You are here:መነሻ ገፅ»ወቅታዊ
ወቅታዊ

ወቅታዊ (174)

ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ዜጎቻችን በቀነ ገደቡ ተጠቅመው 

በሠላም ሳዑዲ ዓረቢያን እንዲለቁ እንመክራለን

አቶ ኑሪ እስማኤል

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በሀገሩ ውስጥ የሚኖሩና የሚሠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሩን ለቀው በሠላም እንዲወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ እየተገባደደ ቢሆንም (ማስጠንቀቂያው የተሰጠው መጋቢት 21 ቀን 2009 ጀምሮ ነው) እስካሁን በኢትዮጽያዊያን ወገኖች በኩል የታየው ምላሽ ቀዝቃዛ ሆኗል። በኢትዮጽያ መንግሥት በኩል ዜጎች በቀነ ገደቡ ተጠቅመው በሠላም ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ጥረት ከማድረግ ጀምሮ የጉዞ ሰነዶችን በማመቻቸት፣ ንብረቶቻቸውን ሲያስገቡ ከቀረጥ ነጻ መብት በመፍቀድ፣ ወደሀገር የተመለሱትን ደግሞ በዘላቂነት ለማቋቋም ቃል ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ አመራር አባልና በኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎች አስመላሽ ኮምቴ የመረጃ፣ የትምህርትና ቅስቀሳ ኮምቴ አባል ከሆኑት ከአቶ ኑሪ እስማኤል መሐመድ ጋር ባልደረባችን ፍሬው አበበ ያደረገው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።


ሰንደቅ፡- በአሁኑ ሰዓት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ወገኖቻችን ቁጥር ይታወቃል? እስካሁን ወደሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ያሳዩ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል ነው?

አቶ ኑሪ፡- በአሁኑ ሰዓት በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ይገመታል። ከእነዚህ ወገኖቻችን ውስጥ ወደሀገራቸው የገቡ ወይም ለመግባት የጉዞ ሠነድ የወሰዱ እስካሁን ከ30 ሺህ አይበልጡም። በአጠቃላይ ያልመጡ ዜጎቻችን ቁጥር ከፍተኛ ነው። ችግሮች ተከስተው ከምንፀፀት ከወዲሁ ባሉት ነገሮች ማኅበረሰባችንን ግንዛቤ በማስጨበጥ ዜጎቻችን መብትና ጥቅሞቻቸው ተከብረው በሠላም ወደ ሀገር የሚገቡበት ሁኔታ ላይ ልንረባረብ ይገባል።


ሰንደቅ፡- በሳዑዲ በሕጋዊ መንገድ እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ይገመታል። ቁጥራቸው በትክክል አይታወቅም?
አቶ ኑሪ፡- ይህንን በተመለከተ እስካሁን ድረስ በኢምባሲ ደረጃ የተመዘገበ ነገር የለም። ያለው ግምት ነው። በግምቱ መሠረት በሕገወጥ መንገድ ወይም ያለሕጋዊ ሰነድ የሚኖሩ ዜጎቻችን ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሕጋዊ መንገድ የገቡ ዜጎቻችን ጭምር የመኖሪያ ፈቃዶቻቸውን ማደስ የማይችሉበት ከባድ ቅድመ ሁኔታ በሳዑዲ መንግሥት በኩል መቀመጡ ይህን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይገመታል። የሳዑዲ መንግሥት በመኖሪያ ፈቃድ እድሳት ክፍያ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አድርጓል። አንድ ሰው በዓመት እስከ 10 ሺህ ሪያል ለመኖሪያ ፈቃድ እድሳት እንዲከፍል እየታሰበ ነው። እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ደግሞ በየዓመቱ በፈቃድ እድሳት ላይ 200 ሪያል ለመጨመር ዕቅድ እንዳለው ተነግሯል። አሠራሩ ውጣ አትበለው፣ ግን እንዲወጣ አድርገው ዓይነት ነው። እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት በሳዑዲ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አለ። ሥራም የለም። አብዛኛው ማኅበረሰባችን የተሰማራው በግል ሥራ ላይ ነው። የመኖሪያ ፈቃድ ካላቸው ዜጎቻችን አብዛኛዎቹ የመኖሪያ ፈቃድ የሚያድሱበት በቂ ገንዘብ የላቸውም። የመኖሪያ ፈቃድ የማደስ አቅማቸው የደከሙ ዜጎች ደግሞ ሕጋዊ ሠነድ ስለማይኖራቸው በሕገወጥነት ይፈረጃሉ።


ሰንደቅ፡- የፈቃድ እድሳቱ በየስንት ጊዜው ነው?
አቶ ኑሪ፡- በየዓመቱ ነው።


ሰንደቅ፡- አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ወደሀገር ቤት ለመመለስ ፍላጎት ያላሳዩበት ምክንያት ምንድነው ትላላችሁ?
አቶ ኑሪ፡- የሳዑዲ መንግሥት የሰጠው የማስጠንቀቂያ ጊዜ በዛሬው ዕለት ባልሳሳት 37 ቀናቶች ብቻ ናቸው የሚቀሩት (ቃለመጠይቁ የተደረገበት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ነው) እነዚህ ዜጎቻችን ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ሲሰደዱ ንብረቶቻቸውን ሸጠው፣ ከዘመድ አዝማድ ገንዘብ ተበድረው ነው። በሦስተኛ ደረጃ ምንም ነገር ዕዳ ሳይኖርባቸው ሠርተው ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱ ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። በአንዳንድ ወገኖች በኩል ሳዑዲ ይህን መሰል ማስጠንቀቂያ ስታወጣ የመጀመሪያዋ አይደለም፣ ምንም አትሆኑም፣ ቀጥሉ በሚል የሚገፋፉም ወገኖችም አሉ። ንብረት ሸጠው እና ተበድረው ወደሳዑዲ የሄዱ ዜጎች ምናልባት ብንመለስ ባለዕዳ እንሆናለን የሚል ፍርሃትና ሥጋት ሊያድርባቸው ይችላል።


ሰንደቅ፡- ዜጎች ወደሀገራቸው እንዳይመለሱ የሚጥሩ ወገኖች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ወገኖች ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፈዋል?
አቶ ኑሪ፡- የማኅበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም ጭምር ዜጎች ወደሀገራቸው እንዳይመለሱ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የሚሰሩ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። አንዳንድ ደላሎችም ከጥቅማቸው ጋር ተያይዞ ዜጎች እንዳይመለሱ የበኩላቸውን ጥረቶች እያደረጉ ነው። እነዚህ ደላሎች በሳዑዲ በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ ዜጎቻችንን 30 ወይንም 40 ግለሰቦች በአንድ ቤት ውስጥ በአነስተኛ ገንዘብ በማከራየት፣ እህቶቻችን ለውጭ ሀገር ዜጎች ለሌላ ዓላማ እያከራዩ የተንደላቀቀ ሕይወት የሚመሩ ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ በሒደታችን ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ሌላው ቀርቶ ከሳዑዲ ዜጎቻችንን በሠላም ለማውጣት ጥረት እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት እንኳን ደላሎቹ በየዕለቱ ዜጎቻችንን እየደለሉ ወደሳዑዲ በሕገወጥ መንገድ እንዲገቡ የማድረግ ተግባራቸውን አላቆሙም። የሕገወጥ ደላሎች ሰንሰለት መቆረጥ መቻል አለበት። በአሁኑ ሰዓት ሳዑዲ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደበፊቱ አይደለም። ምናልባት ከ10 ዓመት በፊት ሰዎች በቀላሉ ሠርተው የሆነ ነገር ሰንቀህ የምትመለስበት ዕድል ነበረ። ያ-ዛሬ የለም። ለምን የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን ተከትሎ ብዙ የሥራ ዕድል የለም። ሌላው ቀርቶ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ዜጎቻችን ጨምር ሥራ አጥተው የተቀመጡበት ሁኔታ ነው ያለው። ዜጎቻችን ይህንን አውቀው ወደ ሳዑዲ መሰደድ እንደሌለባቸው መምከር እፈልጋለሁ። እዚህ ያለው ቤተሰብ እና ወዳጅ በሳዑዲ የሚገኙ ዘመዶቹ መብትና ጥቅማቸው ተከብሮ በሠላም ወደሀገራቸው እንዲገቡ መምከር አለበት። መንግሥትም ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎች የቀረጥ ነፃ መብት የፈቀደበት ሁኔታ አለ። ተመላሾችን በዘላቂነት ለማቋቋምም ቃል ገብቷል። በዚህ ዕድል ዜጎቻችን ሊጠቀሙ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።


ሰንደቅ፡- ቀነ ገደቡ ሲያልፍ ምን ሊከሰት ይችላል?

አቶ ኑሪ፡- ቀነገደቡ ሲያልፍ ሊከሰት የሚችለው ነገር በትክክል አይታወቅም። ግን መገመት ይቻላል። እ.ኤ.አ. በ2013 በዜጎቻችን ላይ የተከሰተው ችግር አይደገምም ብሎ ማሰብ አይቻልም። እንደምናስታውሰው እ.ኤ.አ. በ2013 ያላሰብነው ነገር ነው የተከሰተው። ሳዑዲ በተመሳሳይ መልኩ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ አስጠነቀቀች። የጊዜ ገደብ ተቀምጦ ነበር። ቀደም ብሎ ሦስት ወር ተሰጥቶ ስላልበቃ ተጨማሪ ጊዜም ተሰጥቶ ነበር። በዚያ ጊዜ ገደብ ውስጥ ዜጎቻችንን ያልተንቀሳቀሱበት ሁኔታ ነበር። ከዚያ በኋላ የሳዑዲ የፀጥታ ኃይሎች የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቻችንን ቤት ለቤት እየበረበሩ መያዝ ጀመሩ። በዚህ መካከል በኢትዮጵያዊያኑ እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ጉዳትና ችግር የደረሰበት ሁኔታ እናስታውሳለን። ያኔ የነበረው ሁኔታ አሳዛኝና የኢትዮጵያ መንግሥትንም ያስደነገጠ ክስተት ነበር። በወቅቱ በየዓለማቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቆጥተው በሳዑዲ ኤምባሲዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሞከሩበት፣ የተቃውሞ ሰልፍ የወጡበት ሁኔታ የምናስታውሰው ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተከሰተ ሥርዓት አልበኝነት ተፈጥሮ ዜጎቻችን የበለጠ ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ እዚያ የሚኖሩ ሴቶች፣ እናቶች፣ ህፃናት፣ አረጋዊያን… የበለጠ ተጎጂ ይሆናሉ።


በተጨማሪም እንዲህ ዓነት ችግሮች ሲከሰቱ በሳዑዲ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የቆየው የዲፕሎማሲ ግንኙነት አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል። በአሁን ሰዓት በወዳጅነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ጥሩ ግንኙነት አለን። በዚህ ወቅት ዜጎቻችን ቢወጡ የበለጠ ጥቅሙ ለእነሱ ነው። በሠላም ከወጡ በሌላ ጊዜ በሥራ ኮንትራትም ሆነ በሐጂ ፀሎት ወደሳዑዲ ሊሄዱ የሚችሉበት ዕድል አለ። የጊዜ ገደቡ ካለፈ በኋላ ቤት ለቤት በሚደረገው አሰሳ የተያዙ ወገኖች መታሰር፣ መንገላታት እንዲሁም ንብረታቸውን ማጣት ስለሚያስከትልባቸው ጉዳቱ ከባድ ይሆናል። የሳዑዲ መንግሥት በቅርቡም የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ያሉበትን ቦታ ለጠቆመ ዳጎስ ያለ ወሮታ እንደሚከፍል የሚገልጽ ወረቀት በትኗል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ከአሁን በኋላ ሕገወጥ ሆኖ ሳዑዲ ውስጥ የመኖር ዕድል ማክተሙን ነው።


ሰንደቅ፡- በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ኑሪ፡- በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ነው። እኔም በኮምኒቲው አመራር ውስጥ እየተሳተፍኩ ነው። በሪያል የኢፌዲሪ ኢምባሲ የሊሴፖሴ (የጉዞ ሠነድ) ለተመላሽ ዜጎች በሚሰጥበት ጊዜ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ተሳታፊ በመሆን እያገለገልን እንገኛለን።

“ፍትሕን ያለአግባብ ማዘግየት በሕግ እና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን ያሻክራል”

አቶ ነብዩ ምክሩ ወ/አረጋይ

 

ሰሞኑን በሀገር አቀፍ ደረጃ የፍትሕ ሳምንት ሲከበር ሰንብቷል። በኢትዮጵያ ከሕግ የበላይነት ጋር ተያይዞ ባሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉን እንግዳ ጋብዘናል። አቶ ነብዩ ምክሩ ወ/አረጋይ ይባላሉ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕገመንግሥትና በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በዐቃቤ ሕግ ባለሙያነት፣ በነገረፈጅነት፣ በሕግ አማካሪነት በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሠርተዋል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በማናቸውም ፍ/ቤት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው። ከአቶ ነብዩ ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ቀርል።

ሰንደቅ፡- የሕግ የበላይነት ጽንሰ ሃሳቡ ምንን ያካትታል?

አቶ ነብዩ፡-አንዲት ሀገር የተፃፈ ወይም ያልተፃፈ ሕግ ይኖራታል። የሕግ የበላይነት ዋና ምሰሶ የሚሆነው የተፃፈው ሕግ፣ ሁሉም ሰው ያለአድልኦ በሕግ ጥላ ስር መኖርና በተመሳሳይ በሆነ መንገድ የሕግ ማክበርና ማስከበር ሥርዓት መኖርን የሚያሳይ ሰፊ የሆነ የሕግ መርህ ነው።

ሰንደቅ፡- የሕግ የበላይነት የሚባለው ነገር በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ቦታ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ነብዩ፡- የመንግሥት እና የዜጎች ግንኙነት ሕግን መሠረት ያደረገ፣ ሕግን ያከበረ እንዲሆን የሕግ የበላይነት መርህ ያስገድደናል። ሦስቱ የመንግሥት አካላት (ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈፃሚውና ሕግ ተርጓሚው) ተባብረው በሚሰሩበት ጊዜ የሚኖራቸው ሚና ነው የሕግ የበላይነትን የሚያመላክተው። ወደሀገራችን ስንመጣ ሕግ አውጪው የሕብረተሰቡን ችግሮች የሚፈታ፣ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ያሟላ ሕግ በማውጣት ረገድ የሕግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ ይገባል። በኢትዮጵያ በተግባር ስናይ ባለፉት ዓመታት በሕዝቡ ቅቡልነት ያጡ ሕጎች ሲወጡ አይተናል። እነዚህ በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያጡ ሕጎች ከመነሻው የዜጎች እና የመንግሥትን ግንኙነት ያሻክራሉ ማለት ነው። ከምርጫ ሕጉ ጀምሮ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ፣ የፀረ ሽብር አዋጅ ለአብነት ያህል ማንሳት እንችላለን። እነዚህ አዋጆች ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጣረሱ በርካታ ድንጋጌዎች አሏቸው ተብሎ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብባቸውና ሲተቹ የቆዩ ናቸው። ሕጎቹ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ተቃውሞና ትችትን ያስከተሉ ሕጎች ናቸው።

ወደ ሕግ አስፈፃሚው ስንሄድ በርካታ የመልካም አስተዳደርና ችግሮች እንዳሉበት በራሱ የታመነ ጉዳይ ነው። ይሄ የመልካም አስተዳደር ችግር በራሱ የሕግ የበላይነትን የሚያፋልስ ነው።

ሕግ ተርጓሚው አሁንም ሙሉ በሙሉ ከአስፈፃሚው ጫና ውጪ ነው ማለት አንችልም። ይኼ በራሱ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሒደትን የሚጎዳ ነው። የሕግ ተርጓሚው ዓላማ ሕጎችን መተርጎም ነው። በአሁኑ ሰዓት ፖለቲካው እና ሕግን የመተርጎም መደበኛ ሥራ እየተጣረሰ እየሄደ መሆኑን በብዙ መልኩ እያየን ነው። ስለዚህ ሕግ ተርጓሚው አካል ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ሥራውን ማከናወን የሚችልበት ቁመና ላይ ነው ማለት አንችልም። በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ መጠነኛ መሻሻሎች መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም  እነዚህ መሻሻሎች ግን ሕዝቡን የሚመጥኑና የሕዝቡን እርካታ ያስገኙ አይደሉም።

 

 

ሰንደቅ፡- በመንግሥት በኩል የፍትሕ አካላት በሚል ከሚያስቀምጣቸው መካከል ፍ/ቤቶች፣ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ማረሚያ ቤቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህ አካላት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ አኳያ የሚታዩ መሠረታዊ የሚባሉ ጉድለቶች ምንድናቸው ይላሉ?

አቶ ነብዩ፡- ከመነሻው የፍትሕ አካላት በሚል የተዘረዘሩትን እንዳለ መቀበል ያስቸግረኛል። የጠበቆች ማኅበራትን፣ የሕግ ት/ቤቶችን እንደፍትሕ አካል አይቶ የማይንቀሳቀስ ሥርዓት በራሱ ችግር አለበት ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ አሁን የተጠቀሱት ፖሊስ፣ ፍ/ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ማረሚያ ቤት ብቻ የፍትሕ ባለድርሻ አካል ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አልወስድም። እነዚህ ተቋማት ምን ምን ችግሮች አለባቸው ቢባል ለመዘርዘር ጊዜና ቦታም አይበቃም። በአጠቃላይ ግን የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ ማለት እንችላለን። ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ በፍ/ቤቶች አካባቢ የባለሙያዎች ፍልሰት አለ። ሀገሪቷ አሉኝ የምትላቸው ባለሙያዎች በየጊዜው ሥራቸውን የሚለቁበት ሁኔታ እያስተዋልን ነው። ምክንያታቸው ደግሞ በአመዛኙ ከደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አለመመለስ ጋር የተሳሰረ ነው። ተገቢውን ክፍያ ፈፅሞ ባለሙያዎችን በማቆየት ረገድ ችግሮች አሉ። ተቋማቱ ውስጣዊና ውጫዊ ተጨማሪ ችግሮች አሉባቸው። ተቋማዊ ነፃነታቸው ገና አልተረጋገጠም። ይኸ በሆነበት ሁኔታ የሕግ የበላይነትን ሊያስጠብቁ ይችላሉ ብሎ መወሰድ አይቻልም። የባለሙያዎች እጥረት፣ የአቅም ማነስ አለ። የፍትሕ ማሰልጠኛ ተቋማት ቢኖሩም ሥልጠናው ሳይንሳዊና ችግር ፈቺ በሚሆን መልኩ እየተሰጠ አለመሆኑን በየጊዜው የሚተች ነው። ፖሊሶች ጋር ስትሄድ የሥነምግባርና የብቃት ማነስ ችግሮች አሉ። በሀገሪቱ ውስጥ ውስብስብ የሆኑ ወንጀሎች እየተፈጠሩ ነው። በዚህ ልክ ራሱን ያሳደገ የፖሊስ ምርመራ ተቋምና ባለሙያዎች ግን የሉንም። ፖሊስ ምርመራውን ለማከናወን ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታጠቀ አይደለም። በአብዛኛው በባህላዊና ኋላቀር መንገድ እየተከናወነ ያለ ነው። የእነዚህ ድምር ውጤት የፍትሕ ሥርዓቱ መጎልበት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው እላለሁ።

ሰንደቅ፡- በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ከሚነገሩ ነገሮች አንዱ የፍትሕ አካላት ተቀናጅቶ የመስራት ጉዳይ ይጠቀሳል። ለምሳሌ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ተቀናጅተው በመስራታቸው አዎንታዊ ውጤት መገኘቱ በአንድ በኩል ይገለፃል። በሌላ በኩል ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ተቀራርበው መስራታቸው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። በዚህ ረገድ አስተያየትዎ ምንድነው?

