር ኬቨን የሰጡት ምላሽ፣ “አደጋ ይኖራል። ነገር ግን አደጋው መቶ በመቶ በተቀናጀ ኦፕሬሽን ሊስተካከል የሚችል ነው (risk exist, but are 100% manageable with coordinated operation)” ብለዋል። አያይዘውም፣ በተፋሰሱ ሀገሮች በተለይ በሱዳን በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል በሚያደርጉት ድርድር ከስምምነት ላይ መድረስ ከቻሉ አደጋ የሚባል ሊከሰት አይችልም። ዋናው ጉዳይ በትብብር መስራት ነው።

ሌላው በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል አወዛጋቢ እና ለስምምነት መድረስ እንቅፋት ተደርጎ የሚወሰደው “ጉዳት” እና “ጉልህ ጉዳት” በሚሉ ሀረጎች መካከል ያለው አረዳድ ነው። በስልጠናው ወቅትም ለዶክተር ኬቨን ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄዎች ማከከል አንዱ “ከረጅም ጊዜ ተፅዕኖ አንፃር በተለይ የናይል ውሃ መጠንን መጠቀምና መከፋፈል ጋር በተያያዘ ጉልህ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ነው።” ነበር። ዶክተር ኬቨን ግብፅን በምሳሌ በመውሰድ ሁሉንም በተፋሰሱ ሀገሮች መከከል በተለይ በኢትዮጵያ በሱዳን እና በግብፅ የሚገኙ በውሃ የተሞሉ ግድቦችን ለኃይል ማመንጫ በሚቻለው ደረጃ በተቀናጀ መልኩ በመጠቀም ውጤታማ መሆን ይቻላል። ይህም ሲሆን ምንም አይነት ጉልህ ጉዳት አይደርስም (cause no significant harm) ሲሉ የጥናት ሰነዶችን በጥልቅ በመተንተን አስረድተዋል።

ዶክተር ኬቨን አያይዘውም፣ በሀገሮች መካከል ያለውን አለመተማመን ለመቅረፍ ብቸኛ አማራጭ በሳይንስ የተደገፈ መረጃ መጠቀም ነው። ጥናት ላይ መሰረት ያላደረጉ መከራከሪያዎች ለመተማመን አያስችሉም። ሱዳን ግብፅና ኢትዮጵያ ፈጥነው ከስምምነት መድረስ ከቻሉ በአጭር እና በረጅም ጊዜ በተቀናጀ መልኩ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው። ሳይረፍድ መስማማቱ አዋጪ ነው ብለዋል።

የአሌክሳንደሪያው ስልጠና አዲስ ነገር ይዞ የመጣው በግብፅ በኩል አዲስ ትርክት በዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ ““Impact on life and livelihoods in the basin including forced migration.” በሚል የቀረበው “ጥናታዊ” ወረቀት ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ አስገዳጅ የገበሬዎች ፍልሰት ይፈጠራል የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀርበው ነበር። እንደዶክተር አሊ ገለፃ፣ ከሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ “2 ሚሊዮን የግብፅ ገበሬ” ይፈናቀላል ብለዋል።

በዚህ ነጠብ ላይ ሞቅ ያለ ክርክር ተደርጓል። ለዶክተር አሊ የቀረበላቸው ጥያቄ በጣም ቀላል ነበር። ይኸውም፣ “2 ሚሊዮን ገበሬ ይፈናቀላል የሚለው ድምዳሜ ከየት የጥናት ሰነድ የተገኘ ነው? እርስዎ ያጠኑት ከሆነ አቅርበው ቢያስረዱን ወይም በሶስተኛ ወገን የተጠና የጥናት ሰነድ ካለ ያቅርቡትና እንወያይ?” የሚል ነበር። በዚህ መልኩ ጥያቄ አይቀርብም በሚል የተዘናጉት ዶክተር አሊ አንድም ያቀረቡት የጥናት ሰነድ የለም። በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሽ የላቸውም፤ ተራ ፕሮፖጋንዳ ግን አልነበረም።

ምክንያቱም ዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ የዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው። በምንም መልኩ አለመረጃ ያወራሉ ተብሎ አይታሰብም። ዶክተሩ በአንድም በሌላ ምክንያት አምነው ያቀረቡት የመከራከሪያ ነጥብ አይደለም ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከዓላማ ውጪ የቀረበ ጉዳይ ተደርጎ ግን አይወሰድም።

የዶክተሩና የላካቸው አካል ፍላጎት በቀላል አቀራረብ የህዳሴውን ግድብ ውሃ መሙላት ተከትሎ ሊቀንስ በሚችለው የውሃ መጠን “2 ሚሊዮን የግብፅ ገበሬ ለስደት ይዳረጋል” የሚል አዲስ የፍርሃት ፖለቲካ በአውሮፓ ሀገሮች ለመርጨት የታለመ ነው። ይህም ሲባል፣ በሶሪያ ስደተኞች የተጥለቀለው የአውሮፓ ማሕበረሰብ ስለስደተኞች መስማት አይፈልጉም፤ ተሰላችተዋልም። ይህንን የተረዱት ዶክተር አሊና የላኳቸው አካላት፣ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚፈናቀለው የግብፅ ገበሬ መዳረሻው አውሮፓ ነው፣ የሚል የፍርሃት ፖለቲካ ማስተጋባት ፈልገው የዘየዱት ስለመሆኑ ለማወቅ የሮኬት ሳይንስ አይጠይቅም።

በግብፅ የገበሬዎች ፍልስት የፍርሃት ፖለቲካ በአውሮፓ ማሕበረሰብ ላይ በመርጨት ዶክተር አሊና የላካቸው አካል ምን ይጠቀማሉ ብሎ መጠየቅ አግባብነቱ ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም፣ ግብፅ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ ዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ በመውሰድ አጀንዳ ለማድረግ የማትፈነቅለው ድጋይ የለም። ከሙከራዎቹ አንዱ፣ የዶክተር አሊ መረጃና ጥናት አልባው በሕዳሴው ግድብ ምክንያት “ 2 ሚሊዮን የግብፅ ገበሬዎች ወደ አውሮፓ ይፈልሳሉ” የሚለው አዲሱ የፕሮፓጋዳ ትርከት ነው። ቀላል የሚመስል ሆኖም ግን አደገኛ የፕሮፖጋዳ ዝግጅት የተደረገበት ፈጽሞ ለተጀመረው የመተባበር መንፈስ አጋዥ ያልሆነ አቀራረብ ነው።

በስልጠናውም ላይ ዶክተር አሊ አንዳችም መረጃ ይሁን የጥናት መከራከሪያ ነጥብ ሳያቀርቡ ነበር፤ ስልጠናው የተጠናቀቀው። በተረፈ በሌሎች ባለሙያዎች የቀረቡት የጥናት ወረቀቶች በርካታ ቁምነገሮች ያገኘንባቸው ናቸው።

ክፍል ፖለቲካ
Page 1 of 3

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 42 guests and no members online

Archive

« May 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
  1 2 3 4 5 6
7 8 9 10 11 12 13
14 15 16 17 18 19 20
21 22 23 24 25 26 27
28 29 30 31      

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us