አቶ ነብዩ፡- ቀደም ሲል በዐቃቤ ሕግ ባለሙያነት ሰርቻለሁ። ዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ ተቀናጅተው በሚሰሩበት ጊዜም አገልግያለሁ። ከተሞክሮዬ አንፃር ቅንጅቱ ይኼ ነው የማይባል በርካታ ጥቅሞች አሉት። ጥቅሙ ምንድነው ካልክ በርካታ የመዝገቦች መመላለስ ችግሮችን ማስወገድ ማስቻሉ በቀዳሚነት መጥቀስ ይቻላል። ቀደም ሲል ፖሊስ ምርመራ አካሂዶ ለዐቃቤ ሕግ ይልካል። ዐቃቤ ሕግ እነዚህ ነገሮች አልተሟሉም ብሎ ይመልሳል። በርካታ ምልልሶች ነበሩ። ይህንን መመላለስ በማስቀረት ኅብረተሰቡን ጠቅሟል። ዐቃቤ ሕግ በተሳተፈበት የፖሊስ ምርመራ በክስም ሒደት ውጤታማ ነው። አሁንም ግን ደግሜ የምለው ተቀናጅቶ መስራት ውጤታማ የሚሆነው አመራሩና ባለሙያው ቆራጥነት ሲኖራቸው ነው። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። ጠቅላይ ፍ/ቤት ያለውን ለውጥ እንይ። ጠ/ፍ/ቤት በቅርቡ የተሾሙ አዲስ ፕሬዚደንት አሉ። ግለሰቡ እንደግለሰቡ ቆራጥ በመሆናቸው፣ ችግሩን ደግሞ ቀደም ሲል በሥራ የገጠማቸውና ይህንንም መርምረው ለማሻሻል ቁርጠኛ አቋም በመውሰዳቸው በአሁን ሰዓት ጠ/ፍ/ቤት የነበሩ የቀድሞ ችግሮች አስደናቂ በሆነ ሁኔታ መፈታት ችለዋል። ይሄ የሚያሳየው የአመራሩ ቁርጠኛ መሆን ወደታች ባሉ ፈፃሚዎችና ባለሙያዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ በጎ ተፅዕኖ አሳርፏል። ይህ ዓይነቱ አደረጃጀት በፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ አለ። የአደረጃጀት ችግር የለም። ነገር ግን ወደተግባር በመግባት ረገድ ቁርጠኝነት ያንሳል።

ሰንደቅ፡- በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ከፖሊስ ምርመራ እና የፍርድ መዘግየቶች ጋር ተያይዞ ዜጎች ተስፋ የሚቆርጡበት ሁኔታ የሚከሰትበት እድል ሰፋ ብሎ ይታያል። ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋ እየቆረጡ መምጣታቸው ከሠላምና መረጋጋት አንፃር የሚኖረው ትርጉም ምንድነው?

አቶ ነብዩ፡- የቆየ አባባል አለ። “የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል” የሚል። ፍትሕ ዘግይቶ ቢገኝ እንኳን ከተከለከለ ፍትሕ በእኩል የሚታይ ነው። አንድ ፍትሕ ዘግይቷል ማለት ትርጉም አልባ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ፍትሕን ያለአግባብ ማዘግየት በሕግ እና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን ያሻክራል። ይሄ መሻከር ደግሞ የሕግ የበላይነትን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ያናጋል። ኅብረተሰቡ በፍትሕ አካላት እምነት አጥቷል ማለት ሠላም፣ ፀጥታ እና ደህንነት የምንለውን ነገር አደጋ ላይ ነው ማለት ነው። አንድ ገበሬ ዘንድሮ ሰብሉ በተፈጥሮ አደጋ ቢወድምበት በሚቀጥለው ዓመት ለማምረትና ለማግኘት ተስፋ ያደርጋል። አንድ ገበሬ ግን ፍትሕ ካጣ ተስፋ ይቆርጣል የሚል ሀገርኛ አባባል አለ። ተስፋ ያጣ ዜጋ ደግሞ ያ-የተነፈገውን ነገር በራሱ ኃይል፣ በራሱ አቅም ለማሳካት እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይችላል። ይኸ ደግሞ በሀገሪቱ ሠላም፣ ፀጥታና ደህንነት ላይ አደጋ ይሆናል። በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን ያሳጣል።

ሰንደቅ፡- የሕግ የበላይነት በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ ከተቋማት እና ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል?

አቶ ነብዩ፡- የሕግ የበላይነት የሀገሪቱ ምሰሶ ነው። አንድ ሀገር እንደ ሀገር ስትቀጥል ፍትሕ፣ የሕግ የበላይ ሆኖ ሊመራ ይገባል። ፍትሕ እንዲሰፍን ደግሞ የፍትሕ አካላት ቁርጠኛ መሆን አለባቸው፣ ነፃነታቸው በተሟላ መልኩ መረጋገጥ አለበት። አስፈሪ ሥነምህዳር ይታያል። ይህ መወገድ አለበት። በሕብረተሰቡ በኩል ደግሞ የሚጠበቀው እነዚህ የፍትሕ ተቋማት ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አጋዥ ኃይል መሆን መቻል አለባቸው። ሕዝቡ ለፖሊስ፣ ለዐቃቤ ሕግ፣ ለፍ/ቤት በምስክርነት በሚጠራ ጊዜ፣ ወንጀል በሚያይ ጊዜ በመጠቆም፣ ፍ/ቤት በሚጠራ ጊዜ ተባባሪ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ተባባሪ መሆን መቻል አለበት። ከፈፃሚው ቁርጠኝነት፣ ከዜጋው ደግሞ ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ ነው። ይህ ከሆነ የሕግ የበላይነት የማስከበርን ሥራ ቀላልና ቀልጣፋ እንዲሁም ውጤታማ ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ።¾ 

ወጌን በቀልድ ልጀምር። አንዱ "ታዋቂ የማስታወቂያ ድርጅት" የሬሳ ሣጥን ማስታወቂያ ቢዝነስ አገኘ አሉ። እናም እንዲህ ሠራው። "በቃ…አሁን ገና ምርጥ የሬሳ ሣጥን መጣልዎ ….ለራስዎ ሲገዙ ለልጅዎ ምርቃት ያገኛሉ። ይህኔ ነው መሞት" …ነገርዬው ቀልድ ቢሆንም የምናውቀው እውነትም አለ።


"ፍሪጅ ከሌሎዎት ምኑን ኖርኩኝ" ይላሉ የሚል ማስታወቂያ በኢቲቪ ስንሰማ ኖረናል። ይሄ እንግዲህ ለደሃ ኢትዮጵያዊያን ስድብ መሆኑ ነው።


"በማስታወቂያ ሥራ ውስጥ ግነት ያለ ቢሆንም የኛ ግን በአላዋቂነት ድፍረት የታጀበ መሆኑ ያሳስባል። በየዕለቱ በቲቪ መስኮታችን አዘውትረው እዩኝ …እዩኝ የሚሉት ብዙዎቹ የሥራው ሀሁ ገና ያልገባቸው…በከንቱ ድፍረት ብቻ የተሞሉ ማስታወቂያዎች ናቸው። በየማስታወቂያዎቹ ራሳቸውን እንደመስታወት ካላዩ ሥራ የሠሩ የማይመስላቸው አስተዋዋቂዎች በሽ ናቸው። እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ ኮራ ጀነን ብለው «ደንበኞቻችንን እኛ ከሌለንበት እሺ ስለማይሉ ነው» በማለት በየጊዜው የሚቀርብባቸውን ትችት ከራሳቸው ዕውቅና ጋር አስተሳስረው ሊያስተባብሉ ይሞክራሉ።


በየምሸቱ ኢቲቪን ተመልከቱ። ትንሽዬ ፈጠራ እንኳን ማግኘት አይታሰብም። ሣሙና ለማስተዋወቅ ዳንስና እስክታ….ልብስ ለማስተዋወቅ የሰልፍ ግርግር…ካሳዩ በቃ ተሰራ ማለት ነው። የቆርቆሮን ምርት ጥራትና ጥንካሬ ለማሳየት ሙቀጫ ተይዞ ጣሪያ ላይ የተወጣበት ማስታወቂያ በአሳፋሪነቱ አንረሳውም።


በዘርፉ ታዋቂ ግለሰቦች አሉ። አዋቂዎች ግን እምብዛም የሉም። በዚህ ምክንያት አንዳንዶቹ እንደሕዝብ ስልክ ሳንቲም ለጨመረባቸው ሁሉ አብዝተው በመጮህ ሙያውን ያረከሱ ናቸው።

…………….

ይህ ወግ በአንድ ወቅት የተጻፈ ነው። ግን አሁንም ያለ እውነታ በመሆኑ ደግሞ ማቅረቡ ለዛሬው ርዕሰ ጉዳዩ መነሻነት ይጠቅመኛል በሚል የቀረበ መሆኑ ይታወቅልኝ። እንዲህ ዓይነቱ የተዘበራረቀ፣ ተመልካቹን፣ አድማጩን የናቀ የማስታወቂያ ሥራዎች የገነኑበት ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም አንዱና ዋናው ዘርፉ በሚታወቅ ፖሊሲ የሚመራ ባለመሆኑ እንደሆነ ይገመታል። በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች መነሻ በማድረግ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ያረቀቀውን የማስታወቂያ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የመጨረሻ ረቂቅ ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር በኢሊሊ ሆቴል ተመካክሮበታል።

አቶ ታምራት ደጀኔ በጽ/ቤቱ የሚዲያ አብዝሃነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፖሊሲውን በተመለከተ ባቀረቡት ማብራሪያ የማስታወቂያ ዘርፍ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ተደራሽና ብዝሃነትን የሚያስተናግድ በማድረግ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ገንቢ ሚና እንዲጫወት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ለፖሊሲው መውጣት እንደአንድ መነሻ አስቀምጠውታል።

ዘርፉ ካሉበት ውሱንነቶች መካከል በማዕከላዊነት የማይመራና የተበታተነ መሆኑ፣ የኮንትራት አሰጣጡ የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ያልጠበቀ መሆኑ፣ በባለሙያዎች መልካም ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ፣ እንደአንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ሲቀርብ መቆየቱንና የመሳሰሉት በአቶ ታምራት ገለጻ ላይ ተጠቅሷል። ዘርፉ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ በመሆኑ ውስን የሆነው ሐብት ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚታደልበት ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋና ችግሩም እየከፋ መጥቷል። በተለይም የመንግሥት ማስታወቂያ ዝግጅትና ሥርጭት እንዲሁም የፋይናንስ አስተዳደሩ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋልጠና በከባድ የአሠራር ችግሮች የተተበተበ መሆኑም ተወስቷል። በዘርፉ ግልጽነት፣ተጠያቂነት ያለው ዘመናዊ የብዙሃን መገናኛ አውታሮችን የሚጠቀም፣ ተደራሽ ወጪ ቆጣቢ የማስታወቂያ ሥርዓት አለመገንባቱም እንደተጨማሪ ችግር ተነስቷል።

ይዘትና አቀራረብን በተመለከተም የማስታወቂያ ሥራዎች መልካም ሥነምግባርን መሠረቱ ያደረጉ፣ አሳሳች ወይንም ተገቢ ካልሆነ አገላለጽ ነጻ የሆነ፣ የሴቶች፣ የህፃናት የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ደህንነትና ሞራል የሚጠብቅ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እሴት የሚያከብርና የሸማቹን መብት የማይጎዳ፣ የሚተዋወቅበትን ምርት/አገልግሎት እውነተኛ ባህሪ ጥቅም፣ ጥራትና ሌላ መሠረታዊ መረጃዎችን የሚገልጽ፣ የሌሎች ሰዎች ምርትና አገልግሎት የማያንቋሽሽ፣ የአገር ክብርና ጥቅም የሚጠብቅ፣ የሙያ ሥነምግባርን የሚያከብር፣ በሕግ የተከለከሉ ማስታወቂዎች የማያሰራጭ፣ በስፖንሰር ተጽዕኖ ሥር የማይወድቅ፣ እና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል።

የማስታወቂያ መልዕክት የሚተላለፍበት ቋንቋን በተመለከተ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ቋንቋ እንደሚዘጋጅ በተከታይ በውጭ ሀገር ቋንቋ ሊዘጋጅ እንደሚችል በፖሊሲው ተቀምጧል።

አቶ ታምራት ደጀኔ ባቀረቡት የፖሊሲ ማብራሪያ ላይ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ በጥብቅ ዲስፒሊን የሚመራ መሆኑን ተመልክቷል። ሕጻናትና ወጣቶች ወደአልተፈለገ አስተሳሰብ እንዳያዘነብሉ ለማድረግና በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂዎች የሚሰራጩበት ጊዜ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ እንደሚሆን በፖሊሲው ሰፍሯል። የአልኮል ማስታወቂያ ይዘት በተመለከተ ዝርዝሩ ህግ እንደሚወጣም ተነግሯል።

የመንግሥት ማስታወቂያ ዝግጅት፣ ስርጭትና ክፍፍል ብዝሃነትን የሚያስተናግድ፣ ለሕዝብ ተደራሽ የሆነና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ ለሚዲያ ልማት በጎ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ግልጽነት፣ ፍትሐዊነት ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሰራር እንደሚዘረጋ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ተመልክቷል። በስትራቴጂውም ላይ የመንግሥት ማስታወቂያዎች ፍትሐዊ በሆነ መልክ ለሀገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደሚከፋፈል ደንግጓል።

ረቂቅ ፖሊሲው በቅርቡ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ወደስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

 

እንደማሳረጊያ

የማስታወቂያ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ረቂቅ መዘጋጀቱ ዘግይቷል ከመባሉ በስተቀር አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም። በተለይ የመንግሥት ማስታወቂያ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመገናኛ ብዙሃን እንዲሰራጭ የታሰበውን ዕቅድ በተመለከተ ሁለት ዓይነት አስተሳሰቦች ይንጸባረቃሉ። ይኸውም መገናኛ ብዙሃን የመንግስት ማስታወቂያ የሚወስዱ ከሆነ በመንግስት ተጽዕኖ ስር ስለሚወድቁ ኤዲቶሪያል ነጻነታቸውን ሊያጡ ይችላሉ የሚል እና መገናኛ ብዙሃን ማስታወቂያ ማግኘት ያለባቸው በራሳቸው ጥረት በውድድር መሆን አለበት የሚሉ ወገኖች በአንድ ጎራ አሉ። በሌላኛው ጎራ ደግሞ የመንግሥት ማስታወቂያ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መገናኛ ብዙሃኑ ማግኘት አለባቸው ይላሉ። ለምን ቢባል መንግሥት ፕሬሱ እንዲያድግና እንዲበለጽግ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነትም ጭምር ስላለበት እንዲሁም የማስታወቂያ ስርጭት ወይንም ክፍፍል ከሙስናና ብልሹ አሠራር ያልተላቀቀ፣ ግልጽ መስፈርትና መመዘኛ የሌለው በመሆኑ ይህን ስርዓት በማስያዝ መገናኛ ብዙሃኑ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ማመቻቸት ይገባዋል፣ ኃላፊነቱም ነው በሚል የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።

መንግሥት በረቂቅ ፖሊሲው የመንግሥት ማስታወቂያዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማሰራጨት ተገቢ መሆኑን አምኖበት ያካተተ መሆኑ ምናልባት በአቅም ምክንያት ከገበያ የሚወጡና በትክክል ሥራቸውን ማከናወን የተሳናቸው ፕሬሶች ለማገዝ ይረዳል ተብሎ ይገመታል።¾

“ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢኖር ኖሮ አንድም ሁከትና ብጥብጥ አይከሰትም ነበር”

ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ

ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከተሰማሩ ኢትዮጵያዊን ባለሃብቶች አንዱ ናቸው። በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበራቸው ኢ/ር ዘለቀ በአንድ ወቅት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲን በከፍተኛ የአመራር አባልነት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን ገለል በማድረግ መደበኛ ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባልደረባችን ፍሬው አበበ አነጋግሯቸዋል።

ሰንደቅ፡- ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እያካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ አፈፃፀም ሒደት በግልዎ እንዴት ያዩታል?

ኢ/ር ዘለቀ፡- ይህ ርዕስ ብዙ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ሲሰጡበት፣ ሲወያዩበት የቆዩበት ጉዳይ ነው። መጀመሪያ መታደስ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በእኔ ዕይታ መታደስ ማለት አንድ አሮጌ የሆነ ነገር አድሰህ እንደአዲስ  አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ለምሣሌ ተሸከርካሪ ሞተሩን ልታድሰው ትችላለህ። ያ ተሸከርካሪ በጊዜ ብዛት አቅም እያነሰው ሲሄድ፣ መሥራት የሚገባውን መሥራት አልችል ሲል አሮጌ የሆኑ አካሎቹ ይወገዱና በአዲስ ይተካሉ። ያ መኪና ችግር የሆኑበት ያረጁ አካሎቹ በአዲስ ሲተኩለት ከአዲስ መኪና ጋር ተቀራራቢ የሆነ ጉልበት ማግኘት ይችላል። በጥሩ ሁኔታም ይሠራልሃል። መታደስ ማለት ይሄ ነው። ለምሣሌ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ አሮጌውን ወይም የተቀደደውን ጨርቅ በአዲስ አትጣፈው ይላል። አዲሱ አሮጌውን ቀዶት ነው የሚሄደው። ወደኢህአዴግ ተሃድሶ እንምጣ። ኢህአዴግ መጀመሪያም ተሃድሶ ነበረው። አሁን ‘ጥልቅ’ የሚል ቃል ነው የጨመረበት። ሁልጊዜ ስብሰባ አለ፣ ሁል ጊዜ ተሃድሶ አለ። በተግባር ግን እየታደሱኩኝ ነው የሚለውን መሆን አልቻለም። አርቴፊሻል ነው። አሁን ታድሰናል የሚሉ ሰዎችን በየክልሉ ለሥራ ስንቀሳቀስ እያየናቸው ነው። መታደስ እንዲህ ከሆነ አስፈላጊ አይደለም። ቀደም ሲል የመኪናህን ሞተር አድሰኸ ያ - መኪና በትክክል ዳገት፣ ቁልቁለት ወጥቶ ወርዶ የማይሰራልህ ከሆነ ማደስህ ገንዘብ ከማባከን በስተቀር ፋይዳ የለውም። በተመሣሣይ መንገድ ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶው ጉልበትና ገንዘብ ነው ያወጣው። የተገኘ ውጤት የለም።

ከዚህ ቀደም ሲል ሕዝቡ ተቆጥቷል፣ በጣም አምርሯል፣ ስለዚህ ኢህአዴግ ሕዝቡን ሰምቶ ራሱን ሊያስተካክል ይገባል ብለን ስንነግረው ኢህአዴግ በተቃራኒው ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎናል። ይህን አስተያየት የሚሰጡ ወገኖችን ሁሉ ፅንፈኞች ናቸው፣ ተቃዋሚዎች ናቸው፣ ከሽብር ኃይሎች ጋር የሚተባበሩ ናቸው፤ ሕዝቡ እኔን ይደግፈኛል ሲል ነበር። መጨረሻ ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲቀጣጠል የተጎዳው ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን  ሕዝቡም ነው። ለምሳሌ ፋብሪካዎች ሲቃጠሉ ባለሃብቱ ብቻ ሳይሆን እዚያ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ተጎድተዋል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ መድሃኒት እንኳን ለማስመጣት አቅም እስክታጣ ድረስ ነው፤ የውጪ ምንዛሪ እጥረት የገጠመን። ኢህአዴግ ችግሩን የሚፈጥረው ብቻውን ነው። የጉዳቱ ዳፋ የሚተርፈው ግን ለሕዝብ ነው። በአሁኑ ወቅት በተለይ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ ንረት እየታየ ነው። ይህ የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ምክንያት ነጋዴዎች በሚፈልጉት መጠንና ጊዜ ዕቃ ማስገባት ባለመቻላቸው ነው። በዚህ ችግር ተጎጂ የሆነው፣ ዋጋ እየከፈለ ያለው ይኸው የፈረደበት ደሃ ሕዝብ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በየቦታው የተሃድሶ ስብሰባ ይካሄዳል። ሰዎች ተሰብስበው እንጂ ታድሰው ሲመጡ አታይም። ኢህአዴግ በቅድሚያ የራሱን አባላት የተሃድሶ፣ የለውጡ አካል ማድረግ አለበት። አብዛኛዎቹ የኢህአዴግ አባላት የስብሰባ እንጂ የተሃድሶ አካል ሆነው እያየናቸው አይደለም። ብዙ ጊዜ ከአካባቢያቸው ወጣ ብለው ይሰበሰባሉ። አበልና አንዳንድ ጥቅማጥቅም ተቀብለው ይመለሳሉ። የተለመዱ ሥራዎችን በየቢሮአቸው ይቀጥላሉ። ሕዝቡ ግን አሁንም አገልግሎት ፈልጎ ወደመንግሥት ተቋማት ሲሄድ እየተስተናገደ አይደለም። ብዙ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ናቸው እየተባለ ሥራ የማይከናወንበት ሁኔታ እያስተዋልን ነው። በዚህ አይነት አካሄድ ለውጥ ይመጣል ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ።

ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ ያሉብኝን ችግሮች ከፓርቲዎች ጋር ተወያይቼ ለመፍታት እየጣርኩኝ ነው እያለ ነው፣ የፓርቲዎች ውይይት እንዴት አዩት?

ኢ/ር ዘለቀ፡- ይሄ ነው ቀልዱ። አሁንም ኢህአዴግ እየቀለደ ነው፣ የሚመክረው የለም፣ ሽማግሌ ጠፍቷል የምለው እዚህ ላይ ነው። መጀመሪያ ፓርቲ ማለት ምን ማለት ነው? ፓርቲ ማለት ሕዝብ የሚከተለው አካልና የገዢውን ፓርቲ በሠላማዊ መንገድ ተወዳድሮ ለመተካት የሚሠራ የፖለቲካ ድርጅት ማለት ነው። አሁን ከኢህአዴግ ጋር እየተነጋገሩ ያሉ ፓርቲዎች (ትልቅ ነን ከሚሉት ጀምሮ) ስንት አባል አላቸው? ፓርቲዎቹ ተከታይ ሕዝብ አላቸው ወይ? በሕዝቡ ይታመናሉ ወይ? አንዳንድ ፓርቲ እኮ አንድ ሰው ብቻ ያለበት ነው። አንዳንዱ ከእነሚስቱና ዘመዶቹ ፓርቲ አቋቁሞ የተቀመጠ አለ። ኢህአዴግ ጋር እየተነጋገርን ነው የሚሉ ፓርቲዎች የኋላ ታሪክ ምርጫ ቦርድ ሄደህ አጣራ። ብዙዎቹ ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ የማይጠሩ፣ በቂ አባላት የሌላቸው፣ የፋይናንስ ምንጫቸው የማይታወቅ ናቸው። ጥቂት አንድ፣ ሁለት ብለህ የምትጠራቸው ፓርቲዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ኢህአዴግ ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር ሲወያይ፣ ሲደራደር በምን መልኩ ነው፣ የእነማን ወኪሎች ሆነው ነው? የሚለው መታየት አለበት። ኢህአዴግ በቅድሚያ መወያየት ያለበት ከሕዝብ ጋር ነው።

ሰንደቅ፡- በአጠቃላይ ኢህአዴግ እያካሄደ ባለው ተሃድሶ ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ አያደርጉም?

ኢ/ር ዘለቀ፡- አሁን በተያዘው አካሄድ፣ ምናልባት ሌላ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም። ምናልባት ፓርቲዎች ጎልተው እንዳይወጡ ኢህአዴግ የሚያካሄደው አፈና አለ። ይሄን አፈና ተቋቁመው የሚወጣ ፓርቲ ካለ ምናልባት በአማራጭነት ሊመጡ ይችላል። መጀመሪያ እኮ ሰውየው ነው መታደስ ያለበት። አመለካከቱ ነው ተሃድሶ የሚያስፈልገው። አመለካከቱ ሀገራዊ እስካልሆነ ድረስ ለውጥ አይመጣም። ለምሣሌ አሳማ ታጥበዋለህ፣ ተመልሶ አፈር ላይ ይንከባለላል። ታጥቦ አይጠራም። የኢህአዴግም ሁኔታ እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ኢህአዴግ እንደሚለው ጥልቅ ተሃድሶ በለው! ተሃድሶም በለው! ወደፊትም የጥልቅ ጥልቅ ተሃድሶ ሊል ይችላል፣ ከቃላት በስተቀር የሚመጣ ተጨባጭ ለወጥ የለም።

ሰንደቅ፡- የሕዝባዊ ተቃውሞ መባባስ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ በሥራ ላይ ውሏል፣ ለአንድ ጊዜም እንዲራዘም ተደርጓል። አዋጁ ሠላምና መረጋጋትን በዘላቂነት በማምጣት ረገድ ያለውን አስተዋፅኦ እንዴት ይገመግሙታል?

ኢ/ር ዘለቀ፡- ኢህአዴግ በቅድሚያ ይህ ክስተት እንዳይመጣ ማድረግ የሚችልባቸው ዕድሎች በእጁ ላይ ነበሩ። ለምሣሌ ባለፈው ምርጫ መቶ በመቶ የፓርላማ ወንበር ከአጋሮቹ ጋር ማሸነፉን ሲገልፅ መቶ በመቶ እንዳላሸነፈ ልቡ እያወቀ ነው። ምርጫውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ አድርጎ ሕዝቡ የፈለገውን በነፃነት እንዲመርጥ አድርጎ፣ ቢያንስ የተወሰነ ወንበር እንኳን በተቃዋሚዎች ተይዞ ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ በድንገት የሚፈነዳ ውጥረት ባልመጣ ነበር። ሕዝቡ ቢያንስ በተቃዋሚዎች በኩል ፓርላማ መድረክ ላይ ጥያቄው እየቀረበለት መሆኑ ካወቀ ወደብጥብጥ የሚገባበት ምክንያት የለም። ሁሉን ነገር እኔ ጠቅልዬ ልያዝ፣ የሚል አስተሳሰብ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው። ሌላው የሕዝብ ግንኙነት ሥራው ደካማ ነው። ለምሣሌ ኢህአዴግ መንገድ ይሰራል። በእሱ ተቃራኒ ያሉ ወገኖች ምንም እንዳልሠራ ሲናገሩ፣ በኢህአዴግ ወገን ቢያንስ የተሠራውን በአግባቡ ለሕዝብ ለመግለፅ ባለመቻሉ ሠርቶም እንዳልሠራ ይሆናል። ይሄ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ድክመት ነው ብዬ አስባለሁ።

እርግጥ ነው፣ ከተነሳው ብጥብጥና ሁከት ክብደትና አስጊነት አኳያ በተለይ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማውጣቱ አስፈላጊነቱ ትክክል ነው። ምክንያቱም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ሰዎች ፋብሪካን ከማጥፋት ዘልለው ግለሰቦች ድረስ ወደመሄድ ደረጃ ደርሰው ነበር። ሌላው ወጣቱን ሀገራዊ ራዕይ እንዲኖረው አድርጎ አልቀረፀውም። የድሮውን ትምህርት ታስታውሳለህ። 3ኛ ክፍል ላይ ስለአካባቢህ፣ ስለጎረቤትህ ትማራለህ። አራተኛ ክፍል ላይ ስለኢትዮጵያ ካርታ ትማራለህ። የአርሲ ዋና ከተማ አሰላ፣ የትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ፣ የጎጃም ዋና ከተማ ደብረማርቆስ. . . እየተባልን እየተማርን ነው ያደግነው። ስድስተኛ ክፍል ላይ የዓለም ካርታ ትማራለህ፤ ስለ ዓለም ሁኔታ ታውቃለህ። በአሁኑ ሰዓት በየክልሉ ታጥሮ የተቀመጠ የትምህርት ካሪኩለም ነው ያለን። ስለዚህ በሌሎች አካባቢዎች ያለ ፋብሪካ ለሌላው ምኔም አይደለም ብሎ ሊያስብ ይችላል። አንዳንዱ ተቀጥሮ እንጀራ የሚበላበትን ፋብሪካ አጥፍቶታል። ይሄ ወጣቱ የተገነባበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን የሚጠቁም ነው። ሕዝብን በጥበቃ በዘላቂነት ልታቆመው አትችልም። ትክክለኛና ወንዝ የሚያሻግር ፖሊሲ ያስፈልጋል። ብቸኛ መንገዱ ሕዝብ የሚለውን መስማት፣ ያሉትንም ችግሮች በተጨባጭ መፍታት ብቻ ነው።

ሰንደቅ፡- በእንዲህ ዓይነት የችግር ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ምን መሆን  ነበረበት?

ኢ/ር ዘለቀ፡- የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው፣ ሕዝብን ማንቀሳቀስ አቅም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢኖሩ ኖሮ ትልቅ ሚና ይኖራቸው ነበር። ችግሮች እንዳይባባሱና ሀገር አደጋ እንዳይወድቅ ይረዱ ነበር። በውጭ ሀገር እንደምናየው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝብን አጀንዳ ይዘው ገዢውን ፓርቲ በሠላማዊ መንገድ በማስገደድ ጭምር ወደጠረጴዛ እንዲመጣ፣ የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ስለሚያደርጉ ችግሩ ባለመፈታቱ የሚመጣ ሁከትና ብጥብጥ አስቀድሞ ማስቀረት እንደሚችሉ የምናየው ነው። ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ በዚህች ሀገር ቢኖር ኖሮ አንድም ሁከትና ብጥብጥ አይከሰትም ነበር፣ አንድም ፋብሪካና ንብረት አይወድምም ነበር። በሁከትና ብጥብጥ ምክንያት ዜጎች ለሞትና ለመፈናቀል አይበቁም ነበር። እኛ ሀገር ያሉ ተቃዋሚዎች (ይቅርታ ይደረግልኝና) ቢኖሩም አይጠቅሙም፣ ባይኖሩም አይጎዱም።    

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዛሬ 46 ዓመታት በፊት የተመሠረተና በእንቅስቃሴውም አብዛኛውን የኢትዮጵያ አካባቢዎች (ክልሎች) በመሸፈን ላቅ ያለ ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ነው። ኮሚሽኑ ከሚያደርጋቸው መጠነ ሰፊ የልማትና የርዳታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት (CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ፣ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል በቀዳሚ አርአያነት አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም በቅቷል። ከዚህና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከኮምሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋር ባልደረባችን ፍሬው አበበ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።


ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያለውን አደረጃጀት ቢገልጹልን?


ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ በህግ ክፍል ማስታወቂያ 415/1964 በነጋሪት ጋዜጣ፣ ከታኅሣሥ 26 ቀን 1964 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት በመሆን ተቋቁሞ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲም ሪፐብሊክ መንግሥት፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጄንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት፣ በኢትዮጵያዊ ነዋሪዎች የበጐ አድራጐት ድርጅትነት በምዝገባ ቁጥር 1560 ተመዝግቦ የማህበራዊና የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ የበጐ አድራጐት ድርጅት ነው። ድርጅቱ፣ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ቦርድና የአመራር አባላት ያሉት ኮሚሽን ነው።


በመሆኑም የልማት ኮሚሽን፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የወገን ደራሽ መሆንዋን በማረጋገጥ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የነፍስ አድን ርዳታ በማድረግ ብሎም መልሶ በማቋቋም እና በልማት በማገዝ ፈርጀ ብዙ አገልግሎት ሲስጥ ቆይቶአል፤ አሁንም እየሰጠ ይገኛል።


ሰንደቅ፡- በአኹኑ ሰዓት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዋና ትኩረቶች ምንድን ናቸው?


ብፁዕነታቸው፡- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚስፋፉበትን መንገድ መቀየስ፣ በገጠር የሚኖሩ ዜጐች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ የመቀየስና የመሥራት፣ የኤች.አይቪ/ኤድስ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተቀናጀና የተጠናከረ ሥራ መሥራት፣ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የበኩሉን የስራ ድርሻ ማበርከት፣ በእናቶች እና ሕፃናት ሥርዓት ምግብ ሥራ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ መሳተፍ፣ ስደተኞችን የመቀበልና የማስተናገድ ሥራን አጠናክሮ መቀጠል፣ ችግር ፈቺ የሆኑ የልማት ስራዎችን በማጥናት እና በፕሮጀክት በማካተት የሥራ አጥ ወጣቶችን ና ችግረኛ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኑሮአቸው የተሻሻለ እንዲሆን ማገዝ እና የመሳሰሉት ናቸው።


ሰንደቅ፡- በልማት የተለያዩ ዘርፎች በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራትና ተጨባጭ ውጤቶች ምን ምንድን ናቸው?


ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽኑ ከበርካታ አገር አቀፍና የውጭ በጎ አድራጐት ድርጅቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር በአገሪቷ በሚገኙ ክልሎች ለሚኖሩ አያሌ ማህበረሰቦች ከአሉባቸው ችግሮች እንዲላቀቁ በማድረግ ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን በመሆን አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ይኸውም በበርካታ ወረዳዎች የገጠር ልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር በመስኖ፤ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የተሻሻሉ ግብርና ዘዴዎችን በማሥረጽ፣ በገቢ ምንጭ ተግባራት፣ በአቅም ግንባታ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበረሰብ የአደጋ ጊዜ መቋቋሚያና መጠባበቂያ ፈንድ ማህበራትን በመመስረትና በማጠናከር፣ በሥርዐተ ምግብ አጠቃቀም፣ በሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ በኤች አይቪ እና በመሳሰሉት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።


በሌላ በኩል በኮሚሽኑ ሥር ባለው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች መምሪያ አማካኝነት ከጐረቤት ሀገራት ተሰደው የሚመጡትን እና ከስደት ተመላሾችን፣ ኮሚሽኑ ባቋቋመው የስደተኛ ካምፖች በመቀበል አስፈላጊውን ሰብአዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ አድርጓል። ለዚህም ዐብይ አስረጂ የሚሆነው፣ ልማት ኮሚሽኑ በተገበራቸው በዘላቂነታቸው በተረጋገጡ የልማት ተቋማት እና ለህብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት፣ በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት (CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ ኮሚሽኑ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በቀደምትነት አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም በቅቷል። በተጨማሪም የክልል፣ የዞን እና የወረዳ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የልማት ኮሚሽናችን በተገበራቸው የልማት ሥራዎች በተጠቃሚው ሕብረተሰብ ላይ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በመመልከት ምስጋናና እውቅና እየቸሩን ይገኛሉ።


ሰንደቅ፡- በክርስቲያናዊ ተራድኦ ረገድ፣ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥና በድርቅ ኮሚሽኑ የፈፀማቸው ጉዳዮች ቢዘረዝሩልን? ለምሳሌ፡-


ብፁዕነታቸው፡- ልማት ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት ለዓለም አስጊ ለሆነው የአየር ለውጥ ችግር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአየር ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን በፕሮጀክት ጥናት በማካተት ተግባር ላይ እያዋለ ነው። ይኸውም ለተጠቃሚ አርሶአደሮች የአየር ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝሪያዎችን በማቅረብና በማከፋፈል፣ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ እና ጥበቃ ሥራን በማጠናከር የጎላ ተግባር እያከናወነ ነው።


ልማት ኮሚሽኑ ለቤተ ክርስቲያን ደን ልማትና ጥበቃ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት የቤተክርስቲያ ደን ፕሮጀክት አጥንቶ በአጋርነት የሚሰራ ድርጅት በማግኘቱ በተመረጡ ገዳማት ላይ የደን ጥበቃና ማስፋፋት ሥራን መሠረት በማድረግ የተራቆቱ መሬቶች በደን የሚሸፈኑበትን ሁኔታ ለማስቻል ደረጃ በደረጃ እያከናወነ ይገኛል።


በተጨማሪም ኮሚሽኑ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጅ እና የሶላር መብራት ተከላ በ15 ገዳማት ያከናወነ ሲሆን ለወደፊቱም በሰፊው የሚሠራበት የልማት መስክ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።


የልማት ኮሚሽኑ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተቋማትን በመገንባት እና የመስኖ ልማት በማስፋፋት ወደፊት በድርቅ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ለመቋቋም የሚያችል ስራዎችን በአፋር እና በሰሜን ሸዋ የአፋር አዋሳኝ ወረዳዎች እና በሌሎችም ላይ በሰፊው በማከናወን ላይ ይገኛል።


ሰንደቅ፡- በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች ውስጥ ፣ የሕዝቡ ተሳትፎ ምን ይመስላል?


ብፁዕነታቸው፡- ልማት ኮሚሽኑ ሥራውን እስከ ታች አውርዶ ለመሥራት የሚያስችል የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን በክልል እና በዞን ከተሞች ስላሉት በእነርሱ አማካኝነት ሥራው ማህበረሰቡን መሠረት አድርጎ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በሚንቀሳቀስባቸው የፕሮጀክት ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሥራውን ለማስተዋወቅም ሆነ ከህዝብ ጋር ለመሥራት ምቹ መንገድ በመኖሩ እና የልማት ኮሚሽኑ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስላለው የማህበረሰቡ በልማት ተሳታፊነት በጣም ከፍተኛ ነው። የልማት ሥራዎቻችን በዘለቄታዊነት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የማህበረሰቡ ተሳትፎ የታከለበት በመሆኑ በግልጽ የሚታይ እውነት ነው።


ሰንደቅ፡- የስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን፣ መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላትና መልሶ ማቋቋም በኩል ኮሚሽኑ ሥራዎች ያገኙትን ውጤቶች ቢያብራሩልን?


ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን በመቀበልና አስፈላጊዉን ርዳታ በማድረግ በሀገሪቱ ቀደምት ታሪክ ያላት ስትሆን በዚህም ከአምስት አስርት አመታት በላይ አገልግሎቱን እየሰጠች ትገኛለች። በዚህም ቤተክርስቲያኗ የሀገሪቱ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለስደተኞችና ተመላሾች በተቀናጀ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ሳይጀመሩ እሷ ይህን አገልግሎት በቀደምትነት መስጠቷን ያሳያል። በነበሩት የድጋፍ ጊዜያትም ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊ የሆኑና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ያማከለ ድጋፍና ርዳታ መስጠት ተችሏል።


በሂደትም የቤተክርስቲያኗዋ ክንፍ የሆነዉ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን 1964 በህግ ሲቋቋም የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ እንደ አንድ የስራ ዘርፍ በማካተት በርካታ ተግባራትን ለመፈፀም በቅቷል።


ስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ መመሪያ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሥር በመሆንና የራሱን አስተዳደር በማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።


በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ከመንግሥት፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና እና ከልሎች አለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በበአዲስ አበባና ከተማ አካባቢዋ ባሉ ከተሞች እና በአራም ሀገሪቷ አቅጣጫ በሚገኙ 18 የመጠለያ ጣቢያዎች ማካኝነት ቁጥራቸው በየጊዜ የሚለያይ ቢሁንም በአሁኑ ሰዓት ከ801 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ ሀገር ስደተኞች ማለትም ከደቡብ ሱዳን፤ ከሶማሊያ፤ ከየመን፤ ከኤርትራ፤ ከኮንጎ፣ ከሱዳን፣ ወ.ዘተ ለመጡ ስደተኞች የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።


ይኽውም፡- ኮሚሽኑ ለስደተኞች የመጠለያ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የገንዘብ፣ የጤና፣ የማህበራዊና የስነልቦና ምክር፣ የትምህርትና የሙያ ክዕኖት ስልጠና ድጋፍ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን ይሰጣል። በተጨማሪም ስደተኞች ቤታቸው እንዳሉ ሆነው እንዲሰማቸው ለማድረግ የሚኖሩበት መጠለያ አካባቢ ምቹ የሆነ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ይኸውም የአካባቢ እክብካቤ፣ የአካባቢና የግል ንጽሕና እንዲጠበቅ እንዲሁም የመጡበትን አዲስ አካባቢ እንዲላመዱ የማስተማርና የማሳወቅ ሥራዎች በሰፊው ይከናወናሉ።


በመሆኑም ስደተኞች በሚሰጣቸው የትምህርት እና የሙያ ክህሎት ድጋፍ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ሆነው የተለያዩ የገቢ ምንች የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እራሳቸውን ለማቋቋም ላይ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ ስደተኞችን ከቤተሰብ ጋር በማገኛኘት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል።


ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ስደተኞች የተለየዩ የቁሳቁስ ድጋፍ፤ በኤች አይቪ ኤድስ ድጋፍና እንክብካቤ፤ በግጭት አፈታት በፆታ ጥቃት ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ይሰራል።


ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ከመሰል አገራዊና የውጭ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅትና መተባበር ምን ይመስላል?


ብፁዕነታቸው፡- የልማት ኮሚሽኑ በሚተገብራቸው የልማት ሥራዎች እና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት ከሌሎች ልቆ እስከ መሸለም ያበቃው ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር ተናቦ፣ ተቀናጅቶ እና ተባብሮ በመሥራቱ ነው። እንደሚታወቀው ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚቻለው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተባብሮ መስራት ሲቻል ነው።


ኮሚሽኑ ይህን መርሆ በዋናነት በመከተል በግልጽነት እና በተጠያቂነት እየተንቀሳቀሰ በአነስተኛ በጀት ታላላቅ የልማት ሥራዎችን በመገንባት እውን እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በከፈታቸው የልማት የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችም ሆነ የፕሮጀክት ጽ/ቤቶች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ከሁሉም የልማት ባለድርሻ አካላት ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በፕሮጀክት ሥራ መልካምድራቸው አስቸጋሪ በሆኑ ሥፍራዎች ሁሉ የተለያዩ የልማት ተግባራትን በማከናወን እና ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የካበተ ልምድ ስላላቸው በየፎረሙም በተምሳሌነት የሚቀርቡ ሆነዋል።


ሰንደቅ፡- የኮሚሽኑ ፕሮጀክቶች እና እንቅስቃሴዎች፣በሀገራዊ ሽፋን ያላቸው ስርጭት የተመጣጠነ ነው?


ብፁዕነታቸው፡- አዎን! በእኛ በኩል ሙሉ በሙሉ ባይሆን እንኳ ፕሮጀክቶች ያላቸው ስርጭት በአብዛኛው የተመጣጠነ እንደሆነ እምነታችን ነው። ኮሚሽኑ በአኹኑ ሰዓት በሚያካሂዳቸው 27 የሚሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች እና በ18 የስደተኞች መቀበያ ካምብ አማካኝነት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የፕሮጀክት ወረዳዎች ላይ እየሠራ ይገኛል። ይኸውም በጋምቤላ ክልል፡ ጋቤላ ዙሪያ ወረዳ፣ ፊኝዶ፣ ተርኪዲ፣ ኩሌ፣ ሆኮቡ፣ በቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል፡ በከማሽ፣ በኩርሙክ፣ በሸርቆሌ፣ በባምፓሲ፣ በቶንጎ፣ አፋር ክልል፡ በአርጎባ ልዩ ዞን፣ ሰሙ ሮቢ፣ ዱለቻ፣ በኦሮሚያ ክልል፡ በጉርሱም፣ በጃርሶ፣ በአርሲ ሮቤ፣ በቄለም ወለጋ፣ በሶማሌ ክልል፡ በጂጂጋ፣ በሸደር፣ በቀርቢበያህ፣ በአውበሮ፣ በኮቤ፣ በመልካ ጂዳ፣ በሔለወይኒ፣ በቆልማንዩ፣ አማራ ክልል፡ በሊቦ ከምከም፣ በአንኮበር፣ በጊሼ ራቤል፣ በዳወንት፣ በበርኸት፣ ትግራይ ክልል፡ በክሊተ አውላዐሎ፣ በእንደርታ፣ ሽመልባ፣ አደ አርሹ፣ እፀጽ፣ ደቡብ ክልል፡ ጉራጌ፣ ሙዑር፣ ቡታጀራ፣ ወልቂጤ፣ ሲዳማ፣ ጌዲዮ፣ ይርጋ ዓለም፣ አለታ ወንዶ፣ አላባ፣ አርባ ምንጭ በ10 ወረዳዎች የኤች/አይቪ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ሥራዎች ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች በ150 ወረዳዎች ላይ የኤች/አይቪ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ሥራዎች ያከናውናል።


ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች ሲያከናውናቸው የቆያቸው የልማት ፕሮጀክቶች እየተዘጉ እንደሆነ ይነገራል፣ ፕሮጀክቶቹ የሚዘጉበት አልያም የሚቋረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?


ብፁዕነታቸው፡- ፕሮጀክቶች በተፈጥሮአቸው የጊዜ ገደብ አላቸው ይሁንና በኮሚሽኑ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች እስከ ታች የሚዘልቀውን የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን፣ ፕሮጀክት ጽ/ቤቶችን እና የማህበረሰብ ማህበራትን በመጠቀም ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት በመከተል ሕብረተሰቡ የተለያዩ ሕግጋትን እና ደንቦችን እንዲያወጡ በማገዝ ፕሮጀክት በዘለቄታነት የሚቀትልበትን ሁኔታ እያመቻቸ በራሱ በህብረተሰቡ እየተመራ የሚከናወኑ የፕሮጀክት ዓይነቶች ናቸው።


ይህንን ለማድረግ ፕሮጀክቶች ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲቀጥሉ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ተጋባራት ይከናወናሉ። ተጠቃሚው ሕብረተሰብ በፕሮጀክት ጥናት፣ እቅድ፣ ክንውን፣ ክትትልና ግምገማ እንዲሳተፉ ይደረጋሉ። በዕቅድ ዝግጅት ወቅት የሕብረተሰቡ፣ ማህበራዊ ድርጅቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ የአካባቢ አመራሮች ወዘተ በፕሮጀክት ሂደት ውስጥ ያላቸው ድርሻ በግልጽ እንዲቀመጥ ይደረጋል። የፕሮጀክት መጀመሩን የሚያበስር ዓውደ ጥናት ይዘጋጃል፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የእያንዳንዱ የሥራ ድርሻ በግልጽ ለውይይት ይቀርባል። የፕሮጀክት ተግባራትም እንደተጠናቀቁ በወቅቱ ለሚመለከተው ባለድረሻ አካላት በሕጋዊ የርክክብ ሰነድ ተረክቦ እንዲያስተዳድራቸው ይደረጋል።


ሰንደቅ፡- አንዳንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የበጎ አድራጎት ማህበራት ሕግ አላሰራ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ፣ በዚህ ረገድ ኮምሽኑ የገጠመው ችግር ይኖር ይሆን?


ብፁዕነታቸው፡- ኮምሽናችን ከ46 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየ ነው። በዕድሜው ሶስት መንግሥታት ተፈራርቀዋል። በእነዚህ ዘመናት ሕጎች ተለዋውጠዋል። ኮምሽኑ ሁሉንም እንደአመጣጡ አስተናግዷል። ፈቃድ ሰጪው አካል ቀድሞ በፍትህ ሚኒስቴር ነበር፣ አሁን ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ተቋቁሞ የራሱን ሕግ ይዞ እየሠራ ነው። በእኛ በኩል ቀድሞውንም እንቅስቃሴያችን ተጠቃሚውን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የገጠመን የጎላ ችግር የለም። 70 በ30 የሚለውን ሕግ ቀድመን ተግብረነዋል። ነገር ግን ይህ 10 በ90 (10 ከመቶ በላይ ከውጭ ለጋሾች ገንዘብ መቀበል አይቻልም) የሚለው የውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ብዙም አልተቀበሉትም። እሱ ነው ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው። ሕጉ የሀገሪቱን ሁኔታ፣ የረጂዎችን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም። ለእኛ ግን ትልቅ ተጽዕኖ ግን ይህ አይደለም። የእኛ ትልቅ ተጽዕኖ ሕዝባችን ከተረጂነት መላቀቅ አለመቻሉ ነው። የውጭ እጅ ማየት የትም አያደርስም። የጠባቂነት መንፈስ ያሳድራል። ከጠባቂነት መንፈስ ተላቀቅቀን ባለን ሐብት መጠቀም መጀመር አለብን።


የረጂዎችንም ሁኔታ ስንመለከት ቅድሚያ የሚሰጡዋቸው ችግሮች በዓለም ዙሪያ እየበዙ መጥተዋል። ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ ጎረቤቶቻችን ሱዳንና ሶማሊያ በየዕለቱ ሰዎች እየሞቱ፣ እየተሰደዱ ረጂዎች ለእኛ ቅድሚያ ሰጥተው እጃቸውን ሊዘረጉልን አይችሉም። በዚህ ምክንያት ከልመናና ከፈረንጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ መስራት ይኖርብናል። ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ለተወሰነ ጊዜ ከችግር ለመውጣት ሊጠቅመን ይችላል፣ ለሽግግር ጊዜ ሊረዳን ይችላል። በዘላቂነት ግን የሚጠቅመን አይደለም።


ሰንደቅ፡- ለልማትና ለዕርዳታ የሚውል ሀብት ከሀገር ውስጥ ለማሰባሰብ ዕቅድ አላችሁ?


ብፁዕነታቸው፡- በትክክል፣ የውጭ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የሌለበት ሕግና ደንብ አውጥተናል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ምሁራን ጋር በዚህ ጉዳይ ሕግና ደንብ አዘጋጅተናል። በቀጣይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በሥራ ላይ የሚውል ይሆናል። ይህ ጥናት ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆን ራሳችን እንድንችል የሚረዳን ይሆናል ብለን እናስባለን። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ 10 ሺ የሚጠጉ ሕጻናትን ይንከባከባል። ከእነዚህ ሕጻናት መካከል ወላጅ አልባ የሆኑ አሉ። ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚረዱ አሉ። ለእነዚህ የምናገኘው ዕርዳታ በአሁኑ ሰዓት በግማሽ ቀንሷል። ምን እናድርግ ብለን አይተነዋል። በሃሳብ ደረጃ አንድ ምእመን አንድ ልጅ በፈቃደኝነት ቢይዝ ብለን ብዙ ሕጻናት መርዳትና መደገፍ እንደሚቻል አይተናል። በአሁኑ ወቅት በጉድፈቻ ወደውጭ የሚሄዱ ሕጻናት ምን አሳዛኝ ሁኔታ እየደረሰባቸው እንደሆነ እናውቃለን። ይህ ችግር እንዲቆም እዚሁ በሀገራችን ልንረዳዳ፣ ልንደጋገፍ ይገባናል።


ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሾች ጋር ያለው ግንኙነትና የወደፊት ዕቅዱን ቢጠቁሙን?


ብፁዕነታቸው፡- የልማት ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር የላው ግንኙነት መላካም እና በተሸለ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ዋናው ጉዳይ ለሚረዱን ድርጅቶች፣ ለመንግሥት እና ለተጠቃሚ ማህበረሰብ ታማኝ ሆኖ በመገኘት የታለመለትን ፕሮጀክት በጥራትና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ በጽናት ማከናወን ነው።


ልማት ኮሚሽኑም ዋነኛ ዓላማ የሕብረተሰቡ ኑሮ ተሻሸሎ ማየትና ለተሻለ እድገት ማብቃት በመሆኑ በዚሁ ረገድ ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል። ግለፀኝነት እና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በየጊዜው ከለጋሽ ድርጅቶች አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝ ቆይቷል፣ አሁንም እያገኘ ይገኛል።


በተለይ ኮሚሽኑ የህፃናት ፖሊሲን ቀርፆ እና አፀድቆ በሥራ ላይ ማዋሉ እና የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አጋርነት (Humanitarian Accountability Partnership) ፍሬም ወርክ አዘጋጅቶ እና አፅድቆ በመተግበሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክሯል።


ኮሚሽኑ በቅርቡ ሁሉንም የፕሮጀክት አጋሮች ተወካዮችን በመጋበዝ ባለን የጋራ አጀንዳ እና በቀጣይ ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት በተመለከተ ለመወያየት ዕቅድ በመያዝ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።


ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ ለማጠናከር ምን እየሠራ ነው?


ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽኑ ከውጪ ከሚያገኘው የርዳታ ድጋፍ በተጨማሪ በገቢ ራስን ለማጠናከር እንዲቻል ዓላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የውጭ ርዳታ በእጅጉ እየቀነሰ የመጣ ስለሆነ የተለያዩ የገቢ ምንጭ ዕቅድ ማዘጋጀትና መሥራት ግዴታ ሆኖአል። በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ ለገቢ ምንጭ መምሪያ አደራጅቶ ሥራ ጀምሯል።


በቃሊቲ አካባቢ ከሚገኘው የኮሚሽኑ ጋራዥ እና መጋዘን እንዲሁም የከርሰ ምድር መቆፈሪያ ሪግ ማሽን ጨምሮ ለዚሁ ተግባር በመዋል የገቢ ምንች ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው።


ኮሚሽኑ በአኹኑ ጊዜ የገቢ ምንጩን በበለጠ ለማጠናከር እንዲያስችለው አንድ የሻማ ማምረቻ ፋብሪካ እና በሁለት ቦታዎች ላይ የታሸገ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም መሠረታዊ ጥናቶች በማድረግ ላይ ይገኛል።


ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በእንጦጦ አካባቢ የሆስፒታል ግንባታ እቅድ እንዳለው ይታወቃል፣ ሂደቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ ይቻላል?


ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከ46 ዓመት በፊት የልማት ኮሚሽኑን ሲያቋቁም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን ለመርዳት፣ አባት እናት የሌላቸውን እና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ምዕመናን ከውጪና ከውስጥ በሚገኝ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።


ቤተክርስቲያኒቱ በገዳማት፣ በአድባራትና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብዙ በጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት ስላላት መሬቱን በማልማት ገዳማቱና ህብረተሰቡ ከልማቱ ውጤት እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ እንዲሁም በየአካባቢው የትምህርት ቤትና የጤና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ከመንግስት ጋር በመተባበር መሠረተ ልማት ማካሄድ አንዱ ተግባፘ ነው።


ይህን የጤና አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማዳበር በቅርቡ በእንጦጦ አካባቢ አንድ ራሱን የቻለ ከፍተኛ ሆስፒታል ተቋቁሞ በአይነትና በጥራት አገልግሎት እንዲሰጥ እቅድ ወጥቷል።


ይህ የተጠቀሰው ሆስፒታል በአይነቱም ሆነ በባህሪው የተለየ ከመሆኑም ባሻገር የግንባታው ወጪ ከ370,000,000 የአሜሪካን ዶላር (ሦስት መቶ ሰባ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ) ሲሆን በኢትዮጵያ ብር ሲተመን ደግሞ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር (ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር) በላይ ግምት ተይዞለታል።

 

ሥራው በሚጀምርበት ጊዜም ለ2100 ቋሚና ለ369 ጊዚያዊ በጥቅሉ ለ2469 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።


በተመሳሳይ ሂደት ሆስፒታሉ የልዩልዩ በሽታዎች መታከሚያና ማገገሚያ ክፍሎችና መሳሪያዎች የሚኖሩት ሲሆን የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ የዲፕሎማቲክና የኤምባሲ ሠራተኞችን እና ከልዩልዩ አካባቢ የሚመጡ በሽተኞችን ለማከም ከ200 በላይ አልጋዎች ይኖረዋል።


ቅድመ ጥናቱ እንደሚያሳየው ይህ በቀጥታ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና ከአሜርካን ሀገር ከሚገኝ ሌዠንደር ኮርፕ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በአጋርነት የሚቋቋመው ሆስፒታል የውጪ ምንዛሪን በማስገኘትና በአገሪቱ ውስጥ የቱሪዝምን አገልግሎት ለማስፋፋት እንደሚረዳ ይታመናል።


የአሜሪካ መንግስትና በአሜሪካ ውስጥ ያሉ አበዳሪ ድርጅቶች ብድሩንም ሆነ ለብድሩ ዋስትና ለመስጠት ኃላፊ እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል።


በኢትዮጵያ በኩል ግንባታውንና ከውጪ የሚገኘውን መዋዕለነዋይ እውን ለማድረግ በእንጦጦ አካባቢ ያለውና ለዚሁ ጉዳይ የተከለለውን መሬት ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ እንገኛለን። 

 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጌዲኦ ዞን ከሰኔ ወር 2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ተከስቶ የቆየውን ሁከትና ብጥብጥ የሚመለከት የምርመራ ውጤት ሪፖርት በትላንትናው ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አቅርቧል።

የኮምሽኑ ኮምሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር ሁለት ሰዓት ገደማ በወሰደውና በንባብ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በግልጽ እንዳመለከቱት ሁከትና ብጥብጡ በኦሮሚያ ክልል በ15 ዞኖችና በ91 ወረዳዎች ማለትም በፊንፊኔ ዙሪያ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ በወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ በጉጂ፣ በባሌ ፣በምዕራብና ምስራቅ አርሲ እንዲሁም በአማራ ክልል በ6 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች ማለትም በሰሜን ጎንደር ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በባህርዳር፣በምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም፣ በአዊ ዞን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጌዲኦ ዞን 6 ወረዳዎችና ከተማዎች ያዳረሰ ነው።

የኮምሽኑ ምርመራ መሠረት ያደረገው በዋንኛነት የኢፌዲሪ ሕገመንግስት ምዕራፍ 3 የተቀመጡትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት አጽድቃ የሕግ አካልዋ ያደረገቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን ነው። በዚህ መሠረት በሕገመንግስቱ ድንጋጌዎች መካከል በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብት፣ የነጻነትና እኩልነት መብት፣ የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመዘዋወር ነጻነት፣ ፍትህ የማግኘት መብት፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብት የምርመራው የትኩረት ነጥቦች እንደነበሩ ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል።

በኮምሽነሩ ሪፖርት መሠረት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ሁከትና ብጥብጥ ብቻ 462 ሲቪል ሰዎች፣ 33 የጸጥታ ኃይሎች፣ በድምሩ 495 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። 338 ሲቪልና 126 የጸጥታ ኃይሎች በድምሩ 464 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን በመቶ ሚሊየን የሚገመት የሕዝብ፣ የመንግሥትና የግል ባለሃብቶች ንብረት ወድሟል።

በተለይ በኦሮሚያ ክልል መስከረም 22 የተከበረው የእሬቻ በዓል ላይ በተሰቀሰቀሰ ሁከትና ብጥብጥ ለመቆጣጠር የተተኮሰ አስለቃሽ ጢስ ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎች ወደገደል በመግባታቸውና በመረጋገጥ አደጋ የ56 ሰዎች ሕይወት ማለፉን በኮምሽኑ ምርመራ ማረጋገጡን የተጠቀሰ ሱሆን የሁከትና ብጥብጥ ግልጽ አደጋ መደቀኑ እየታወቀና እየታየ በዓሉ እንዲካሄድ መደረጉ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ መሆኑን ኮምሽኑ በመጥቀስ በዚህ ውሳኔ ውስጥ ያሉ የመንግሥት አካላትና የበዓሉ አዘጋጅ ኮምቴ አባላት በየደረጃው ሊጠየቁ ይገባል ብሏል። በተጨማሪም በዓሉ የሚካሄድበትና ሰዎች ለመሞት መንስኤ የሆነው ሆራ አርሰዲ ገደል አስቀድሞ መደፈን ይገባው እንደነበር ዶክተር አዲሱ ጠቅሰው ይህ ባለመደረጉ ለደረሰው አደጋ የሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ተጠያቂ ናቸው ሲል አስታውቀዋል። በእሬቻ በዓል ወቅት በስፍራው የተሰማሩ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ሁኔታውን ለማረጋጋት ትግዕስት በተሞላበት መንገድ ሙያዊ ተግባራቸውን መፈጸማቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ብጥብጥ ለማስነሳት የተዘጋጁ ኃይሎች መኖራቸው እየታወቀ ተገቢው እርምጃ በወቅቱ ባለመውሰዳቸው ተጠያቂ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ጌዲኦ ዞን በ4 ወረዳዎችና በ 2 የከተማ መስተዳድሮች ማለትም ዲላ ከተማ፣ ዲላ ዙሪያ ወረዳ፣ወናጎ ወረዳ፣ይርጋጨፌ ወረዳ፣ ይርጋጨፌ ከተማና ኮሸሬ ወረዳ ሁከትና ብጥብጡ መስከረም 27 ቀን 2009 ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ለሁለት ቀናት መካሄዱን አስታውሷል። መንስኤ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ የይዞታ ውሳኔ ጉዳይ አንቀበልም የሚሉ ወገኖች ያስነሱት መሆኑ ታውቋል። በዚህ ሁከትና ብጥብጥ ዘርና ጎሳን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መድረሳቸውን ኮምሽኑ አስታውቋል። በዚህ ጥቃት 34 ሰዎች ሲሞቱ፣ 60 የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 4 ሺህ ያህል ሰዎች ተፈናቅለዋል። በዚህ ድርጊት እጃቸው ያለበት የመንግስት አስተዳደር አካላትና ግለሰቦች ተጠያቂ መሆናቸውን የክልሉ መንግሥት ለተፈናቃዮችና ለተጎጂዎች መልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ተመልክቷል።

በአማራ ክልል በ6 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች ማለትም በሰሜን ጎንደር ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በባህርዳር፣በምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም፣ በአዊ ዞን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጌዲኦ ዞን 6 ወረዳዎችና ከተማዎች ሁከትና ብጥብጥ መታየቱን የኮምሽኑ ሪፖርት ያሳያል። በተለይም በሰሜን ጎንደር ዞን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ሰልፎችና አለመረጋጋት የነበረ ሲሆን ህዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም በመተማ ወረዳ የነበረው በሕግ ዕውቅና የሌለው ሰልፍ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በቅማንት ብሔረሰብና በአማራ መካከል ግጭት ተነስቶ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም መንስኤ ሆኗል። በተጨማሪም በሰሜን ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አካባቢ ብሔርን ማዕከል ያደረገ ጥቃት በትግራይ ተወላጆች ላይ መፈጸሙን ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር በሪፖርታቸው አመልክተዋል።

አያይዘውም በ2008 ዓ.ም በተለያዩ አካባቢዎች “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም፣ የአማራ ክልል ካርታ ተቆርጦ ወደትግራይ ክልል ሄዷል፣ የትግራይ ብሔር የበላይነት አለ፣ የራስ ዳሸን ተራራ የሚገኘው በትግራይ ክልል ውስጥ ነው ተብሎ በመማሪያ መጽሐፍ መታተሙ አግባብ አይደለም እንዲሁም በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል የሚገኘው የጸገዴ ወሰን ጥያቄ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” በሚሉ ምክንያቶች በተለያዩ ጊዜያት ሁከትና ብጥብጥ እንደነበረ ሪፖርቱ ያስረዳል። ይህ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የፌዴራል የጸረ ሽብር ግብረኃይል በጎንደር ከተማ ማራኪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ከለሊቱ 10፡30 ሰዓት ባለው ጊዜ ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሯል። የነበረው አለመግባባት ወደተኩስ ልውውጥ አምርቶ የአካባቢው ነዋሪዎችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የህይወት መጥፋትን አስከትሏል። ይህን ችግር ተከትሎ እንደፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ድረገጾችና በኢሳት ቴሌቭዥን በኩል ሁከቱን ለማባባስ በመሞከሩ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ህገወጥ ሰልፍ መካሄዱንና ይህንንም ተከትሎ በየአካባቢው ሰልፎች መካሄዳቸውን ዶ/ር አዲሱ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተነሳው ሁከት 110 ሲቪል ሰዎችና 30 የጸጥታ አባላት ሲሞቱ፣ 276 ሲቪል ሰዎችና 100 የጸጥታ ኃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በሁሉም አካባቢዎች ለተነሱ ግጭቶች እንደመንስኤ ከተቀመጡት መካከል ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖር፣ የሥራ አጥነት፣ ሙስናን የብልሹ አሰራር መንሰራፋት፣ የልማት ዕቅዶች በወቅቱ ተግባራዊ መሆን ያለመቻል፣ የኑሮ ውድነትና የመሳሰሉ ችግሮች ተመልክተዋል።

በግጭቶቹ እጃቸው አለበት ከተባሉት መካከል በኦፌዲሪ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ በየደረጃው ያሉ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ኮምሽኑ አሳስቧል።¾

 

“በግብጽ አብያተ ክርስቲያናት እሁድ ዕለት በደረሰ የአጥፍቶ መጥፋት የቦምብ ጥቃት 45 ያህል ክርስቲያን ምዕመናን የመገደላቸው ዜና ዓለምን ያስደነገጠ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ዓመት ከደረሱ የቦምብ ጥቃቶች መካከል ታህሳስ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በካይሮ ከተማ የደረሰው የቦምብ ጥቃት ከ25 በላይ ግብጻውያን ክርስቲያኖችን መግደሉንና ከ50 በላይ የሚሆኑትን ማቁሰሉ የሚታወስ ነው። እሁድ ዕለት በሁለት ማለትም በአሌክሳንደሪያ የቅዱስ ማርቆስና በቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተክርስቲናት በጸሎት ላይ በነበሩ ምዕመናን ላይ ሆን ተብሎ በተቀነባበረ የቦምብ ጥቃት ከደረሰ በኃላ የአልሲሲ አስተዳደር ለሶስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል። ረቂቅ አዋጁ ለጸጥታ ኃይሎች ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪዎችን እንዲይዙና እንዲፈትሹ ሥልጣን የሚሰጥ ነው። ረቂቅ አዋጁ የግብጽ ፓርላማ ካጸደቀው በኋላ በሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል። ለቦምብ ጥቃቱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው (ISIS) ኃላፊነቱን ወስዷል። በአሁን ሰዓት ግብጻዊያን ወንድምና እህቶቻችን የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ላይ ናቸው።

ስለዕለተ ሰንበቱ ጥቃት


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በአህያ ውርንጭላ ኹኖ፣ “ሆሣዕና በአርያም” እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበትን ዕለት በምናስብበትና በሕማማቱ ዋዜማ በምንገኝበት በስምንተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት (የፀበርት እሑድ)፣ ዛሬ፣ በሰሜናዊ ግብጽ የታንታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በአሌክሳንደርያ የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ደጃፍ፣ በአሸባሪዎች በተፈጸሙ ተከታታይ የቦምብ ጥቃቶች፣ ከ45 በላይ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ተገደሉ፤ ከመቶ ያላነሱ ቆሰሉ።


ከሟቾቹ 29ኙ፣ በናይል ዴልታ ከተማ በሚገኘው የታንታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ በምእመናኑ መቀመጫ የፊት ወንበሮች ሥር በተጠመደው ቦምብ የተገደሉቱ ሲኾኑ፤ 71ዱ ደግሞ በፍንዳታው የተጎዱ ናቸው።


ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ መንበረ ፕትርክናው በሚገኝባት በወደብ ከተማዋ የእስክንድርያ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በራፍ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ዘልቆ ለመግባት ከሞከረ አጥፍቶ ጠፊ መታጠቂያ (suicide vest) የነጎደው ቦምብ፣ ቢያንስ 18 ሰዎችን መግደሉንና ከ40 ያላነሱትን ማቁሰሉ ተጠቅሷል፤ ከተገደሉት ሦስቱ፣ አጥፍቶ ጠፊው ወደ ካቴድራሉ ዘልቆ እንዳይገባ ያስቆሙት ወንድና ሴት ፖሊሶች መኾናቸው ታውቋል።


ጥቃቱ የተፈጸመው፣ በካቴድራሉ ጸሎተ ቅዳሴውንና የበዓለ ሆሣዕናውን ሥነ ሥርዓት የመሩት የኮፕቱ ፖፕና የእስክንድርያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ፣ በካቴድራሉ ውስጥ እያሉ እንደነበር ተገልጿል። “እንዲኽ ያሉ እኵይ ድርጊቶች፣ የግብጽን ሕዝብ አንድነትና ስምምነት አያዳክመውም፤” ብለዋል ቅዱስነታቸው፣ ለሀገሪቱ ቴሌቭዥን ሲናገሩ።


ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን፣ በከፍተኛ ቁጥርና በጅምላ ለመፍጀት የታቀደበትን ይህንኑ ጥቃት፣ ያቀናበርኹት እኔው ነኝ፤ ሲል፣ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን በድረ ገጹ አስታውቋል።


25 ምእመናን ከተገደሉበትና 49 ከቆሰሉበት ካለፈው ታኅሣሥ ጥቃት ወዲኽ፣ በአምስት ወራት ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ የተፈጸመው የዛሬው ፍጅት፣ ከጠቅላላው ሕዝብ 10 በመቶ የሚኾኑት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች፣ በቀላሉ ተጋላጭ የአሸባሪዎች ዒላማ (the softest targets) እየኾኑ እንዳሉ አረጋግጧል። ከሆሣዕና ክብረ በዓል ጋራ በተያያዘ፣ የጸጥታ ጥበቃው በተጠናከረበት ይዞታ ውስጥ መፈጸሙ ደግሞ፣ የክርስቲያኖችን መፃኢ ሕይወት ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፤ ተብሏል።


ከእሁዱ የታንታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍንዳታ ቀደም ብሎ፣ በዚያው ከተማ አንድ መስጊድ ውስጥ የተጠመደ ቦምብ፣ በጸጥታ ኃይሎች እንዲከሽፍ መደረጉና እስላማዊ ቡድኑም በክርስቲያኖች ላይ አስከፊ ጥቃት እንደሚያደርስ በግልጽ ሲዝት መቆየቱ፣ በቂ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ኾኖ ሳለ፣ የእሁዱ ተከታታይ ፍጅት መፈጸሙ፣ የጸጥታና የደኅንነት አካሉን አስተማማኝነት ጥያቁ ውስጥ እንደሚከተው ተመልክቷል።


በታንታ፣ ጥቃቱ የተፈጸመበት ግዛት የደኅንነት ሓላፊ ከሓላፊነታቸው እንዲገለሉ የተደረገ ሲኾን፣ የጦር ሠራዊቱም፣ ከፖሊስ ኃይሉ ጋራ በመቀናጀት የሀገሪቱን ወሳኝ ተቋማት ጥበቃ እንዲያጠናክር፣ በፕሬዝዳንት አብዱል ፈታሕ አል-ሲሲ ከተመራው የወታደራዊ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ፣ በተላለፈ ትእዛዝ መሠማራቱን አኸራም ኦንላየን ዘግቧል።


ድረ ገጹ ቆይቶ እንዳስታወቀው፣ በጥቃቱ የተገደሉና የተጎዱ ወገኖች የሚታሰቡበት፣ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን፣ በፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት ታውጇል።


የሰላም ምልክት የኾነውን የተባረከ የሆሣዕና ዘንባባ (ፀበርት)፣ እንደመስቀል እየሠራን በየቤታችን፣ በራሳችንና እንደቀለበት በጣታችን ሰቅለንና ሰክተን በምንታይበት ዕለተ ሰንበት፣ በአሸባሪው የአይ ኤስ ቡድን የተፈጸመው አሠቃቂ ጥቃት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተወገዘ ነው።


ሐዘናቸውንና አጋርነታቸውን ለግብጽ ሕዝብና መንግሥት እየገለጹ ካሉት የሀገርና የሃይማኖት መሪዎች መካከል አንዱ የኾኑት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር፥ የሆሣዕና ዘንባባ፣ ትእምርተ ሰላም መኾኑን ማስታወስ እንደሚገባና ጽንፈኞች፥ የሕዝቡን ማኅበራዊ ዕሴትና ትስስር በመበጣጠስ ሊፈጥሩ የሚመኙትን ዕልቂት ለመመከት፣ ተደጋግፎ በጋራ መዋጋት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ሐራ ዘተዋህዶ ዘግቧል።


ለግብፃዊያን ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶቻችን መፅናናትን እንመኛለን። 

ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን፤

የተከሰተ “ፍጥጫ”. . . የለም፣ . . . ተቀራርቦ መወያየትና ሕጋዊ አካሄድ መከተል ግን ያስፈልጋል!

(ከጭነት ትራንስፖርት ብ/ማ/ ዳይሬክቶሬት)

 

መጋቢት 13 እና 20 ቀን 2009 ዓ.ም በወጡት የሰንደቅ ጋዜጦች “ምላሽ የሚሻው ፍጥጫ. . .” “. . . በመሸበር ማደር. . .” የሚሉት ርዕሶች የተሳሳቱ ስለሆነ መታረም አለባቸው። መ/ቤቱ ከማንም ጋር “ፍጥጫ” ውስጥ የገባበት ሁኔታ የሌለና ካደራጃቸው የትራንስፖርት ማህበራትና ድርጅቶች፣ ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ያለውና የሬጉላቶሪ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን በቅድሚያ እንዲታወቅ እናሳስባለን።

 

በጋዜጦቹ ላይ የሠፈሩትን ሐሰቦች ተመልክተናል። በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚከተለው ማብራሪያና ምላሽ በጋዜጣ እንዲወጣ እንጠይቃለን።

 

ዝግጅት ክፍሉ በመጀመሪያው ጋዜጣ ገፅ 4 ላይ ባለስልጣን መ/ቤት አዋጅን በመመሪያ እንደሚጥስ በመግለፅ “በማንአለብኝነት” አካሄድ እንደሚሄድ . . ወዘተ በማለት ተገቢነት የሌላቸውን ቃላቶች በመጠቀም ከኃላፊነት በወጣ ስሜት ጽፏል። ዝግጅት ክፍሉ መ/ቤቱ የሚያከናውናቸውን ትላልቅ ሕዝባዊና አገራዊ ጉዳዮችን ቀረብ ብሎ መጠየቅና መረዳት ባይችል ቢያንስ ያለው ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ ሥርዓት ባሕርይ መ/ቤቱ በማን አለብኝነት እንዲሄድ የማይፈቅድለት መሆኑን እንኳን ማወቅ ይገባው ነበር። ዝግጅት ክፍሉ ትክክለኛና የተሟላ መረጃ ሳይኖረው ወደ አንድ ወገን አድልቶ ዳኝነቱን ለእራሱ አድርጎ ፈርጇል። እንዲህ ዓይነት ሚዛናዊነት አለ ወይ? በቃለ- ምልልሱም ቢሆን ቃላቶችን ከሃሳብ ውስጥ ነጥሎና አጉልቶ በማሳየት አሻሚና የተለየ መልዕክት እንዲያስተላልፉ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል። ይህ የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነምግባር መገለጫ ለመሆኑ ለእኛ ግልጥ አይደለም። የተለየ ተልዕኮ ከሌለ በስተቀር።

 

ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስ መጋቢት 13/2009 በወጣው ጋዜጣ ላይ ከሰፈሩት መካከል አዋጅን በመመሪያ በመሻር ማህበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ፈርሰው እንዲደራጁ እንደተደረገ፣ መመሪያ ቁጥር 1/2006 በማህበራት ሕልውናና ዕድገት ላይ ችግር ማስከተሉ፣ ሞዴል መተዳደሪያ ደንብ.. ማህበራት የራሳቸውን ደንብ እንደ ጥንካሬያቸውና ተጨባጭ ሁኔታ በነፃነት እንዳያወጡ እንዳደረጋቸው. . . ወዘተ የሚሉት ተጠቅሰዋል።

 

በመሰረቱ ከ2006 ዓ.ም በፊት የነበሩት የጭነት ትራንስፖርት ማህበራት አደረጃጀትና ሥራ አፈፃፀም ሲታይ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችንና አገልግሎት የጨረሱ ኤንትሬዎችን በአንድ ማህበር ያደራጀ፣ አገራችን እያስመዘገበች ካለችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ዕድገትና የአገልግሎት ጥራት የሌለው፣ በዘመናዊ አሰራርና በጠንካራ ውድድር ላይ የተመሰረተ አሰራር የማይከተልና ኢንቨስትመንት ሳቢ ያልነበረ፣ በዋጋም ቢሆን ውድ እንደነበረ. . ከዋና ዋና ገጽታዎቹ ጥቂቶቹ እንደሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይህንን ኋላ ቀር አደረጃጀትና አሰራር የኢኮኖሚ ዕድገቱ ከሚጠይቀው ፍላጎት ጋር ማጣጣም የግድ ስለነበረ በጭነት ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ውስጥ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት የተወዳዳሪነት አቅሙን በአደረጃጀትና በአሠራር በማሳደግ የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ማምጣት አስፈላጊ ነው።

 

በመሆኑም መ/ቤቱ በአዋጅ 468/97 በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት በንግድ የመንገድ ማመላለስ ሥራ ላይ የተሰማሩ ማህበራትን የመመዝገብ፣ ስለ አሰራራቸው መመሪያ የማውጣትና የመከታተል በተሰጠው ስልጣን መሰረት መመሪያ ቁጥር 1/2006 አውጥቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአዲሱ አደረጃጀት በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥና በሥራው ላይ በተሰማሩ ባለንብረቶች ዘንድ ውጤቶች ተገኝተዋል። ማህበራት አደረጃጀታቸውና አሰራራቸው በመሻሻሉ በገበያ ውስጥ ተወዳድረው የመርከቦችን ጭነት በጨረታ በመውሰድ መሥራት መቻላቸው፣ አዲሱ አደረጃጀት ከበፊቱ የተሻለ የውድድር አሰራር በመፍጠሩ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ የጭነት ተሸከርካሪዎች ወደ ዘርፉ መቀላቀላቸው፣ አምና ተከስቶ ከነበረው የዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ የተገዛው ከፍተኛ መጠንያለው ስንዴና የአፈር ማዳበሪያ እንዲጓጓዝ በማህበራትና ድርጅቶች የተደረገው ሀገራዊ ርብርብና የተመዘገበው ውጤትና ለዚህ የተሰጠው ዕውቅና . .  ወዘተ ብቻ እንደ አብነት ማንሳት ይበቃል። በመሆኑም በመመሪያው ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለይቶ በጥናት ላይ በመመስረት ወቅታዊ እንዲሆንና እንዲሻሻል ሃሳብ ማቅረብ አግባብ ሆኖ እያለ ወደ ድሮ እንመለስ. . መመሪያው ለማህበራት ያመጣው ጠቀሜታ ስለሌለ መፍትሔው “የማህበራት ህብረት” መመስረት ነው የሚለው መንደርደሪያ የሚያስኬድ አይደለም።

 

ሌላው መመሪያው እያንዳንዱ የጭነት ተሸከርካሪ ባለንብረት የማህበር አባል የመሆን ግዴታ እንደሚጥልበት የተገለፀው ሃሳብ የተሳሳተ ነው። መመሪያው በአዋጅ የተፈቀደውን በግል፣ በማህበርና በኩባንያ ተደራጅቶ መሥራትን አይከለክልም። አሁንም በርካታ በግላቸው የሚሰሩ ትራንስፖርተሮች አሉና።

 

ሌላው ሞዴል መተዳደሪያ ደንብን አስመልክቶ የቀረበው የተሳሳተ ሃሳብ ነው። ሞዴል መተዳደሪያ ደንቡ ስለማህበራት ዓላማ፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ ስለ አባልነት፣ መብትና ግዴታ፣ ስለማህበራት ድርጅታዊ አወቃቀር፣ ስልጣንና ተግባር፣ ስለ ማህበራት ሥራ አመራር ቦርድ እና ኦዲትና ኢንስፔክሽን አመራረጥ፣ ስለ ፋይናንስ አስተዳደር. . . ወዘተ አካቶ የያዘ፣ ማህበራት ተመሳሳይ ዓላማ፣ አደረጃጀትና አሰራር  እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሰነድ ነው። ይህንን ደንብ እንደመነሻ በመውሰድ ማህበራት የራሳቸውን ደንብ አዘጋጅተው በጠቅላላ ጉባዔ ያፀድቃሉ። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ ሞዴሉ የማህበራትን ነፃነት የሚጋፋ ነው ማለት አግባብ አይደለም።

 

መ/ቤቱ/ዳይሬክቶሬቱ ከመልካም አስተዳደር አንጻር የሚታዩ ችግሮችን በስፋት ለይቶ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚፈቱትን በዕቅድ በማካተት ከሕዝብ ክንፍ ጋር በቋሚ መድረክ በየጊዜው እየገመገመ በርካታ ችግሮች ፈቷል። እየፈታም ይገኛል። ይህ በቅርቡ የሕዝብ ክንፍ ኮሚቴ ለትራንስፖርት አመራሮች ባቀረበው ሪፖርት ተቀባይነት ያገኘ እውነታ ነው። በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች በተለያዩ የጋራ መድረኮች በየጊዜው የሚገመገሙበት ሁኔታ እያለና ሃሳብን መግለፅ እየተቻለ ሌላ አካሄድ መጠቀም ለምን እንዳስፈለገ ለእኛ ግልጽ አይደለም። በተለይም ከድለላ ሥራ ጋር በተያያዘ የሚታዩትን ችግሮች በወሳኝነት መልኩ ለመቅረፍ የተጀመረውን የተቀናጀ አሰራር ማጠናከር እንደተጠበቀ ሆኖ የአንድ ወገን ጥረት ብቻ በቂ ስለማይሆን እኔም ከችግሩም ከመፍትሔውም የራሴ ድርሻ አለኝ ብሎ (. . . የተቀሩት ጣቶች ወደ ባለቤቱ ያመልክታሉና. . እንደሚባለው) የተጀመረውን የለውጥ ትግል መቀላቀል እንጂ ዳር ቆሞ ተጠያቂነትን ወደ አንድ ወገን ለማላከክ መሞከር በመካሄድ ላይ ላለው ለውጥ የሚያግዝ አይደለም።

 

መጋቢት 20/2009  በታተመው ጋዜጣ ላይ “በወቅቱ አልነበርኩም” ማለት ለቀረበው ጥያቄ ማህበራት በአዲስ መልክ ማደራጀት ሲጀመር አልነበርኩም ነው እንጂ ተጠያቂነትን ወደ ሌላ አካል ለማስተላለፍ እንደመፈለግ ተደርጎ የተተረጎመው ትክክል ያልሆነና ቅንነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው። መታወቅ ያለበት ዳይሬክቶሬቱ መ/ቤቱ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት ብቻ ሳይሆን መመሪያው እምርታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በትክክል የሚያምን መሆኑን ነው።

 

በአጠቃላይ የተነሱት “የማህበራት ሕብረት ባለድርሻ አካላት” ሀሳቦች አዲስ አይደሉም። አዲስ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ቢኖር በቅርቡ ትራንስፖርተሮች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ህጋዊ ባልሆኑ ተግባራት ላይ እንዳይሳተፉ የሚያሳስቡ ደብዳቤዎች ለማህበራት ወጪ መደረጋቸውን ተከትሎ መምጣቱ ነው። የ“ማህበራት ህብረት”ን ለመመስረት አስፈላጊነቱንና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ሳይንሳዊ በሆነ ሁኔታ ከሌሎች ካደጉ አገሮች ልምዶች ጋር ተተንትኖ በመሠረቱ ሃሳቡ ላይ ተቀራርቦ መወያየት፣ መተማመን ላይ መድረስና ሕጋዊ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ እራሱን ችሎ ሊሄድ የሚችል ሃሳብ ነው። ይህንን አካሄድ በፍጥጫ መልክ መተርጎም በትራንስፖርት አገልግሎት መለወጥና መሻሻል ያለባቸው ሥራዎች ቢኖሩም የተደረጉ ጥረቶችንና የተመዘገቡ ስኬቶችን ማሳነስና ጥላሸት መቀባት ወደ “ማህበራት ህብረት” ምስረታ ማማ የሚወስድ መንገድ መሆን የለበትም። በአገራችን እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማህበራት ወደ አክሲዮን ማህበረት እንዲሸጋገሩ ግፊት የሚያደርግ እንጂ ሌላ አደረጃጀት የሚጠይቅ አይመስለንም።   

ለፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን፤

አንበሳውን እያሳዩዋችሁ ፋናውን ካላየሁ አላምንም

ለምን ትላላችሁ?

ከሙሉዓለም ፍቃዱ (ከአዲስ አበባ)

ረቡዕ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓም በተሰራጨው ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ምላሽ የሚሻውየትራንስፖርት ማሕበራት ሕብረትና የባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት ፍጥጫ በሚል ርዕስ የተሰናዳውንና ከመ/ቤቱ ባለሥልጣን ጋር የተደረገውን ቃለ-ምልልስ  አነበብኩ። ነገረ-ሀሳቡን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወጃጆቼም ጋር ተወያየሁበት።

የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት በአንድ አገር፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሥነ-ልቦናዊ ዕድገት ዙሪያ ያለው ጠቃሚነት ከሥነ-ተፈጥሯችን የተቀናጀ የአሰራር ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። መንገድ በሁለንተናችን እንደተዋቀረ የደም ሥር ሲሆን ተሽከርካሪዎች ደግሞ በውስጡ የተለያዩ ጠቃሚ ንጥረ-ነገሮችን ይዞ እንደሚያመላልሰው ደም ይመሰላሉ። የሁለቱ ተፈጥሯዊ መንትያ አሰራር ለሰውና ለአገር ሕልውና አይተኬ ሚና የሚጫወቱ አውታራት የመሆናቸው ነገር ተመሳሳይና አንድ ነው። ልዩነታቸው ከፈጣሪ የሆነው፣ የሕይወታችን መንገድና ትራንስፖርት በረቂቅ ጥበብና ፍጽምና የሚመራ ሲሆን፣ ሰው ሰራሹ መስመርና የማጓጓዣው አገልግሎት ግን፤ ከአህያ፣ ፈረስና ጋሪ ጀምሮ እስካለንበት የዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ድረስ የሰውን ፍላጎት ሳያረካ ዛሬም ድረስ መሻሻልን እንደጠየቀ ያለ አምሣላዊ ክንዋኔ ነው። በመቀጠልም ከማሰላሰሌ በኋላ በውስጤ የተመላለሰውን ሀሳብና ትዝብታዊ ዕይታዬን ጉዳዩን በእውነትና በግልጽ ላስተናገደው ሰንደቅ ጋዜጣ ለመጻፍ ወሰንኩ።

 

የመደራጀት መብትና የውይይቱ ፋይዳ

ወደ ርዕሰ ነገሬ ከመግባቴ በፊት፣ በኛ በኢትዮጵያውያን  ዘንድ በግልም ሆነ በጋራ በሚያጋጥሙን ችግሮችና ከዚያም ጋር ተያይዞ በሚሰማን ቅሬታ ዙሪያ፣ የማናምንበትንና ያልፈቀድነውን ነገር እምቢ/አይደለም! ብሎ ፊት ለፊት በተቃውሞ ከመጋፈጥ ይልቅ በየደረጃው ወደተቀመጡ ባለሥልጣናት ስንቀርብ፤ በደሌን ይረዱልኛል፣ ችግሬን ያስወግዱልኛል የሚል ተላላ ዕምነት በልባችን በማሳደር፣ ዕንቁ መብታችንን በኩርፊያ፣ በፍርሃትና በዝምታ ከፈን ገንዘን ተዐምራዊ ውጤት የመጠበቃችን፣ ራስን አታላይ የጋራ ባህሪያችንን ሁላችንም በያለንበት መስክ በልባች የምናምነው ሀቅ ነው። ባይፈርድልን እንኳን፣ ዛሬ ባይሆን ነገ ይፈጸምልኛል በሚል ተስፈኝነት ተሸብበን፣ በአፍ አምነንና በልብ መንነን፣ የምንመለስና ዘወትር ያደባባዩን በሹክሹክታ ማውራት የሚመቸን፣ ለመብትና ጥቅማችን ባይተዋር የሆንን፣ ፀፀትና ቁጭት በደባልነት የተቆራኙን ማኅበረሰብ ነን።

 ባለሥልጣኖቻችንም ከሁሉም ተርታ ዜጋ ይበልጥ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ጭምር ለሕዝብ አገልግሎት ያቀረቡና ግዴታም ያለባቸው፣ ስለተቀበሉት አደራና ኃላፊነትም ሊደክሙ የተገባ መሆኑ ይዘነጋል። ሕዝብን ዝቅ ብሎ በእውነት፣ ታዛዥነትና በትህትና ማገልገል ግዴታቸው መሆኑ ይረሳና፤  የግብርና ታክስ ግዴታዎቻቸውን እየተወጡ፣ ደሞዝ በሚከፍሏቸው የእንጀራቸው ጌቶች ላይ (በሕዝብ)፣ እንዳሻቸው የመናገር፣ የማድረግና የማስደረግም መብት ያላቸው ተደርጎ የመወሰዱና የመታመኑ ጉዳይ የብዙ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና መዋቅራዊ ችግሮቻችን ጠባሳ ሆኖ እንዳለ በታሪክም የተመዘገበና ዛሬም በተግባር ከነአንገፍጋፊ ምሬቱ የምንጋተው ፍቺ ያጣንለት እንቆቅልሻችን ነው። ይህ በቢሮክራሲው አካባቢ ያለ የተለመደ ገዢ ባህሪ፣ ሰብዓዊም ሆነ ቁሣዊ ልማትን ከማነጽ ይልቅ፣ የመናድ ጸባይ ስላለው ሳንፈራና ሳንታክት በየአጋጣሚውና በየመድረኩ ልንዋጋው፣ ልናርመውና ልንገስጸው ይገባል።

በመቀጠልም የዜጎችን በተለያየ የሙያ፣ የዕምነትና የአመለካከት ዘርፎች በነፃነት የመደራጀት መብትን አስመልክቶ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት በግልጽ የተቀመጠውን የዜጎች ሁሉ የማይገሰስ የጋራ መብትን መነሻ አድርገን እንጂ ዝም ብለን በቀቢጸ ተስፋ የተነሳሳን አለመሆኑ ሊታወቅልን ይገባል። የሕጎች ሁሉ የበላይ ሆኖ፣ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠው መሠረታዊ መብት ደግሞ፣ ወደ መሬት ወርዶ የሰብዓዊና የዜግነት መብቶቻችንና ጥቅሞቻችን እስትንፋስ እንዲሆን፣ በየጊዜውና በየደረጃው የመተርጎሚያ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ድንጋጌዎች ከማዕቀፉ ክበብ ይወጡለታል። ይህንንም ስል ጊዜና ሁኔታዎች በተለዋወጡ ቁጥር፣ በነበረበት የሚፀና ምንም ነገር የለምና የሚወጡ ልዩ ልዩ መመሪያዎችም ቢሆኑ እንደሚከለሱና እንደሚታደሱ የሚታወቅ ነው። ከዚህ በመለስ ግን ብዙ ዜጎቻችን፣ ዋጋ የከፈሉበትንና መንግሥትም በጽናት ሲለፋበትና ሲደክምበት የኖረውን፣ እንደ ተራራ ከፍ ብሎ የሚታየውን የዜጎችን ሁሉ ሕገ-መንግሥታዊ መብት፣ መመሪያ እያጣቀሱ መሸራረፍና መፃረር ወንጀልና ኢ-ሕገ-መንግሥታዊነት ነው። ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በዐዋጅ የተሰጠን ደንብ የማውጣት ሥልጣን በአቋራጭ/በሾኬ ጠልፎና ሽሮ ደርሶ መመሪያ አውጪ የሆኑት የባለሥልጣኑ መ/ቤት ሹማምንት፤ እንዴት? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹… ማደራጀት በአዋጅ የተሰጠን ሥልጣን ነው..›› የሚል ዐይነ-ደረቅ ምላሽ በመስጠት የጋዜጠኛውንም የኛንም ልብ የሚያደርቁት የዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ወልዴ ምላሽ ሁኔታ፤ አንበሣውን እያሳዩት ፋናውን ካላየሁ አላምንም ብሎ ችክ እንዳለው አውቆ የተኛ ተሟጋች ከመሆን አይዘልምና፤ አደብ ገዝተው እርምት ቢያደርጉ ለክብራቸውም፣ ለሥራችንም እንደሚበጅ ሊመከሩ የሚገባ አይመስለኝም። ጨው ለራሱ ሲል መጣፈጥ አለበትና።

በእኔ በኩል ግን ሕገ-መንግሥታዊ መብትን መሠረት በማድረግ ‹‹ብሔራዊ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት ሕብረት› በወርሃ ታህሣሥ 2008 ዓም በጠቅላላ ጉባዔ ሙሉ ፈቃድና ተሳትፎ ሲመሰረት የባለሥልጣኑ መ/ቤት እንዲገኝ መጋበዙ ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ትራንስፖርተሩ ሲደራጅ የዳር ተመልካች ሳይሆን ባለቤትም ነው ከሚል እሳቤና ዕምነት በመነጨ ነበር። ሆኖም ግን ባይገኙም ጠ/ጉባዔው 11 የዳሬክተሮች ቦርድና 3 የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላትን መርጦ ምሥረታውን ዕውን በማድረግ ለሚመለከተው የመንግሥት አካልም በጊዜውና በአግባቡ አሳውቋል።

ይህ ሲሆን፣ በምሥረታው አስፈላጊነትና፣ በክልከላው መካከል ያለው ግራ-ገብ ዕውነታ፣ እንዳለ ሆኖ፤ የማኅበራቱ ሕብረት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን የማይተካ፣ መሪ የመንግሥትነት መዋቅራዊ ሚና፣ እንደሌለ በመቁጠር ሳይሆን፣ ሁለቱም አካላት በየራሳቸው መደላድልና ማዕቀፍ ውስጥ፣ ወንበር-ገፍ ባልሆነ ጥምረት፣ አብረው ለተመሠረቱበት ዓላማ የመሥራታቸውን አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ከልብ በሚያምን የተረጋገጠ የግንዛቤ መሠረት ላይ በመቆም ነው። ይህም ከማንአለብኛዊ ግላዊ፣ ቡድናዊውና ስሜታዊ ጥቅም አንጻር ሳይሆን፤ ከአገራዊ አስፈላጊነቱና ጠቀሜታው አንጻር በማመዛዘን ጭምር እንደሆነ የባለሥልጣን መ/ቤቱ ሊያውቅ ይገባል። ከሁሉም በላይና በተለይም ደግሞ ግለሰቡ ስሜታዊና ምክንያታዊ ያልሆነ፣ በተቃርኖ የተሞላ ተራ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱን ባይደፍሩት ይበጃቸው ነበር ይሰማኛል።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እመራዋለሁ የሚለውን የዘርፍ ችግር፣ በጊዜው ማወቅና ለመፍትሄውም በቅድሚያ መትጋት ያንንም ሚዛናዊ፣ ግልጽና ከሸፍጥ በፀዳ አግባብ መሳየትና ማረጋገጥ፣ የባለድርሻ የኃላፊነት ወጉና ግዴታውም መሆኑ የሚታመንና የሚገባም ነው ብዬ  አምናለሁ። የየመዋቅሩ ኃላፊዎች ሕገ-መንግሥታዊ መሠረትነት ያለውን፣ በሕብረት የመደራጀት ሰብዓዊ ፍላጎትን፣ በቅንነትና በጥልቀት የመረዳት፣ በስኬታማነቱ ዙሪያም የሚፈጠሩ ተያያዥ ችግሮችን፣ በግልጽና በጋራ መድረክ በመምከር፣ የሚና ወሰኖችን በመለየት፣ ከአደረጃጀቱ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩና የሚፈጠሩ አላስፈላጊ የሀብትና ንብረት ብክነትን በሚያስወግድ ብልሃት፣ ማገዝና መሥራት፣ ለሁሉም ወገን ዘላቂ ጥቅም እንደሚያረጋግጥ የሚታመን ይመስለኛል። መንግሥትም ይሄንን ጉዳይ በአትኩሮት እንደሚከታተለው አልጠራጠርም። ምክንያቱም መንግሥታችን በጥልቅ ተሃድሶው ማግስት “ያልዘራሁት በቀለብኝ፤ ዱባ ያልኩት ቅል ሆነብኝ” ከሚል ያረፈደ ጸጸት እዋላጅ ፍጻሜ በኋላ፤ ይሄ ሁሉ ጉድ በኔ መዋቅር ውስጥ አለ እንዴ? ማለት አይፈልግምና።

አስገራሚው የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት በዐዋጅ የተቋቋሙ 80 ማኅበራትን ያለ ጥናት በትኖ መዋቅራዊ የአሰራር ስህተት እንዳልፈጠረ ሁሉ ዛሬ መዘዙ ተጠያቂነት ሲያስከትል፣ አቶ አለማየሁ ቀደም ሲል በነበሩበት የሥልጣን እርከን ዘርፉን ሲያተረማምሱ አንደነበር፣ እንደማናውቅና መረጃም እንደሌለ በመቁጠር፣ ወደ ግላዊ ሚና አውርደው፣ የኃላፊ በሳል ምናባዊ ባህሪን በማያንጸባርቅ ቃል “ … በጊዜው እኔ አልነበርኩም … የተከፋፈሉት ማኅበራት እንጂ፣ ግለሰቦች አይደሉም…. ተጠያቂዎች የቦርድ አባላትና ሥራ አስኪያጆች ናቸው። …. እኛ ማኅበራትን እንጂ ንብረታቸውን አናስተዳድርም።በማለት ገመናቸውን በማይሸፍን የሰበብ ጢሻ ስር ሲወሸቁ በግርምት ታዝቤያቸዋለሁ። እኚህ ግለሰብ ባለሥልጣን በማናለብኝነት በንብረታችንና በብዙ ሺህ ቤተሰቦቻችን ሕይወት፣ አሰቃቂ ፍርድ ከመስጠታቸው በላይ፣ አገርንም በሚጎዳ አቅጣጫ እንደተንቀሳቀሱ ሊታመንና ሊገቱ ይገባል። ለመሆኑ በዚህ የሥልጣን ዕርከን የተቀመጠ ጎምቱ ኃላፊ፣ ንብረታቸውንና ባለቤቶቹን ከማኅበሩ ነጥሎ፣ በከፊል እንደሚያገባውና በከፊል ደግሞ እንደማያገባው፣ በግዴለሽነት ሲናገር መስማት ታዛቢን አያደናግርም? ለመሆኑ ንብረቱ ከሌለ ማኅበሩስ እንዲኖር ይጠበቃል? መለስ ይሉና ደግሞ ‹‹ …እስከማውቀው ክፍተቶች ነበሩ።… ጥርት ባለ ሁኔታ አልተገባበትም።›› ይሉናል።

ከአዲሱ የማኅበራት አደረጃጀት ጋር በተያያዘ፣ አዋጁ አንድ ሰው ከአንድ ማኅበር ሥምሪት በላይ ሊንቀሳቀስ አይችልም በሎ ክልከላ ቢያደርግም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግን አዋጁን ጥሶ አንድን ሰው በንብረቱ የደረጃዎች መለያየት ምክንያት ከአንድ ማኅበር በላይ በሁለትና በሦስት ቦታ እንዲከፋፈል አስገድዶታል። መስፈርቱ በመኪኖች የአገልግሎት ዕድሜ ማለትም ከ1-10 ዓመት 1ኛ ደረጃ፤ ከ10-20 ዓመት 2ኛ ደረጃ፤ ከ20 ዓመት በላይ ደግሞ 3ኛ ደረጃ በማለት መደልደሉ፣ አንድን ባለንብረት በተለያዩ ማኅበራት እንዲደራጅ ማስገደዱ፣ ንብረቱን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር አመቺ ካለመሆኑም በላይ፣ የገዛ ንብረቱን የማስተዳደር መብትና ጥቅሙን እንደሚያሳጣው ሲገለጽላቸው ደግሞ ከሦስት ዓመታት በኋላ ‹‹… የመመሪያውን አስቸጋሪነት በመመልከት፣ ድጋሚ ለመከለስ እየሰራን ነው።›› ይላሉ። ስለመደራጀታችን ካላቸው፣ ግልጽ የወጣ ጥላቻና፣ ከተጋቡት የእልህ መንፈስ አንጻር ከዚህም በላይ የእንግልትና የእንክርት ጊዜ እንደሚያመቻቹልን ለመገመት የነበረውንና አሁንም አብሮን ያለውን ችግር ማየት ብቻ በቂ መስለኛል። በመንግሥታችንም በኩል በመዋቅሩ ተሸጉጠው ጥቅመኛ የግል ሥራቸውን የሚሰሩ ችግር አባባሽ አረሞችን ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ከምርታማ የሥራ አካባቢው በግምገማ በመለየት መንቀል ይገባዋል የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ።

አንድ የአገሪቱ ወሳኝ የልማትና ዕድገት አውታር ዘርፍስ፣ የገጠመው የተዝረከረከ ችግር ይህን ያህል ጊዜ መቆየት ይገባው ነበር? አንድስ ባለሥልጣን እንዲህ በጣም ወሳኝ በሆነ ዘርፍ ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ የበላዩቹን የመጠምዘዝ ጉልበት እስኪኖረው መቆየቱ ሊመረመር አይገባምን? የባለንብረቶች ማኅበራት ግላዊ፣ ቡድናዊና አገራዊ ጥቅማቸውን አርቀው በማሰብ፣ በሰለጠነ አግባብ ተደራጅተው ሲገኙ፣ ባጎደሉት ሞልቶ ከማገዝና ከማበረታታት ውጪ እንደ ባላንጣ በተቃርኖ ቆሞ ‹‹… ገና ጉዳቱና ጥቅሙ መጠናት አለበት።››፤ ‹‹.. እነሱ ማኅበራቱን እኛ እንምራ ነው የሚሉት …›› በሚል ገበርና ፈርሱ ባልለየ ድንፋታና ዘለፋ፣ በግልጽ ሀሳብ ላይ ውስብስብ ስሜት የሚፈጥር መደዴ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነውን? ለመሆኑ ጥያቄው በተቋም ደረጃ የማኅበራት ህብረት እንዳልሆነ ሁሉ ‹‹ሰዎቹ›› እያሉ ያብጠለጠሏቸው የሕብረቱ ቦርድ አመራሮች በአዋጅ የተሰጣቸውን መንግሥታዊ ሥልጣን ቀምተው እኛ እንምራ አሉ እንዴ? ጥያቄው ተደራጅቶ በህብረት የመስራት እንጂ የሥልጣን ጥያቄ ነበር? ማንም እውነቱ ቸል ሲባል፣ በደንታ ቢስ ንግግር ሲጎነተልና በሚጎዳ ዝምታ ሲገፋ አይወድም። እውነት የማኅበራት ሕብረት ምሥረታ መንገድና መድረሻ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ዕይታና መረዳት የተሰወረ ሆኖ ነውን? ወይንስ የግሎባላይዜሽን ዘመንን ባልዋጀ ኋላ ቀር፣ አምባገነናዊና ሰወርዋራ አካሄድ፣ አገራዊና ክልላዊ ተወዳዳሪነታችንን ለማቀጨጭ ነው? እንደ እኔ ግን የግለሰቡ ዓላማ የራሱንና የጥቂቶችን ጥቅም የሚያስጠብቅ አሰራርን ማዕከል ያደረገ ግፈኛና አድሏዊ አሰራሩን ለመቀጠል ግትር መሆኑ፤ በሕብረት ተደራጅቶ በበለጠ ጥንካሬ በመሥራት ላይ ያለንን የጋለ ስሜት ለመበረዝ ካለው ጭካኔ በላይ ሊጤን፣ ሊመረመርና ሊጋለጥ የሚገባው ነቀርሳ አከል ችግር እንዳለ የሚመለከተው አካል ሁሉ አኳኋናቸውን ልብ እንዲለው ላሳስብ እወዳለሁ።

ማኅበራት በህብረት መደራጀታችንን እንደ ነውር ቆጥረው ‹‹ሕገ-ወጦች›በማለት የዘለፉንና ያብጠለጠሉን እኚህ ባለሥልጣን፤ ጋዜጠኛው ‹‹… ደንብ የማውጣት ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠ ሆኖ ሳለ፣ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ከምን መነሻ ተንደርድሮ መመሪያ ሊያወጣ ቻለ?›› ሲል ላነሳላቸው የህግ ጥሰት ጥያቄ ከህግ ክፍላቸው መልስ ቢሰጥ እንደሚሻል ተናግረው በ‹‹አይመስለኝም›› ዘለውታል። ለምን? እውነት ምላሹ የህግ ሊቀ-ጠበብትነትን የሚጠይቅ፣ ለትርጉም የሚያሻማ ይዘት ኖሮት ነው? ሞዴል መተዳደሪያ ደንብን በተመለከተም  ‹‹…ማኅበራት ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚያስችላቸውን መተዳደሪያ ደንብ ማውጣት ይችላሉ። እኛ የምናቀርብላቸው ሞዴል በዝቅተኛ ደረጃ ማሟላት ያለባቸውን ነው።›› ሲሉ መልሰዋል፣ እውነት አለመሆኑን ግን ማኅበራት እናረጋግጣለን። እኛ በምናፈሳችሁ ብቻ ተንቆርቆሩ ዓይነት አባዜ እንዳለባቸው የታወቀ የአደባባይ ምሥጢር ነው።

ሌላው አሳዛኝም ኃላፊነት የጐደለው ተግባር እንደሆነ የተሰማኝ፣ በመ/ቤቱ የተመዘገቡ ማኅበራት በዐዋጅ 468/1997 በተደነገገው መሠረት የተደራጁ ናቸው? ሳያሟሉ የተመዘገቡ የሉም? አደረጃጀቱ ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ ነው? ተብሎ ሲጠየቁ ፈቃድ አውጥተው ሲሰሩ የነበሩ ከ300-500 የሚደርሱ ማኅበራት እንደነበሩና ነገር ግን ፈቃዳቸውን መልሰው መክሰም ሲገባቸው፣ ቀድሞ በተሰጣቸው የተሻረ ፈቃድ እየተጠቀሙ፣ የሥምሪት መውጫ ደረሰኝ እየቆረጡ የሚሰሩ እንዳሉ አምነዋል። ማመናቸው ጥሩ ነው። ግን ደፈር ብለው የጭነት መኪኖች ሳይኖራቸው በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተመዝግበው፣ ፈቃድ ተሰጥቷቸው አየር ባየር የሚሰሩ አጉራሽ ደላሎች እንዳሉም ቢያምኑ አደንቃቸው ነበር። የመረጥነውና ያከበርነው መንግሥትም በግለሰቦች የተቀማውን ሕዝብ አገልጋይ መዋቅሩን ማስመለስ እንዳለበት በአጽንዖት ላሳስብ እወዳለሁ። ምክንያቱም የባለሥልጣን መ/ቤቱ ኃላፊዎች ወደ ቀውስ የሚመራ አሰራርን በሚያመክን መርህ በሚጓዝ መንግሥት ስር ያሉ አይመስሉምና። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተቆጪ፣ ገሳጭ፣ ተቆጣጣሪ፣ ተው እረፍ፣ የሚለው አካል ያለ አይመስለውም። በተለያየ ጊዜ ከባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ሰምቶና አጣርቶ መልስ የሚሰጥ የበላይ አካል እንደሌለ ነው የሚገባን። ለመሆኑ በመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መድረክ መ/ቤቱ ችግር እንዳለበት የጥናቱ ሠነድ አሳይቷል። ሆኖም ግን ለውጥ ሲጠበቅ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ሆነና ይሄው እንዳለን አለን። በሪፖርት ብቻ የተገኘ መሻሻል እንዳለ በማስቀመጥ የምናውቀውንና በደባልነት አብሮን ያለውን ችግር እንደተቀረፈ በማስመሰል ሊያልፉት ሞክራሉ። ወደታችም ተወርዶ ተገልጋዩ የሚያነሳውንና የሚያውቀውን ከመስማት እንደማስተንፈሻ ከመስማት በዘለለ የችግሩን ሥር በገደምዳሜ ማለፍ እንጁ በእውነት የመዳሰሱ ጉዳይ የህልም እንጀራ ሆኖብናል።

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በጉያው ብዙ ኪራይ ሰብሳቢ ሙሰኞች፣ አሉባልተኞችና ከሕዝብ የሚያለያዩት አታላዮች እንዳሉ በተካሄዱ ግምገማዎች ጠንቅቆ ያውቅ ይመስለኛል። ወይንስ የዕርምት እርምጃ ለመውሰድ በማያስችል ደረጃ ይሆን ይሄንን መጠነ ሰፊ ችግር የተመለከተው? እነዚህ በወገናዊነትና በጥቅማጥቅም የተገነባ ህብረት የመሠረቱ ‹‹የልማት ተቆርቋሪዎች››ን ጠራርጎ የትራንስፖርቱን ዘርፍ ለመታደግ ጊዜ የማይሰጠው አደጋ ከፊቱ እንደተደቀነ ቢያውቅም ላሳስብ እወዳለሁ። የዕርምት ውጤቱንም ለማየት እጓጓለሁ። ባለሥልጣኑ፣ ጋዜጠኛው ስለ ሕገ-ወጥ ማኅበራት ሲጠይቃቸው፤ መውጫ ሲቆርጥ ስለተገኘ አንድ ሰው ያወራሉ። ያ ግለሰብ ተቋማዊ ውክልና እንዳለው ተስቷቸው  ይሆን? ይህ ምላሽ ጥያቄውን ካለመረዳት ሳይሆን፣ ሆነ ተብሎ የተዛባ ግንዛቤ ለመፍጠር በግዴለሽነት የተነገረ እንደሆነ ግልጽ ነው። አንባብያን፤ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በፈረሰ ማኅበር ስም፣ መውጫ እየቆረጡ የሚሰሩ ሕጋዊ ያልሆኑ ማኅበራት የሚፈጥሩትን ችግር፣ ለዓመታት ማስወገድ ያልቻለው፣ በምን አይበገሬ የጀርባ ምክንያት ይሆን? በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ውስጥ በዜጎች መካከል አድሏዊ አሰራር የሚያራምድ አካል እንዳለስ ይህ ማረጋገጫ አይሆንም? ጥቂቶችን ለመጥቀም ተብሎ ብዙሃንን የሚበድል የዝርፊያ ትስስር በቁጥጥር ሥርዓት የሚይዘውስ መቼ ይሆን?

የማኅበራቱ ሕብረት፣ የአገራችን ሕገ-መንግሥትና ልማታዊ መንግሥታችን፣ ባመቻቹት ዕድል ተጠቅመው፣ በተባበረ ኃይል በጋራ እንስራ፣ ብለው መደራጀታቸው ይሄን ያህል ውዝግብ ሊያስነሳ የሚገባ ነበር? በሕገ-ወጦች አሰራርና ሙስና-ወለድ መሻረክ፣ እርምጃ ለመውሰድ ይህን ሁሉ ጊዜ የዘገየ ባለሥልጣን፣ ምነው ለመጽደቅ ብቅ ባለች የህብረት አደረጃጀት ቡቃያ ላይ በጭካኔ የመንቀል እርምጃ ለመውሰድ ፈጠነ?

የተቋማዊ ኅልውናቸውን አከርካሪዎች የሆኑትን ትራንስፖርተሮች፣ በማን አለብኝነትና አርቆ ማሰብ በተለየው ጥድፊያ፣ ከሥራችን ከነቀሉና ካጠወለጉ በኋላ፣ ጥረታቸውንና ተስፋቸውን ሁሉ እንደ በጋ ዳመና ከበታተኑ፣ ወደ ኪሳራና ተስፋቢስነት አዘቅትም ከወረወሩን በኋላ፣ ዛሬ የሚነገራቸውን እውነት አንሰማ ብለው፣ ጉልበተኛው ጊዜ ሀሳብና ጥያቄያችን አግባብ መሆኑን ነገ ሲያረጋግጥላቸው ያጠወለጉትንና የነቀሉትን ተቋማዊ ኅልውና ከየት አምጥተው መልሰው ሊተክሉ ይሆን? ግርምትንና ብስጭትን እየፈጠረብን ያለው የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት አይነኬ ባለሥልጣናት እየፈጠሩት ያለው አሳረኛ ትርምስስ መቼ ያበቃ ይሆን?

ለመሆኑ በአገራችን ተመሳሳይ አደረጃጀቶች የሉም?

የሠራተኞች ማኅበራት ህብረት አለ፣የሙያ ማኅበራት ህብረቶች ፌዴሬሽኖችና ኮንፌዴሬሽኖችም አሉ፤ የየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ዓለም አቀፍና አገር-በቀል የልማትና ሰብዓዊ ድርጅቶችም በዓላማቸው ተመሳሳይነት የተነሳ በአንድ የሕብረት ጥላ ሥር ተደራጅተው እንደሚንቀሳቀሱ እናውቃለን። (ሲ.አር.ዲ.ኤ ከ300 የማያንሱ ማኅበራትን ያቀፈ፣ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ትምህርት መረብ ከ30 የማያንሱ የተለያዩ ማኅበራትን በአንድነት ያቆራኘ፣ የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች የጋራ መድረክ ከ50 የማያንሱ ድርጅቶችን ያሰባሰበ … ወዘተ። ተቀናጅተው በአንድነት መሥራታቸው ጥቅም እንጂ ጉዳት አላስከተለም። በመንግሥትም በኩል ይሄንን አደረጃጀት የሚያስተናግድ ማዕቀፍ አሰናድቶ የመንቀሳቀሻ መስኩን አስፍቶላቸዋል። ይህ ለአገራችንና ለወገናችን ሲጠቅም እንጂ ሲጎዳ አልታየም። ታዲያ የኛስ በህብረት መደራጀት ጉዳቱ ምን ላይ ይሆን? ለጋራ ጥቅማችንና ዕድገታችን መልካም ዕድል ፈጥራል ወይስ የሥጋት ምንጭ ነው?

ሌላው ጉዳይ ከወራት በፊት በባለሥልጣን መ/ቤቱ ጠያቂነት ተጠንቶና ተሠንዶ እንዲቀርብ የተደረገው የኬንያ፣ የደቡብ አፍሪካና የናይጄሪያ የአደረጃጀትና አሰራር ተሞክሮዎችን  እንዲያመላክት የቀረበው ሠነድ፣ ከተወሸቀበት ወጥቶ እንዲመረመር፣ የአገራችንም ማኅበራት ህብረት እንደ እህት ማኅበራት፣ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የተሳለጠ ድንበር ተሸጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲችል፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መክሮ፣ ለባለሥልጣን መ/ቤቱ አመራር እንዲሰጥ፣ የተጀመረው አርዓያዊ የመደራጀት መብት፣ ተከብሮና ተጠናክሮ፣ የዜግነት መብትና ግዴታችንን በአግባቡ እንድንጠቀምበት፣ አፋጣኝ እርምጃ ቢወሰድ እኛም፣ መንግሥታችንም፣ አገራችንና መላው ዜጋዋ ሁሉ በጋራ ተጠቃሚ እንደምንሆን በሁላችንም ዘንድ የሚታመን ነው ብዬ አምናለሁ።

 

እንደ ማጠቃለያ

የባለሥልጣን መ/ቤቱ፣ የጭነት ትራንስፖርት ብቃት ማረጋገጫ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር፣ አቶ አለማየሁ ወልዴ፣ መንግሥት ዐዋጅና መመሪያ ባያወጣ እንኳን፣ ይህ ጤናማ በህብረት የመደራጀትን ጉዳይ፣ እሳቸውን በግል ሊያስቆጣና ሊጎዳ የሚችልበት ይፋ የወጣ የአደባባይ ምክንያት ባይኖርም፤ በዚህ መልክ በሚዲያ መገለጣቸው በግል ለእሳቸውና ለሚመሩት መዋቅር የጀርባ ጦስ እንዳለው መጠርጠር ተገቢ ይመስለኛል። በሕብረት የመደራጀትን አስፈላጊነት የመገንዘብ ብቃት አንሷቸው እንዳልሆነም የያዙትን ማዕረግ ካስገኘላቸው  በልምድ ከዳበረ በሳል ዕውቀታቸው አንጻር መጠርጠር ፌዘኛ እንደሚያሰኘኝ ግልጽ ነው። ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን የሚያምኑበትንም ነገር በመልካም ቃልና ሚዛናዊ ምክንያት፣ በወዳጅነት መንፈስ ማስረዳትም ለምን እንዳልሰመረላቸው ሲታሰብ የዋህ ልብን ያጠራጥራል። ባለሥልጣኑ ምንም እንኳን ያለው ዐዋጅ የመደራጀት መብት ፈቅዶ፣ ዝርዝሩን ባያስቀምጥም ክልከላ እንዳላደረገ አጠናቀው እንደሚያውቁ ቢገባንም፤ ‹‹በሕገ-መንግሥት ላይ የተጠቀሰውን የመደራጀት መብት ብቻ እንደ ፍጹም መብት አድርጎ ወደ መደራጀት መብት መሄድ አይደለም፡›› በማለት ይቀጥሉና ምፀት በሚመስል አግቦ ‹‹እኛም ዓላማቸውን ተቀብለን፣መንግሥት እንዲፈቅድ በጋራ ግፊት ማድረግ አለብን። እኛም አጋዥ እንፈልጋለን።›› በማለት ቀኙን እያሳዩ ግራ ያጋቡናል። በሌላም በኩል አንዳንዴ የዕድል ነገር ሆኖ አንዳንድ ሰው በክፉነት ብቻ ሳይሆን አሳሳች ባሳሳታቸው ሰዎች ምክንያት በጥሩነቱም ሊነቀፍ ይችላል። እናም ክቡርነትዎ በዕውቀት ማነስም ሆነ በመረጃ ስህተት መልካም ሰብዕናዎንና የተከበረ ወንበርዎን ያለአግባብ ተጋፍቼም ከሆነ ልታረም ዝግጁ ነኝ። እስኪ የከርሞ ሰው ይበለን።¾

በፍሬው አበበ

ኢህአዴግ በጥልቅ ተሀድሶ ውስጥ ነው። ይህ ተሀድሶ መነሻ ሲደረግ ኢህአዴግ የገጠመው ችግር የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌ በአመራሩ ውስጥ እያደገ መምጣት ነው የሚል በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ የድርጅቱ ዋንኛ ችግር ጠባብነት፣ ትምክህትና ብልሹ አሠራር ሲሆኑ መገለጫውም ሙስና  ነው የሚሉ ወገኖች በሌላ በኩል ታይተዋል። በዚህም ተባለ በዚያ ግን ሁሉም ችግሮች በኢህአዴግ ውስጥ ማቆጥቆጣቸው የሚያስማማ ነው። እነዚህን ችግሮች መነሻ በማድረግ ባለፉት ወራት በእያንዳንዱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ውስጥ ግምገማዎች ተደርገዋል። ግምገማው ወደመንግሥት ተቋማትም ተሸጋግሮ ሲከናወን ሰንብቷል። በውጤቱም 50 ሺህ ያህል አባላት በጥፋት ተገምግመው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑ ተረጋግጠኦል።

 

የጥልቅ ተሀድሶው ሒደት

ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንዳሉት በከፍተኛ አመራሩ ጭምር ችግሮች መኖራቸው የታመነበት ነው። የመንግሥትን ሥልጣን ሕዝብና አገርን ለመለወጥ ከማዋል ይልቅ የግል ጥቅምን ማራመጃ ለማድረግ የሚካሄድ ጥረትና ሥልጣንን ካለአግባብ ለመጠቀም የመሻት ዝንባሌ በሰፊው ታይቷል። 

ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ሀገሪቱን የሚመራው ፓርቲና መንግሥት ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውሰዋል። አያይዘውም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ የባለፉት 15 ዓመታት የተሀድሶ እንቅስቃሴን በጥልቀት በመገምገም የተጀመረ ሲሆን ግቡም በተሀድሶ ጊዜ የተቀመጠና ባለፉት 15 ዓመታት በተግባር ላይ ውለው ውጤት ያስገኙልንን አመለካከቶችና መስመሮች ይበልጥ በጥልቀት ለማስቀጠል እንዲሁም በሒደቱ ያጋጠሙንን የአመለካከት ዝንፈቶችና በተግባር የታዩ ህጸጾችን በማረም በሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት የተመሠረተውን የህዳሴ ጉዞአችንን ይበልጥ በጥራት ማፋጠንን ማዕከል ያደረገ ነው። በዚህም መሠረት በመሪው ፓርቲ ውስጥ የተለኮሰው እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል በስኬቶቻችንና በጉድለቶቻችን ዙሪያ ጥልቅ መግባባት የተፈጠረበትና ለተግባር አፈጻጸማችን ምቹ ሁኔታዎችን እያስገኘልን ይገኛል ብለዋል።

ይህ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ በፓርቲ ውስጥ ተጀመረ እንጂ የመንግስት አካላትም ሆነ ሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎች የተሃድሶው አካል ለማድረግ እየተፈጸመ ያለ ነው። እስካሁን በፐብሊክ ሰርቪሱ ሆነ በተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለኮሰው የጥልቅ ተሃድሶ ለቀጣይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዋና ፋይዳውም የተጀመረውን የሀገራችንን ህዳሴ በጥራትና ዋናው ባለቤት በሆነው ህዝቡና የተለያዩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተሳትፎ የአብዛኛው ሕዝብ እኩል ተሳትፎና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሄድ ነው። በመሆኑም አሁን የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ተግባራዊ የአፈጻጸም እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ  በጥልቅ የመታደስ ጉዞ ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል ያለበት ይሆናል። .... በሚል አስቀምጠውታል።

 

አፈጻጸሙ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከየካቲት 27-28/2009 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት የተፈፀሙ መሆናቸውን መገምገሙን ይፋ አድርጓል። የተሃድሶ ንቅናቄው በየደረጃው ባለ አመራር፣ አባላት፣ በሲቪል ሰርቫንቱ እና በህዝቡ ደረጃ ሰፊ ውይይት መደረጉንና በተሃድሶ አጀንዳዎቹ ላይም በተሻለ ሁኔታ የጋራ መግባባት መደረሱንም ተመልክቷል። መድረኮች በአመራርና በአባላት መካከል ለመተጋገል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ከመሆኑም በላይ በሲቪል ሰርቫንቱና በህዝቡ ዘንድም የተነሱ ችግሮች ይፈታሉ የሚል ተስፋ ማሳደሩን አይቷል። በተሃድሶው ሀገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም ያስገደዳትን አስከፊ ሁኔታ በመቀልበስ የተጀመረው ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል መግባባት እንደተፈጠረም ኮሚቴው ገምግሟል።

 

በአጠቃላይ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው ባለፉት 15 የተሃድሶ ዓመታት በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ መስኮች የተመዘገቡ ወርቃማ ስኬቶች ላይ ህዝቡ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል። በተመሳሳይ ሁኔታ የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል የሆኑት የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶችና ተግባራት የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አደጋ መሆናቸውን በመግባባት በቀጣይ ትግል የህዳሴ ጉዞውን ማደናቀፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ በማድረስ ሀገራዊ ህዳሴውን እውን ለማድረግ ህዝቡ መነሳሳቱንም ኮሚቴው ተመልክቷል።

 

የመልሶ ማደራጀት ስራው በተመለከተም በተለይ ከክልል ቀጥሎ ባሉ የአስፈፃሚ አካላት ምደባ በብዙ አካባቢዎች በአባላትና በህዝቡ ቀጥተኛ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን በአመራሮቹ ምደባ ላይ ባለቤትነቱን በማረጋገጥ ያገለግሉኛል ያላቸውን እውቅና የሰጠበት በተቃራኒው አያገለግሉኝም ያላቸውን ደግሞ በትግል በአመራርነት እንዳይቀጥሉ ማድረጉን ኮሚቴው የገመገመ ሲሆን አሰራሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቅጣጫ አስቀምጧል።

ኢህአዴግ በጥልቅ ተሀድሶ ሒደት ከ5 ሚሊየን አባላቱ ውስጥ ወደ 50 ሺ የሚሆኑ አባላቱ ላይ እርምጃ መውሰዱን አዲስ ራዕይ መጽሔት በመጋቢት 1 ቀን 2009 ዕትሙ ለንባብ አብቅቷል። እነዚህ አባላት እርምጃ የተወሰደባቸው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ከኃላፊነት ዝቅ ማድረግ ወይም የማንሳት፣ ከድርጅት የማባረር የመሳሰሉ አስተዳደራዊና ድርጅታዊ እርምጃዎች ናቸው። እነዚህ አባላት ላይ እርምጃው የተወሰደው ከተገመገሙ በኋላ መሆኑም ይታወቃል።

ይህም ሆኖ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሩን መንካት አልቻለም፣ በሚል በተደጋጋሚ ለሚቀርብበት ክስ “ማስረጃ የለንም” በሚል ምላሽ ይሰጣል። መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሩን በግምገማ የቀጣ ድርጅት ከፍተኛ አመራሩን በተመሳሳይ መንገድ መቅጣት ለምን እንዳልቻለ አነጋጋሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሒደቱን ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው።

አዲስ ራዕይ በዚህ ዕትሙ በተለይ ከፍተኛ አመራሩ ለምን አልተነኩም በሚል በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎች ላይ ትንታኔ ለመስጠት ሞክሯል። “ከፍተኛ አመራር ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የሚቀየሩትም መቀየር ያለባቸውም የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብና በመንግሥት ሕግ መሠረት ከኃላፊነት እንዲነሱ የሚያደርግበት ሁኔታ ሲኖር ነው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት ባገኘ የግል የመልቀቂያ ጥያቄና ለቦታው የተሻለ ዕጩ ሲገኝ እንዲሁም በኃላፊነት የማያስቀጥል ጥፋት መፈጸሙ ሲረጋገጥ የሚሉት ይገኝበታል። ከዚህ ውጪ ግን እንደድርጅት የነበረውን ስህተትና ጉድለት ስለሚጋራ ወይንም ብዙ ሒስ ስለቀረበበትና በአግባቡ ስላልተቀበለ….በመሳሰሉ መመዘኛዎች በየትኛውም አካል ላይ ያለን አመራር ከኃላፊነት ማውረድ ተገቢ አይደለም” በሚል ያስቀምጣል።

ይህ ጹሑፍ “ያለማስረጃ አንከስም” የሚለውን አቋም የሚያጠናክር ሲሆን ያለበቂ ማስረጃ በግምገማ ብቻ ከሃላፊነታቸው የሚነሱ ሰዎች መኖራቸው ሲታሰብ ደግሞ ድርጅቱ ለአንድ ጉዳይ ሁለት ዓይነት መመዘኛዎችን እየተጠቀመ እንዳይሆን ያሰጋል።

በአሁኑ ወቅት የጥልቅ ተሀድሶው መገለጫ በየመ/ቤቱ ረጅም ቀናት የፈጁ ስብሰባዎችን ማድረግ መስሎ እየታየ ነው። መገለጫው በግምገማ የተወሰኑ ሰዎችን ወይንም ግለሰቦችን ማብጠልጠል የሆነባቸው መድረኮችም አሉ። ከምንም በላይ አስገራሚው ደግሞ በሙስናና ብልሹ አሠራራቸው የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ሁሉ የጥልቅ ተሀድሶ ዓላማ አቀንቃኞች ሆነው በየመድረኩ የመታየታቸው ነገር ነው። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ሒደቱ በሕዝብ ዘንድ ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው።

ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ ኢህአዴግ በተገኘው ማስረጃ ልክ ሰዎችን ተጠያቂ እያደረገ መምጣቱ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ጠቆም አድርገዋል። “…በምንም መልኩ የስርቆት ወይም የሙስና ወንጀል ላይ መረጃ የተገኘበት ግለሰብ በየትኛውም መንገድ አይታለፍም፤ በተገኘው የማስረጃ ልክ ግለሰቦችን ተጠያቂ እያደረግን መጥተናል ብለዋል። አክለውም ሙስና ውስብስብ የሆነ ወንጀል በመሆኑ መረጃ ይዞ የሚመጣ አካል ካለ እርምጃ ለመውሰድ አንዘገይም” ብለዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ኢህአዴግ ሥልጣንን ለግል መጠቀሚያ ያደረጉ ሹሞች መኖራቸውን በአደባባይ አምኖ ቀብሏል። ሕዝብ ደግሞ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው፣ ለምን ተጠያቂ አይሆኑም የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው። የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የኢህአዴግ ቀጣይ የቤት ሥራ ሆኗል።¾


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 1 of 13

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us